የእለት ዜና

ዳያስፖራዎች በኢንቨስትመንት እንዲሳተፉ አምስት ዘርፎች መዘጋጀታቸው ተገለጸ

የገናን በዓል ምክንያት በማድረግ ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ ጥሪ የተደረገላቸው ዳያስፖራዎች በአምስት ዋና ዋና ኢንቨስትመንት ዘርፎች እንዲሠማሩ በየዘርፉ ዝግጅት መደረጉን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ።

በኢትዮጵያ አንድ ሚሊዮን ዳያስፖራዎች የገናን በዓል በኢትዮጵያ እንዲያከብሩ ጥሪ መቅረቡን ተከትሎ፣ ዳያስፖራዎች በተለያዩ ኢንቨስትመንት ዘርፎች መዋዕለ-ነዋያቸውን እንዲያፈሱ እና የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት ሀብት ለውጪ ኢንቨስተሮች እንዲያስተዋወቁ ልዩ ዝግጅት መደረጉን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሌሊሴ ነሜ ገልጸዋል።

የዳያስፖራው ማኅበረሰብ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ተሳታፊ እንዲሆን አራት ዋና ዋና የኢንቨስትመንት ዘርፎች መዘጋጀታቸውን የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነሯ ለሊሴ ጠቁመዋል። የዳያስፖራው ማኅበረሰብ እንዲሳተፍባቸው ከተዘጋጁት ዋና ዋና የኢንቨስትመንት ዘርፎች መካከል ማኑፋክቸሪንግ፣ ግብርና (አግሪካልቸር)፣
ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ ሎጅስቲክስ እና የጤና ዘርፍ መሆናቸውን ኮሚሽነሯ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ወደ ኢትዮጵያ የመጡ ዳያስፖራዎች በተጠቀሱት አራት ዋና ዋና የኢንቨስትመንት ዘርፎች እንዲሳተፉ የተለያዩ የኢንቨስትመንት ዕድሎች ማስተዋወቂያ ዝግጅቶች በጋራ ማዘጋጀታቸውን ገልጸዋል። ኹለቱ ኮሚሽኖች ካዘጋጇቸው የኢንቨስትመንት ማስተዋወቅ ሥራዎች መካከል፣ የኢንቨስትመንት ፎረም፣ ኢግዚቢሽን እና የምክክር መድረክ ይገኙበታል።

ዳያስፖራው በተዘጋጁለት የተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዲሳተፍ እና ኢትዮጵያ ያላትን የኢንቨስትመንት አቅም ለማስተዋወቅ በሚካሄዱ ዝግጅትች ላይ
እንዲገኝ ጥሪ ተደርጓል። በተመሳሳይም ክልሎች እና ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ያሏቸውን የኢንቨስትመንት አማራጮች እንደሚያቀርቡ የኢንቨስትመንት ኮሚሽነሯ ጠቁመዋል።

ዳያስፖራው በቀረቡለት የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዲሳተፍ የኢንቨስትመንት አማራጭ የሚተዋወቅበት የኤግዚቢሽንና የምክክር መድረክ ከጥር 3 አስከ 6/2014 እንደሚካሄድ ተመላክቷል። የተደረገላቸውን ጥሪ ተቀብለው ለመጡትም ሆነ በተለያዩ ምክንያቶች ወደ አገራቸው መምጣት ላልቻሉት ዳያስፖራዎች አገራዊውን የኢንቨስትመንት አማራጭ ለማስተዋወቅ ዝግጅት መደረጉን የአዲስ አበባ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ግርማ ሰይፉ ተናግረዋል።

ዳያስፖራዎች ያሉትን የኢንቨስትመንት አማራጮች የሚመለከትበት እና የሚመዘግብበት ‹‹ኢንቨስት ኢትዮ ዶት ኮም›› የተሰኘ ድረ-ገጽ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።
የኢንቨስትመንት ፎረሙና የምክክር መድረኩ የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት አቅምና መንግሥት ለዘርፉ የሠጠውን ትኩረት የሚረዱበት፣ ከዚህ በፊት መዋዕለነዋይ አፍሰው ውጤታማ የሆኑ ኢንቨስተሮች ልምድ የሚያካፍሉበት መሆኑንም ኮሚሽነር ግርማ ገልጸዋል። በኢንቨስትመንት መሳተፍ የሚፈልጉ ዳያስፖራዎች በኢትዮጵያዊነታቸው ወይም በውጪ ፓስፖርት እንደየ ፍላጎታቸው መሠማራት ይችላሉ ተብሏል።

በኢንቨስትመንት የሚሠማሩ ዳያስፖራዎች የሚያገኙት አገልግሎት በኢትዮጵያዊነት ከሆነ በአገር ውስጥ ኢንቨስተርነት፣ ከፈለጉ በውጪ ኢንቨስተርነት በተቀመጡ የሕግ አሠራሮች እንደሚስተናገዱ ተመላክቷል። በሌላ በኩል፣ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ባለው ጦርነት በአማራ እና በአፋር ክልል ጉዳት የደረሰባቸው ኢንዱስትሪዎችን ወደ ሥራ ለማስገባት ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን የኢንቨስትመንት ኮሚሽነሯ ተናግረዋል።

በአማራ ክልል ኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ጉዳት ከደረሳበቸው ኢንዱስትሪ ፓርኮች አንዱ ሲሆን፣ በኢንዱስትሪ ፓርኩ ውሰጥ የነበሩ ፋብሪካዎችን መልሶ የማቋቋም ሥራዎች መጀመራቸውን ጠቁመዋል። በኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ የወደሙ ፋብሪካዎችን መልሶ ለማቋቋም እና ወደ ሥራ ለማስገባት በጀት ተይዞ ወደ ሥራ
መገባቱን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መግለጹ የሚታወስ ነው።


ቅጽ 4 ቁጥር 166 ታኅሣሥ 30 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!