የፈሪ ትግል

0
1067

ባሕላችን፣ ትውልዶችን ጭካኔ እያስተማረ በማሳደግ ላይ የተመሠረተ ነው የሚሉት በፍቃዱ ኃይሉ፥ ተጨባጭ ያሏቸውን ማሳያዎች በማስረጃነት አቅርበዋል። ዴሞክራሲን ለመኖር ጭካኔን የሚቃወሙ፣ ጭካኔያዊ ጀብደኝነትን የሚሸሹ፣ ተደራድረው የሚያድሩ ትውልዶችን ኮትኩቶ ማሳደግ ይገባል ሲሉ ምክረ ሐሳባቸውን ሰንዝረዋል።

 

አንዲት ቬጋን ጓደኛዬን ለምን ቬጋን (አትክልት ብቻ በሊታ) ለመሆን እንደወሰነች ጠይቄያት ነበር። ከቆጠረችልኝ ምክንያቶች ውስጥ የመጀመሪያው “ጭካኔን (cruelty) መቃወም” የሚል ነበር። ሰዎች ሥጋ ለመብላት ካላቸው ፍቅር የተነሳ ከብቶችን ማረድ እና ደማቸውን ማፍሰስ እንደ ዋዛ የሚያደርጉት ነገር ነው። ሙግቷ ይህ እንደ ማኅበረሰብ ሕዝባችንን ጭካኔ ያስተምራል የሚል ነበር። እኔም እንደርሷ ቬጋን አልሆንኩም እንጂ ‘ጭካኔ አያስተምርም’ ብዬ የምከራከርበት ሕሊና አላገኘሁም።

ጭካኔ በአገራችን እንደ ጀግንነት ነው የሚታየው። ከዚያ መለስ ሲል ደግሞ እንደ ስርዓት ማስያዣ ነው የሚቆጠረው። በእኔ ዕድሜ ያሉ ሰዎች በልጅነታቸው በወላጆች፣ በአሳዳጊዎች፣ በጎረቤቶች እንዴት እየተገረፉ እንዴት ያድጉ እንደነበር ለማስረዳት መሞከርም አያስፈልግም። በቤተሰብ ዱላ እና ግርፊያ ያደጉ ልጆች ትምህርት ቤት በመምህራኖቻቸው ሰበብ አስባብ እየተፈለገ ያለ ርህራሔ ይገረፋሉ፣ በእንብርክክ እንዲፏቀቁ፣ አጎንብሰው እና እጃቸውን በእግራቸው ጠልፈው ጆሯቸውን ይዘው በመቆም እንዲሰቃዩ ይደረጋሉ። የሚያሳሱ ታዳጊዎች ሆነን በዚህ ሁኔታ ውስጥ ስናልፍ መምህራኖቻችንም ይሁኑ ቤተሰቦቻችን ቅንጣት ታክል አያዝኑልንም ነበር፤ ቢያዝኑልንም አዘኔታቸውን አያሳዩንም ነበር። ከዚህም ያለፉ ታዳጊዎች ከፍ ብለው መንግሥትን ከተዳፈሩ ደግሞ ተረኛው ገራፊ የመንግሥት ቅጥረኛ ይሆናል። ከገራፊዎቹ ሁሉ የትኞቹም አይፀፅታቸውም። ሁሉም ድርጊታቸው አግባብ ስለመሆኑ “አሳማኝ” ማስተተባበያ አላቸው።

አስታውሳለሁ፣ ከጥቂት ዓመታት በፊት የመኖሪያ ሰፈራችን ውስጥ አንድ ሌባ ተያዘ፤ የሰፈሮቼ ልጆች እየዘለሉ ባላቸው አቅም በእርግጫ ደበደቡት። ማንም ይህንን እንደስህተት የቆጠረው ሰው አልነበረም። ከዚያ በኋላ በደም የተበከለውን ሌባ ለፖሊስ ወስደው አስረከቡት። ፖሊሶች ሌባውን ሲረከቡ በካልቾ እና በዱላ ነው።
ጭካኔን ባሕላችን ያደረግነው፣ ድብደባን ደንባችን ያደረግነው እንዲህ እንዲህ እያልን ነው።

በዚህ ዓይነት የታነፀ ማኅበረሰብ ውስጥ መደራጀት እንጂ የሚከብደው ከተደራጁ በኋላ በደቦ ጥቃት እና ጭካኔ ላይ መሠማራቱ – እውነቱን ለመናገር – ምንም የሚያስገርም ነገር የለውም። ሁላችንም ከሰውነታችን ውስጥ አውሬነታችንን አጉልተን እንድናሳድግ እየተማርን ነው እዚህ የደረስነው። የበለጠ የሚያሳዝነው ግን ጭካኔን ከፍቅር ጋር አገናኝነተን የምንመለከተው መሆኑ ነው።

