የግድቡ ስፋት የጣናን ሃይቅ አንድ ዐሥረኛ ያክላል
በሳምሶን ብርሃኔ
ለአራት ዓመታት አካባቢ የዘገየውና መንግስትን ከ11 ቢሊየን ብር በላይ ተጨማሪ ወጪ ያስወጣው በወልቃይት ወረዳ የሚገኘው የዛሬማ ሜይዴይ የመስኖ ግድብ ለማጠናቀቅ ተጨማሪ አንድ ቢሊየን ብር በጀት እንደሚያስፈልግ ተገለፀ።
በአፍሪካ ውስጥ ከሚገኙት ትላልቅ ግድቦች ተርታ ይሰለፋል ተብሎ የሚጠበቀው ዛሬማ ሜይዴይ ግድብ በሚቀጥሉት ሶስት ወራት ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት መሆን ቢጠበቅበትም ግድቡ የመጀመሪያ ዲዛይን የውሃ ማስተንፈሻ ባለመካተቱ ቀሪውን ሥራ ለማጠናቀቅ ተጨማሪ ሁለት ዓመታት እንደሚያስፈልገው ታውቋል።
በውሃ ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር የፕሮጀክቱ ጊዜያዊ ዋና አስተባባሪ ወንድምይብዛ ፀጋዬ ‹‹ፐሮጀክቱ ሲጀመር የተሟላ ዲዛይንና ጥናት አለመሠራቱ ለግድቡ መዘገየት ምክንያት ነው›› ብለዋል። ማስተንፈሻና የቀሩ ሥራዎችን ለመጀመር ቅድመ ሁኔታዎች የተጠናቀቁ ሲሆን በአሁኑ ወቀት የግድቡ አጠቃላይ አፈፃፀም 90 ነጥብ 59 በመቶ ደርሷል በማለት አክለዋል።
በመላ አገሪቱ በፌደራል ደረጃ እየተከናወኑ ካሉት ስድስት የግድብና የመስኖ ዝግጅት ፕሮጀክቶች መካከል ትልቁ እና በዓይነቱ ልዩ የሆነው ዛሬማ ማይዴይ የተጀመረው በ2003 በስኳር ኮርፖሬሽን ሲሆን ለማጠናቀቅ ሦስት ዓመታት ይወስዳል ተብሎ በመጀመሪያ ታቅዶ ነበር። ይሁንና ኮርፖሬሽኑ ግድቡን በታቀደው ጊዜ ባለማጠናቀቁ በ2009 ለውሃና መስኖ ኢነርጂ ሚኒስቴር ለማስረከብ ተገዷል። በወቅቱም በፓርላማ 3.2 ቢሊየን ብር በተፈቀደ ተጨማሪ በጀት ሚኒስቴሩ ግንባታውን መጀመሩ ታውቋል።
የዛሬማ ሜይዴይ ፕሮጀክት ዋና ሥር ተቋራጭ በስኳር ኮርፖሬሽን የተቀጠረውና በኤፈርት ስር ካሉ ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነው ሱር ኮንስትራክሽን ሲሆን ንዑስ የሥራ ተቋራጩ ደግሞ የቻይናው ጂያንዢ ዋተር እና ሃይድሮፓወር የተባለው ድርጅት ናቸው።
ፕሮጀክቱ ከአዲስ አበባ በ1ሺ 300 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በትግራይ ክልል በምዕራባዊ ዞን ወልቃይት ወረዳ የሚገኝ ሲሆን ያረፈበት አካባቢ በደርግ ጊዜ የሕወሀት ታጋዮች ማሰልጠኛ ቦታ መሆኑን የታሪክ ድርሳናት ያሳያሉ።
የመስኖ ግድቡ ግንባታ 50ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የሸንኮራ አገዳን ለማምረትና በቀን 24ሺህ ቶን አገዳ የመፍጨት አቅም ላለው የስኳር ፋብሪካ የውሃ ምንጭ እንዲሆን ታልሞ መጀመሩ ታውቋል። ውሃ የመያዝ አቅሙ የጣናን ሐይቅ አንድ ዐሥረኛ የሚያክል ሲሆን ወደ 35 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር ይጠጋል። የግድቡ የውሃ ምንጮች ዛሬማ ወንዝና ገባሩ የዱኩኮ ወንዝ ሲሆኑ ተከዜ ወንዝም ከግድቡ ስድስት ኪ.ሜ ርቀት ላይ ይገኛል።
በተጨማሪም የግድቡ ግንባታ ባልተሟላ ዲዛይን ወለታ ተፈርሞ የተጀመሩ መሆኑ የተለያዩ የፌደራል ኦዲተር መስሪያ ቤት ኦዲት ሪፖርትና ሌሎች መረጃዎች ያሳያሉ። <<በተጨማሪም ግንባታው ከመጀመሩና በጀት ከመለቀቁ በፊት ዝርዝር የቅድመ አዋጭነት ጥናት መሠራት የሚገባው ቢሆንም አልተሰራላትም›› ሲሉ የመስኖ ባለሙያው ወንድምይብዛ ገልፀዋል። ፕሮጀክቱ ሥራ ከጀመረ በኋላም በስትዲዮ ጋሊ ኢንጀነሪያ አማካሪ ድርጅት የተሠራ የአዋጭነት ጥናት በሚመለከታቸው ባለሙያዎች ስለመገምገሙና ይሁንታ ስለማግኘቱ የሚስረዳ ማስረጃ በፌደራል ኦዲተር ተጠይቆ ሊቀርብ አለመቻሉ የመስሪያ ቤቱ ባለፈው ዓመት ሪፖርት ያሳያል።
