የእለት ዜና

በጥሬ ቆዳ ንግድ ላይ የተሰማሩ አካላት ለጥሬ ቆዳ ብክነት ምክንያት ሆነዋል ተባለ

በኢትዮጵያ በርካታ ጥሬ ቆዳ ምርት ቢኖርም፣ ደላሎች በመሀል በመግባት ተጠቃሚው በርካሽ ገዝተው ለፋብሪካዎች በውድ ዋጋ በማቅረብ፣ ብክነት ሲፈጥሩ
መቆየታቸውን የቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ለአዲስ ማለዳ ገለጸ።

ማኅበረሰቡ ቆዳ ዋጋ አያዋጣም እያለ እንዲጥለውና በእርድ ወቅትም ለጥሬ ቆዳ ጥንቃቄ እንዳያደርግ እክል መፍጠሩን ነው ኢንስቲትዩቱ የጠቆመው። በመሆኑም ይህን
ችግር ለመቅረፍ የቆዳ ፋብሪካዎች በቀጥታ ከማኅበረሰቡ ጥሬ ቆዳ እንዲገዙ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ፈቃድ መሰጠቱን የቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የኮሚኒኬሽን እና ህዝብ ግንኙነት ቡድን መሪ ብሩክ ጥላሁን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

እንዲሁም፣ በአገሪቱ ሰፊ የቆዳ አቅርቦት እያለ ነገር ግን የቆዳ ፋብሪካዎች ስርጭት በአንድ አካባቢ ብቻ የተወሰነ በመሆኑ በቀጣይም በክልሎች የቆዳ ፋብሪካዎች
እንዲገነቡ የማድረግ መፍትሄ መያዙን አመላክተዋል።

ለአብነትም በደቡብ፣ አፋር እና አማራ ክልሎች በሰፊው እርድ የሚፈጸም መሆኑን አንስተው፣ ነገር ግን የቆዳ ፋብሪካዎች በአዲስ አበባ እና ሞጆ አካባቢ ብቻ የተከማቹ
በመሆኑ ምክንያት ብዙ ጥሬ ቆዳ በየአመቱ እንደሚባክን አስረድተዋል። በዚህ ጊዜም ኅብረተሰቡ ያለው አማራጭ ጥሬ ቆዳውን በወረደ ዋጋ ለነጋዴዎች መሸጥ ወይም ደግሞ መጣል ነው ካሉ በኋላ፣ ፋብሪካዎች በቀጥታ ከማህበረሰቡ የመግዛት አቅማቸውን ባሳደጉ ቁጥር ግን የቆዳ ዋጋ ከፍ ስለሚል ማህበረሰቡ ለቆዳ ጥንቃቄ ያደርጋል ነው ያሉት።

አሁን ላይ ፋብሪካዎች ጥሬ ቆዳን በቀጥታ ከማህበረሰቡ እንዲገዙ እና ጥሬ ቆዳን የሚጠቀሙ ፋብሪካዎችን በየአካባቢው ከመገንባት ባለፈ ደላሎችን እንዲህ አድርጉ፣
በዚህ ዋጋ ግዙ ለማለት፣ አገሪቱ ከምትከተለው ነጻ ገበያ ስርዓት ጋር የሚጋጭ በመሆኑ አስቸጋሪ መሆኑን ቡድን መሪው ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም ጥሬ ቆዳን ለመሰብሰብ ለተለያዩ ተቋማት ማለትም፣ ለግብርና ሚኒስቴር፣ ለኢንዱስትሪ ግብዓት አቅራቢዎች እና መሰል ሌሎች የሚመለከታቸው ተቋማት
የተሰጠ በመሆኑ የነበረው የተግባርና ኃላፊነት መወራረስ ክፍተት ፈጥሮ መቆየቱን አንስተዋል። ይህ አሁን ላይ ቢያንስ ተቋማቱ በየራሳቸው ሲያደርጉት የነበረውን ተግባር በጋራ በመነጋገር እንደሚፈጽሙትም ነው የጠቀሱት።

በተጨማሪም፣ ቤት ውስጥ የሚፈጸም እርድ ከፍተኛ የጥሬ ቆዳ ብክነት እንደሚፈጥርና ይህን ለማስቆምም፣ ማህበረሰቡ በቄራ ለማሳረድ ያለው የገንዘብ አቅም አናሳ መሆን እንዲሁም ቤት ማረድን እንደ ጠቃሚ ልማድ መውሰዱ ችግሮች መሆናቸውን አመላክተዋል።

በዚህም ስለ ቆዳና ቆዳ ውጤቶች ለማህበረሰቡ በቂ ግንዛቤ በመፍጠር ለቆዳ ያለውን ዋጋ እና ጥንቃቄ ለማሳደግ ቋሚ ማስታወቂያ ህዝብ በብዛት በሚገኝባቸው
ቦታዎች ላይ ለማስነገር እንደ መፍትሄ መታየቱንም ቡድን መሪው ሳይገልጹ አላለፉም።

የጥሬ ቆዳ አቅራቢዎች ማህበር ፕሬዘዳንት ብርሀኑ አባተ በበኩላቸው፣ ቆዳን በአግባቡ የሚሰበስብ አካል ባለመኖሩ ብዙ ብክነት እንደሚፈጸም ጠቅሰው፣ አሁን ላይ
ማህበራቸው በመላ አገሪቱ ያሉ ነጋዴዎች ወደ ስራ እንዲገቡና ጥሬ ቆዳን በአግባቡ እንዲሰበስቡ ቅስቀሳ እያደረገ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። ለነጋዴዎች ብቻ
ሳይሆን ህብረተሰቡም ቆዳ ጥቅም የለውም ብሎ እንዳይጥለው እያሳሰብን ነው ሲሉ ተናግረዋል። አክለውም፣ ነጋዴዎች ብክነት ፈጥረዋል ብለው እንደማያምኑና አሁን ላይ ችግር የሆነው የሚሰበስብ አለመኖሩ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

የቆዳ ዘርፉ ተገቢውን ትኩረት ቢሰጠው በአገሪቱ ከውጭ የሚገባውን የቆዳ ምርት በመተካት፣ ከፍተኛ የስራ ዕድል እና የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለመቅረፍ ትልቅ ሚና
እንዳለው ይነገራል።


ቅጽ 4 ቁጥር 166 ታኅሣሥ 30 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!