መነሻ ገጽዜናአቦል ዜናበሰሜኑ ጦርነት ጉዳት ደርሶበት የነበረው የደሴ ሙዝየም ሊገነባ ነው

በሰሜኑ ጦርነት ጉዳት ደርሶበት የነበረው የደሴ ሙዝየም ሊገነባ ነው

በሰሜኑ ጦርነት ጉዳት ደርሶበት የነበረው የደሴ ሙዝየም ሊገነባ መሆኑን የደሴ ከተማ አስተዳደር ባህል ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።

የደሴ ከተማ አስተዳደር ባህል ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ስር የሚገኘው የደሴ ሙዝየም ልማት ኃላፊ መረሳ አየነው እንደገለጹት፣ በሙዚየሙ ውስጥ የዘመናት የታሪክ፣ የባሕል፣ የሥነ ጥበብ ውጤቶች እና ሌሎችም የፈጠራ ሥራዎች፣ ተፈጥሮአዊ እና ሰው ሠራሽ ቅርሶች እንዲሁም መረጃዎች ነበሩ፡፡ ነገር ግን እነዚህ ቅርሶች በሰሜኑ ጦርነት በሕወሓት ቡድን ዝርፊያ እና ውድመት ደርሶባቸዋል።

የደሴ ከተማ አስተዳደር ባህል ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ከክልሉ መንግሥት ጋር በመሆን 44 ሚሊዮን ብር በጀት በመያዝ በሕወሓት ቡድን በከተማዋ የሚገኘውና ጉዳት ከደረሰበት ከመርሆ ግቢ በተጨማሪ፣ የደሴ ሙዝየም ግንባታን ለመጀመር እንደታቀደ እና ይህም በቀጣይ ነሐሴ ወር ሥራው እንደሚጀመር ኃላፊው ጠቁመዋል።

በሙዝየሙ ውስጥ ጉዳት የደረሰባቸውን የጣራ፣ የበር፣ የመስኮት እና ሌሎች አካላትን ቅያሬ እንዲሁም ግንባታ ለሚያስፈልጋቸው ከማከናወን ባሻገር በቡድኑ የተዘረፉና የወደሙ ተንቀሳቃሽ ቅርሶችን በሌሎች ቅርሶች የመተካት ሂደት ይከናወናል ነው የተባለው።

የወደሙ እና የተዘረፉ ቅርሶችን የሚገልጽ በፎቶ ግራፍ የተደገፈ መረጃ አለ ያሉት ኃላፊው፣ በግዥ የሚገኙ ቅርሶችን ግዥ ከመፈፀም ባለፈ በማኅበረሰቡ ዘንድ ከወደሙት ጋር ተመሳሳይነት ያላቸውን ቅርሶች በመነጋገር ለመተካት ጥረት ይደረጋል ብለዋል።

በተጨማሪ ተዘርፈው በከተማዋ እና በአጎራባች አካባቢ ተበታትነው የሚገኙ ቅርሶች ካሉ ኅብረተሰቡ በማፈላለግ እና በማሰባሰብ ቅርሶችን ወደ ሙዝየሙ እንዲያስገቡ፣ እንዲሁም ጥቆማ እንዲሰጡ በሐይማኖት አባቶችና በመገናኛ ብዙኀን በማስነገር እየተሠራ መሆኑንም ኃላፊው ጠቁመዋል።

ኃላፊው አክለውም፣ በከተማዋም ሆነ እንደክልል በጤናው ዘርፍ፣ በትምህርት ተቋማት፣ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ እና በሌሎችም ዘርፎች ላይ ጦርነቱ ከፍተኛ ተፅእኖ አሳድሮ የነበረ መሆኑን ተከትሎ፣ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ዘርፎች ላይ ዞኑም ሆነ የክልሉ መንግሥት ትኩረት ማድረጉን ተከትሎ ለሙዝየሙ የግንባታ ሥራ መራዘም ተጠቃሽ ነው ብለዋል።

የደሴ ሙዝየም እና የመርሆ ግቢ ሙዝየም በክልሉ ከሚገኙ ሙዝየሞች ውስጥ በቀዳሚነት ተጠቃሽ እንደመሆናቸው መጠን፣ እንደ ቀድሞው የመዝናኛ እና የምርምር ማእከልነታቸው እንዲመለስ ከመንግሥት በተጨማሪ የግል ተቋማት እና ግለሰቦች ለግንባታው የሚያግዙ ቁሳቁሶችንም ሆነ የገንዘብ ድጋፍ በማበርከት ለሙዝየሙ አሻራቸውን እንዲያሳርፉ ኃላፊው ጠቁመዋል።

በሙዝየሙ 22 ክፍሎች ውስጥ ከሚገኙ አስደናቂ እና ማራኪ ቅርሶች መካከል የመጀመሪያው አፄ ምኒልክ ከጅቡቲ እና ከፈረንሳይ መንግሥት ጋር ግንኙነት ያደረጉበት የስልክ ቀፎ፣ በአድዋ ጦርነት ጊዜ ያገለገሉ የተለያዩ የጦር መሣሪያዎች፣ በ1890 ከፈረንሳይ መንግሥት የተበረከተ መድፍ፣ በኢትዮ-ጣልያን ጦርነት ጊዜ በኢትዮጵያዊያን የተማረከው የአየር መቃወሚያ ጉዳት ደርሶባቸዋል ብለዋል።

በተጨማሪ ከ450 ዓመት እድሜ በላይ ያስቆጠሩ የሸክላ ውጤቶች፣ አፄ ምኒልክ በአድዋ ጦርነት ጊዜ በጦር ሜዳ የተጠቀሙባቸው የጦር ሜዳ መነፅሮች እንዲሁም ከብር እና ከወርቅ የተሠሩ ታሪካዊ እና በአጠቃላይ ከ450 በላይ ውድ ቅርሶች ውድመት እና ዝርፊያ ተፈፅሞባቸው የነበረ ሲሆን፣ ጠፍተው የነበሩ18 ቅርሶች መመለሳቸውን ኃላፊው ጠቁመዋል።

እነዚህ ቅርሶች ተዘርፈው በከተማዋ ተገኝተው በኅብረተሰቡ ጥቆማ መሠረት ለሙዝየሙ እንደተመለሱ እና ከእነዚህ መካከል በአድዋ ጦርነት ወቅት ያገለገሉ ሦስት ጎንዴ መሣሪያ፣ ሦስት የንጉሥ ሚካኤል ብርሌዎች፣ ሦስት ጦሮች፣ ሦስት ጋሻዎች እና ኹለት የፕላስቲክ ወንበሮች ሲሆኑ፣ ቀሪዎች የቡና መውቀጫ ናቸው ተብሏል።

የደሴ ሙዝየም ከ1973 በፊት በንጉሥ ሚካኤል ቤተ መንግሥት ውስጥ ሆኖ የኢትዮጵያ ሕዝብን ባሕል፣ ታሪክ እና ማንነት የሚያሳዩ ሰነዶች ተሰንደውበት ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ የቆየ መሆኑም ተወስቷል።

ሙዝየሙ በ1973 በኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ተመርቆ ሥራ የጀመረ መሆኑንም ኃላፊው ጠቅሰዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 196 ሐምሌ 30 2014

 

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች