የእለት ዜና
ከህወሓት ነጻ በወጡ በራያና አላማጣ አካባቢዎች ዳግም ጦርነት መጀመሩን ነዋሪዎች ገለጹ

ከህወሓት ነጻ በወጡ በራያና አላማጣ አካባቢዎች ዳግም ጦርነት መጀመሩን ነዋሪዎች ገለጹ

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀው ህወሓት ተቆጣጥሯቸው የነበሩ የራያ አካባቢዎች ከሳምንታት በፊት ነጻ መውጣታቸውን ተከትሎ ወደየቤታቸው የተመለሱ ነዋሪዎች፣ በድጋሚ ጦርነት ተከፍቶብናል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናገሩ።
የሕወሓት ቡድን ለአምስት ወራት ተቆጣጥሯቸው የነበሩ የራያ ቆቦና አንዳንድ የራያ አዘቦ አካባቢዎች ከሳምንታት በፊት በኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል ቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ተከትሎ ተፈናቅለው የነበሩ ነዋሪዎቹ ወደ ቤታቸው ቢመለሱም፣ ሰሞኑን ግን በድጋሚ ጥቃት እየተሠነዘረባቸው መሆኑን ነው የአካባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ የተናገሩት።

ሕወሓት ለአምስት ወራት ተቆጣጥሯቸው የነበሩት ዋጃ፣ ጥሙጋ፣ አዲስ ቅኝ የተሰኙት ቦታዎች ከሳምንታት በፊት ነጻ መውጣታቸውን ተከትሎ ነዋሪዎቹ ወደየቤታቸው መመለሳቸው ይታወሳል። ነገር ግን፣ ከባለፈው ታኅሣሥ 30/2014 ከጠዋቱ አራት ሰዓት ጀምሮ፣ በህወሓት ታጣቂ ቡድን በድጋሚ ጦርነት ተከፍቶብናል የሚሉት የአካባቢው ነዋሪዎች፣ ንጹኃን መሞታቸውን፣ ንብረት መዘረፉን፣ ቤት መቃጠሉን እና ዳግመኛ ለመፈናቀል መገደዳቸውን ገልጸዋል።

ያሬድ ደመና የተባሉ የአዲስ ቅኝ አካባቢ ነዋሪ፣ ታጣቂ ቡድኑ ከታኅሣሥ 30/2014 ጀምሮ አካባቢያቸው ላይ ጥቃት መሠንዘሩን የተናገሩ ሲሆን፣ በጥቃቱም የአምስት አርሶ አደሮች ሕይወት አልፏል ነው ያሉት።

“የገናን በዓል በጦርነት ውስጥ እየተሯሯጥን ነው ያሳለፍነው” ያሉት ያሬድ፣ ሞተው ቀብራቸው ከተፈጸመ አምስት ሰዎች በተጨማሪ፣ እስከ ጥር ኹለት 2014 ድረስ ሬሳቸው ያልተነሳ ሰዎች መኖራቸውን በአካባቢው ተገኝተው መመልከታቸውን ጠቁመዋል።
ከህወሓት በሚሠነዘረው ጥቃት ምክንያት አካባቢያቸውን ለቀው ከአራት ቤተሰቦቻቸው ጋር በቆቦ ከተማ እንደሚገኙ የጠቆሙት ሌላኛው የአዲስ ቅኝ ዜሮ አምስት ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አማረ ጥጋቡ በበኩላቸው፣ አዲስ ቅኝ የተባለው አካባቢ ከታኅሣሥ 30/2014 ጀምሮ በድጋሚ በህወሓት ቁጥጥር ሥር ነው ያለው ብለዋል።

ጥቃቱ የተጀመረው ከረፋዱ አራት ሰዓት ጀምሮ ነው የሚሉት አማረ፣ “በታጣቂ ቡድኑ አዲስ ቅኝ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና አባተ ገበየሁ የተባሉ ግለሰብ (የቀበሌው ሊቀ መንበር ናቸው) ቤት ተቃጥሏል። በአካባቢው ተተክሎ የነበረው የኔትወርክ ማሠራጫም ወድሟል፤ ከዚህ ቀደም የተረፈው የነዋሪዎቹ ንብረት እየተዘረፈ በመኪና እየተጫነ ነው” ብለዋል።

