መነሻ ገጽዜናአቦል ዜናዳግም በተቀሰቀሰ ጦርነት ሕወሓት ሦስት የቆቦ ወረዳ ቀበሌዎችን መቆጣጠሩ ተነገረ

ዳግም በተቀሰቀሰ ጦርነት ሕወሓት ሦስት የቆቦ ወረዳ ቀበሌዎችን መቆጣጠሩ ተነገረ

10 ንጹሐን ሰዎች ተገድለዋል ተብሏል

በኢትዮጵያ መንግሥትና በሕወሓት መካከል ዳግም በተቀሰቀሰ ጦርነት ሕወሓት ሦስት የቆቦ ወረዳ ቀበሌዎችን መቆጣጠሩን የአካባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።

በሰሜን ወሎ ዞን ቆቦ ወረዳ የሚገኙ ስሚዛ ጊዮርጊስ፣ መቀነት ጋሪያ፣ ጃን አሞራ የተባሉት ቀበሌዎችን ሕወሓት መቆጣጠሩን የአካባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትና በአካባቢው ያሉ ሚሊሻዎች ታጣቂ ቡድኑ የሚሰነዝረውን ጥቃት ለመመከት ቢሞክሩም ይህ ዘገባ እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስ ለጥቃት ምቹ የሆኑ ስትራቴጅክ ቦታዎች በሕወሓት ቁጥጥር ስር ናቸው ተብሏል።

ከዚህም በተጨማሪ በግዳን ወረዳ ሙጃና ላስታ አካባቢ አልፎ አልፎ የሕውሓት ቡድን ሰርጎ በመግባቱ ቦታው አፋጣኝና ልዩ ትኩረት እንደሚያሻው ነዋሪዎቹ ጥቆማ ሰጥተዋል።

በደጋማው አካባቢ የሚገኙ ንጹሐን ዜጎችን ታጣቂ ቡድኑ ሚሊሻ ናችሁ በማለት እየገደለ ነው የተባለ ሲሆን፤ እስከ አሁን ቁጥራቸው በግልጽ ያልታወቁ ነገር ግን ከ10 በላይ እንደሚሆኑ የሚገመት ሰዎች መገደላቸውንም ነዋሪዎች ተናግረዋል።

ይህ እስከ አሁን የተረጋገጠ ነው እንጂ የሟቾች ቁጥር ከዚህ ሊልቅ እንደሚችልም ተመላክቷል። ከሰዎች መሞት በዘለለም የሚሊሻ ቤተሰብ ናችሁ በሚል ሰበብ ከዚህ ቀደም በነበረው ጥቃት የተረፈው የበርካታ ነዋሪዎች ንብረት እየተዘረፈ መሆኑን ነው አዲስ ማለዳ ከቦታው የሰማችው።

እስከ አሁን ከደረሰብን ግፍ በትክክል አላገገምንም ያሉት ነዋሪዎቹ፤ ታጣቂ ቡድኑ በሚያደርሰው ጥቃትና የማስፋፋት ድርጊት ስጋት እንዳደረባቸው ገልጸው፤ ከዚህ የከፋ ጉዳት ከመድረሱ በፊት የወገን ኃይል እንዲደርስላቸው አሳስበዋል።

ታጣቂ ቡድኑ ከላይ ከተዘረዘሩት ደጋማ ስፍራዎች በተጨማሪ በአዲስ መልኩ ጥቃት የቀሰቀሰው በራያ ቆቦ ወረዳ በሚገኙ ቆላማ ቀበሌዎች ነው ተብሏል።

ሕወሓት ከዚህ ቀደም በንጹሐን ላይ ጉዳት ሲያደርስ በነበረባቸው ዋጃ፤ ጥሙጋ፤ ድንጋይ ቀበሌ እንዲሁም ጎለሻ የተባሉ ቀበሌዎች ላይም ለሦስተኛ ጊዜ ጥቃት የማድረስ ሙከራ ማድረጉን ነዋሪዎቹ ተናግረዋል። ጦርነቱ በይፋ ዳግም የተቀሰቀሰውም ባሳለፍነው ሰኔ 16/2014 ጀምሮ ነው።

ጎለሻ፤ ዋልካ መንደር እንዲሁም አገዳ ቀበሌ በመባል የሚታወቁት የራያ ቆቦ ወረዳ አካባቢዎችን ታጣቂ ቡድኑ ጥቃት ለማድረስ ተስፋፍቶ የነበረ ቢሆንም፤ የወገን ኃይል ባደረገው ጥቃት ወደኋላ ማፈግፈጉን መስፍን መጎስ ከተባሉት የአካባቢው ነዋሪ አዲስ ማለዳ ሰምታለች።

በዚህም ታጣቂ ቡድኑ ተቆጣጥሯቸው ከነበሩት ዋጃ፣ ጥሙጋ እና አየር ማረፊያ የተባሉ ሥፍራዎች ድል የመቀዳጀት እድሉ ከሽፎ ወደ አላማጣ በማፈግፈጉ ፋኖና ሚሊሻ እነዚህን ቦታዎች መቆጣጠራቸው ነው የተሰማው።

በነበረው ውጊያ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ባደረገው መሣሪያ የማቀበል እርዳታ ፋኖ እና ሚሊሻ የአንበሳውን ድርሻ ይዘው ነበር ሲሉ ነው መስፍን ለአዲስ ለአዲስ ማለዳ የተናገሩት።

ታጣቂ ቡድኑ በራያ ቆቦ ወረዳ በቆላማው ክፍል እንደ አዲስ በቀሰቀሰው ጥቃት ሲዋጋ የነበረው ሞርታርን ጨምሮ በሌሎች ከባድ መሣሪያዎች በመታገዝ የነበረ ቢሆንም፤ የንብረት ውድመትና ዝርፊያ ከማድረሱ በዘለለ በንፁሐን ላይ ያደረሰው ጉዳት የለም ተብሏል።

ታጣቂዎቹን በተመለከተ ግን ዋጃ ላይ በርካታ ያልተነሳ ሬሳ መኖሩ የተመላከተ ሲሆን፤ ምንም እንኳ ጥቃቱ ቢቀዛቀዝም አሁንም ቢሆን አካባቢው ጥበቃ እና ትኩረት እንደሚያስፈልገው ተመላክቷል።


ቅጽ 4 ቁጥር 190 ሰኔ 18 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች