ኢትዮጵያ እና ዓለም ዐቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ( IFRS) ትግበራ

0
1261

የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ አዋጅ 847/2007 ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ሲሆን ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን ያስገኛል የሚሉት ቶፊቅ ተማም፥ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሰጠው የሒሳብ አያያዝና ኦዲት ስርዓተ ትምህርት ውስጥ የዓለም ዐቀፍ ፋይናንስ ሪፖርቶች አዘገጃጀትና አቀራረብ እንዲሁም የኦዲት ደረጃዎች አለመካተት በዋና ተግዳሮትነት ጠቅሰዋል፤ ሌሎቹንም ዘርዝረዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በአገሪቱ ጥራት ያለው የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ስርዓት እንዲተገበር እንዲሁም የፋይናንስ ግልጽነት ይሰፍን ዘንድ በማሰብ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ አዋጅ 847/2007 አውጥቷል። አዋጁ በኀላፊነት የሚመራ እንዲሁም በገለልተኝነት ይቆጣጠር ዘንድ የኢትዮጵያ ሒሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ አቋቁሞ ወደ ሥራ ገብቷል። አዋጁን ተግባራዊ በማድረግ የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ጥራት ያለው የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ስርዓት በመዘርጋት የተመቸ የንግድና ኢንቨስትመንት በማበረታታት የሚኖረውን ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዲሁም የተጠናከረ የሒሳብ አያያዝና ኦዲት ሙያ፤ በአገሪቱ ማስፈን የኢኮኖሚ ዕድገቱን በመደገፍ በማበረታታት እና በማረጋጋት የሚጫወተውን ቁልፍ ሚና የተገነዘበ ነው። በዚህም መሰረት በአገር ውስጥ በሚገኙ ከፍተኛ የፋይናንስ ተቋማት እንዲሁም በግል፣ በመንግሥት በተለይ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች እና መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት ላይ ይህ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ አዋጅ አውጥቷል።

በአዋጁ መግቢያ ወጥ የሆነ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀት አቀራረብ ሕግ መኖሩ ያልተማከለ የነበረውን የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ በማማከል ግልጽነትና ተጠያቂነት የሚያጎለብት ነው። እንዲሁም የአገሪቱን የኢኮኖሚ ምሰሶዎችን ለመደገፍ የፋይናንስ ቀውስና የድርጅቶችን የውድቀት ሥጋት እንዲሁም ተያያዥነት ያላቸውን አሉታዊ የኢኮኖሚ ውጤቶች ለመቀነስ ከድርጅቶች የሚገኘውን የፋይናንስ መረጃ አቅርቦት የዓለም ዐቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት ደረጃን የጠበቀ ነው። ከፍተኛ ጥራት ያለውን የዓለም ዐቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ደረጃዎች ተቀብሎ በሥራ ላይ ማዋል የአገራችን ኢኮኖሚ ዕድገት እምቅ አቅም ለመጠቀምና አጠናክሮ ለማስቀጠል ወሳኝ ሚና ይጫወታል።

የእነዚህ ደረጃዎች መተግበር ዓለም ዐቀፍ ኢንቨስተሮች በአገራችን የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ የጥራት ደረጃ ላይ የሚኖራቸውን አመኔታ በመጨመርና ኢንቨስትመንትን በማበረታታት የኢኮኖሚ መረጋጋትን፤ የሀብት አስተዳደር ግልፅነት ብሎም ተጠያቂነት በተቋም እና በመንግሥት ደረጃ እንዲጠናከር በማድረግ በአገሪቱ የዕድገት አቅም ላይ ጥልቅ የሆነ ውጤት ለማምጣት ይረዳል። እንዲሁም በአጠቃላይ መልካም አስተዳደርን ለማሻሻል በመንግሥት በኩል የሚደረገውን ጥረት በማገዝ ረገድ ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገራት ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገትን ከማረጋገጥ አኳያ እንቅፋት እንደሆኑ የሚታወቁትን ሙስና እና የኪራይ ሰብሳቢነት ባሕሪያትን ለመቀነስ እንደሚያግዝ ቦርዱ ባዘጋጀው የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ መገንዘብ ይቻላል።

