መነሻ ገጽርዕስ አንቀፅለሕዝብ የማሳወቅ ግዴታችሁን ተወጡ!

ለሕዝብ የማሳወቅ ግዴታችሁን ተወጡ!

የአንድ አገር መንግሥት ተጠሪነቱም ሆነ አገልግሎቱ ለሕዝብ እንደሆነ ይታወቃል። ይህ ሳይሆን ቢቀር አምባገነን ገዢ እንጂ መሪ የሚባል የመንግሥት አካል እንደማይኖር ቃሉ በራሱ ያስረዳል።

የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ እንደሚያሳየው ሕዝብ ከመንግሥት መረጃ የሚጠብቀውን ያህል፣ መንግሥት የሚያስተዳድረውን ኅብረተሰብ መረጃ እንዳያገኝ ሲያፍን ነው የሚስተዋለው። መረጃ ማግኘት መብት እንደመሆኑ፣ መረጃውም ሆነ አድራሹ በማንም ቢሆን ለምንም ምክንያት ከሕግ ውጪ ሊታፈን እንደማይገባ አዲስ ማለዳ ታምናለች።

ሠሞኑን ፖለቲከኞች፣ ግለሰቦች፣ ታጣቂዎችና ጋዜጠኞች ታፈኑ ሲባል እንደምንሰማው፣ ለሕዝብ መድረስ የሚገባው መረጃ መታፈን ከጀመረ ዘመናትን አስቆጥሯል። ለውጥ የተባለው የአመራር ቅያሬ ከተደረገም ወዲህ፣ ገና ከመነሻው ግብፅ የተደረገን ስምምነትም ሆነ ንግግር ለማወቅ ሕዝቡ እንደቋመጠ ቀርቷል።

እንደቀልድ በደጋፊዎች እየተሸፋፈነ በተቀናቃኞችም እየተወሳሰበና እየተጠመዘዘ መቅረብ የተጀመረው መረጃን የመንፈግ አልያም የመደበቅና አዛብቶ የማቅረብ ሁኔታ መሻሻል ሳያሳይ እስከ አሁን ቆይቷል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ የተደረገው የግድያ ሙከራን አጣርተው መረጃ ያቀርባሉ እንደተባሉት የውጭ ኃይሎች፣ ቀጥለው የተከሰቱት የኢንጂነር ስመኘው ግድያም ሆነ የአማራ ክልል ባለሥልጣናት ተገዳደሉ መባል በገለልተኛ ወገን ተጣርቶ ሁሉም የተቀበለው መረጃ ይፋ ሳይደረግ ተድበስብሶ ቀርቷል።
ትክክለኛ መረጃ ከመነሻው ጀምሮ በወቅቱ መለቀቅ አለመቻሉ ሕዝቡ ለአወናባጆችም ሆነ ለአሉባልታ እንዲጋለጥ ከማድረጉ ባሻገር፣ ያልተገባ ድጋፍም ሆነ ተቃውሞ ለመንግሥትም ሆነ ለተቃዋሚዎቹ እንደሚቸር አዲስ ማለዳ ማስገንዘብ ትፈልጋለች።

መረጃ አሁን ላለው ዘመናዊ ለሚባለው ትውልድ የሞት ሽረት ጉዳይ መሆኑ ሊታመንበት ግድ ይላል። እውነታውን ትተው የፈለጉትን ማዳነቂያውን ብቻ እየለዩ ሚዲያ ፊት መቀመጥ፣ የተራ አሉባልተኛ ድርጊት እንጂ የመንግሥትም ሆነ የባለሥልጣናት የእለት ተእለት ተግባር መሆን አልነበረበትም።

የሰሜኑ ጦርነትን በተመለከተ፣ የተጀመረ ቀን በሰዓታት ልዩነት የወጣው መረጃ፣ ታማኝነቱ እንደሰሚው አቋም ሊለያይ ቢችልም፣ ፍጥነቱ ግን የሚያስመሰግን ነበር። ይህ ሂደት ግን ሽንፈት ነው ሊያስብል በሚችል መልኩ አለመዝለቁ ብዙ ሊያስገምት የሚችል ነው። ከትግራይ የተወጣበት ሂደትም ሆነ ጦርነቱ እዚህ ደብረሲናን አልፎ ዋናዋ መዲና እስኪቃረብ ኅብረተሰቡ መረጃውን የሚያገኝበት መንገድ እንደ አገር የሚያሳፍር ነበር።

እውነቱን የተናገሩ ጋዜጠኞች እንዲባረሩ በኋላም እንዲታሰሩ ከማድረጉ ባሻገር፣ ኅብረተሰቡ ትክክለኛውን መረጃ አግኝቶ እንዳይዘጋጅም ሆነ እጣ ፋንታውን በጸጋ እንዳይቀበል ማድረጉን ብዙዎች ይስማሙበታል። ይህ ተግባር ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግንባር ተገኙ ሲባል ተገልብጦ ቶሎ ቶሎ እንደ ፕሮፓጋንዳ እንዲዘገብ ተደርጎ ነበር።

ይህ ዓይነት ያልተገባ አሰራር በሌሎች አገራትም ሊኖር ቢችልም፣ ከአገራችን ታሪክና ባህል አኳያ ተቀባይነት ይኖረዋል ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው። በአምባገነንነት የሚፈረጁት የቀድሞ መሪዎች እንኳን ከሕዝባቸው የሚደብቁት ነገር ስለማይኖር፣ ሁሉንም ድርድርንም ጨምሮ ምክራቸውን በአደባባይ ያከናውኑ እንደነበር ጠላቶቻቸው ከጻፉትም የታሪክ ማስረጃ ማወቅ ይቻላል።

