ነገረ-አባይ እና ኢትዮጵያ ከግብጽ ጋር ጊንጥ እና ዔሊነት እስከመቼ?

0
1317

ሰሞኑን ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ግብጽ አቀረበችው ስለተባለው ምክረ ሐሳብ የብዙ መገኛኛ ብዙኀንን ትኩረት ስቧል፤ አዲስ ማለዳም በጉዳዩ ዙሪያ ከኹለት ሳምንት በፊት ርዕሰ አንቀጽ መጻፏ ይታወሳል። ይህን ጉዳይ መነሻ በማድረግ ብርሃኑ ተስፋዬ የሚከተለውን መጣጥፍ እነሆ ብለዋል።

በጥንታዊት ሕንድ አንድ የሚነገር ታሪክ አለ። ከዕለታት በአንዱ ቀን ጊንጥ ወደ ዔሊ ተጠግቶ “እባክህ ይህን ወንዝ አሻግረኝ” ሲል ይጠይቀዋል። ዔሊም ጊንጥ “ብትነክሰኝስ” ብሎ ሲፈራ እና ሲቸር ከቆየ በኋላ መቼስ በሐዘኔታ ጊንጥን ሊያሻግር በመወሰን ከጀርባው አሳፈረው። በወንዙ መሐል ላይ ሲደርሱ ጊንጥ ዔሊን ለመንደፍ ሞከረ። በዚህ የጊንጥ ውለታ ቢስነት ዔሊ በጣም ተቆጣ። “ከተሳቢዎች ሁሉ ርጉም እና ምስጋና ቢስ አይደለህምን? እኔ ባላሻግርህ እዛ ወንዝ ላይ ውሃ በወሰድህ ነበር። እናም ምላሹ ለእኔ ይህ ይሁን? እግዚአብሔር የሰጠኝ ጋሻ ባይኖር ለሞት በሚያደርስ ዘንግ ወግተኸኝ ነበር”። ማፈሪያ የሌለው ጊንጥም በሚያስተዛዝን ድምጽ መለሰ “በእኔ አትፍረድብኝ። ይህ የእኔ ችግር አይደለም። ተፈጥሮዬ ነው። መንደፍ ሕጋዊ ልማዴ ነው” ሲል መለሰ። እንግዲህ ዔሊ ድንጋይ ልብሱ ባይኖር ለጊንጥ ደግ አደርግሁ ሲል በጊንጥ ተነድፎ ሞቶ ነበር። ይህን መሰል ተረት በሩሲያም ከእንቁራሪት ጋር ተያይዞ ይነገራል። ነገር ግን እንቁራሪት መከላከያ ስለሌላት በምህረት የለሹ ጊንጥ ስትነደፍ ጊንጥንም ውሃ ሲበላው ይነገራል።

ከላይ የጠቀስኩትን ተረት መንደርደሪያ ማድረጌ ወድጄ አይደለም። መሰል እውነተኛ ታሪክ በእኛው ዘመን ከታላቁ የኢትዮጵያ ወንዝ ከአባይ ጋር ተያይዞ በተደጋጋሚ እየተከሰተ በመመልከቴ እና በመታዘቤ ነው። ከሰሞኑ በዐረቢኛ እና በግብጽ የእንግሊዝኛ ጋዜጦች እንዲሁም በዋዜማ ሬዲዮ የተባለ የአማርኛ አሰራጭ ግብጽ ከሰሞኑ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ አቀረበችው ስለተባለ ሐሳብ ብዙ ተዘግቧል።

አዲስ ማለዳ ጋዜጣም በቅጽ 1 ቁጥር 43 ነሐሴ 25/2011 ዕትሟ “የፖለቲካ ልዩነታችን ለውጪ ኀይሎች እንዳያስከነዳን” በሚል ርዕስ ርዕሰ አንቀጿ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኀይሎች እርስ በርስ ሲበላሉ ግብጽ “ኢትዮጵያን ቅኝ ግዛቷ ለማድረግ ደፋ ቀና እያለች” እንደሆነ በድርድሩ ውስጥ ካሉ ሰዎች አገኘሁት ባለችው መረጃ መርዶ ነግራናለች። በርግጥ ይህን መርዶ አስቀድሞ ያረዳን ሬዲዮ ዋዜማ በሐሙስ 16/2011 “የዜና መጽሔት” እወጃዋ “የኢትዮጵያ ውስጣዊ መዳከም እና አለመረጋጋት ለግብጽ የልብ ልብ ሳይሰጣት አልቀረም” በሚል ርዕስ በቀረበው ሐተታ የግብጽ የውሃ እና መስኖ ሚኒስትር ሞሐመድ አብድል አቲ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ሙሌት በተመለከተ ሰነድ ማቅረባቸውን በመዘገብ የሰነዱ ይዘት በኢትዮጵያውያን የቴክኒክ ባለሙያዎች ዘንድ ተቀባይነት እንዳላገኘ ጠቅሷል። ዋዜማ በማከልም በግብጽ ከቀረቡት ሐሳቦች መካከል የግድቡ በዓመት የሚፈሰው ውሃ የተፈጥሮ መጠኑን የጠበቀ እንዲሆን ከመጠየቅ ጀምሮ እስከ በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ ቁጥጥር ማካሔድ ድረስ ይህም ማለት ግብጽ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለሙያዎቿን ልካ የግድቡን ኦፕሬሽን እንዲሁም ሌሎች እንቅስቃሴዎቻችንን እንድታይ የሚፈቅድ ሰነድ እንደሆነ ተጠቅሷል።