ማሰቃየት ከቤት እስከ ፖሊስ ጣቢያ
ኢትዮጵያውያን ልጆች በወላጆቻቸው በበርበሬ እስከ መታጠን ድረስ ያሉ ማሰቃየት ይደርስባቸው ነበር። በባሕል እና ወግ እንዲሁም በፍራቻ የታጠረችው የኔ እናት እንኳን “የሴት ልጅ እንዳታሰኘኝ” በማለት በየጊዜው እና በየሰበብ አስባቡ ትገርፈኝ ነበር። (“የሴት ልጅ” የሚለው የተሳሳተ አመለካከት አባቱ ያላሳደገው ልጅ ይባልጋል ከሚል አስተሳሰብ የመነጨ ነው፤ የኔ አባት በልጅነቴ በሥራ ምክንያት ርቆ ይኖር ስለነበር ነው እናቴ ይህን ማለቷ።) የኋላ ኋላ ታ-ኔሂሲ ኮትስ የተባለ ጥቁር አሜሪካዊ የመብት ተሟጋች ጸሐፊ በልጅነቱ ወላጆቹ ይገርፉት እንደነበረና ምክንያታቸውም ‘አድጎ የጎዳና ሕይወት፣ የዕፅ ሱስ፣ የፖሊስ ጭካኔ ይቀማኛል’ የሚል ስጋታቸው እንደነበር ያትታል። ያንን ጽሑፍ ሳስብ የኔም እናት ከዚያ ስጋት የተለየ እንዳልነበራት ተረድቻለሁ። ወላጆቻችን እኛን ከክፉ ለመጠበቅ ከማሰቃየት የተሻለ መፍትሔ አልታየቸውም፤ ሆኖም በዱላ ብዛት ሥነ ምግባር የያዙ ልጆች ስለመኖራቸው እጠራጠራለሁ።

የማሰቃየት ነገር ሲነሳ የሚገርመኝ አሁን ተዘግቶ ለጉብኝት የበቃው ማዕከላዊ የሚባለው የፖሊስ ጣቢያ ውስጥ ታስሬ በነበርኩበት ጊዜ የገጠመኝ ነገር ነው። ያኔ በድብደባ ያሰቃዩን የነበሩት መርማሪ ፖሊሶቻችን ይሏት የነበረችው አንድ ነገር አለች። የሕዝቡን ደኅንነት ለመጠበቅ የእኛን ሰብኣዊ መብቶች መጣስ እንደሚችሉ ይናገሩ ነበር። በእርግጥም ራሳቸውን እንዲህ ብለው ማሳመናቸው ለማሰቃየት ተግባራቸው የማይፀፀቱበትን ሰበብ እንደፈጠሩ አድርጌ አስበው ነበር። ሁሉም ሰዎች ለጭካኔያቸው “ተመጣጣኝ” ብለው የሚሉትን ሰበብ አስባብ ያበጃሉ።

ባሎች ሚስቶቻቸውን ሲደበድቡ እንደ ፍቅር መግለጫ የሚቆጥሩት ብዙ ናቸው። “ስለምወዳት ገደልኳት” የሚል ዓረፍተ ነገር ቢሰሙ የማይገረሙበት አገር ነው – ኢትዮጵያ። የቀድሞው ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኀይለማርያም “አገራቸውን ይወዱ ነበር” ይባልላቸዋል፤ ብዙ ዜጎቻቸውን ያስጨፈጨፉ መሆናቸውን ግን ማንም አይክድም። ዜጎቻቸውን ለመጨፍጨፍ ያልሳሱ ፕሬዚዳንት አገራቸውን ይወዱ ነበር የሚያስብላቸው ለመሬቱና ለሰማዩ ባላቸው ፍቅር ብቻ ነውን?

“ወንድነት”እና ጭካኔ
የለውጥ ዕድሎች በኢትዮጵያ ለምን እንደሚከሽፉ ተመራማሪው ዶናልድ ሌቪን የጻፉትን ጽሑፍ በቅርቡ አነበብኩት እና ከዘረዘሯቸው ምክንያቶች ውስጥ “ወንድነት” አንዱ ምክንያት መሆኑ አስገረመኝ። ሌቪን “ያልተሳኩ [የለውጥ] ዕድሎች ላይ ሁሉ ካስተዋልኳቸው ነገሮች ውስጥ አንዱ የወንድነት ምግባር እና የተዋጊነት መንፈስ ነው” ይላሉ። ወንድነት በኢትዮጵያ እርሳቸው እንደበየኑት “ጠላቶችን የመደምሰስ ባሕርይ ነው”። በእዚህም ምክንያት ለውጦች በመገዳደል ይቋጫሉ። ይህም ከ1953ቱ መፈንቅለ መንግሥት ጀምሮ፣ ከ1966ቱ አብዮት በኋላ፣ ከ1983ቱ ለውጥ በኋላ፣ ከ1997ቱ ምርጫ በኋላ ታይቷል። አሁንም ወደዚያው እየሔድን ሊሆን ይችላል…