አዲስ ማለዳ በቆቦ ከተማ ዕውቀት ጮራ ትምህርት ቤት ተጠልለው ከሚገኙት የአዲስ ቅኝ ነዋሪዎች በተጨማሪ ከአላማጣ፣ ዋጃና ጥሙጋ የመጡ ሰዎችንም በስልክ አነጋግራለች። በዕውቀት ጮራ ከሚገኙት የአላማጣ ነዋሪዎች መካካል ሙሉጌታ አስማማው የተባሉት ግለሰብ “በታኅሣሥ 30/2014 ሙሃ ለንጫ፣ ሰሌን ውኃ፣ እንዲሁም ድንጋይ ቀበሌ በሚባሉት የራያ አላማጣ አካቢዎች ኃይለኛ ጦርነት ነበረ፤ በዚህም የአካባቢው ማኅበረሰብ ዳግም ተፈናቅሏል” ነው ያሉት።

ጥቃቱ ሲፈጸም የወገን ኃይል በአካባቢው እንደነበር የጠቆሙት ሙሉጌታ፣ “ተቃራኒ ቡድኑ ቆርጧቸው ሲገባ ወደ ኋላ በማፈግፈጋቸው፣ ወደ ቀያችን ከተመለስን ሳምንት ሳይሞላን በድጋሚ ተፈናቅለናል” ሲሉ የገጠማቸውን ችግር አብራርተዋል።
ሙሉጌታ አክለውም፣ “ከገና በዓል ማግስት ጀምሮ ጥቃቱ እንደቀጠለ ነው፤ ሴቶች እየተደፈሩ ነው፤ ንብረት እየወደመ ነው” ያሉ ሲሆን፣ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ንጹኅን ለሞት ተዳርገዋል ሲሉ ጠቁመዋል።

ነዋሪዎቹ፣ ይህ ችግር በድጋሚ የተፈጠረው ጦርነቱ ራያ አካባቢ ሲደርስ መከላከያ ሠራዊቱ ባለበት እንዲቆም ስለታዘዘ ነው ያሉ ሲሆን፣ ነገሩ በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ከቀጠለ ሠላምን ማረጋገጥ አይቻልምና መንግሥት መፍትሔ ሊሰጠው ይገባል በማለት አሳስበዋል።
የራያ አላማጣ ወጣቶችና ሕፃናት ጉዳይ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ገነት በርሔ በበኩላቸው፣ ማኅበረሰቡ ከገና በዓል ማግስት ጀምሮ ቤቱን ለቆ ወጥቶ ከፊሉ በቆቦ ከተማ በዘመድ ቤት፣ ከፊሉ ደግሞ በድንጋይ ቁልል አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተጠግቶ ነው ያለው በማለት ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

በድንጋይ ቁልል ትምህርት ቤት ብቻ ሦስት ሺሕ ተፈናቃዮች አሉ የሚሉት ኃላፊዋ፣ የቆቦ አካባቢ ነዋሪም ተፈናቅሎ የኖረ ስለሆነና የመብራትም ሆነ የወፍጮ አገልግሎት ስለሌለው ድጋፍ ማድረግ አልቻለም። አዲስ የሚገቡም ተፈናቃዮችም ስላሉ አሁን ላይ የተፈናቃዮች ቁጥር እየጨመረ ነው ብለዋል።

አዲስ ማለዳ ለችግሩ መፍትሔ ለማምጣት ምን እየተደረገ እንደሆነ ምላሽ ፈልጋ ለቆቦ ከተማ ከንቲባ አዲሱ ወዳጆ (ዶ/ር) በተደጋጋሚ ስልክ ብትደውልም ስልክ ባለመመለሳቸው ምላሻቸውን ማካተት አልቻልም።

ተመሳሳይ ርዕሶች

ነጻ በወጡ አካባቢዎች የውኃ ዕጥረት ለመቅረፍ ውኃ በቦቴ ለማኅበረሰቡ እየቀረበ ነው ተባለ – ዜና ከምንጩ (addismaleda.com)

በአማራ ክልል የወደሙ የጤና ተቋማትን ሥራ ለማስጀመር ጥናት እየተካሄደ ነው – ዜና ከምንጩ (addismaleda.com)


ቅጽ 4 ቁጥር 167 ጥር 7 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!