የወሰን ድርድር ወይስ የከተማ አጥር?

1
3102

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና በኦሮሚያ ክልል መካከል የወሰን ማካለል ሥራ መጠናቀቁን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በይፋ መናገራቸው ተሰምቷል። ድርጊቱ ከታቀደ ወደ ሰባት ዓመታት ገደማ ያስቆጠረ ነው። ዓላማውም በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ ሥፍራዎችን ወደ ኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት እንዲሁም በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ዙሪያ የሚገኙ አንዳንድ ሥፍራዎችን ወደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥር በማስገባት ወሰን ማካለልን ነው።

ይሁን እንጂ ድርጊቱ የሕዝብ ይሁንታን ያላገኘ እና ወደ ፌደሬሽን ምክር ቤት መቅረብ ሲገባው፤ በብልጽግና አመራሮች ብቻ የተከናወነ በመሆኑ ትችት አስከትሏል። የአዲስ ማለዳው ኢዮብ ትኩየ በጉዳዩ ዙሪያ የተለያዩ ምሁራንን በማነጋገር የሐተታ ዘማለዳ ርእሰ ጉዳይ እድርጎታል።

ለሰባት ዓመታት በበርካቶች በኩል እሰጥ አገባ ሲያስነሳ የኖረው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት መካከል ወሰን የማስቀመጥ ጉዳይ ተግባር ላይ መዋሉ እየተሰማ ነው።

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአዲስ አበባና የኦሮምያ ልዩ ዞን መካከል ያለው የአስተዳደር ወሰን ጉዳይ ባሳለፍነው ነሐሴ 10/2014 በስኬት መጠናቀቁን ገልጸዋል።

ታዲያ የወሰን ማካለሉን ተግባራዊ ለማድረግ የተጀመረው እንቅስቃሴ በመንግሥት በኩል ትግበራውን ቀድሞ በተጠናቀረ ‹‹በአዲስ መልኩ ተዘጋጅቷል›› በተባለ ጥናት ነው ቢባልም፤ በማህበረሰቡ፤ በሕግ ባለሙያዎች እንዲሁም በፖለቲካ ተንታኞች በኩል ሕገ ወጥ ስለመሆኑ እየተነገረ ነው።

በመሆኑም፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር ባሉ የተለያዩ ክፍለ ከተሞች የሚገኙ ቦታዎችን ወደ ኦሮሚያ ክልል ለማካለል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና የኦሮሚያ ክልል ባለድርሻ አካላት በአዲስ መልኩ መመሪያ ማስተላለፋቸው የባለፈው ሳምንት አነጋጋሪ ጉዳይ ሆኖ ነበር።

አሁናዊና ተግባር ላይ የዋለው የወሰን ማካለል ጉዳይ እስከዛሬ ድረስ አስተማማኝ ውሳኔ ተሰጥቶበት ‹‹እንዲህ ይሆናል›› ያልተባለ፣ ነገር ግን ቀድሞ በጉርምርምታ ሲድበሰበስ የኖረ፤ የውስጥ ለውስጥ የትችት ሽርሽር የጀቦነው አከራካሪ ጉዳይ ነበር።

ከአራት ዓመታት ወዲህ ባለው መንግሥት በኩል የሚስተዋለው ሥርዓት፣ ብሔር ተኮር ፖለቲካ የተሸረበበት ስለመሆኑ በየወቅቱ መንግሥት የሚያወርዳቸው መመሪያዎች ያሳያሉ ስለመባሉ የተለያዩ አካላት የሚሰነዝሩት አስተያየት ያሳያል።

ለአብነትም ከዚህ በፊት አዲስ አበባ የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማ ናት ሲባል መሰማቱ የሚታወስ ነው። ከሳምንታት በፊት የኦሮሚያ ክልል ባንዲራ በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ይውለበላባል መባሉ በርካታ ትችት እያስነሳ ያለ ሌላኛው ጉዳይ ነው። ይህንኑ ጉዳይ በማስመልከት በምክር ቤት ውሏቸው ጥያቄ ላቀረቡ አካላትም፣ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አበቤ አዲስ አበባ ‹‹የኦሮሚያ ዋና ከተማ ናት›› ማለታቸው ይታወሳል።