እንግዲህ ግብጽ ከላይ እንደተጠቀሰችው ጊንጥ ሆነች ማለት ነው። ኢትዮጵያም ብትነደፍ ብትነደፍ የጊንጧ መርዝ የማይገድላት እግዚአብሔር በፈጠረላት በአለት ልብሷ አማካኝነት ሆነ ማለት ነው። ለዚህ ማሳያ እንዲሆነን ከታሪክ ሰበዝ መዘዝ መዘዝ አድርገን እንመልከት። ይህ የሚጠቀሰው የታሪክ ሰበዝ አነስ ያለው ስንደዶ ነው እንጂ…. ከ1820ዎቹ ጀምሮ እንጥቀስ ቢባል ጉዱ ብዙ ነው… ጠባሳው ግልጽ እና የሚታይ ነው። ሌላው ቀርቶ በዘመነ ደርግ እና ኢሕአዴግ ግብጾች በኢትዮጵያ ላይ ያደረሱት ግፍ በቃል የሚገለጽ አይደለም። አሁን ትኩረት የምናደርገው ከታላቁ የሕዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ያለውን ያውም እጅግ የተመጠነውን ነው።

“ጊንጧ ዔሊዋ ላይ እንዴት ወጣች?”
ጊዜው ታኅሣሥ 2003 ነው። የወቅቱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ነብስ-ኄር መለስ ዜናዊ በጥቂት የቅርብ ሰዎቻቸው ብቻ ይታወቅ ስለነበረው አንድ አገራዊ ጉዳይ የፖለቲካ ውሳኔ አሳልፈው ፊርማ ሊፈረም ኢትዮጵያ ድግስ ላይ ነበረች። የሚሊኒዬም ድልድይ ሲመረቅ “ይህ የሚሊኒዬም ድልድይ ሲመረቅ በዚህ የአባይ ሸለቆ የልማት ተዓምር እንደሚኖር ማመላከቻ ነው” ሲሉ የገለጹትን ቀጣዩን ድግስ እውን ሊያደርጉ ጫፍ ደርሰዋል። ፕሮጄክት ኤክስ (Project X) ተብሎ ያኔ ለሚታወቀው፣ በአጼ ኀይለሥላሴ ዘመን ድንበር ግድብ የሚባለው በኋላም ሚሊኒዬም እና ለመጨረሻ ጊዜ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተብሎ የተሰየመው በአባይ ላይ ከሚሠሩት ግድቦች ግዙፉን ግድብ በተመለከተ መንግሥታቸው በተጠቀሰው ወር ከጣሊያኑ የግንባታ ኩባንያ ሳሊኒ ጋር ውል እየቆረጠ ነበር።

ወዲያው በጥር እና የካቲት ወሮች በቱኒዝያ ቡአዚዝ በተባለ ወጣት ራስን መሰዋዕት በማድረግ የተጀመረው አመጽ በመላው የዐረቡ ዓለም ሲዳረስ በቅርብ ርቀት የምትገኘውን ግብጽንም አንኳኳ። በወቅቱ ኢትዮጵያ ግድቡን ለመገንባት ደፋ ቀና ስትል እንደነበር የተረዳው የግብጽ የሆስኒ ሙባርክ መንግሥት ኢትዮጵያን ለመበተን ሽር ብትን ሲል ቀድሞ በአመጽ ተወገደ። በኹለቱ አገራት መካከልም አዲስ ግንኙነት ለመጀመር ዕድል ተከፈተ። በካይሮ የተፈጠረውን ለውጥ ተከትሎ የግብጽ የሽግግር መንግሥት ከተለያየ የኅብረተሰብ ክፍል የተወጣጡ ግብጻውያን ያሉበትን የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ተወካዮች ወደ ኢትዮጵያ ላከ። የልዑካን ቡድኑ በአዲስ አበባም ከመንግሥት ኀላፊዎች የወቅቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ጨምሮ፣ የሐይማኖት መሪዎች እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን አገኘ። ሲቀጥል ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም ተጉዞ ከምሁራን ጋር ተወያየ። አዲስ ምዕራፍ፣ አዲስ የግንኙነት ገጽ በኢትዮጵያ እና በግብጽ መካከል እንደተጀመረ አበሰረ።

