የእለት ዜና

መንግስት የ122 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጄት ጥያቄ አቀረበ

በሰሜን ኢትዮጵያ በተካሄደው ጦርነት ምክንያት ተጨማሪ ገንዘብ በማስፈለጉ የገንዘብ ሚኒስቴር፣ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት የ122 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጄት ጥያቄ ማቅረቡ ተገለጸ።
ጥያቄው የቀረበው በተከሠተው ጦርነት ምክንያት መንግሥት በሚሰበስበው ገቢ ያለውን የክፍያ ጥያቄ መመለስ አዳጋች በመሆኑ እና ያለውን የተጨማሪ ወጪ በበጄት ሽግሽግ መሸፈን ባለመቻሉ ነው ተብሏል።
ተጨማሪ በጄቱ ለአገር ደኅንነት ማስጠበቂያ፣ ለሰብዓዊ ዕርዳታ፣ በጦርነትና ግጭቶች ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ማቋቋሚያ፣ እንዲሁም ለሌሎች አስፈላጊ የመንግሥት ሥራዎች ማስፈጸሚያነት የሚውል መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር አመልክቷል።
በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ከተከሰተው ጦርነት ጋር ተያይዞ ላጋጠሙ ወጪዎች፣ በድርቅ ለተጎዱ፣ ለተፈናቀሉ እና ለተመላሾች የዕለት ዕርዳታ አቅርቦት፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል፣ ለማዳበሪያ አቅርቦት ድጎማ፣ እንዲሁም ለጎርፍ መከላከል በሚል ባለፈው ዓመትም 26.4 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጄት መጽደቁ የሚታወስ ነው።
በዚህ ዓመት በገንዘብ ሚኒስቴር ተዘጋጅቶ የቀረበው የተጨማሪ በጄት ጥያቄ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ከአራት ዕጥፍ በላይ ጨምሮ 122 ቢሊዮን ብር ደርሷል።
ይህ የተጨማሪ በጄት ጥያቄው በሚኒስትሮች ምክር ቤት ታይቶ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚቀርብ ሲሆን፣ ተቀባይነት ካገኘ በቀጥታ ሥራ ላይ እንደሚውል የገንዘብ ሚኒስቴር አመላክቷል።
ባለፈው ዓመት፣ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ለ2014 ከፍተኛውን ዓመታዊ በጀትን ማጽደቋ አይዘነጋም።
የአገሪቱ ዓመታዊ በጀት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመሔድ ላይ ሲሆን፣ የዚህ ዓመት በጀት ግን 561 ቢሊዮን ብር ሆኖ በሚኒስትሮች ምክር ቤትና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጸድቋል።
ይህም በጄት 2013 ከነበረው በ85 ቢሊዮን ብር ከፍ ብሎ፣ በአገሪቱ መንግሥት የበጀት ታሪክ ከፍተኛው ለመሆን ችሏል። አሁን የተጠየቀው ተጨማሪ በጀት ሲታከልበት ደግሞ አጠቃላይ የዓመቱ በጀት ከ680 ቢሊዮን ብር በላይ ይሆናል ነው የተባለው።


ቅጽ 4 ቁጥር 165 ታኅሣሥ 23 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!