የእለት ዜና

የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ ረቂቅ ዐዋጅ ፀደቀ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ ረቂቅ ዐዋጅን በአብላጫ ድምፅ አፀደቀ።
ዐዋጁ በ13 ተቃውሞ እና በ1 ድምፀ-ተአቅቦ በአብላጫ ድምፅ ነው የፀደቀው።
የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች እና ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደርጎበት በተገኙ ግብዓቶች መሠረት በአንቀጾች ላይ ክለሳና ማስተካከያ ተደርጎ መጽደቁ የተነገረለት ረቂቅ ዐዋጁ፣ በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባትን ለመፍጠር በማሰብ ተዘጋጅቷል ተብሏል።
በረቂቅ ዐዋጁ ላይ ከሰሞኑ ይፋዊ የሕዝብ ውይይት እንደተካሄደበት ምክር ቤቱ አስታውቋል።
በውይይቱ ማቋቋሚያ ዐዋጁንና ኮሚሽኑን የተመለከተ ማብራሪያ የሠጡት የፍትሕ ሚኒስትሩ ጌዲዮዎን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር)፣ ስለ ኮሚሽነሮች ሹመት እና ኮሚሽነሮቹ መሉ ጊዜያቸውን ሥራ ላይ የሚያውሉ እንደሆነ አስረድተዋል።
ሆኖም የውይይቱ ተሳታፊዎች ኮሚሽኑ እውነተኛና ችግር ፈቺ ሆኖ እንዲቋቋም መጠየቃቸውን ያስታወቀው ምክር ቤቱ፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት ይሾማሉ ስለተባሉ ኮሚሽነሮች ገለልተኛነትና ከገንዘብ ሚኒስቴር የሚገኝ ነው ስለተባለው የኮሚሽኑ የበጄት ጉዳይ ጥያቄዎች ጠይቀዋል።
ኮሚሽነሮቹ ከፖለቲካ፣ ከኃይማኖት እና ከብሔር ወገንተኝነት የፀዱ፣ ችሎታና ብቃታቸው የተረጋገጠ፣ እንዲሁም አገርና ሕዝብን ለማሻገር ቁርጠኛ የሆኑ ሕዝብ ያመነባቸው ሊሆኑ እንደሚገባም በውይይቱ ተጠይቋል።
የረቂቅ ዐዋጁ ርዕስ አገራዊ የምክክር መድረክ ከማለት ይልቅ፣ ‹‹ብሔራዊ የመግበባት መድረክ›› ቢባል የሚሻል እንደሆነም ሐሳብ ቀርቦ ነበር።
ለጥያቄዎቹ ምላሽ የሠጡት ጌዲዮዎን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ አገራዊ የምክክር መድረኩ ዋና ዓላማ አገራዊ መግባባትን ለመፍጠር እስከሆነ ድረስ በርዕሱ ላይ ማሻሻያ ሊደረግበት እንደሚችል ገልጸዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 165 ታኅሣሥ 23 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!