ይህ ቡድን ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ ኹለት መሰረታዊ ጥያቄዎችን ይዞ ነበር። አንደኛው ኢትዮጵያ የምትገነባው ግድብ ግብጽን የሚጎዳ እንዳይሆን ለመማጸን ሲሆን ኹለተኛው በወቅቱ ፊርማ ላይ የነበረው የአባይ የትብብር ስምምነት (Cooperative Framework Agreement-CFA) ግብጽ የተረጋጋ መንግሥት እስክትመሰርት ድረስ እንዳይጸድቅ ትብብር እንዲደርግ ለማድረግ ነበር። ኢትዮጵያ ኹለቱንም “እሺ ብላ” ተቀበለች። የሕዳሴ ግድብ ግብጽን እንደማይጎዳ ማረጋገጫ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በወቅቱ የግብጽ የሽግግር ጠቅላይ ሚኒስትር ከነበሩት ኤሳም ሻርፍ ጋር በመነጋገር የሦስቱ አገራት ኮሚቴ እንደሚቋቋም ፈቃዳቸውን ሰጡ። የትብብር ስምምነቱም መጽደቁ እንደሚዘገይ ለግብጽ አረጋገጡ። እንግዲህ የግብጽ የልዑካን ቡድን በኋላም ጠቅላይ ሚኒስትር ኤሳም ሻርፍ ወደ ዔሊዋ ኢትዮጵያ ሲመጡ፣ “እባካችሁ ግብጽ ሽግግር ላይ ስለሆነች… አመጽ የሚባል ወንዝ አለባት እና ይህን እስክታልፈው አሻግሯት። ተባበሩን። አብረን እንዘልቃለን።

አብረን የአንድ ወንዝ ውሃ እየጠጣን ነው… ደማችን አንድ ነው። አብረን እንዝለቅ። አብረን እንደግ። አብረን እንሻገር” በሚል መሐላ እና ግዝት ነበር። እንዲያውም አንዲት በቴሌቪዥን ቀርበው የነበሩ የግብጽ ኮፕቲክ ሴት (አንገታቸው ላይ ጨረቃ እና መስቀል ያንጠለጠሉ) “ከአሁን በኋላ በቅኝ ግዛት የተደረጉ ስምምነቶች ለአገራችን አይበጁም። አዲስ የግንኙነት ምዕራፍ ከፍተናል” ሲሉ አወጁ። የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንም ደጋግሞ በተለያየ ቋንቋ አስተላለፈው። ጊንጧ ዔሊዋ ላይ ወጣች። ይሁን እንጂ ይህች ጊንጥ በሽግግሩ ሒደትም ተሻግራም ከዔሊዋ ጀርባ ሆና ንክሻዋን ቀጥላለች። አሁንም ከዔሊዋ ጀርባ አልወረደችም።