ዶናልድ ሌቪን በአብዮቱ ሰሞን ያገኙት አንድ አብዮታዊ ሶሻሊስት የነገራቸውን በመጥቀስ የዚህን አባዜ አደገኝነት አስፍረውታል – “የኢትዮጵያ ሕዝብ አሁን 30 ሚሊዮን ነው። የ3 ሚሊዮን ሰዎች ሞት ለኢትዮጵያ ስኬት ያን ያህል ትልቅ ዋጋ አይባልም”። አሁንም እንደዛ የሚሉ ሰዎች ገጥመውኛል፤ ነገር ግን ከመስዋዕቶቹ መካከል አንደኛው ለመሆን ፈቃደኛ መሆናቸውን እጠራጠራለሁ።

የፈሪ ትግል
ደረጄ ዓለማየሁ የተባሉ የቀድሞ የመኢሶን አባል በ1985 የጻፉት “ታዝቤ ዝም ከምል” የሚል የ47 ገጽ መጣጥፍ አስተሳሰቤ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ካሳደሩ መጣጥፎች አንዱ ነው። ጸሐፊው ለመጣጥፉ መነሻ የሆናቸው የትግል አጋራቸው የሆኑት ኀይሌ ፊዳ ከመሞታቸው በፊት በደረሰባቸው ማሰቃየት ምሥጢሮቻቸውን ለያኔው የማዕከላዊ መርማሪዎች ተናግረዋል በሚል ያናናቃቸው ጽሑፍ “እፎይታ” ላይ መታተሙን በመቃወም ነበር።

ከደረጄ መጣጥፍ ውስጥ ልቤ ውስጥ ተሰንቅሮ የቀረው አባባላቸው “ዴሞክራሲ የአሸናፊ መፈንጫ ሳይሆን የተሸናፊ መብት ማረጋገጫ ነው፤ … ዴሞክራሲ ሽጉጥ የሚማዘዙ ጀግኖች ሲያሰኛቸው ይዋጣልን የሚባባሉበት ሳይሆን፥ በምንም ዓይነት ሁኔታ ሽጉጥ ላለመማዘዝ የወሰኑ ‘ፈሪዎች’ ተከባብረው በሰላም አብረው ለመኖር የሚፈጥሩት የፖለቲካ ስርዓት ነው” ይላል።

ደረጄ “የጀግንነትን” መዘዝም በዚያው መጣጥፋቸው አመላክተዋል። ተዋግተው ማሸነፍ የሚችሉ ሰዎች ተዋግተው ሁሉንም ይወስዳሉ እንጂ መቼም ተደራድረው ዴሞክራሲን እንደማይመሠርቱ ይተርኩልናል። እርሳቸው አሳምረው እንደገለጹት “ለአገሬ እሞትላታለሁ” የሚለው ሰናይ የሚመስል ሐረግ ራሱ የዴሞክራሲ ፀር ነው። ምክንያቱም “ለአገሬ እሞትላታለሁ” ያለ ሰው “ላገሬ እገልላታለሁ” ከማለት አይመለስምና።

እኔም በበኩሌ ሰዎችን እየገደሉ፣ ለሰዎች ነጻነት ማምጣት አለ ብዬ አላምንም። ባሕላችን፣ ትውልዶችን ጭካኔ እያስተማረ በማሳደግ ላይ የተመሠረተ ነው። ለጭካኔ እና ለጭካኔያዊ ጀግንነት ትልቅ ቦታ የሚሰጥ ነው። ታዲያ ኢትዮጵያ በእነዚህ ጀብደኞች እና ነፍሰ በላዎች መታመሷ ሊያስገርመን አይገባም። ያልዘራነውን አናጭድምና። መፍትሔውም ተቃራኒው ነው። ጭካኔን የሚቃወሙ፣ ጭካኔያዊ ጀብደኝነትን የሚሸሹ፣ ተደራድረው የሚያድሩ ትውልዶችን ኮትኩቶ ማሳደግ። ይህን ማድረግ ከቻልን ዴሞክራሲን አፍርተን እንሸመጥጣታለን።

ቅጽ 1 ቁጥር 44 ጳጉሜ 2 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here