ታዲያ የኦሮሚያ ባንዲራ በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች ይውለበለባል ተብሎ የወረደው መመሪያም አዲስ አበባን ወደ ኦሮሚያ ክልል <ለማካተት> ቀዳሚው ማሳያ ነው እየተባለ ነው።

በሌላ በኩል፣ በኦሮሚያ ክልል (ወለጋ) የሚገኙ ነዋሪዎች ከሦስት ዓመት በላይ ለሆነ ጊዜ በተደጋጋሚ በታጣቂዎች መጨፍጨፋቸው ገና እልባት ያልተሰጠው ክስተት ሆኖ እያለ፤ ሰላም ባለበት ሥፍራ ወሰን ማካለል ከመንግሥት የማይጠበቅ ጉዳይ ስለመሆኑ ቅሬታቸውን የሚናገሩ አሉ።

ታዲያ በይፋ እየተተገበሩ ያሉት ማለትም በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ ነዋሪዎች በተደጋጋሚ በታጣቂዎች መጨፍጨፍ፤ የኦሮሚያ ባንዲራ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ለማውለብለብ መመሪያ ማውረድ፤ የአማራ ተወላጆችን ወደ አዲስ አበባ ከተማ እንዳይገቡ ደብረ ብርሃን ሲደርሱ መከልከል፤ ከሰሞኑ ሕዝበ ውሳኔ ሳይሰጥበት በአዲስ አበባና በኦሮሚያ መካከል ከተተገበረው ወሰን ማካለል ተዳምሮ ብሔር ተኮር አካሄድ ነው እያስባለ ነው።

በመሆኑም፣ ሰሞነኛው የወሰን ማካለል እንቅስቃሴ አዲስ አበባን ወደ ኦሮሚያ ክልል ለማስገባት የለየለት ተግባር እንጂ ለሕዝብ ጥቅም ያማከለ እንዳልሆነ ነው እየተገለጸ ያለው።

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ የኦሮሚያ ክልል ባለድርሻ አካላት፤ አክቲቪስቶችና ምሁራን በበኩላቸው፣ አዲስ አበባን ‘‘ፊንፊኔ” ብለው በመጥራት የኦሮሚያ ዋና ከተማ ሲሉ በተደጋጋሚ ይደመጣሉ።

አሁን አሁን ደግሞ አዲስ አበባን ወደ ኦሮሚያ ክልል ለማካለል እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ ጉዳዩን ይበልጥ እያናረውና በርካቶችን እያስቆጣ ይገኛል።

የተካለሉ ቦታዎች

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የሚካለሉ ስፍራዎች ከዚህ በፊት በተገኘ መረጃ ሲነገር የቆየ ሲሆን፤ ባሳለፍነው ነሐሴ 10/2014 የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ መናገራቸው ተሰምቷል።

ከንቲባዋ ተናግረዋል በተባለው መሰረት በኦሮሚያ የአዲስ አበባ ዙሪያ ልዩ ዞን ውስጥ በመግባት በርቀት በአዲስ አበባ የተገነቡ ኮንዶሚኒየሞች ኮየ ፈጬ፤ ቱሉዲምቱ በከፊልና ጀሞ ቁጥር ኹለት የሚገኙበትን ወደ ኦሮሚያ ልዩ ዞን እንዲካለሉ መደረጋቸውን አሳውቀዋል።

እንዲሁም በኦሮሚያ የተገነባውን የቆጣሪ ኮንዶሚኒየም ማለትም ለቡ አካባቢ፤ ከፉሪ ሃና እና በኦሮሚያ ያሉ ኮንዶሚኒየሞች ጨምሮ እስከ ቀርሳ ወንዝ ያለውን ወደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እንዲካለሉ በማድረግ ስምምነት ላይ መደረሱንም ከንቲባዋ መናገራቸው ተሰምቷል።

