የእለት ዜና

“ተጠርጣሪዎች ክሳቸው የተቋረጠው ዐቃቢ ሕግ በተለያዩ ምክንያቶች ክሱን መቀጠል እንደማይፈልግ በማስታወቁ ነው።”፡- የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት

ማክሰኞ ጥር 3/2014 (አዲስ ማለዳ) በቅርቡ በሶስት የተለያዩ መዝገቦች ክሳቸው የተቋረጠ ተጠርጣሪዎች ዐቃቢ ሕግ በተለያዩ ምክንያቶች ክሱን መቀጠል እንደማይፈልግ በማስታወቁ መሆኑን የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ገለፀ።

ታህሳስ 28፣2014 በሙሉ ወይንም በከፊል በተከሳሾች ላይ በሶስት መዝገቦች የቀረቡ ክሶችን እንዲቋረጡ የፍትህ ሚኒስትሩ ለሚመለከተው ችሎት ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት ሕጋዊ ስርዓቱን ተከትለው መስተናገዳቸውን ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

በመሆኑም የክስ ሂደታቸው እንዲቋረጥ ከቀረቡት በከሳሽ ዐቃቤ ሕግ እና በተከሳሾች እነ ጀዋር ሲራጅ መሀመድ (በድምሩ 20 ተከሳሾች)፣ በከሳሽ ዐቃቤ ሕግ እና በተከሳሾች እነ እስክንድር ነጋ (በድምሩ 7 ተከሳሾች) እንዲሁም በከሳሽ ዐቃቤ ሕግ እና በተከሳሾች እነ ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል (በድምሩ ስድስት ተከሳሾች ላይ የቀረበው ክስ) የሚመለከቱ እንደሚገኝበት ፍርድ ቤቱ አመልክቷል፡፡

የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት የሕገ-መንግስት እና ሽብር ጉዳዮች አንደኛ ወንጀል ችሎት የፍትህ ሚኒስትሩን ማመልከቻ በመመርመር በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 943/2008 አንቀጽ 6(3)ሠ መሰረት ክሱን ያነሱ መሆኑን ካረጋገጠ በኋላ ተከሳሾቹ እንዲለቀቁ “ተከሳሾች በሌላ ወንጀል የማይፈለጉ ከሆነ” ከእስር እንዲለቀቁ ትዕዛዝ ለማረሚያ ቤት አስተላልፎ ተፈጻሚ መሆኑንም በመግለጫው አመልክቷል፡፡

አሁን በስራ ላይ ባለው ሕግ መሰረት ከሳሽ ዐቃቢ ሕግ በተለያዩ ምክንያቶች ክሱን መቀጠል እንደማይፈልግ ሲያመለክት ፍ/ቤቱ የክስ ይቋረጥ ጥያቄውን በመቀበል በእስር ላይ የሚገኙት ተጠርጣሪዎች እንዲለቀቁ የታዘዘ መሆኑ ሕጋዊ አሰራር መሆኑ ግንዛቤ እንዲፈጠር በሚል መግለጫውን እንዳወጣ አስታውቋል፡፡

ፍ/ቤቱ በነጻነት የመስራት ደረጃ ላይ ለመድረሱ ከዚህ በፊት በተጠርጣሪዎች ሰብዓዊ እና የሕክምና አገልግሎት ጥያቄ በተመለከተ፣ እንዲሁም የምስክሮችን ከመጋረጃ ጀርባ ይሰሙ/ አይሰሙ የሚሉትን እና ሌሎች አስቸጋሪ ክርክሮችን ዳኞቻችን ተገቢ ነው ያሏቸውን ብይን ጭምር በማሳረፍ ሲከናወን እንደነበርም አስታውሷል፡፡

:- ሙሉ ማብራሪያው ከስር ተያይዟል።
____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!