ንክሻ አንድ
ግብጽ በችግሯ ጊዜ “አሻግሪኝ” ያለቻትን ኢትዮጵያን መንከስ በሽግግሯ መሐል ሆና ነበር የጀመረችው። ገና በሽግግር ላይ የነበረችው ግብጽ በድርድር ሒደቱ ወቅት ኢትዮጵያ በተለይ የግድቡን ልዩ ልዩ የንድፍ እና የጥናት ሰነዶች ስታቀርብ ነበር ኢትዮጵያን መንደፍ የጀመረችው። መጀመሪያ ግድቡ እንዲስተጓጎል ለማድረግ በተለይ ቁመቱ ይጠር፣ ስፋቱ ይነስ ወዘተ በሚል ክርክር እማይገባው ነገር ውስጥ ዘው ብላ መግባትን መርጣ ነበር፤ ግን አልተሳካላትም!
ይሁን እንጂ ወዲያው የሽግግሩ መንግሥት ጊዜው አብቅቶ ሙስሊም ወንድማማቾች በትረ ሥልጣኑን በእነ ንጉሥ ፋሩቅ እና ፉአድ ቤተ መንግሥት ሲያደላድል ከአገሪቱ የደኅንነት እና ወታደራዊ ተቋማት ጋር ሆኖ ኢትዮጵያን ማወኩን ተያያዘው። ከሁሉም የከፋው ግን ዓለም አይቶ ያዘነበትም፤ የሳቀበትም የወቅቱ የግብጽ ፕሬዝዳንት ሞሐመድ ሞርሲ የፖለቲካ መሪዎችን እና የሐይማኖት ተወካዮችን ሰብሰበው በቀጥታ በቴሌቪዥን በሚተላለፍ ፕሮግራም ላይ “ኢትዮጵያን ምን እናድርጋት?” በሚል አጀንዳ አንዳንዱ “እንውረራት…”፣ ሌላኛው “እናስፈራራት…” ወዘተ እያለ ሲደሰኩር መሰማቱ ነው። ከዚህ ሲያልፍ “ባጎረስኩ እጄን ተነከስኩ” እንዲሉ ፕሬዝዳንቱ ራሱ አደባባይ ላይ ወጥተው “ለአንዲት ጠብታ ውሃ፣ ደማችን አማራጭ ነው” ሲሉ ኢትዮጵያ ላይ ደነፉ። ኢትዮጵያ ውስጥም “ውሃ ከደም ይወፍራል” እንደሚባል አልሰሙም መሰል…! የመጀመሪያው ዋና ጊንጣዊ ንክሻ ይህ ነበር። ኢትዮጵያ ይህን ጊዜ በትዕግስት አለፈችው….

ንክሻ ኹለት
የግብጹ የአሁን ፕሬዝዳንት መከላከያ ሚኒስትር እያሉ የሾማቸውን ሞሐመድ ሞርሲ በመፈንቅለ መንግሥት አስወግደው አድሊ መንሱር የሚባሉ የኹለተኛ የሽግግር መሪ ሰይመው ነበር። በዚህ ጊዜ የነበሩት የአገሪቱ የውሃ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ግድቡን አቁሙት እስከማለት ደርሰው እንደነበር የሆነ ጋዜጣ ላይ ማንበቤ ትዝ ይለኛል። ከዚህ ያለፈው ግን በድርድር ሒደቱ ውስጥ የነበሩት ንክሻዎች ናቸው። በማናቸውም የድርድር ሒደት በራሷ ውሃ፣ በራሷ ግድብ “እንደራደር፣ እንመካከር” ያለችው ኢትዮጵያ ከግብጽ ያተረፈችው መመስገንን ሳይሆን “ቅኝ እንግዛሽ” ዓይነት ንግግርን ነው። በማናቸውም የድርድር ሒደቶች የግብጽ ወገን ማሳካት የሚፈልገው ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ዘመን በእንግሊዝ የተደረጉ ኢትዮጵያን የማይመለከት የ1927/1929 (እ.ኤ.አ.) “ውል” ተብዬ ሰነድ እንዲሁም በ1952/1959 (እ.ኤ.አ.) በሱዳን እና በግብጽ የተደረገ “ስምምነት” በኢትዮጵያ ላይ ለመጫን መሞከር ነበር። (በነገራችን ላይ የ1959ኙ (እ.ኤ.አ.) ስምምነት በግብጽ እና በግብጽ የተደረገ ዕቃ-ዕቃ ጨዋታ ነበር። በወቅቱ በ1958 (እ.ኤ.አ.) በመፈንቅለ መንግሥት ወደ ሥልጣን (በግብጹ ጋማል አብድል ናስር አጋዥነት እንደሆነ ይታመናል) የመጣው የኢብራሒም አቦድ መንግሥት ከሱዳናዊነት ይልቅ ግብጻዊነት ያጠቃው ስለነበረ ነው። ለዚህም ነው የ1959ኙ ስምምነት ግብጽ እንደጻፈችው ሆኖ የተፈረመው)። ከዚሁ ሲያልፍም የግብጽ መንግሥት በመላው ዓለም በተለይ በአውሮፓ፣ በአሜሪካ እና በኤዥያ ከፍተኛ ዘመቻ በማድረግ ስለ ግድቡ መጥፎ ነገር ከማውራቱ እና ከማስወራቱ ባሻገር ለኢትዮጵያ ማናቸውም ዓይነት ድጋፍ እንዳይደረግ ለማድረግ ይጥር ነበር። ሳሊኒም ከጉባ ነቅሎ እንዲወጣ ያላደረገው ጥረት አልነበረም። ዔሊዋ ኢትዮጵያ ግን ዕድሜ ለድንጋይ ልብሷ ይህንንም ንክሻ አለፈችው።