የሕዝቡ እጣ ፈንታ

ዓለም ከጫፍ እስከ ጫፍ በብዙ ውስብስብ መሰናክሎች የተሸበበች ውጣ ውረድ የበዛባት የሰው ልጆች መናኸሪያ ሆና ትስተዋላለች። ታዲያ እንኳን የዘር ፖለቲካ ተስፋፍቶ አንዱ ብሔር ሌላኛውን እንደባላንጣ በቆጠረበት ጊዜ፣ በሰላማዊ ዘመንም ቢሆን ከኖሩበት ቦታ ከአንዱ ወደ ሌላኛው መካለል እንዲሁ ቀላል የማይባል ውጣውረድ ማስከተሉ አይቀሬ ነው።

ጉዳዩ ውሳኔ ላይ የደረሰው የብልጽግና አባላት ተሰባስበው በወሰኑት ሥልጣናዊ መከታቸው ቢሆን እንጂ የሕዝብ ፍላጎት እንዳልተጨመረበት በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ነዋሪዎች ይናገራሉ።

ወደ ኦሮሚያ ክልል እንዲካለሉ የተደረጉት ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ እንደገለፁት ከሆነ፤ መንግሥት ይህን ወሰን ከማካለሉ በፊት በጉዳዩ ዙሪያ ሊያነጋግራቸው ይገባ እንደነበር ቅሬታቸውን አንስተዋል።

ለወሰኑ የቀረቡ ምክንያቶችና አሳማኝታቸው

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር የሚገኙ ወረዳዎችን ወደ ኢሮሚያ ክልል እንዲሁም አንዳንድ ሥፍራዎች ወደ አዲስ አበባ የማካለል አስፈላጊነቱ በብልጽግና ፓርቲ በኩል እንደ ምክንያት የተዘረዘሩ ጉዳዮች አሉ። አንደኛውና የመጀመሪያው ምክንያት ከተማዋ በከፍተኛ ሁኔታ ሰፍታለች በሚል ጥንስስ ስለመሆኑ ጉዳዩን አስመልክቶ ተዘጋጀ በተባለው ጥናት ተጠቅሶ ይገኛል።

ይኸውም፣ አዲስ አበባ በየጊዜው መጠኗ ከልክ በላይ በመስፋቱ በዙሪያው ያሉ የኦሮሚያ አርሶ አደሮችን እያፈናቀለ ከመሆኑም በላይ አርሶ አደሮቹ ከተፈናቀሉ በኋላ በቂ የመቋቋሚያ ካሳ ባለመሰጠቱ እንግልት ላይ በመሆናቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ችግሩን ለመፍታት በጥናት መመርኮዝ መሻታቸውን የሚገልጽ ነው።

ከዚህ ቀደም ጥናቱን ያገላበጡና በፖለቲካዊ ጉዳዮች ጥልቅ እውቀት ያላቸው ምሁራን ደግሞ ለወሰን ማካለሉ የተሰነዘረውን ምክንያት እርባና ቢስ እና አስመሳይነት የተሞላበት ሲሉ ይተቻሉ።

<<ጥናቱ እርባና ቢስና አስመሳይነት የተሞላበት እንጂ እንደተባለው የአርሶ አደሮችን እንግልት ግምት ውስጥ ያስገባ አይመስልም።>> የሚሉት የፖለቲካ ተንታኙ አሰፋ አያሌው ናቸው።

እስከ አዲስ አበባ መሀል ከተማ ድረስ ገብቶ ወደ ኦሮሚያ ክልል ለማካለል ማቀድ ብቻ ጥናቱ አዲስ አበባ የኦሮሚያ ዋና ከተማ ናት እያሉ በሚለፍፉ አመራሮች እንጂ፣ በሕዝብ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ አለመሆኑን ፍንትው አድርጎ ይገልጻል ነው ያሉት ተንታኙ።

በማኅበረሰቡ በኩል ውዝግብ ፈጥሮ የተስተዋለው እና ‹‹ምላሽ እንሻለን›› ያስባለው ጥያቄም የከተማዋ መስፋት ለአርሶ አደሩ መፈናቀል ምክንያት ሆኗል ከተባለ፤ የእርሻ መሬት ከሌለው መሃል ከተማ ገብቶ ወደ ኦሮሚያ ክልል ወሰን መትከልን ምን አመጣው? የሚል ነው።

በሌላ በኩል የተነሳው ቅሬታ ደግሞ ድርጊቱ አርሶ አደሩን ለማፈናቀል እና ብጥብጥ ከማነሳሳት የዘለለ ጥቅም የሌለው ስለመሆኑ ነው።

