የእለት ዜና

የአጎዋ ገበያ “ሳንጠቀምባቸው” በቆዩ የገበያ ዕድሎች ይተካል ተባለ

ኢትዮጵያ ምርቷን ወደ አሜሪካ ገበያ ትልክ የነበረበትን እና በቅርቡ የታገደውን የአጎዋ ገበያን፣ ከዚህ በፊት ከቀረጥ ነጻ በሌሎች አገራት ለኢትዮጵያ ተሠጡ የገበያ አማራጮች እንደሚተኩት የንግድና ቀጠናዊ ትሥሥር ሚኒስቴር ለአዲስ ማለዳ ገለጸ።

ሠፊ ከሆነው የአፍሪካ ገበያ በላይ በርካታ ያልተጠቅምንባቸው የገበያ አማራጮች አሉ የሚለው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ፣ የአሜሪካን ገበያ በተለያዩ ምክንያቶች ምርጫችን አድርገን የቆየን ቢሆንም፣ አሁን ላይ የአጎዋ ገበያን ለመተካት ከዚህ በፊት ለኢትዮጵያ ተሰጥተው ነገር ግን ያልተጠቀምንባቸው ገበያዎችን ለመጠቀም ጥናት ተካሂዷል ሲል ነው ያስታወቀው።

የንግድና ቀጠናዊ ትሥሥር ሚኒስቴር የንግድ ግንኙነትና ድርድር ዳይሬክተር ጀነራል ሙሴ ምንዳኤ ለአዲስ ማለዳ በሰጡት ማብራሪያ፣ ከ2001 ጀምሮ ከቀረጥ እና ከኮታ ነጻ ከጦር መሣሪያ ውጭ ማንኛውንም ምርት ወደ አውሮፓ እንድንልክ የገበያ አማራጭ ተሠጥቶናል ነው ያሉት።

ይህም ትልቅ የገበያ አማራጭ መሆኑን ጠቅሰው፣ በአጎዋ በኩል ወደ አሜሪካ ይላኩ ለነበሩት የጨርቃ ጨርቅ እና የአበባ ምርቶች ሠፊ የገበያ መዳረሻ መሆኑን አንስተዋል።

እንዲሁም፣ በተመረጡ ምርቶች ላይ ከጃፓን፣ ካናዳ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬት እና ቱርክ ተመሳሳይ የገበያ ዕድሎች መኖራቸውን ካነሱ በኋላ፣ ከኢትየጵያ ወደ ጃፓን ከሚላኩ ምርቶች ውስጥ 90 በመቶ የሚሆኑት ከቀረጥ ነጻ ናቸው ብለዋል።

ቱርክም ወደ 4000 የሚጠጉ የተመረጡ የምርት ዓይነቶችን ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ ከ20006 ጀምሮ የፈቀደች በመሆኑ፣ በቀጣይ ገበያውን በሥፋት ለመጠቀም መታሰቡን አመላክተዋል።

የሰሜን አሜሪካዋ አገር ካናዳም ከወተት ምርቶች በስተቀር ለሌላ ምርቶች ከቀረጥ ነጻ የገበያ ዕድል የሠጠች እና በተለይ ለኢትዮጵያ ቆዳ ምርት ውጤቶች ይበልጥ የገበያ መዳረሻ እንደሆነች ነው ያሳዩት።

የአፍሪካ ገበያን አጠቃቀም በተመለከተ ኃላፊው በሰጡት ሐሳብ፣ በነጻ ገበያ ትሥሥር የቆዳ ምርቶች ወደ ተለያዩ አፍሪካ አገሮች እየተላኩ ሲሆን፣ በተለይ ለጫማ ምርቶች በቂ ገበያ መኖሩን ጠቁመዋል። ሆኖም ብዙ የአፍሪካ አገራት ጨርቃ ጨርቅ ስለሚያመርቱ ለጨርቃጨርቅ ምርቶች የአውሮፓ ገበያን መጠቀም የተሻለ አመራጭ እንደሆነ ነው የተናገሩት።

በዚህም የጨርቃጨርቅና አበባ ምርቶች ወደ ጣሊያን፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ኔዘርላንድ፣ ቤልጅየም እና እንግሊዝ ይላካሉ ብለዋል። በተጨማሪም፣ የኢትዮጵያን ምርቶች ለመግዛት ፍላጎት ያላቸው 15 የእስያ አገራት መኖራቸውን ገልጸው፣ የቅባት እህሎችም በዋናነት ወደ ቻይና፣ እስራኤል እና ፓኪስታን እንደሚላኩ አንስተዋል።

ዳይሬክተር ጀኔራሉ ምርታቸውን በአጎዋ ገበያ ይሸጡ የነበሩ ኢትዮጵያ ውስጥ ላሉ አምራቾች እስካሁን በደንብ ያልተጠቀምንበት ሠፊ የገበያ አማራጭ መኖሩን አስረድተናቸዋል በማለት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር ባንቲሁን ገሰሰ በበኩላቸው፣ በተለይ የኢትዮጵያ ጨርቃጨርቅ ምርቶችን የሚገዙ የረዥም ጊዜ የገበያ ትሥሥር ያላቸው ትላልቅ የውጭ ኩባንያዎች አሉ። ይህም ብቻ ሳይሆን ሠፊ የአፍሪካ ገበያ መኖሩን ተመልከተናል በዚህም ሥራ የሚያቆም ኩባንያ አይኖርም ብለዋል።

አክለውም፣ የአፍሪካን ገበያ ከመላመድ እና ደንበኛ ከማፍራት በተጨማሪ፣ ከምሥራቁ ዓለም አገራት፣ ከወዳጅ አገሮች፣ እንዲሁም ከወዳጅ ገዥ ካምፓኒዎች ጋር የበለጠ የገበያ ትሥሥር በመፍጠር ሠፊ የገበያ አማራጭ ለመፍጠር መታሰቡን ነው የጠቆሙት።

ተመሳሳይ ጽሁፍ 

“አሜሪካ ኢትዮጵያን ከአጎዋ ተጠቃሚነት ያስወጣችብትን ውሳኔ ልታጤነው ይገባል”፡-የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር – ዜና ከምንጩ (addismaleda.com)

ከአጎዋ መታገድ የሚያስከተለው የኢኮኖሚ ጫና ምን ያህል ነው? – ዜና ከምንጩ (addismaleda.com)

የ‹አጎዋ› ማስፈራሪያ – ዜና ከምንጩ (addismaleda.com)

ያለፋል እንጂ ያልፋል! – ዜና ከምንጩ (addismaleda.com)


ቅጽ 4 ቁጥር 166 ታኅሣሥ 30 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!