ንክሻ ሦስት
በማናቸውም አገር ውስጥ በመንግሥታት እና ሥልጣን ላይ ባሉ አካላት ድክመት ምክንያት ብዙ ፈተና ያጋጥማል። የኢሕአዴግ መንግሥት ራሱን መለወጥ ባለመቻሉ እና የሕዝብን ጥያቄ መመለስ ተስኖት ስለነበር በአገራችን የተለያዩ አቅጣጫዎች ልዩ ልዩ ሰልፎች እና ነውጦች የተስተዋሉባቸው ሦስት ዓመታት ለግብጽ ሰርግ እና ምላሽ ነበሩ። በካይሮ የፕሮፖጋንዳ ቴሌቪዥን እንዲሰራጭ ከመፍቀድ ጀምሮ በተለያዩ የሚዲያ አውታሮች በጋዜጣ፣ በቴሌቪዥን እና በሬዲዮ በመታገዝ ጸረ-ኢትዮጵያ ዘመቻ ያካሒዱ ነበር። የአገሪቱ መንግሥት በበላይነት የሚመራው የአል አህራም የጥናት ማዕከል “ተመራማሪዎች” ሳይቀሩ “ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ነውጥ ለግብጽ የሚጠቅማት በመሆኑ ተቃውሞውን የሚመሩትን አካላት መደገፍ እንደሚገባ” በአደባባይ ይቀሰቅሱ ነበር። ጉዳዩን በቅርብ እንደሚከታተል አንድ ግለሰብ ከሰማሁዋቸው እና ካየሁዋቸው ብጨምር ንክሻዎቹ ብዙዎች ናቸው። በእርግጥ በዚህ ጊዜ አንዳች ድርድር በሕዳሴ ግድብ አለ ከተባለ የግብጽ ሚዲያዎች ዘመቻ ጸረ ኢትዮጵያ የሆነ ፕሮፖጋንዳቸውን በወቅቱ በትጥቅ ትግል ላይ የነበሩ ኀይሎችን ጭምር ቃለ መጠይቅ እያደረጉ በጋዜጣ ያትሙ ነበር። መልዕክቱ ግልጽ ነበር። ኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይዋ የራሷ ነውና የግብጽን ሴራ አልፋ እንደ አገር በለውጥ ጎዳና ላይ ንክሻውን ተሻግራ አለች፤ ትኖራለችም።

ንክሻ አራት
የአገራችን ለውጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ካመጡ ወዲህ በቀጠናችን ብዙ ነገሮች ተቀያይረዋል። ከኤርትራ ጋር የተፈጠረው ሰላም ዋና ተጠቃሽ ነው። ከዚሁ ባሻገር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሚመሩበትን “የመደመር ፍልስፍና” በምሥራቅ አፍሪካ ተግባራዊ የማድረግ ሐሳብ እንዳላቸው በተለያየ አጋጣሚ መጥቀሳቸው የሚታወቅ ነው። በዚህ ረገድ አካባቢያዊ ውህደት በቶሎ ለማሳካት እንዲቻል አንዱ ኀይል መር በመሆኑ ከአባይ ተፋሰስ አገራት ጋር በተለይ ከግብጽ ጋር መስማማት ቅድሚያ ሰጥተው የሠሩት ጉዳይ ነበር። በዩጋንዳ ከፕሬዝዳንት ሙሴቬኒ ጋር ከተወያዩ በኋላ በሰኔ 2010 ወደ ካይሮ በማቅናት ከፕሬዝዳንት አብድል ፋታህ አል ሲሲ ጋር ተወያዩ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “የግብጽ ሕዝብ እንዲረጋጋ እባክህ በአላህ ሥም ማልልኝ” ብለው የግብጹ መሪ በቀጥታ በቴሌቪዥን በሚተላለፍ ንግግር ላይ ሲጠይቋቸው “ወላሂ… ወላሂ… ግብጽን አንጎዳም” ብለው ማሉ። ይህ የኢትዮጵያ የምን ጊዜም አቋም በመሆኑ ምንም ጉዳት የለውም። የጠቅላይ ሚኒስትሩ መሐላ እና መገዘት ግን ግብጽን ያረካ አይመሥልም። “ወንድሜ ሆይ” ብለው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን የጠሩት የግብጹ መሪ እውነት ወንድም ሆነው ይሆን? በፍጹም። ኢትዮጵያን ክፉ ለማስመሰል አሁንም የግብጽ ወገን በመላው ዓለም እየዞረ እየሰበከ እንደሆነ ጉዳዩን በቅርበት ከሚከታተሉ ሰዎች ማረጋገጥ ችያለሁ። በከፍተኛ ደረጃ በምዕራበውያን አገራት እና በዐረቡ ዓለም ግብጾቹ ዘመቻ እንዳበዙ ሰምተናል። ይሄ ሁሉ ኢትዮጵያን ለመጉዳት የሚረጭ መርዝ ነው።
ትልቁ ንክሻ ከላይ አዲስ ማለዳ ርዕሰ አንቀጽ ያደረገችው እና ዋዜማ ሬዲዮ በነሐሴ 16 የዘገበው ጉዳይ ነው። የግብጽ ወገን ያቀረበው ሐሳብ ኢትዮጵያን የመንከስ ነው። ጉዳዩን በዋዜማ ሬዲዬ ካየሁ ወዲህ መረጃዎችን ሳሰባስብ እና ጉዳዩን ከሚከታተሉ ሰዎች ጋር በነበረኝ ውይይት እንደተረዳሁት በአንድም በሌላ መልኩ በዋዜማ ሬዲዬ የቀረበውን ሐተታ የሚያረጋግጥ ሆኖ አግኝቸዋለሁ። የግብጽ መንግሥት ባቀረበው ሰነድ መሰረት “ኢትዮጵያ በዓመት 40 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ከግድቡ ውሃ እንዲለቀቅላት መጠየቋን፣ ግድቡ የሚሞላው በግብጽ ይሁንታ እንደሆነ፣ እንዲሁም ግብጽ ዳሷን እና ማማዋን በጉባ ተራሮች ላይ ቀልሳ ኢትዮጵያ ግድቡን ኦፕሬት ስታደርግ መከታታል እንደምትፈልግ” በግልጽ መጠየቋን መረዳት ችያለሁ።

