የእለት ዜና

የልማታዊ “ሴፍቲኔት” መረጃን ለማስተዳደር የተዘጋጀው ቴክኖሎጅ በ“ሰርቨር” ዕጥረት ወደ ሥራ አልገባም

የከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔት መረጃዎችን በዘመነ መልኩ ለማስተዳደር ያስችላል ተብሎ የነበረው መተግበሪያ (Management Information System)፣ በ“ሰርቨር” ዕጥረት ምክንያት እስካሁን ወደ ሥራ አለመግባቱ ተሰማ።
የቀድሞው የፌዴራል የሥራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ፣ በ2014 በተደረገው አዲስ የመንግሥት ምሥረታ ወደ ከተማ ልማትና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር፣ እንዲሁም ወደ ሥራና ክህሎት ተከፍሏል። ኤጀንሲው ከመክሰሙ በፊት በፌዴራል የከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ፣ የወጣቶች ሥራ ፈጠራ ፕሮጀክት፣ እንዲሁም የከተሞች የልማት ሴፍቲኔት ፕሮጀክት ሥራ መረጃዎችን ዘመናዊ በሆነ መልኩ ማስተዳደር የሚያስችል መተግበሪያ ተሠርቶ ተጠናቆ ወደ ሥራ እንደሚገባ ተገልጾ ነበር።

ይሁን እንጂ፣ ኤጀንሲው ለኹለት ሲከፈል ወደ በከተማ ልማት ሚኒስቴር ከተካተቱ የሥራ ክፍሎች ውስጥ ካሉ የቴክኖሎጅ ባለሙያዎች አዲስ ማለዳ የደረሳት መረጃ የሚያመላክተው፣ የልማታዊ ሴፍቲኔት መረጃን በዘመነ መልኩ ማስተዳዳር ያስችላል ተብሎ የነበረው መተግበሪያ እስካሁን ወደ ሥራ አለመግባቱን ነው።

ዘመናዊ መተግበሪያውን ሥራ ለማስጀመር የሚያስችሉ ኹሉም ቴክኒካዊ ሥራዎች ቢጠናቀቁም፣ ሥርዓቱ (ሲስተሙ) ሙሉ ለሙሉ ወደ ሥራ እንዲገባ የሚያስችል የሰርቨር አቅርቦት ባለመኖሩ፣ ዘመናዊ የልማታዊ ሴፍቲኔት መረጃ መተግበሪያው ወደ ሥራ አለመግባቱን የቴክኖሎጅ ባለሙያው ጥላሁን ከበደ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ሌሎች ሥራዎች ስለተጠናቀቁ ሥራውን መጀመር ይቻላል የሚሉት ጥላሁን፣ የሰርቨር አለመኖር ግን መተግበሪያው ሥራ ላይ እንዳይውል መሰናክል ሆኗል ሲሉ ገልጸዋል።
እንደ ጥላሁን ገለጻ ከሆነ፣ የቴክኖሎጅ ባለሙያዎቹ ለድርጅቱ ማኔጅመንት ሰርቨሩን እንዲገዛ ወይም በውሰት እንዲያመጣ ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን፣ ይህ ዘገባ እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስ ግ ምላሽ እንዳላገኙ ነው ለአዲስ ማለዳ የገለጹት።
የልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮጀክት መረጃ በዘመነ መልኩ ለማስተዳደር የሚረዳው መተግበሪያ በሰርቨር ዕጥረት ምክንያት እስካሁን ወደ ሥራ ባይገባም፣ ሌሎች ኹሉም ሥራዎች ስለተጠናቀቁና በሙከራም ስለተረጋገጡ ሰረቨሩ ከተገዛ በኋላ ሥርዓቱን (ሲስተሙን) መጀመር እንደሚቻል ጥላሁን ገልጸዋል።

ዘመናዊ መተግበሪያው ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ ሲያልቅና ወደ ተግባር ሲገባ፣ እስካሁን የሚሠሩባቸው ሙሉ የልማታዊ ሴፍቲኔት ባህላዊ ማስተዳደሪያ ሥራዎችን በቀላልና ቀልጣፋ በሆነ መንገድ ለማከናወን የሚያስችል መሆኑን መገንዘብ ተችሏል።
ይህ ዘመናዊ መተግበሪያ፣ ከሴፍቲኔት ተመዝጋቢዎች ጀምሮ ያሉ እስከዛሬ ሲከናወኑ የነበሩ አድካሚና ጊዜ የሚጨርሱ ተግባራትን በ‹ኢንተርኔት› በመጠቀም አቀላጥፎ ለመሥራት ያስችላል ሲሉ ባለሙያው ለአዲስ ማለዳ አብራርተዋል።

ባለሙያው አያይዘውም፣ አዲስ የሚጀመረው የመረጃ መተግበሪያ ሥርዓት የሴፍቲኔት ተመዝጋቢዎችን በሥርዓት (ሲስተም) ለመመዝገብ፣ እስካሁን በአካል በመገኘት ሲደረግ የነበረውን የሴፍቲኔት ክፍያን በባንክ ቤት ለመላክ፣ የተለያዩ የግዥ ተግባሮችን ለመቆጣጠር፣ እንዲሁም የሚከናወኑ ሥራዎችን ከሥር ከሥር ለመገምገም ያስችላል ነው ያሉት።

ከዚህም በተጨማሪ፣ ዘመናዊ መተግበሪያው የሴፍቲኔት ዕርዳታ ተሳታፊዎችን ምዝገባ በማሻሻል የታለመለትን ሚና መጫወት ያስችላል የሚሉት ጥላሁን፣ ይኸውም የትኛው ግለሰብ የከፋ ችግር ኖሮበት በሴፍቲኔት ምዝገባው መካተት እንዳለበት፣ እንዲሁም የትኛው ግለሰብ መካተት ሳይኖርበት እንደተመዘገበ ሥርዓቱ (ሲስተሙ) አጣርቶ (ፊልተር አድርጎ) ለመሳየት ስለሚያስችል ነው ሲሉ ነው ያብራሩት።

በዚህም የመተግበሪያ ሥርዓቱ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው ግለሰቦች ሳይመዘገቡና በተቃራኒው ዕርዳታ ሳያሻቸው ድርብ ገንዘብ ለማግኘት የተመዘገቡ ሰዎችን ለይቶ ለማውጣት የሚያስችል፣ የተጭበረበረ ሥራ እንዳይኖርና የልማታዊ ሴፍቲኔቱን ዓላማ በትክክለኛው አሠራር ለማስኬድ የሚግዝ መሆኑን ነው ከገለጻው መረዳት የተቻለው።

መተግበሪያዉን እያበለጸገ የሚገኘዉ አፍሪኮም ቴክኖሎጂ የግል ኩባንያ ሲሆን፣ በነባር 72 ከተሞችና በተጨማሪ 11 ከተሞች፣ በአጠቃላይ በ83 ከተሞች መተግበሪያዉ ተግባራዊ እንደሚሆንና ሥራው የተጀመረው ከዓለም ባንክ ጋር በተደረገ ስምምነት እንደሆነ መገንዘብ ተችሏል።


ቅጽ 4 ቁጥር 166 ታኅሣሥ 30 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!