የዓለም ዐቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ደረጃዎች የአገራችን ቀደምት ተሞክሮ እንዲሁም ለአዋጁ መውጣት መንስኤ የሆነውን ጥናት ስንመለከት፤ በኢትዮጵያ የሚገኙ የተለያዩ የግል እና የመንግሥት ተቋማት የሚያዘገጁት የፋይናንስ ሪፖርት ዓለም ዐቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ነው የሚል መከራከርያ የተለያዩ በሙያው ላይ ያሉ አካላት ያቀርባሉ። ይሁንና የዓለም ባንክ እና የዓለም የገንዘብ ድርጅት የዓለም ዐቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አተገባበር ደረጃዎችን መነሻ በማድረግ በጋራ አጥንተው ባቀረቡት የጥናት ሪፖርት መሰረት ከሆነ፤ አሁን ያለው የሒሳብ አያያዝና እና የሪፖርት ስርዓት የዓለም ዐቀፍ ደረጃዎችን ያልተከተለ ነው።

ኢትዮጵያ የዓለም ዐቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት ደረጃዎች እንድትተገብር ካስገደዷት ምክንያቶች ማለትም ከዓለም ባንክ እና የዓለም የገንዘብ ድርጅት ጥናት በመለስ ሌላኛው ምክንያት ኢትዮጵያ ምንም ዓይነት የአካውንቲንግ ደረጃ የሌላት መሆኑ ነው። ይህም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳብ አለመቻሉ በዋነኛነት ሲጠቀስ፤ አበዳሪዎች፣ እርዳታ ሰጪዎች፣ የዓለም ዐቀፍ ተቋማት የዓለም ዐቀፍ ሪፖርት አቀራረብ ደረጃዎች እንደ ሌሎች አገራት እንዲተገብሩ መጠየቃቸው ሌላው ምክንያት ነው። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የኢኮኖሚ ዕድገት እያሣዩ እንዲሁም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እየጨመረ በሚገኝባቸው አገሮች ኢንቨስተሮችን ለመሳብ ግልፅ፤ እንዲሁም ታማኝ የሆነ ዓለም ዐቀፍ ደረጃን ያሟላ የሒሳብ ሪፖርት መሻታቸው በዋነኛነት ሲጠቀስ በአስተማማኝ እና ዓለም ዐቀፍ ደረጃዎችን በጠበቀ የሒሳብ ሪፖርት የሚሳቡ ኢንቨስተሮች በሚያከናውኗቸው የልማት ተግባራት ለኢኮኖሚ ዕድገት አዎንታዊ የሆነ ሚናም ይጫወታል።

ከዚህ በተጨማሪም አሁን ዓለም አንድ ወጥ በሆነ የአካውንቲንግ ደረጃ እንዲሁም ዓለም ዐቀፍ የሆነ የፋይናንስ ሪፖርት መጠቀም መጀመሩና ወጥ በሆነ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ቋንቋ መግባባት በመጀመሩ፤ ኢትዮጵያም የዚህ አካል እንድትሆን ያስችላታል።

የተለያዩ አገራት የዓለም ዐቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ስርዓት ተግባራዊ ማድረጋቸው የተለያዩ ጠቀሜታዎች አስገኝቶላቸዋል። ከእነዚህም ውስጥ በአገር ውስጥ የሚዘጋጁ የፋይናንስ መግለጫዎች በሚያስገኙት ተነፃፃሪ የፋይናንስ መግለጫዎች፤ ተነፃጻሪ ከሆኑ የተሻለ ኢንቨስትመንት ውሳኔ ለመስጠት ሲረዳ፤ ከሌሎች አቻ ዓለም ዐቀፍ ተቋማትም ጋር በቀላሉ ተነፃፃሪ እንዲሁም ተወዳዳሪ የፋይናንስ ሪፖርት ለማዘጋጀት ይረዳል።

በሪፖርት አቅራቢ አካላት በዓለም ዐቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አቀራረብ ደረጃዎች መሰረት የተዘጋጁ የተቋማት የፋይናንስ ሪፖርቶች ፍላጎት ላላቸው ሰዎች ግልፅ የሚሆንበት አሠራር መዘርጋቱ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የፋይናንስ ሪፖርት የግልፅነት ስርዓት ላልዳበረባቸው አገራት የፋይናንስ መረጃ ግልፅነት እና ተደራሽነትን ይጨምራል። ደረጃውን የጠበቀ በዓለም ዐቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አቀራራብ ደራጃን ተመርኩዞ የተሠራ ሪፖርት የሕዝብን አመኔታ ያገኛል። ከዚህ ባለፈም በአሳሳች የሒሳብ መግለጫዎች ምክንያት በሕዝብ ጥቅም ላይ ሊደርስ የሚችል ጉዳትን ሊቀንስ ይችላል ተብሎ ሲጠበቅ፤ የግብር ስርዓቱን ውጤታማነት በማሻሻል የአገር ውስጥ ገቢ የሚያሳድግ ይሆናል።

ይህን የዓለም ዐቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አቀራረብ ትግበራ ስርዓት ለመዘርጋት በተለያዩ የአገሪቱ ታላላቅ የፋይናንስ ተቋማት በአማካሪነት የተቀጠሩ ዓለም ዐቀፍ ድርጅቶች የእውቀት ሽግግር የሚገኝበትን ዕድል ይፈጥራል። እንዲሁም የተለያየ ሪፖርት ለተለያዩ አካላት በሚቀርበብበት ጊዜ ለተጨማሪ ወጪ ከመዳረግ የሚያድን ሲሆን የአክስዮን ገበያ ማዕከል ለማቋቋም አስቻይ ሁኔታን ይሆናል።

በዓለማችን ያሉ ያደጉ እና በማደግ ላይ ያሉ እንዲሁም የዓለም ዐቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት ደረጃዎችን ተግባራዊ ያደረጉ አገራት፤ ይህንን ትግበራ በሚያካሒዱበት ወቅት የተለያዩ ተግዳሮቶች ያጋጠሟቸው ሲሆን ኢትዮጵያም በዚህ ረገድ ተግዳሮቶች እንደሚያጋጥሟት እሙን ነው። ከእነዚህ ተግዳሮቶች መካከል በመንግሥት እና ግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሰጠው የሒሳብ አያያዝና ኦዲት ስርዓተ ትምህርት ውስጥ የዓለም ዐቀፍ ፋይናንስ ሪፖርቶች አዘገጃጀትና አቀራረብ እንዲሁም የኦዲት ደረጃዎችን ያካተተ ያለመሆኑ ነው፤ በዚህም ሳቢያ በዓለም ዐቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት ደረጃዎች ዙሪያ ሰፊ የእውቀት ክፍተት ይታያል። ክፍተቱን ለመቅረፍ ተባብሮ መሥራት እንዲሁም የተጀመሩ ሥራዎችን አጠናክሮ መቀጠል ያሻል። ይህም የሚሆን ከሆነ የዓለም ዐቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት ደረጃዎችን በአግባቡ ተረድተው ትግበራውን በአግባቡ የሚያስቀጥሉ ባለሙያዎችን ለማፍራት ያስችላል።

የዓለም ዐቀፍ የፋይናንስ ስርዓት ትግበራ ሒደት ውስጥ ካሉ ቀዳሚ ተግዳሮቶች መካከል በተለይ ትግበራው የሚሰጠውን ጥቅም አስመልክቶ በጉዳዩ ዙሪያ መገናኛ ብዙኀንን በመጠቀም የሚሰጡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ውስን መሆናቸው ይጠቀሳል። በሌላ በኩል በተለይ የተለያዩ የድርጅት ባለቤቶች፤ የተለያዩ ተቋማት ኀላፊዎች የዓለም ዐቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት ስርዓት ለመተግበር የሚወጡ ወጪዎችን ይፈራሉ ወይም አይፈልጉም። እነዚህም ለሠራተኞች ሥልጠና፣ ለአማካሪዎች ክፍያ እንዲሁም አሁን ያለውን አሠራር ወደ አዲስ አሠራር ለመለወጥ የሚወጡ ወጪዎች ሲሆኑ፤ በዚህ ሳቢያ ለትግበራው ያላቸው ፍላጎት አናሳ መሆኑ ይጠቀሳል።

ዓለም ዐቀፍ የፋይናንስ ደረጃዎችን ለመተግበር ሲታሰብ ከዓለም ዐቀፍ የሪፖርት ደረጃዎች ጋር የማይጣጣሙ ሕጎች በሚኖሩ ወቅት እነዚህን ሕጎች ለውጦ እንዲጣጣሙ ማድረግ አንዱ ተግዳሮት ነው። በቂ የሆነ የዓለም ዐቀፍ ሪፖርት ደረጃዎች እውቀት እና ክህሎት ያላቸው የሒሳብ ባለሙያዎች እና ኦዲተሮችም ያስፈልጋሉ። ይህንን የሚያሟሉ ባለሙያዎች ቁጥር ማነስ አንድ ተግዳሮት ሆኖ ሲጠቀስ ከዚህ በተጨማሪም በየጊዜው የሚወጡ አዳዲስ ደረጃዎችን በወቅቱ ተረድቶ ተግበራዊ ማድረግ ላይ ክፍተት ይታያል።