የግብጽ ድፍረት ይህ ነው። በአጭሩ የግብጽ መንግሥት ጥያቄ አዲስ ማለዳ ጋዜጣ በርዕሰ አንቀጿ እንደገለጸችው “ኢትዮጵያን ቅኝ እንግዛት” የሚል ነው። ግብጽ ይህን ድፍረት ያመጣችው ኢትዮጵያ “ተዳክማለች። አልተረጋጋችም” ከሚል ስሌት ይሆናል መቼም። በእርግጥ የፖለቲካ ኀይሎቻችን የጎሳ ጎተራቸው ተቀርቅረው እንካ ስላንትያ ከገጠሙ ብልጡ ግብጽ አጋጣሚውን ሊጠቀም ቢሞክር የሚደንቅ አይሆንም። ጥፋቱ የአገሪቱ የፖለቲካ ኀይሎች ነው። ይህን አይተው ግብጾች መድፈራቸው ባያስገርምም ማበሳጨቱ ግን አይቀርም። አንድ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ እና በጉዳዩ ዙሪያ ምርምር ያደረጉ የዩኒቨርሲቲ መምህር በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ሳዋያቸው “እንዲህ ዓይነት የግብጽ ጥያቄ ከመጣ የአድዋ ጦርነትን፣ የዶጋሊን፣ የመተማን፣ የጉንደት እና ጉራዕን፣ የአምስቱ ዓመታት የጸረ ፋሽስት ጦርነቶች ማድረግ አያስፈልግም” ነበር ብለውኛል፤ በጣም እስማማለሁ።

በኢትዮጵያ በኩል ይህን ጉዳይ በተመለከተ ከምኒልክ በቀዳማዊ ኀይለሥላሴ እና መንግሥቱ ኀይለማርያም እስከ መለስ ዜናዊ፣ ኀይለማርያም ደሳለኝ እና ዐቢይ ድረስ የኢትዮጵያን የአባይ ወንዝ የተመለከተ አቋም እና ፍላጎት እንዲሁም ጥቅም በተመለከተ ሁሉም አንድ ዓይነት፣ የማያወላዳ እና ግልጽ አቋም ማራመዳቸው ነው። ሁሉንም መሪዎች አንድ ከሚያደርጓቸው ጉዳዮች አንዱ ይሔው የአባይ ጉዳይ ነው። ግብጽም ምን ንክሻዋ የኢትዮጵያን ድክመት እየተከተለ የሚመጣ ቢሆንም ይህን ጠንቅቀው እንደሚያውቁት እና እንደተከላከሉ አያጠራጥርም። ጉንደትን፣ ጉራዕን እና ጉባን በአንድ ላይ እንደሚያዩ ምንም አያወላዳም። ንክሻው ግን እነሆ ቀጥሏል!

