የእለት ዜና

ከአዲስ አበባ ወደ ሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ለሚደረግ ጉዞ የትራንስፖርት ዋጋ በዕጥፍ ጨመረ

ከአዲስ አበባ እና ከደብረ ብርሃን ከተማ ወደ ሰሜኑ የኢትዮጵያ ከፍል የሚጓጓዙ ተሳፋሪዎች በትራንስፖርት ዕጥረት ምክንያት ከታሪፍ በላይ በዕጥፍ እየከፈሉ መሆኑን ገለጹ፡
አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ወደ ሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የተጓዙ እና በጦርነቱ ምክንያት ተፈናቀለው የነበሩና ወደአካባቢያቸው የተመለሱ ተጓዦች እንደሚሉት ከሆነ፣ የትራንስፖርት ዕጥረት በመኖሩ የተነሳ ከታሪፍ በላይ እየከፈሉ መሆናቸውን ነው ያመላከቱት።

ከቅሬታ አቅራቢዎቹ መካካል ብርሃኑ ኃይሉ የተባሉ ተጓዥ፣ ከአዲስ አበባ እስከ ቆቦ ከተማ ድረስ ለመሔድ እስከ አንድ ሺሕ 100 ብር መክፈላቸውን የገለጹ ሲሆን፣ ከዚህ በፊት የነበረው የመደበኛ ታሪፍ ዋጋ 450 ብር እንደነበር አስታውሰዋል።
“ወደ ላምበረት መናኸሪያ ሦስት ጊዜ ብመላለስም መናኸሪያ ውስጥ መኪና ማግኘት አልቻልኩም” የሚሉት ብርሃኑ፣ የትራንስፖርት ዕጥረት መኖሩን ተከትሎ ወደ ሰሜኑ ከፍል የሚያቀኑ ተጓዦች ከመደበኛው ታሪፍ ዕጥፍ በላይ እየከፈሉ ከዕቅድ ውጭ ለሆነ ወጭ እየተዳረጉ ነው ብለዋል።

አዲስ ማለዳ ከቅሬታ አቅራቢዎቹ የደረሳት መረጃ እንደሚያመላክተው ከሆነ፣ ከደብረ ብርሃን ወደ ደሴ ከተማ ለመሄድ 500 ብር የትራንስፖርት ክፍያ ይጠየቃል።
ከደብረ ብርሃን ወደ ወልዲያና ቆቦ ከተማ የተጓዙት ሰዎች በበኩላቸው፣ በታሪፉ የሚጭን መኪና ሊያገኙ ባለመቻላቸው፣ ከታሪፍ ውጭ ከዕጥፍ በላይ ለመክፈል እንደተገደዱ ጠቁመዋል። ከዚህ ጋር በተያያዘ የሺ ኃይሉ የተባሉት እናት፣ በጦርነቱ ምክንያት ተፈናቅለው ይኖሩ ከነበረበት የደብረ ብርሃን ከተማ ተነስተው ወደ ቆቦ ለመሄድ አንድ ሺሕ ብር እንደከፈሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

እንደ ዘመን ባስ፣ ዋሊያ ባስና ኖህ ትራንስፖርት ያሉ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጭዎች ተፈናቃዮችን ወደየአካባቢያቸው በነጻ ለማድረስ ቃል ቢገቡም፣ ወጣቶች ግን አገልግሎትን እያገኙ አይደለም ተብሏል።
አዲስ ማለዳ ለችግሩ ዝርዝር ምላሽ ለማግኘት የአማራ ክልል ትራንስፖርት ቢሮ የሎጅስቲክ ዋና ዳይሬክተር ውቤ አጥናፉን ያነጋገረች ሲሆን፣ ዳይሬክተሩም ወቅታዊ ችግሮች ሲኖር በትራንስፖርት ዋጋ ላይ የ50 በመቶ ጭማሪ ሊኖር እንደሚችል ገልጸው፣ ነገር ግን አንድ ሺሕ ብር ሊደርስ የሚችል የዋጋ ጭማሪ ሊኖር ይችላል ብለው እንደማያምኑ ተናግረዋል።

ዳይሬክተሩ አያይዘውም፣ የ50 በመቶ ጭማሪ ሲደረግ 350 ብር የነበረው ታሪፍ 450፣ እንዲሁም 200 የነበረው ታሪፍ 300 ብር ሊሆን እንደሚችል የገለጹ ሲሆን፣ ሹፌሮች ከመናኸሪያ ውጭ ስለሚጭኑ ነው እንጂ፣ የትራንስፖርት ዋጋ ታሪፉ ከ450 ሊበልጥ አይችልም ነው ያሉት።

ችግሩ የነዳጅ ዋጋ መጨመርን ተከትሎ ከተደረገው የታሪፍ ጭማሪ ጋር የተገናኘ አለመሆኑ ተገልጿል። ዳይሬክተሩ እንደሚሉት፣ በተሻሻለው ታሪፍ መሠረት 100 ኪሎ ሜትር ላይ የተደረገው የአምስት ብር ጭማሪ በመሆኑ፣ የታሪፍ ክለሳው አሁን የተከሠተው የዋጋ ጭማሪ ላይ አይደርስም ብለዋል።

ይልቁንም ለችግሩ መከሠት ዋናው ምክንያት አካባቢው በጦርነት ቀጠና ውስጥ ስለነበር ሹፌሮች አጋጣሚውን ምክንያት በማድረግ ከመደበኛው ታሪፍ ውጭ ስለሚያስከፍሉ ነው ብለዋል። የትራንስፖርት ዕጥረት መኖሩንም የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ ችግሩን ለመቅረፍ ከሚመለከተው አካል ጋር ኹሉ እየተነጋገርን ነው ብለዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 165 ታኅሣሥ 23 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!