የእለት ዜና

የምርጫ አስፈጻሚዎች ምርጫ ቦርድ የመጨረሻ ክፍያ አልከፈለንም አሉ

በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ላይ የምርጫ ክልል አስፈጻሚ ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩ አካላት፣ ምርጫ ቦርድ በገባልን ውል መሠረት የመጨረሻውን ክፍያ እስካሁን ሊከፍለን አልቻለም ሲሉ ቅሬታቸውን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ውል የፈጸምነው ሰኔ 14/2013 የተካሄደውን ምርጫ እንድናስፈጽም ነበር የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፣ የመጨረሻው ክፍያ ከምርጫ በኋላ የምርጫ ቁሳቁሶችን እንደመለስን እንደሚፈጸምልን ውል የገባን ቢሆንም፣ እስካሁን የሚሰማን አካል አጥተን ክፍያ አልተፈጸመልንም ነው የሚሉት። የምርጫ ቁሳቁሶችን ጳጉሜ ላይ ማስረከባቸውንም ገልጸዋል።

በአማራ ክልል በአንድ ወረዳ ውስጥ የምርጫ ክልል አስፈጻሚ ነበርኩ ያሉት አበበ ሙጨ፣ ከምርጫ ቦርድ ጋር ከተዋዋልነው 37 ሺሕ ብር ውስጥ፣ 40 በመቶ የሚሆነው ክፍያ ምርጫ እንዳለቀ የምርጫ ቁሳቁሶችን ከመለስን በኋላ ወዲያውኑ እንዲከፈል የተዋዋልን ቢሆንም፣ ዕቃ መልሰንም እንኳ ክፍያ ሳይፈጸምልን አራት
ወራት ሊጠጋ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ለዚህም ምክንያቱ ምን አንደሆነ አናውቀውም። ስንደውልም እንሱ ሲፈልጉን እንጂ እኛ ስንፈልጋቸው ማግኘት አንችልም ነው ያሉት። በአካል ሔደን ለመጠየቅም ከቦታ ዕርቀት አንጻር የማይቻል ነው ብለዋል። የምርጫ ቁሳቁሶችን ጳጉሜ ላይ ካስረከብን በኋላ መጀመሪያ ለ‹አይሲቲ› መሪዎች፣ ቀጥሎ ለምርጫ ጣቢያ አስመራጮች ተከፍሏል። ዕቃ ባናስረክብ ኑሮ ለእነሱም አይከፈልም ነበር ነው ያሉት።

ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የምርጫ ክልል አስፈጻሚዎች አስተባባሪ በበኩላቸው፣ ከነሐሴ እስከ መስከረም አጋማሽ ባለው ጊዜ ውስጥ ዕቃዎችን አስረክበን ደረሰኝ
ተቀብለናል ነው ያሉት። ሆኖም ግን ቅሬታችንን የምንገልጽለት አካል ባለመኖሩ የወቅቱን ኹኔታ እንደ ምቹ አጋጣሚ ተጠቅመው በመመሳጠር ገንዘባችንን ሊቀሙ የተዘጋጁ አካላት አሉ የሚል ሥጋት አድሮብናል ሲሉ ነው ቅሬታቸውን የገለጹት።

ስልክ ደውለን ስንጠይቅ ጠብቁ ይገባል ይሉናል፤ አንዳንዴ ደግሞ ያልመለሳችሁት ዕቃ አለ ይሉናል። ሆኖም ያልተመለሱ የድምጽ መስጫ ሳጥኖች ቢኖሩም አይጠቅሙም ብለው እነሱ የተውት ነው በማለት ተናግረዋል። መመለስ ያለበትን ዕቃም ቢሆን ተረከቡን ብለን ለምነን ነው የሠጠናቸው ያሉት ቅሬታ አቅራቢው፣ አሁንም ክፍያችንን የሚከለክል የቀረ ጠቃሚ ዕቃ የለም፤ ሳጥኑና የተቆራረጡ ቻርጀሮችን ከሆነ በጠየቁን ጊዜ ለማስረከብ ዝግጁ ነን ብለዋል።

መክፈል ስለማይፈልጉ እንጂ ይህን አድርጉ ብለው ጠይቀውን ዕምቢ ያልናቸው ነገር የለም። የቀረብን ገንዘብም ከ15 እስከ 20 ሺሕ ብር የሚደርስ ነው በማለት አብራርተዋል። በክልሉ በአብዛኛው ዞኖች ከሚገኙ የምርጫ ክልል አስፈጻሚዎች ጋር እንደሚደዋወሉ እና ለማንም እንዳልተከፈለ መረጃ እንዳላቸው ገልጸው፣ እንደ አገርም በሌሎች ክልሎች ለሚገኙ የምርጫ ክልል አስፈጻሚዎች የተከፈለ አይመስለኝም የሚል ዕምነታቸውን አጋርተዋል።

ቅሬታ አቅራቢው አክለውም፣ ለድካማችን የሚገባን ይህ አልነበረም፤ አሁንም ከፍተኛ ቅሬታ ቢያድርብንም ከአራት ወር በላይ ያለ ምክንያት ጠብቀናልና ቢያንስ ከዚህ በኋላ በቅርቡ ሊከፈለን ይገባል ሲሉ አሳስበዋል። አዲስ ማለዳ ምርጫ ቦርድ ውስጥ በኃላፊነት ለሚሠሩ አካላት ደውላ ስለ ጉዳዩ ምላሽ ብትጠይቅም ሐሳብ ለመስጠት ፈቃደኝነታቸውን ሳይገልጹ ቀርተዋል። በጉዳዩ ላይ መልስ ይሰጣሉ ከተባሉት የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተሯም መልስ ለማግኘት የተደረገው ተደጋጋሚ ሙከራ ሳይሳካ
ቀርቷል።


ቅጽ 4 ቁጥር 166 ታኅሣሥ 30 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!