ምን ይበጃል?
ምን ይበጃል የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ የአባይ ውሃ ለኢትዮጵያ ምን እንደሆነ መመልከቱ ቁልፍ ይሰጣል። የአባይ ውሃ ለኢትዮጵያ ሕይወት ነው። የመኖር እና ያለመኖር ጥያቄ ነው። በተደጋጋሚ ባይገለጽም ቁጥሮቹ እና ሳይንሱ ይህን እውነት ያረጋግጥልናል። የአባይ ወንዝ በኢትዮጵያ የናይል ተፋሰስ አካል በመሆኑ ከእነ ተከዜ እና ባሮ አኮቦ ጋር በመሆን የኢትዮጵያን ከ70 በመቶ በላይ የውሃ ሀብት ይሸፍናል። ይህ ማለት የኢትዮጵያ የውሃ ሀብት ጥገኝነቱ በአባይ፣ ተከዜ እና ባሮ አኮቦ ላይ ነው ማለት ነው። ይህ ተፋሰስ አሁን ባለው የፌዴራል አወቃቀር ትግራይ፣ አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ እና ደቡብ ክልልን የሚያካልል ነው። የአገሪቱንም 36 በመቶ የቆዳ ስፋት ይሸፍናል። በዚህ ተፋሰስ ውስጥ በቀጥታ የሚኖረው ሕዝብም ወደ 45 በመቶ ይጠጋል። ከላይ በተጠቀሱት ክልሎች የሚኖረው ሕዝብ ደግሞ የአገሪቱን ከ90 በመቶ በላይ የሚሸፍን ነው።

ወደ ኢኮኖሚ ሲመነዘር ይህ ወንዝ የኢትዮጵያ በልቶ የማደር እና ያለማደር ጥያቄ መልስ ነው። አገራችን “አረንጓዴ ረሐብ” መታወቂያዋ የሆነው ይህን የመሰለ የውሃ ሀብት ይዛ የምትራብ በመሆኗ ነው። ተፋሰሱ ኢትዮጵያ ካላት ወደ 45 ሺሕ ሜጋዋት ኀይል የማመንጨት አቅም ከ30 ሺሕ በላይ የሚሆነውን ይሸፍናል። ይህ የኀይል አለኝታ ተግባር ላይ ስናውለው የአገሪቱን የኀይል አቅርቦት ሙሉ በሙሉ ከመሸፈን አልፎ ለውጭ ገበያ የሚቀርብ መሆኑ አያጠራጥርም። የአገሪቱን ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለማስፋፋትም እና በአገሪቱ በተለያየ አቅጣጫ ያለሥራ የተቀመጠውን በሚሊዮኖች የሚቆጠር ወጣት ወደ ሥራ ለማሰማራት ዓይነተኛ ሚና አለው። በአገራችን በመስኖ ሊለማ የሚችል ሰፊ መሬት አለ። የአገሪቱ የመስኖ አለኝታ ውስጥ 2/3ኛው ወይም ወደ 2.7 ሚሊዮን ሔክታሩ የሚገኘው በአባይ፣ ተከዜ እና ባሮ-አኮቦ ተፋሰስ ውስጥ ነው። ይህን ወንዝ የማልማት እና ያለማልማት ጥያቄ የሞት እና የሽረት ወይም የህልውና ጥያቄ ነው ማለት ነው። የሕዳሴ ግድብ ግንባታ የተጀመረውም በዚሁ ማዕቀፍ ሥር ነው። ስለሆነም ይህ የኢትዮጵያ መሰረታዊ ጥያቄ በመሆኑ የኢትዮጵያ መንግሥት ይህን የማስጠበቅ ኀላፊነት አለበት ማለት ነው።

ይሁን አንጅ አባይ ድንበር አቋርጦ የሚፈስ ወንዝ ነው። በዓለማቀፍ ወንዞች አጠቃቀም ሕግ መሰረት አገራት ፍትሐዊ እና ሚዛናዊ የመጠቀም መብት እንዳላቸው ተደንግጓል። በመሆኑም ለአባይ ወንዝ አጠቃቀም መፍትሔው ይህን ዓለማቀፍ መርህ እና ደንብ መተግበር ነው። ትብብር ከምንም በላይ የሚጠቅመውም የውሃ ተቀባይ አገራትን ነበረ። ለዚህም ነው ሁሉም የአባይ ወንዝ ተጋሪ አገራት የአባይ/ናይል የትብብር ስምምነት እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ2010 በኢንቴቤ ዩጋንዳ ከዐሥራ ሦስት ዓመት ድርደር በኋላ የተፈራረሙት። ግብጽ ሱዳንን አስከትላ ተቃወሞች። ግብጽ ለዘመናትም እነዚህ አገራት እንዳይተባበሩ እና በጋራ እንዳይቆሙ ለማድረግ ስትጥር ቆይታለች። ለዚህ ነው ቻላቸው አሸናፊ “አንዲቷ ጎረቤት ያለውን ስትቀዳው፣ እኛ ብዙ ሆነን ተጠማን ከጓዳው” ሲል የገለጸው። ለግብጽ የሚጠቅመው ትብብር ነው። ለወንዙ ተጋሪ አገራት የሚጠቅመው ይህ ነበር፤ በጋራ መቆም።