ሌላው ተግዳሮት ተደርጎ የሚወሰደው የተደራሽነት ጉዳይ ሲሆን ይህም ቦርዱ መቀመጫውን አዲስ አበባ እንደማድረጉ በቋሚነት የራሱን ቅርንጫፍ ቢሮዎች በየክልሎች ከፍቶ አገልግሎት መስጠት አለመቻሉ ነው። ይህም በአገር ዐቀፍ ደረጃ ተግባራዊ ማድረግ ለታቀደው የዓለም ዐቀፍ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ስርዓት ትግበራ ፈታኝ እንዲሆን አድርጎታል። በተለያዩ ተቋማዊ እና ቴክኒካዊ ችግሮች ምክንያት የቦርዱን የፋይናንስ ሪፖርቶች አዘገጃጀትና አቀራረብ ግምገማ እና ክትትል የማያልፉ የሒሳብ መግለጫዎች ሊያገጥሙ ይችላሉ የሚል ሥጋትም አለ።

ሌላው በተቋማት ላይ ያሉ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መሰረት ልማቶች በሚፈለገው መጠን አለመዘርጋቱ በዓለም ዐቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት ትግበራ ተግዳሮት ሆኖ ይታያል። በተጓዳኝ የባለድርሻ አካላት የቅንጅት እና የቁርጠኝነት ማነስ፤ ከተቋማት የበላይ ኀላፊዎች በቂ ድጋፍ ማግኘት አለመቻል፣ ለውጥን መሸሽ እንዲሁም የሙያ ማኅበራት በዓለም ዐቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት ትግበራ ረገድ ያላቸው ተሳትፎ ውሱን መሆኑ ይጠቀሳል። በተያያዘ ወደ ዓለም ዐቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት ደረጃዎች ትግበራ መግባት ያለባቸው ተቋማት አሁን ከሚጠቀሙበት የሒሳብ አያያዝ ዘዴ ወደ ዓለም ዐቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት ደረጃዎች ለመሸጋገር የሽግግር እቅድ በአግባቡ አለመተግበሩ ይጠቀሳል።

አንዱ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ በኢትዮጵያ የተሻለ የዓለም ዐቀፍ ሪፖርት ደረጃዎች ትግበራ ይኖር ዘንድ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የዓለም ዐቀፍ ደረጃዎች ሥልጠና በበቂ ሁኔታ ማግኘት ይገባቸዋል። ይህን ለማሳካት በቂ የሥልጠና ግብዓት እንዲሁም ሥልጠናውን በተመጣጣኝ ክፍያ ለማድረስ ተግዳሮቶች እያጋጠሙ ይገኛሉ።

አሁን ያለውን የዓለም ዐቀፍ ፋይናንስ ሪፖርት ደረጃዎች ሥልጠና በዋነኛነት በቦርዱ በሚገኙ ባለሙያዎች እና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አማካኝነት በዋነኛነት እየተሰጠ ነው። በሙያ በቂ እውቀት ባላቸው የግል የሥልጠና እና የማማከር አገልግሎት በሚሰጡ ድርጅቶች በተለያዩ ተቋማት ለሚገኙ ባለሙያዎች እንዲሁም በግል መሰልጠን ለሚፈልጉ አካላት ሥልጠና እየተሰጠነው። በሌላ በኩል ያለ በቂ ዝግጅት፤ አቅም እንዲሁም የሥልጠና ግብዓት የዓለም ዐቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት ደረጃዎች ሥልጠና በአንዳንድ አካላት እየተሰጠ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል። ይህም የሥልጠናውን ጥራት የሚቀንስና በዓለም ዐቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት ደረጃዎች ላይ ያለውን የእውቀት ክፍት ለመሙላት ተግዳሮት ሆኖ ሲገኝ በሌላ በኩል በተለይ ከመዲናዋ ውጪ ባሉ ከተሞች በዓለም ዐቀፍ የፋይናስ ሪፖርት ደራጀዎች ላይ ሥልጠናው በአግባቡ ተደራሽ አለመሆኑ እንደተግዳሮት ይጠቀሳል።

