የእለት ዜና

በምዕራብ ኦሮሚያ ከ1 ሺህ 800 በላይ የሸኔ አባላት ላይ እርምጃ መወሰዱ ተገለፀ

ዕሮብ ታህሳስ 27/2014 (አዲስ ማለዳ) በምዕራብ ኦሮሚያ ከአንድ ሺህ 800 በላይ የሸኔ አባላት ላይ እርምጃ መወሰዱን የምዕራብ ዕዝ ኦሮሚያ ልዩ ኃይል አዛዥ ረዳት ኮሚሽነር ጋሊ ከማል ገለፁ።

ረዳት ኮሚሽነር ጋሊ ለኢትዮጵያ ፕሬስ እንደገለጹት፤ በምዕራብ ኦሮሚያ ላይ በተለያየ ጊዜ በታቀደ መልኩ በተካሄደ ዘመቻ በአንድ ሺህ 836 በአካባቢው በሚንቀሳቀሱ የጥፋት ኃይሎች ላይ እርምጃ ተወስዷል።

ከእነዚህ ውስጥ አንድ ሺህ 643 የጠላት ታጣቂዎች መገደላቸው፣ 106 የሚሆኑት ደግሞ እጅ የሰጡ መሆናቸውና 87 የሚደርሱ የሽብር ቡድኑ ተላላኪዎች ደግሞ መያዛቸውን ተናግረዋል።

በምዕራብ ኦሮሚያ ሸኔ፣ በቤኒሻንጉል አዋሳኝ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሰው ቤኒን የተባለ አማፂ ኃይልና አማራን የማይወክሉ ከአማራ የወጡ ፅንፈኛ ኃይሎች በአካባቢው በስፋት በመንቀሳቀስ ኅብረተሰቡ ላይ በተለያየ መንገድ ችግር እያደረሱ መሆኑን አመልክተው፤ በተለይም እነዚህ የጥፋት ኃይሎች በምስራቅ ወለጋ ዞን በጥምረት እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ አረጋግጠናል ብለዋል፡፡

የምስራቅ፣ ምዕራብና ቄለም ወለጋ አብዛኛው አካባቢዎች የክልሉ ልዩ ኃይል የጸጥታ ጥበቃ የሚያካሄድባቸው መሆናቸውን ጠቁመው፤ በምስራቅ ወለጋ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ስምሪት ከተሰጠው በኋላም በጥምረት የተለያዩ አሰሳዎችና እርምጃዎች በመወሰዳቸው በሽብር ቡድኑ ላይ ኪሳራ እየደረሰበት መምጣቱን ገልጸዋል፡፡
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!