የእለት ዜና

በአፋር ክልል ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ተገለጸ

ሐሙስ ታህሳስ 28/2014 (አዲስ ማለዳ) በአፋር ክልል ከአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት የቅድመ ማስጠንቀቂያና ፈጣን ምላሽ ዳይሬክተር የሆኑት መሐመድ አብደላ የሕውሃት ቡድን በክልሉ በከፈተው ወረራ ምክንያት ከሁለት ሚሊዮን በላይ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን ተቁመው፤ ከተፈናቃዮቹ ውስጥ ከአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ገልፀዋል።

እንደ መሐመድ ንግግር፤ አራት የአፋር ዞኖች በሸፈነው የቡድኑ ጥቃት ከዞን አንድ ሁለት ወረዳዎች ከዞን አምስትና ከዞን ሁለት ሙሉ ወረዳዎችን ማጥቃቱና በዞኖቹ በተከፈተው ጥቃት ምክንያት ከሁለት ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ያለቤትና ንብረት መቅረታቸውን ገልፀዋል።

ቡድኑ በክልሉ ባደረገው ወረራ ምክንያት የተፈናቀሉት ዜጎች የሚለበስ ልብስ፤ የሚቀመስ ምግብ ሳይዙ እግሬ አውጪኝ ብለው ወደ መጠለያው መምጣታቸውን የጠቆሙት መሐመድ ወደ ቀድሞ መኖሪያቸው ይመለሱ ቢባል እንኳን ስፍራው ለመኖር ምቹ እንዳልሆነም ገልጸዋል።

መሐመድ ተፈናቃዮቹ በቀድሞ ቀያቸው የሚበሉት የሌላቸው፣ እንስሳዎቻቸው የሞቱባቸውና ቤቶቻቸው የፈረሱባቸው በመሆናቸው ሁሉም የኅብረተሰቡ ክፍል ተፈናቃዮቹን በመልሶ የመገንባት ሥራ ላይ ትኩረቱን ሰጥቶ ሊረባረብ እንደሚገባውም ገልጸዋል።

እንደ መሐመድ ንግግር፤ አብዛኞቹ ተፈናቃዮች ከቤተሰቦቻቸው ጋር ስለተሰደዱ ምግብ፤ መጠለያ፤ የሕፃናት አልሚ ምግብ ያስፈልጋቸዋል።

ከአንድ ወር በላይ ክልሉ ለብቻው ተፈናቃዮችን ሲደግፍ መክረሙን የገለፁት መሐመድ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ግብረሰናይ ድርጅቶች የመንግሥት የልማት ድርጅቶችና ሌሎችም የኅብረተሰብ ክፍሎች የአቅማቸውን አስተዋጽኦ እያደረጉ እንደሚገኙ ጠቁመዋል ሲል ኢፕድ ዘግቧል፡፡

ከግለሰብም ይሁን ከባለሀብቶች የሚገኙ እርዳታዎች በአንድ ቋት ውስጥ እንዲሰባሰብ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ የገለጹት መሐመድ የተሰበሰበው ድጋፍም በአደጋ መከላከል በኩል እንዲገባ በማድረግ ቀጥታ ለተጎጂዎች የማድረስ ተግባርን እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

ድጋፍ እያደረጉ ላሉ ወገኖችም በክልሉ ሥም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!