የእለት ዜና

“ንፁሃን ተመርጠው ይገደላሉ ሐብት ንብረታቸው ይወድማል ”፦በሸኔ ቡድን ጥቃት የደረሰባቸው የጉዱሩ ወረዳ ነዋሪዎች

አርብ ጥር 6 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉዱሩ ዞን ጉዱሩ ወረዳ ንፁሃን ተመርጠው ይገደላሉ፣ ሐብት ንብረታቸው ይወድማል፣ በቀያቸው በነፃነት መኖር አይችሉም ሲሉ በሽብርተኝነት የተፈረጀው የሸኔ ቡድን ጥቃት የደረሰባቸው ነዋሪዎች ተናገሩ።

የግለሰብ ቤቶች፣ የቀበሌ ጽ/ቤቶች፣ የአርሶአደር መሰረታዊ ማህበራትና ሌሎች ተቋማት በሽብር ቡድኑ መውደማቸውን ኢፕድ በአካባቢው በተለያዩ ቀበሌዎች በመገኘት ባደረገው ቅኝት ለማየት ችሏል።

በወረዳው በሮ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ታደሰ በላይና ባለቤታቸው በሕይወት ዘመናቸው ያፈሩት ሐብት በሽብር ቡድኑ ሙሉ በሙሉ ወድሟል። ይህን ጥቃት ያደረሱበት ዋነኛ ምክንያት ደግሞ የጥፋት ቡድኑ ታደሰ የያዙትን የጦር መሳሪያ በተደጋጋሚ እንዲሰጣቸው በጠየቁት መሰረት ሊያገኙ ባለመቻላቸው ብቻ ነበር።

‹‹ሕይወታችንን ለማትረፍ ስንል ምንም ሳንይዝ ከቤት ወጥተናል። በሕይወት ዘመኔ ያለእረፍት ቀን ከሌት ሰርቼ ያፈራሁትን ሐብት ሙሉ በሙሉ አውድመውብኛል›› ሲሉም ተናግረዋል።

ሰዎችን በመግደል፣ በማፈናቀል እንዲሁም ሕዝብን በማንገላታት ምንም አይነት ትግል የለም ያሉት ታደሰ ለኦሮሞ ሳይሆን በኦሮሞ ላይ ነው ትግል እያደረጉ የሚገኙት ብለዋል።

“ይህን የወደመብኝን ቤት ለመገንባት በርካታ ዘመናትን ስለፋ ቆይቻለሁ። ነገር ግን ሁለት ዓመት ሳልኖርበት ከነ ሙሉ ንብረቱ ይኸው ወደ አመድ ተቀይሮብኛል” በማለት ነበር የጥፋት ኃይሉ ያደረሰባቸውን በደል የገለፁት።

ሸኔ እኔ ላይ ብቻ ሳይሆን በመላው የአካባቢ ሰዎች ላይ ጉዳትና እንግልት በማድረስ የአካባቢው ነዋሪዎች ወደ ተለያዩ ቦታዎች እንዲፈናቀሉ ምክንያት መሆኑን ገልፀዋል።

በቀበሌው ሌላኛዋ የሽብር ቡድኑ ሰለባ ታቱ ደበላ ደግሞ ባለቤታቸው የአናፂነት ሙያ ያላቸው፣ ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ በሚሊሻ የአካባቢውን ሰላም ለማስከበር የሚተጉ ግለሰብ ናቸው። በዚህም ምክንያት ሽፍታው ቡድን ሲያሳድዳቸው መቆየቱን ተናግረዋል።

የሸኔ ቡድን እንዳያገኘኝ ስል ዛሬ አንድ የዘመድ ወይም የወገን ቤት ካደርኩ ነገ ደግሞ አድራሻዬን ካልቀየርኩ ይገድሉኛል በማለት ስንንከራተት ነው የከረምኩት። እነሱ ግን ቤቴ በመሄድ ከቤት ውስጥ ሁሉንም ቁሳቁስ ወደ ውጪ በማውጣት የሚጠቅማቸውን ዘርፈው ሌላኛውን አቃጥለውብኛል ብለዋል።

ቡልቶ ቶሌራ ሌላኛው የቡድኑ ሰለባ የሆኑ የቀበሌው ነዋሪ ሲሆኑ፤ እኚህ ግለሰብ በቀበሌው የሚሊሻ ታጣቂ በመሆናቸውና የቡድኑን ጥሪ ባለመቀበላቸው እንዲሁም የመንግሥትን መሳሪያ አሳልፈው ባለመስጠታቸው የመኖሪያ ቤታቸው ላይ ጥቃትና ዝርፊያ እንደደረሰባቸው ተናግረዋል።

ይህ ቡድን ንፁኃንንና በመንግሥት መስሪያ ቤቶች ውስጥ የሚሰሩ ሠራተኞችን በመምረጥ ይገደላል፤ ከዚህም ባሻገር ሐብት ንብረታቸው ያወድማል፣ በቀያቸውም በነፃነት መኖር ይነፍጋቸዋል ሲሉ ገልፀዋል።
____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!