ወሰኑን በተመለከተ የተቀመጠው ጥናትም ‹‹አዲስ አበባ ከተማ ሆና ሳለ የእርሻ መሬት ምን ይሰራል፤ ይህ ድርጊት ሆን ተብሎ አርሶ አደሩን ለማፈናቀልና ወጣቱን ለብጥብጥ ለማነሳሳት እየተከናወነ ያለ ድርጊት ነው›› በማለት ቅሬታ ተነስቶ ነበር።

ታዲያ ይህ በእንዲህ እያለ ጉዳዩን ያልተቀበለው ሕዝብ ውሳኔ ሳይሰጥበት የማካለል ሥራው ሊከናወን መመሪያ መውረዱ በፖለቲካ ባለሙያዎች በኩልም ቅሬታን አስነስቷል።

የፖለቲካ ተንታኙ በበኩላቸው ይህንኑ ጥያቄ በተመለከተ ምላሽ ሲሰጡ፣ መንግሥት የሕዝብ አገልጋይ ነኝ በሚል ስብከት የአዲስ አበባን ከተማ ወደ ኦሮሚያ ክልል ለማስገባት ሲል ያስቀመጠው ፍልስፍና እንጂ ለአርሶ አደሩ ተብሎ የተደረገ አይመስለኝም ብለዋል።

ይሁን እንጂ፣ በኹለቱ አመራሮች መካከል የተደረገው ጥናት ‹‹ፊንፊኔ ኬኛ›› የሚለውን የኦሮሚያ ክልል አመራሮችን ፍላጎት ለማሳካት ያለመ ስለመሆኑ ከማኅበረሰቡ ባለፈ የፖለቲካ ብቻ ሳይሆኑ የሕግ ምሁራንም በአጽንኦት እየገለጹ ነው።

በመሆኑም፣ በኹለት ስፍራዎች መካከል ወሰን ለማካለል ጥልቅ ጥናት ማድረጉ ሕገ መንግሥታዊና ሥርዓታዊ መሆኑን ባይካድም፣ የአዲስ አበባውና የኦሮሚያው ግን በምልሰት ሊታይ እንደሚገባ ነው ከፖለቲካ ባለሙያዎች መገንዘብ የተቻለው።

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ያሉበት አካባቢ ወደ ኦሮሚያ ክልል ይካለላል የተባሉ ነዋሪዎች በጉዳዩ እንዳልተስማሙ ይገልጻሉ። ነዋሪዎቹ እንደሚሉት ከሆነ፤ የአዲስ አበባ ከመጠን በላይ መስፋት እና ወደ ኦሮሚያ ክልል ትካለላለች በሚሉት  ኹለት ጉዳዮች መካከል ምንም የሚገናኝ አሳማኝ ነገር እንደሌለ ነው።

ነዋሪዎቹ በተያያዘም፣ የአዲስ አበባ ከተማ ወደ ኦሮሚያ ክልል እንዲሁም የኦሮሚያን ክልል ወደ አዲስ አበባ ማካለሉ በሕዝቡ መካከል ድንበር አበጅቶ ልዩነት በመፍጠር ጥላቻን ከማንገሥ ይልቅ በነዋሪዎቹ በኩል ምንም ዓይነት ፋዳ ሊያመጣ እንደማይችል ሳይናገሩ አላለፉም።

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ በበኩላቸው፣ ጉዳዩን በተመለከተ ባለድርሻ አካላት ሰሞኑን ባደረጉት ውይይት የነበረውን ሂደት ሲያብራሩ “በዚህ የአስተዳደር ወሰን የሰራነው አጥር አይደለም። በሕዝቦች መካከል አጥር ልናበጅ አንችልም። ይልቁንም በጠንካራ መሰረት ላይ የተገነባውን የሕዝቦችን አንድነትና አብሮነት የሚያፀና ነው።” ማለታቸው አይዘነጋም።