የግድቡ መነሻ ወጪ 4.1 ቢሊየን ብር የነበረ ቢሆንም ነገር ግን በ 2009 ዓ.ም በተደረገ በሁለት የውጪ ድርጅቶች በተሠራ የዲዛይን ማሻሻያ መሠረት የፕሮጀክቱ አጠቃላይ ወጪ በከፍተኛ ሁኔታ አድጓል። ይህም፤ የፕሮጀክቱን ዋጋ መጀመሪያ ከነበረው 347.7 በመቶ ጨምሮ ወደ ብር 14.5 ቢሊዮን ከፍ በማለቱ የኮንትራት ውለታው እንደገና እንዲከለስ አስገድዷል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሚንስቴሩ በፓርላማ በተደረገ ስብስባ በፌደራል ኦዲተር መስሪያ ቤት መወቀሱ አይዘነጋም። በተጨማሪም አሸናፊ አላቸው የተባሉ የመስኖ ኢንጀነሪንግ ባለሙያ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፤ ‹‹ከግንባታ በፊት ጠለቅ ያለ ጥናት አለመደረጉ የግድቡ አዋጭነት አጠራጣሪ ያደርገዋል›› ብለዋል።
በርግጥ የዛሬማ ሜይዴይ የመስኖ ግድብ ላይ የታየው ጭማሪ በቁጥር ከፍ ያለ ቢሆንም ለአገሪቷ በአይነቱ የመጀመሪያ አይደለም። ከአሥር ዓመታት በኋላ ግንባታው ከሁለት ወራት በፊት የተጠናቀቀው በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን ፋርጣ ወረዳ የሚገኘው ርብ መስኖ ግድብ በ1.6 ቢሊዮን ብር በጀት ግንባታው የተጀመረ ቢሆንም በተያዘለት ጊዜ ገደብ ባለመጠናቀቁ፣ በጀቱ እስካለፈው ዓመት ጥቅምት 2010 ድረስ 3.7 ቢሊዮን ብር አድጓል። በተመሳሳይ መልኩ በግንባታ ላይ ያለው የመገጭ መስኖ ግድብ ከ 2.4 ቢሊየን ወደ 5.6 ቢሊየን አድጓል።
በመላ አገሪቱ በግንባታ የሚገኙ የመስኖና የግድብ ፕሮጀክቶች ሙሉ ለሙሉ ተጠናቀው ለኅብረተሰቡ አገልገሎት መስጠት ሲጀምሩ በአጠቃላይ 210ሺህ ሄክታር መሬት በማልማት ከ153 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ መሆኑን ከውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር የወጣው መረጃ ጠቁሟል። በተጨማሪም ሚኒስትሩ በኦሮሚያና በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ውስጥ በመገንባት ላይ ያለው የጊዳቦ የመስኖ ልማት ግድብ በዚህ ዓመት ለማጠናቀቅ አቅዷል። ግድቡ 20.80 ሜትር ከፍታ የሚኖረው ሲሆን ርዝመቱም 269 ሜትር እንደሚኖረው ጠቁመው፤ ግድቡ ሲጠናቀቅም 117 ነጥብ 82 ሚሊየን ሜትር ኩብ ውሃ የማጠራቀም አቅም ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል። ግድቡ ሲጀመር ሰባት ሺሕ ሔክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ የነበረ ሲሆን በኋላ ፕሮጀክቱ እንዲያድግና ዐሥር ሺሕ ሔክታር እንዲያለማ ተወስኗል፤ በዚህም ከ 100 ሺ በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ሊያደርግ እንደሚችል ተገልጿል። በተጨማሪም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በዘንድሮ የበጀት ዓመት በፌደራል ደረጃ አዲስ የመስኖና ግድብ ፕሮጀክት እንደማይጀመርና የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በማጠናናቅ ላይ ትኩረት ተሠጥቶ እንደሚሠራ ታውቋል።
በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ቦታዎች የሚገነቡ የመስኖ ፕሮጀክቶች በተወሰነላቸው ጊዜ መጠናቀቅ ባለመቻላቸው፣ አገሪቷን በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በማስወጣት ላይ ናቸው። በቅርቡ የብሔራዊ ፕላንና ልማት ኮሚሽን እነዚህን ችግሮች ለመፍታትና ከዚህ በኋላም የሚጀመሩ ፕሮጀክቶች በሥሩ እንዲያልፉ ራሱን የቻለ ዳይሬክቶሬት ማቋቋሙ አይዘነጋም።