ኢዜማ ከ70 በላይ በሚሆኑ አገራት ዓለምአቀፍ የድጋፍ ማኅበር አቋቋመ

0
815

የኢትዮጲያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ከ70 በላይ በሚሆኑ በመላው ዓለም በሚገኙና ኢትዮጵያውያን በሚኖሩባቸው ከተሞች ላይ የዓለማቀፍ የድጋፍ ማኅበሩን የማቋቋም ሥራ መጀመሩን አስታወቀ።

ኢዜማ ከምሥረታው ጀምሮ በሀገር ውስጥ 400 በሚደርሱ የምርጫ ወረዳዎች አባላትንና ደጋፊዎችን ማደራጀቱን ለአዲስ ማለዳ ያስታወቁት የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ናትናኤል ፈለቀ፣ ፓርቲው የጀመረውን ሀገራዊ ጥረት ለማገዝና በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ኢኮኖሚያዊ፤ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ተገቢውን ተሳትፎ በማድረግ ለሀገራቸው እድገት የአቅማቸውን ገንቢ አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ በማሰብ፣ የኢዜማ ዓለም አቀፍ የድጋፍ ማኅበርን ማቋቋምና ማደራጀት ተገቢ ነው ብሎ በማመኑ ማኅበሩን አቋቁመናል ብለዋል።

በመሆኑም የዓለማቀፍ የድጋፍ ማኅበሩን የማቋቋም ሥራ ከ70 በላይ በሚሆኑ በመላው ዓለም በሚገኙና ኢትዮጵያውያን በሚኖሩባቸው ከተሞች ላይ የተጀመረ ሲሆን፣ ማንኛውም የኢዜማ መሠረታዊ የፖለቲካ መርህ በሆኑት ዜግነትን መሰረት ያደረገ ፖለቲካ እና በማኅበራዊ ፍትህ የሚያምን/የምታምን ኢትዮጵያዊ ሁሉ በየከተሞች በሚመሠረቱት የድጋፍ ማኅበራት አባል መሆን እንደሚችሉ አስታውቀዋል።

እንደ ናትናኤል ገለጻ፣ የኢዜማ ዓለም አቀፍ የድጋፍ ማኅበር ፓርቲው በሀገር ውስጥ በተቋቋመበት መንገድ በአባላት በሚመረጡ አስተባባሪዎች የሚመራ ሲሆን፤ በክፍለ ዓለም ደረጃና በአጠቃላይ በዓለማቀፍ ደረጃ የሚመረጡ አመራሮችም በተመሳሳይ መልኩ በዴሞክራሲያዊ መንገድ በከተሞች ላይ በተዋቀሩት አባላት የሚመረጡ ይሆናል። በሀገር ውስጥ ማንም ሰው በወረዳው አባል ሳይሆን በሌሎች የፓርቲ መዋቅሮች መሳተፍም ሆነ አመራር መሆን እንደማይችለው ሁሉ በዓለማቀፍ የድጋፍ ማኅበሩም በከተሞች ላይ አባል ሳይሆኑ በሌሎች የማህበሩ የድጋፍ እንቅስቃሴዎች መሳተፍ አይችሉም።

ኢዜማ በፓርቲው ፕሮግራምም ባዘጋጀው በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ፖሊሲ ላይ በግልፅ እንዳስቀመጠው፣ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በሀገር ውስጥ እንደሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በሀገራቸው ጉዳይ እኩል ይመለከታቸዋል ብሎ በማመኑ ይህንን አደረጃጀት መፍጠሩን አስታውቋል።

ኢዜማ እስካሁንም በሀገራቸው እየታየ ላለው የተስፋ ጭላንጭል ግዙፍ አስተዋፅዖ አበርክተዋል ብሎ በፅኑ ያምናል ሲሉ የገለጹት ናትናኤል፣ አሁንም ሆነ ወደፊት በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ጉዳይ ላይ የማይተካ ሚና እንደሚጫወቱ ይረዳል ብለዋል።

ፓርቲው በሀገር ውስጥ በሚገኙ የምርጫ ወረዳዎች እንዲሁም በውጭ ሀገራት ኢትዮጵያውያን በሚኖሩባቸው ከተሞች ሁሉ ሕዝብን በስፋት እያደራጀሁ ነው ብሏል።

ቅጽ 1 ቁጥር 46 መስከረም 10 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here