ከሥልጠና ጋር ተያይዞ ያለውን ችግር ለመቅረፍ በቦርዱ በፍኖተ ካርታ እንደተቀመጠው በአገሪቱ የዓለም ዐቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት ደረጃዎችን በብቃት መስጠት የሚችል የዓለም ዐቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት ደረጃዎች ማስልጠኛ ማዕከል ማቋቋም ያሻል። ይህም የተሻለ ሥልጠና ለብዘኀኑ ተደራሽ የሚያደርግ ሲሆን በየጊዜው በሚሻሻሉ ደረጃዎች ላይ ተገቢውን እውቀት በመስጠት ደረጃዎቹን በአግባቡ ለመረዳት እና ለመተግበር ያስችላል። እንዲሁም ለባለሙያዎች ተከታታይ የሆነ የሙያ ማጎልበቻ በወጥነት ለመስጠት ያግዛል።

ሌላው ጉዳይ በዓለም ዐቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት ትግበራን ተመርኩዞ ቦርዱ ባዘጋጀው የስትራቴጂክ እቅድ እንደተጠቀሰው ከቦርዱ ባለድርሻ አካላት አንዱ መንግሥት ነው። መንግሥት በአገሪቱ ኢንቨስትመንት እና የኢኮኖሚ ዕድገት የሚደግፍ እና የሕዝብን ጥቅም የሚያስጠብቅ በአግባቡ የሚመራ የሒሳብ አያያዝና ኦዲት ሙያ በአገሪቱ ውስጥ እንዲፈጠር ጠንካራ ፍላጎት አለው። ቦርዱ የሕዝብ ጥቅምን የሚያከብር እንዲሁም ሙያውን ቀልጣፋና ስኬታማ በሆነ መልኩ ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ስርዓቶችን በአግባቡ መዘርጋት ይጠበቅበታል። ኢንቨስተሮችም በበኩላቸው የሚያደርጉት ማንኛውም የኢንቨስትመንት ውሳኔ አስተማማኝ በሆኑ መረጃዎች ይደገፉ ዘንድ ጥራቱን የጠበቀ የሒሳብ አዘገጃጀት፣ አቀራረብ እና የኦዲት አገልግሎት እንዲኖር ይሻሉ። ሪፖርት አቅራቢ አካላት፣ የኦዲት ድርጅቶች እና ሌሎች ተቆጣጣሪ አካላት ከቦርዱ የሚጠብቋቸው የተለያዩ አገልግሎቶች ሲኖሩ ቦርዱም እነዚህን ባለድርሻ አካላት በአግባቡ ለማስተናገድ የተለያዩ ተግባራት እያከናወነ ነው። ይህንንም ተግባር በተሸለ ሁኔታ አጠናክሮ መቀጠል ከቦርዱ ይጠበቃል።

በመንግሥት በኩል ለቦርዱ የሚያደርገውን ድጋፍ በተለይ የፋይናንስ እና የቦርዱን አቅም ለመገንባት ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅበታል። በቂ ክህሎት እንዲሁም ብቃት እና ልምድ ያላቸውን ባለሙያዎች በቦርዱ ለማቆየት ድጋፍ ማድረግም ሌላው ነው። በቦርዱ የፋይናንስ ሪፖርት የሚያቀርቡ ተቋማት ቁጥር በከፍተኛ በሚባል ደረጃ እየጨመረ በሚገኝበት በዚህ ጊዜ፤ ተገቢውን ክትትል እና ግምገማ የሚያደርጉ ባለሙያዎች ቁጥር አናሳ መሆኑ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ይኖረዋል። በመሆኑም መንግሥት ይህን ተገንዝቦ የባለሙያዎች ቁጥር ይጨምር ዘንድ ድጋፍ ሊያደርግ ሲገባ፤ መሻሻል ያለባቸው ሕጎች በሚኖሩ ጊዜ ተገቢውን ድጋፍ ያደርግ ዘንድ ይጠበቃል። ከላይ እንደ ዋነኛ ተግዳሮት የተነሳውን የተደራሽነት ችግር ትኩረት ሰጥቶ መፍታትም ከመንግሥት ይጠበቃል።

ቶፊቅ ተማም በአንድ የግልተቋም ውስጥ የIFRS ሥልጠና አስተባባሪ ናቸው። በኢሜል አድራሻቸው tofick1970@gmail.com ሊገኙ ይችላሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 40 ነሐሴ 4 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here