ሕዝቡን እንደጦር የሚፈራና የማይፈራ መንግሥትን ከሚለዩት ባሕሪያት መካከል፣ እያንዳንዷን ነገር ከኅብረተሰቡ ዕይታ ሰውሮ በድብቅ ማድረግ ዋነኛው እንደሆነ ይታመናል። ከዚህ አንፃር አሁን ያለው የኢትዮጵያ መንግሥት የውጭ ጠላትንም ሆነ ፈጣሪን ከሚፈራው ይልቅ ሕዝቡን ስለሚፈራ የሚያደርገውን ተግባር ተሸሽጎ ይፈፅማል ማለት ይቻላል።

ይህን የሚያስብለው ከተቀናቃኞቹ ጋር የሚያደርጋቸውን ስምምነቶችም ሆኑ ድርድሮች ደብቆ ከማድረጉ ይልቅ ይበልጥ የሚያሳስበው በኹሉም ጎራዎች ያሉ የተደራዳሪ ተወካዮች በምስጢራዊ መንገድ ለመነጋገር መስማማታቸው ነው። ይህን ዓይነት በፖለቲከኞች ብቻ የሚወሰን መላውን ሕዝብ የሚነካ ተግባር ሊቀር እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ታምናለች።

ከጦርነቱ መቀዛቀዝ ወዲህ አሁንም ለተፋፋመ ውጊያ ዝግጅት እንደሚደረግ እየተነገረ ባለበት ወቅት፣ ጎን ለጎን የሚደረግ ድርድር እንዳለ ይሰማል። መንግሥት ምንም ዓይነት ድርድር እያደረግሁ አይደለም እያለ በተደጋጋሚ ለማስተባበል ቢሞክርም፣ በተቃራኒው ያለ እውነታን የሚያንፀባርቁ መረጃዎች ግን አደራዳሪ ነን ከሚሉ ዓለም ዐቀፍ ተቋማትም ሆኑ ዝነኛ ሰዎች ሲነገር ይሰማል።

በኬንያ ነበረ ስለተባለ ድርድርም ሆነ በናይጄሪያው የቀድሞ መሪ በተደጋጋሚ ስለሚደረጉ የምልልስ ተግባሮች መንግሥት ምንም ዓይነት ፍንጭ ለሕዝቡ ሳይሰጥ ወራት ተቆጥረዋል። ከመንግሥት በተቃራኒው ረድፍ የተሰለፈውና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀው አካል ግን በተቃራኒው ድርድር እየተደረገ እንደሆነ ለሚመራውም ሆነ ለሚገዛው የማኅበረሰብ ክፍል የተዛባ ሆነም አልሆነ፣ በአንፃራዊነት በተሻለ መረጃን ሲያቀርብ ይስተዋላል።

ከአሸባሪ ጋር መነጋገር በሕግ ማስጠየቁ እንዳለ ሆኖ፣ ለድርድር አይደለም ቢባልም የመንግሥት ባለሥልጣናት አደራዳሪ የተባሉ አገራትን ያለወትሯቸው መጎብኘታቸው ለሌላ ውዥንብር በር መክፈቱን አዲስ ማለዳ ትታዘባለች።

ሕዝብ በኑሮ ውድነት ተወጥሮ መጪው ሕይወቱ ምን እንደሚመስል ከሚያሳስበው በላይ የአገሪቱ እጣ ፋንታ ይበልጥ እንደሚያሳስበው፣ አገር አደጋ ላይ ወደቀች ሲባል ማን ፈጥኖ እንደሚደርስ የታየበት የቅርብ ታሪካችን አመላካች ነው። ይህ ሆኖ ሳለ ታዲያ፣ እንዲህ ስለሕዝብ ደኅንነትም ሆነ ስለአገሩ የሚጨነቅን ሕዝብ ከመረጃ ነጥሎ እንደፈለኩት አደርጋለሁ ብሎ መሞከር ከታሪክ አለመማር መሆኑ ሊታወቅ ይገባል።

ትክክለኛ መረጃ በተገቢው መንገድና ጊዜ ለሕዝብ ይፋ አለመደረጉ የሚያስከትለውን የዘመናት መዘዝ ከሐውዜኑ ታሪክ መማር ግድ ይላል። በአንድ እውነታ ላይ ማኅበረሰቡ ሊያቀራርበው የማይችል ጽንፍ የረገጠ የተለያየ አመለካከት እንዲኖረው የሚያደርገው፣ በማስረጃ የተደገፈ መረጃን በወቅቱ መንፈግ መሆኑን አዲስ ማለዳ ታስገነዝባለች።

በቀድሞ ዘመን በራስ አሊ እና በደጃች ውቤ መካከል በተደረገ የአንድ ቀን ውጊያ፣ መረጃ በወቅቱ ለተዋጊው አለመድረሱ ድል ከአንዱ እጅ ወደሌላው ደጋግማ እንድትመላለስ ማድረጉን ታሪክን የሚያስተውሉ ሊማሩበት ይገባል። ስለውጊያ ሂደቱ የተጠየቀ አንድ አርሶ አደር ተዋጊ ክስተቱን ላልነበሩት ሲያስረዳ በማወሳሰቡ፣ አጥርቶ እንዲነግራቸው ሲጠይቁት በመለሰው ምላሽ ሁኔታውን መረዳት ይቻላል። ገዢዎቹ በወጉ ያላደረጉትን እኔ እንዴት በወጉ አድርጌ ልንገራችሁ በሚል ለድልም ሆነ ለሽንፈት ወሬም ቢሆን የመረጃ አስፈላጊነትን ባልተማረ አንደበቱ አስረድቷል።


- ይከተሉን -Social Media

ቅጽ 4 ቁጥር 187 ግንቦት 27 2014

ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች