የእለት ዜና

ሲንቄ ባንክ አጠቃላይ ካፒታሉን ወደ 7.7 ቢሊዮን ብር ማሳደጉን አስታወቀ

ባንኩ በ740 ሚሊዮን ብር ዋና መሥሪያ ቤት እያስገነባ ነው

የቀድሞ የኦሮሚያ ብድር እና ቁጠባ ተቋም የአሁኑ ሲንቄ ባንክ፣ አጠቃላይ ካፒታሉን ከ2.8 ቢሊዮን ብር በ175 በመቶ በማሳደግ 7.7 ቢሊዮን ብር ማድረሱን ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።
ወደ ባንክ ካደገ የወራትን ዕድሜ ያስቆጠረው ሲንቄ ባንክ፣ 2019/20 በጄት ዓመት በማይክሮ ፋይናንስነት ከነበረው 2.8 ቢሊዮን ብር፣ የብሔራዊ ባንክ ያሳለፈውን አዲስ ባንኮች መመሥረቻ የሚያስፈልገውን ዝቅተኛ መጠን ግማሽ ቢሊዮን ብር እና ነባር ባንኮች ያላቸውን ካፒታል ወደ አምስት ቢሊዮን እንዲያሳድጉ የሚያዘውን መመሪያ ተከትሎ፣ የቀድሞ ኦሮሚያ ብድር እና ቁጠባ ተቋም ባለ አክሲዮኖች ባሳለፉት ውሳኔ የተከፈለ ካፒታሉን 4.4 ቢሊዮን ብር ማድረሱን ለማወቅ ተችሏል።

በ22 ባለአክሲዮኖች የተመሠረተው ባንኩ፣ አጠቃላይ የሀብት መጠኑ ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ11 በመቶ ዕድገት በማሳየት 16 ቢሊዮን ብር መድረሱ ተመላክቷል። የባንኩ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ዘውዴ ተፈራ፣ ባንኩ በቅርንጫፎቹ ላይ የ‹ኮር ባንኪንግ› እና የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት ማሟላትን ተቀዳሚ ሥራው አድርጎ እየሠራ መሆኑን ገልጸው፣ በቀጣይም የሰው ሀብት ላይ የመሥራት ዕቅድ መያዛቸውን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በ2020/21 በጄት ዓመት ከ400 በላይ የሚሆኑ ቅርንጫፎቹ ሙሉ በሙሉ የባንክ ፍቃድ እንዲያገኙ ለማድረግ ባንኩ ከብሔራዊ ባንክ ጋር እየሠራ መሆኑን ዘውዴ ገልጸዋል። በበጄት ዓመቱ ባንኩ ከ2.3 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ያገኘ ሲሆን፣ ከባለፈው በጄት ዓመት ጋር ሲነጻጸር ገቢው የ383 ሚሊዮን ብር ጭማሪ አሳይቷል። ከወለድ የተገኘው ገቢ 14 በመቶ ዕድገት በማሳየት ለጭማሪው የአንበሳውን ድርሻ በመወጣት ከ 1.94 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ አስገኝቷል ተብሏል።

በተጨማሪም ከተለያዩ የአገልግሎት ክፍያዎች የተገኘው ገቢ 26.1 በመቶ ጭማሪ በማሳየት 48.4 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ ከ1.8 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ባንኩ ማስመዝገቡ ታውቋል። በዚህም ለሠራተኞች የተከፈለ ደሞዝ እና ጥቅማጥቅም 44 በመቶ ሆኖ ከፍተኛውን ድርሻ የያዘ ሲሆን፣ ባንኩ 560 ሚሊዮን ብር ማትረፉ ታውቋል።

ባንኩ፣ የባንክ እና ማይክሮ ፋይናንስ ሥራ በመሥራት ላይ እንደሚገኝ የተገለጸ ሲሆን፣ ‹ቲዩብ ፍሌክስ› የተሠኘ ‹ኮር ባንኪንግ› ሥርዓት በ240 ሚሊዮን ብር በሚጠጋ ወጪ ተገዝቶ፣ ከዚህ ቀደም ባንኩ ይጠቀምበት የነበረውን ‹ኦሚኒ ኮር ባንኪንግ› በመቀየር ሒደት ላይ ነው ተብሏል።

የኮር ባንኪንግ ሥርዓት መቀየር አስፈላጊ የሆነው ኦምኒ የተሰኘው ኮር ባንኪንግ ከዘመናዊነት አንጻር ወቅቱ ያለፈበት በመሆኑ እንደሆነ የገለጹት ተጠባባቂ ፕሬዝዳንቱ፣ ባንኩ ከ ኃምሳ ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማውጣት የመረጃ ማዕከል (ዳታ ሴንተር) እንዳስገነባ ገልጸዋል። በዚህም ባንኩ ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ በቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት ላይ ወጪ እንዳደረገ ተጠቁሟል።

ባንኩ ከ6.1 ቢሊዮን ብር በላይ ተቀማጭ ገንዘብ መሰበሰብ መቻሉን የገለጹት የባንኩ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት፣ ካለፈው ተመሳሳይ ወቅትም ጋር ሲነጻጸር የአንድ ቢሊዮን ብር ዕድገት አሳይቷል ብለዋል።

በሌላ በኩል ሲንቄ ባንክ ለዋና መሥሪያ ቤት እና ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውል በ1400 ካሬ ሜትር ላይ የሚያርፍ ባለ 14 ወለል ሕንጻ በ740 ሚሊዮን ብር ወጪ ማስገንባት መጀመሩ ታውቋል። የባንኩን ዋና መሥሪያ ቤት ግንባታ “ሶምኬት ኢንጅነሪንግ ኤንድ ኮንሽትራክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር” የተባለ ተቋራጭ እንደሚያከናውነው ተገልጿል።

በማይክሮ ፋይናንስ ዘርፍ ላይ የተሠማሩ ብድር እና ቁጠባ ተቋሞች ወደ ባንክ የማደግ ጥያቄ ለብሔራዊ ባንክ ያቀረቡ ሲሆን፣ እስካሁን ፈቃድ ከተሰጣቸው መካከል የአማራ ብድር እና ቁጠባ ተቋም ይገኝበታል። የአማራ ብድር እና ቁጠባ ተቋም ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ላይ ፀደይ ባንክ በሚል ሥያሜ ወደ ባንክ ያደገ ሲሆን፣ 9.2 ቢሊዮን ብር ካፒታል እና 36 ቢሊዮን ጠቅላላ ሀብት ያለው ተቋም ነው። ፀደይ ባንክ ወደ 9 ሚሊዮን የሚጠጋ ደንበኛ ሲኖረው፣ ከዚህም ወስጥ 1.5 ሚሊዮን የሚሆኑት ተበዳሪ ደንበኞች እንዳሆኑ ታውቋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 165 ታኅሣሥ 23 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!