ይህንኑ ማብራሪያ የሰሙ አስተያየት ሰጪዎች ደግሞ፣ ያለ ሕዝብ ፍላጎት በሺዎች የሚቆጠሩ ኮንዶሚኒየሞችን ወደ ኦሮሚያ ክልል ማካለል በሰላም የኖረውን ሕዝብ ለማባላት እንጂ ሌላ ምን ትርጓሜ ይሰጠዋል ሲሉ ተሰምተዋል።

ፖለቲካዊ አንድምታ

መንግሥት አዲስ አበባ ከልክ በላይ ሰፍታለች በማለት ነው የወሰን ክለላውን ይፋ ያደረገው። ይሁን እንጂ በጉዳዩ ዙሪያ የቀረበው ምክንያት በምሁራን ዕይታ በምንም ዓይነት ቅድመ ሁኔታ አሳማኝነት የሌለው ነው እየተባለ ይገኛል።

ጉዳዩ <አያ ጅባ፣ ሳታመኻኝ ብላኝ> ዓይነት ነው ያሉት የፖለቲካ ተንታኙ አብዱ ይማም ናቸው።

የአንድን ከተማ እድገት እዚህ ላይ ይቁም የሚል ብያኔ አለ ወይ የሚሉ ጥያቄዎችም በበርካቶች በኩል ሲሰነዘሩ የተስተዋለ ሲሆን፤ የፖለቲካ ተንታኙም ምላሽ ሰጥተዋል።

እንደ አብዱ ገለጻ ከሆነ፤ እስካሁን ባላቸው እውቀት መሰረት አንዲት እንኳን በከተማ ስፋት ብዙ በሚጠበቅባት በኢትዮጵያ በሌሎች ከፍተኛ የከተማ ክምችት ባለባቸው የዓለም አገራትም ከተማ እየሰፋ ስለሆነ ወሰን ይካለል የሚል ትዕዛዝ እንደማያውቁ አንስተዋል።

የከተማ መስፋፋት ለኢኮኖሚ እድገት፤ ለማህበራዊ ትስስር እንዲሁም የተሻለ ኑሮን ለማምጣት ይረዳል እንጂ፤ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገራት ጉዳት የሚያመዝን አይመስለኝም ሲሉ ሙያዊ አስተያየታቸውን ተናግረዋል።

ሰሞኑን በመዋሰን ላይ ባሉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና በኦሮሚያ ክላልዊ መንግሥት መካከል ያሉ ነዋሪዎች እስከዛሬ በሰላም ተፈቃቅረውና ተሳስበው የኖሩ መሆናቸው የሚታወቅ ሲሆን፤ አሁን ላይ በድንበር ማካለሉ ግን ሌላ መዝዝ እንደሚያመጣም አብዱ ገልጸዋል።

እንደ አብዱ አስተያየት ከሆነ፤ ለአብነት ብንጠቅስ እንኳ የአዲስ አበባ ከተማ  የኦሮሚያ ክልል ነዋሪዎች በትራንስፖርትና በውሃ አገልግሎት ተመጋጋቢ ናቸው ብለው፤ በእነዚህ ሕዝቦች መካከል አጥር መሥራቱ ግን ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚሰፋ ተናግረዋል።

በርካታ አካላት የወሰን ማካለሉን ጉዳይ ብሔር ተኮር ነው ሲሉ አስተያየት የሰጡበት ሲሆን፤ “ፊንፊኔ ኬኛ” የሚሉ አካላት ከተማው ሰፍቷል በሚል ሰበብ ወሰን መሥራት ‹‹የእኛ›› የሚለውን ዓላማ ማስፈጸሚያ ነው ብለዋል።

የወሰን ማካለሉ ከሕግ አንጻር

የሕግ ባለሙያዎች በበኩላቸው፣ የአዲስ አበባ ከተማ ወደ ኦሮሚያ መካለል ከጥንሰሱ ጀምሮ ሰሞኑን እስከደረሰበት ይፋዊ የትግበራ መመሪያ ስርጭት፣ ብሔር ተኮር ፖለቲካዊ ይዘት የተሞላበት እንጂ አሳማኝ ምክንያት እንደሌለው ነው የሚናገሩት።

