የእለት ዜና

“ትምህርት ሚኒስቴር 50 ዘመናዊ አዳሪ ትምህርት ቤቶችን ያስገነባል”:- ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ

ዕሮብ ታህሳስ 27/2014 (አዲስ ማለዳ) ትምህርት ሚኒስቴር በመላ ኢትዮጵያ 50 ዘመናዊ ደረጃቸውን የጠበቁ አዳሪ ትምህርት ቤቶችን ለማስገንባት የሚያስችል ፕሮጀክት ማዘጋጀቱን የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ አስታወቁ።

በትምህርት ቤቶቹ የዲዛይን ዝግጅቱ ላይም ከኢትዮጵያ አርክቴክቶች ማኀበር ጋር ውይይት እያካሄደ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በኢንተርኔት አማራጭ የቪዲዮ መልዕክታቸው፤ በኢትዮጵያ 48 ሺህ ትምህርት ቤቶች ቢኖሩም ደረጃቸውን የጠበቁት 0 ነጥብ 01 በመቶዎቹ ብቻ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በአጠቃላይም ስድስት ትምህርት ቤቶች ብቻ ናቸው ደረጃ አራት ላይ የሚገኙት ብለዋል።

ስለዚህም ኢትዮጵያ ደረጃቸውን የጠበቁ የአካልና የአዕምሮ ማበልጸጊያ ትምህርት ቤቶች ያስፈልጓታል፤ ለዚህም ደረጃቸውን የጠበቁ አዳዲስ ትምህርት ቤቶችን መገንባት አለብን ብለዋል።

የኢትዮጵያ አርክቴክቶች ማኀበር በበጎ ፈቃደኝነት የትምህርት ቤቶቹን የግንባታ ዲዛይን ለማዘጋጀት ፈቃደኛ መሆኑን የገለጹት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፤ በዚህ አገራዊ ፕሮጀክት ለመሳተፍ ፈቃደኝነታቸውን ላሳዩ ኢንጂነሮችም ምስጋና አቅርበዋል።

የፕሮጀክቱን አጠቃላይ ዝግጅት በተመለከተ የኢትዮጵያ አርክቴክቶች ማኀበር አመራርና አባላት ከትምህርት ሚኒስቴር አመራሮች ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ኢፕድ ዘግቧል።
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!