የግብጽ ልኂቃን ፍላጎት ግን በአጭሩ ትብብር ሳይሆን ኢትዮጵያን በመዳፋቸው ሥር አድርገው እንደልባቸው እየቀጠቀጡ ውሃውን የሚወስዱበት ጓዳ ለማድረግ ነው። ኢትዮጵያን በተፈጥሮ ጠላትነት የሚያይ ሸውራራ መነጸር እንዳላቸው የማይታበል ሐቅ ነው።

የግብጽ የነበረ፣ ያለ እና ወደፊትም የሚኖር ጸረ-ኢትዮጵያ አቋም አባይን እንዳንጠቀም ማድረግ እና ያለን ማናቸውም የአገራችን ጥቅም ለመንጠቅ እና ኢትዮጵያን በድኅነት ስትማቅቅ የምትኖር ሆና ማየት ከዚህ ሲከፋም እንድትፈራርስ እና እንድትበታተን ማድረግ ነው። ይህ የግብጽ ኢትዮጵያን የተመለከተ አቅጣጫ እና አመለካከት በ19ኛው ክፍለ ዘመን ዋርነር ሙዚንጀር በተባለ ስዊዛዊ የተቀረጸ ነው። ግብጽ በኢትዮጵያ ላይ ያለውን አቋም ይቀይራል ብሎ ማሰብ ጊንጥ ጊንጥነቱን ተወ ማለት ነው። ስለሆነም ኢትዮጵያ ግብጽ የሚባለው አገር የሚቀየር ሳይሆን የማይቀየር ተፈጥሯዊ እና ታሪካዊ ጸረ ኢትዮጵያ አመለካከት ያለው የህልውናችን ፈተና እንደሆነ በማሰብ መንቀሳቀስ አለባት።

የግብጽ የአሁን አካሔድም የኢትዮጵያን ህልውና፣ ህልም እና ራዕይ ለመንጠቅ እና ለማኮላሸት ነው። የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከተማሪ እስከ ምሁር፣ ከቀን ሠራተኛ እስከ ባለሀብት፣ ከጉሊት ቸርቻሪ እስከ አስመጪ እና ላኪ፣ የመንግሥት ሠራተኛ፣ ምስኪን ኢትዮጵያውያን ነገን ተስፋ በማድረግ ለአገር ዕድገት ካላቸው ቀንሰው እየገነቡት ያለ የኢትዮጵያ ሕዝብ የላብ እና የወዝ ውጤት የሆነ ታላቅ ግድብ ነው። ይህን ግድብ ምንም ይሁን ምን የመጠበቅ እና የማጠናቀቅ ኀላፊነት የሁሉም ኢትዮጵያዊ ነው።

የፖለቲካ ኀይሎቻችን የውስጥ ችግራችሁን እየፈታችሁ ሁላችሁንም ቀርጥፎ ሊበላ ያሰፈሰፈውን የጋራ ጠላታችሁንም እያስተዋላችሁ እንድትራመዱ ይመከራል። የሕዳሴ ግድብን በተመለከተ ሁላችሁም በአንድ ላይ በጋራ የምትቆሙበት ጊዜ እንደሆነ አስቡ። የመቶ ሚሊዮን ሕዝብ ጉዳይ አናታችሁ እንዳለ አስባችሁ በጋራ ተሰለፉ። መንግሥትም አሁን ያለውን የግብጽ ወገን ተናካሽ አካሔያድ ለሕዝቡ ሊያሳውቅ ይገባል። በእርግጥ ከአሁን በፊት እንደተደረገው በስክነት እና በእርጋታ መጓዝ ጥቅሙ ከፍ ያለ ነው። ነገር ግን የግብጽ አካሔድ ጠንክር ብሎ እየመጣ ስለሚመስል ሕዝቡን ማሳወቅ ጊዜ ሊሰጠው የሚገባ ሊሆን አይገባም። ጋዜጠኞችም ጉዳዩን እያነፈነፉ የዜግነታቸውን ሊወጡ ይገባል።

ብርሃኑ ተስፋዬ በአፍሪካ እና መካከለኛው ምሥራቅ ዙሪያ ንባብ የሚወዱ እና ምርምር የሚያደርጉ ባለሙያ ናቸው።

ቅጽ 1 ቁጥር 45 መስከረም 3 2012

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here