የእለት ዜና

ፀደይ ባንክ በቀጣይ ሦስት ወራት ውስጥ ሥራ እንደሚጀምር ተነገረ

ፀደይ ባንክ ወደ ባንክነት ደረጃ ካደጉ የማይክሮ ፋይናንስ ወይም ብድር እና ቁጠባ ተቋማት ግንባር ቀደሙ የአማራ ብድር እና ቁጠባ ተቋም ሲሆን፣ በቀጣይ ሦስት ወራት ውስጥ የሙከራ ሥራውን እንደሚጀምር ማወቅ ተችሏል።
በ1989 በወጣው የማይክሮ ፋይናንስ ሕግ መሠረት፣ የኢትዮጵያ የመጀመሪያው የፋይናንስ ተቋም ሆኖ የተቋቋመ ሲሆን፣ በአሁኑ ሰዓት ሥራን ለመጀመር የሚያሰችለውን ፍቃድ ከብሔራዊ ባንክ ወስዶ የቦርድ አመራሮች እና ጊዜያዊ ሥራ አስፍጻሚ ያስቀመጠ መሆኑ ታወቋል፡፡ በተጨማሪም ለባንኩ ፕሬዝዳንትነት የሚሆን ዕጩ እየተፈለገ መሆኑ ለማወቅ ተችሏል።

የባንኩ የፋይናንስ ሥራ ኃላፊ ወልደትንሳኤ እሽቴ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ ፀደይ ባንክ ቀደም ብሎ ወደ ሥራ መግባት ያልቻለው 471 ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች እና አንድ ሺሕ 107 ሳተላይት ጽሕፈት ቤቶች ሙሉ በሙሉ በአማራ ክልል የሚገኙ እና በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው በመሆኑ ነው፡፡ በተለይም በመጀመሪያው ድንገተኛ ጥቃት ጎንደር እና ሰሜን ወሎ የሚገኘው ተቋም ሙሉ ለሙሉ ወድሟል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡
“የወደመውን ንብረት ለማወቅ ኮሚቴ ተዋቅሮ ጥናት እየተከሄደ ነው” ሲሉ ወልደትንሳኤ እሽቴ ጨምረው ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እንደ አማራ ብድር እና ቁጠባ ታቋም ያሉ ተቋማት ወደ ባንክ መሸጋገር የሚችሉበትን ዕድል የከፈተ መመሪያ ይፋ ያደረገው በነሐሴ 2012 ነበር።
በገጠር እና በከተማ በግብርና እና በሌሎች ሥራዎች፣ እንዲሁም በጥቃቅን እና አነስተኛ የሥራ መስኮች ለተሠማሩ ሰዎች ብድር መሠጠት ዋና ዓላማቸው ሆኖ ከተቋቋሙ የኢትዮጵያ አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት፤ በ24 ወራት ውስጥ ወደ ባንክ እንዲሸጋገሩ ይኸው መመሪያ ይፈቅዳል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ይፋ ባደረገው መመሪያ አሁን ወደ ባንክ በሚያድጉት ተቋማት ላይ የመንግሥት ድርሻ ወይም የክልል እና የከተማ አስተዳደር ድርሻ ከ70 በመቶ መብለጥ የለበትም ይላል። 30 በመቶውን ደግሞ ለግል ባለሀብቶች ክፍት እንደሚያደርጉ ተጠቁሟል። ይኸ ደግሞ የግል ካፒታልን በማመንጨት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያበረክታል ሲሉ የባንክ እና ፋይናንስ ሴክትር ባለሙያ አድም መሐመድ ለአዲሰ ማለዳ አስርድተዋል።

የ9.2 ቢሊዮን ብር ካፒታልና 36 ቢሊዮን ብር ጠቅላላ ሀብት ያለው ተቋሙ፣ 37 ወለል ከፍታ ያለው የዋና መሥሪያ ቤቱን ሕንጻ ልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ ዘጠኝ ሠንጋ ተራ አካባቢ እየገነባ ይገኛል፡፡ ሕንፃው የሥራ ቦታ ሆኖ ከማገልገሉም ባሻገር፣ ለተለያዩ ተቋማት ለምሳሌ ለኢንሹራንስ፣ ለባንክና ለሌሎች ልዩ ልዩ አገልግሎቶች ኪራይ የሚውል ይሆናል ሲሉ የባንኩ ኃላፊ ተናግረዋል።

በ4024 ካሬ ሜትር ቦታ ያሚያርፈው ሕንጻ፣ አጠቃላይ ወለሎቹ 76,568 ካሬ ሜትር ስፋት የሚኖራችው ሲሆን፣ የሕንጻውን ፕሮጀክት በ 2.09 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጭ ለመገንባት መጀመሪያ ውል ተይዞ የነበረ ቢሆንም ፣ በዲዛይን ማሻሻያ ለውጥ ምክንያት አሁን ዋጋው ከ2.41 ቢሊዮን ብር በላይ ከፍ ብሏል፡፡

የሕንፃው ተቋራጭ ‹ዊ ዩ ኮርፖሬሽን› የሚባል የቻይና ኩባንያ ሲሆን፣ አማካሪ ድርጅቱ ደግሞ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን፣ ዲዛይንና ሱፐርቪዥን ሥራዎች ኮርፖሬሽን መሆኑን የፋይናንስ ኃላፊው ገልጽዋል። የዋና መሥሪያ ቤቱ ሕንጻ በኅዳር ወር ተጠናቆ መረከበ የነበረበት ቢሆንም፣ በውጭ ምንዛሬ ዕጥረት ምክንያት ሥራው በተፈለገው መጠን እንዳልተከናወነ ኃላፊው ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 166 ታኅሣሥ 30 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!