የእለት ዜና

የማዕድን ሚኒስቴር ከስምንት የከሰል ድንጋይ አውጪ ኩባንያዎች ጋር ስምምነት ተፈራረመ

ሐሙስ ጥር 5 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የማዕድን ሚኒስቴር 6 ቢሊየን ብር ካፒታል ካላቸው 8 የድንጋይ ከሰል አውጪ ኩባንያዎች ጋር ስምምነት ተፈራርሟል።

ኩባንያዎቹ በሙሉ አቅማቸው ወደ ሥራ ሲገቡ ኢትዮጵያ ከውጭ የምታስገባውን የከሰል ድንጋይ ሙሉ ለሙሉ ያስቀራሉ ነው የተባለው።

በስምምነቱ ወቅት የማእድን ሚኒስትሩ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ኩባንያዎቹ ፕሮጀክቶቹ አገራዊ መሆናቸውን ተገንዝበው በተቀመጠለት ጊዜ እንደሚያጠናቅቁ ተስፋ አለኝ ብለዋል።

ኢ/ር ታከለ ከውጪ የሚገቡ የማዕድን ግብአቶችን በአገር ውስጥ ለመተካት ያለው ሥራ በፍጥነት በተግባር እየተገለፀ ይገኛል ማለታቸው ይታወሳል።

ከትላንት በስትያ ጥር 03 2014 ከብረት አምራቾች፣ ሙያተኞች፣ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች እና የተለያዩ ባለ ድርሻ አካላት ተውጣጥቶ ከተቋቋመ ሀገራዊ የብረት ምርት ስትሪግ ኮሚቴ ጋር ሥራው የደረሰበት ሂደት ተገምግሟል።

በቀጣይም የመጀመሪያ የቅድመ አዋጪነት ጥናት እና የፋብሪካ ግንባታ ቦታ መረጣ በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅም ከስምምነት ላይ መደረሱን ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።

የብረት ምርትን ሙሉ በሙሉ በአገር ውስጥ ለመተካትም የሶስት ዓመት የፕሮጀክት ጊዜ መቀመጡም ተገልጿል።

ፕሮጀክቱን የሚያስተባበር “ፕሮጀክት ፅህፈት ቤት” በማዕድን ሚኒስቴር አስተባባሪነት መዋቀሩን ያስታወቁት ኢ/ር ታከለ ሥራውም በመንግስት፣ የአገር ውስጥ ባለሀብቶችና በውጪ ባለሀብቶች በጋራ የሚከናወን ይሆናል ብለዋል።
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!