የእለት ዜና

ለማኅበራዊ ፍትሕ የታገለ ወይስ ሥደተኛን ያገለለ?

በሣምንቱ መጀመሪያ ሰሞን መነጋገሪያ ከነበሩ ጉዳዮች አንዱ፣ ከደቡብ አፍሪካ አንድ የማኅበረሰብ አንቂ ወጣት ኢትዮጵያ ገባ ተብሎ በባለሥልጣናት ጭምር አቀባበል ተደረገለት የመባሉ ጉዳይ ያስነሳው ውዝግብ ነው። ግለሰቡ የ37 ዓመት ወጣት መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ምንም ዓይነት መንግሥታዊ ሥልጣን የሌለው መሆኑ የአቻ ላቻ አቀባበል ሥርዓትን ያቃወሰ ነው ሲሉ ከአቀባበሉ ጀምረው የተቹት ነበሩ።

ሎታታ ላክስ የተባለው ግለሰብ በደቡብ አፍሪካ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተሠሚነቱ እየጨመረ የመጣ የማኅበረሰብ መሪ ነው ተብሎ አዲስ አበባ እንደገባና አቀባበል እንደተደረገለት የዘገቡት የመንግሥት ሚዲያዎች ብቻ አልነበሩም። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤትም ጭምር በፌስቡክ ገጹ ሳይቀር መግለጫ እንደሰጠ ወሬውን ተቀባብለው አራግበውት ነበር።

ከዚህ ቀደም ስሙ ተሰምቶ የማይታወቅ አንድ ወጣት እንዲህ አይነት በወጀብ የታጀበ አቀባበል ተደረገለት ተብሎ ወሬው ሲራገብ ግራ ገብቷቸው ማነው ብለው ለማጣራት የሞከሩ፣ ባገኙት ውጤት ተደንቀው “ምነው ሰው ጠፍቶ ነው?” በማለት የሆነውን ኮንነዋል።
ግለሰቡ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ለሥራ ደቡብ አፍሪካ የገቡ ስደተኞች ከአገራችን ይውጡ በማለት ቅስቀሳ በማድረግና ጥቃት እንዲፈጸምባቸው በመቀስቀስ የሚታወቅ መሆኑን በመረጃ አስደግፈው አስነብበዋል። ለውጭ አገር ዜጎች ከፍተኛ የሆነ ጥላቻ አለው የተባለ ወጣትን እንዲህ አቀባበል ማድረጉ ፖለቲካዊ ጥቅም ቢኖረውም እንኳን ወሬውን አጋግሎ ማዳረሱ ምን ታስቦ ነው በሚል የሚዲያዎችንም ሆነ የመንግሥትን ተግባር ለማሳጣት የሞከሩ ጊዜ አልፈጀባቸውም ነበር።

የመንግሥት አካላት፣ ግለሰቡ ብዙ ደጋፊ በአገሩ እንዳለው በመግለጽ የ “#በቃ” ንቅናቄ ደጋፊ እንደሆነ፣ እንዲሁም ወጣት እንደመሆኑ የኢትዮጵያን ወጣት መሪ ለማገዝ እንደመጣ አስወርተዋል። የደቡብ አፍሪካ ሶዌቶ ከተማ ወጣቶችን በማስተባበር ምክር ቤት መሥርቶ ይመራቸዋል በማለት፣ ማኅበራዊ ፍትሕን ለማስፈን ዘመቻ እንደጀመረ ወጣት አድርገው አቅርበውታል። የማኅበረሰብ አንቂ በማለትም ለማንቆለጳጰስ ቢሞከርም ኋላ ላይ የወጣበትን መረጃ ለማስተባበል የቻለ አልነበረም።

ግለሰቡ በውጭ ዜጋዎች ላይ ያለውን ጥላቻ በግልጽ ከማሳየቱ በላይ፣ ዝነኛ መሆኑ እንጂ እነማንን እንደሚጠላ. እዚህስ መጥቶ ማንን ምን ሊያስተምር እንደሚችል፣ ምንም የተባለ ነገር የለም። ማን ወጪውን ሸፍኖ እንዳመጣውም ሆነ ለምን እሱ እንደተመረጠ ባይነገርም፣ እዚሁ መጥቶ የተለመደ ቅስቀሳውን እንዳልተወ የጻፈውን ጠቅሰው ዕርማት ይወሰድበት ያሉ አሉ። ደቡብ አፍሪካ ለደቡብ አፍሪካውያን በሚል መፈክር አዲሱ የፈረንጆቹ ዓመት የአብዮት ዘመን እንደሚሆን በይፋ የሚቀሰቅስን ሰው፣ የፍትሕ ታጋይ አድርጎ ማቅረቡ ለደቡብ አፍሪካውያን፣ ለመንግሥታቸውና ለሌሎች አፍሪካውያን ምን አይነት መልዕክት ያስተላልፋል የሚለው እንዲጤን የጠየቁ በርካቶች ናቸው።


ቅጽ 4 ቁጥር 166 ታኅሣሥ 30 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!