በበርካታ አካላት በኹለት ወይም ከዚያ በላይ በሆኑ ክልሎች መካከል የድንበር ማካለል ያደርጉ ዘንድ ሚዛን ደፊ ምክንያት ከተገኘ እንኳን ትልቁ ዓላማ ሕዝቡ በሰላም በፍቅር ተስማምቶ እንዲኖር ስለሆነ ሕዝበ ውሳኔ ተጨምሮበት፤ በሕግ ማዕቀፍ ተገንብቶ ሊሆን እንደሚገባ ነው የሚታመነው።

ይሁን እንጂ፣ በአዲስ አበበ ከተማ አስተዳደር ስር የሚገኙ ስፍራዎችን ወደ ኦሮሚያ ክልል እንዲሁም የኦሮሚያ ክልል አንዳንድ ቦታዎችን ወደ አዲስ አበባ የማካለል ውሳኔው በብልጽግና ባለሥልጣናት ብቻ ውሳኔ ላይ የደረሰ፤ የሕዝቡን ሪፈረንደም (ሕዝበ ውሳኔ) ያላካተተ ስለመሆኑ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የሕግ ባለሙያዎች ተናግረዋል።

የአስተዳደር ወሰን የማካለል ውሳኔ ሕዝቡን አሳታፊ መሆን አለበት የሚሉት በማንኛውም ፍርድ ቤት የሕግ አማካሪና ጠበቃ ጥጋቡ ደሳለኝ ናቸው።

ሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎች ትልቁ ኃላፊነታቸው ሕዝቡን ማስተዳደር እንደመሆኑ መጠን፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ወሰኑን ለማካለል ሕዝቡን አሳታፊ በሆነ መልኩ ነው ማድረግ ያለባቸው ብለዋል።

የሕግ አማካሪው በተያያዘም፣ ‹‹ሕዝቡን ያሳተፈ ካልሆነ መሬት ብቻውን ትርጉም የለውም። መሬት ሕይወትም፤ ጥቅምም፤ አቅምም የሚኖረው ሰው ሲሰፍርበት፤ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ሲሳለጥበት፤ የኢንቨስትመንት ፍሰት ሲኖርበት ነው›› ሲሉ ገልጸዋል።

አዲስ አበባ ከልክ በላይ ሰፍታለች የሚለውና ለወሰን ማካለሉ እንደ ምክንያት ተቀምጦ የተስተዋለው ጉዳይ በማህበረሰቡም ሆነ በፖለቲካ ባለሙያዎች በኩል አሳማኝ ምክንያት አይደለም የሚል ትችት በተደጋጋሚ ተነስቶበታል።

የሕግ ባለሙያዎች በበኩላቸው፣ ሕዝቡን ቁጭ አድርጎ ሳያወያዩ እንዲሁ አዲስ አበባ ሰፍታለች በሚለው ምክንያት ውሳኔ ላይ መድረሱ በሕዝቡ መካከል ተቀባይነትን ሊያሳጣ ይችላል ይላሉ።

በሕጉ መሰረት የሰዎች ፍላጎት ደግሞ ቅድሚያ ቦታ ይሰጠዋል ያሉት ጥጋቡ፤ ስለዚህ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ከፍተኛ አመራሮችና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በወሰን አካባቢ ያሉትን ነዋሪዎችን መብትና ፍላጎት ቁጭ አድርገው በመጠየቅ፤ ምክንያታዊና ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ችግሩን መፍታቱ የተሻለ ነው ብለዋል።

የከተማ አስተዳደሩና የክልሉ መንግሥት በሕዝቡ በኩል ጉዳዩ ተቀባይነት የተነፈገው ከመሰላቸው ደግሞ፤ በመጨረሻ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ጉዳዩን በማሳወቅ በሕገ መንግሥቱ መሰረት በከተማ አስተዳደሩና በክልሉ አጎራባች ወረዳዎች የሚገኙ ነዋሪዎችን ጥቅምና ፍላጎት መሰረት ያደረገ ሪፈረንደም (ሕዝበ ውሳኔ) ማካሄዱ ሌላኛው አማራጭ ሊሆን ይገባል ባይ ናቸው።

ይሁን እንጂ፣ ስለ ወሰኑ አዳነች አቤቤ ተናግረዋል እንደተባለው፣ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ በአመራር ደረጃ ሲመከርበት ቆይቶ፤ በሕገመንግሥትና በአዲስ አበባ ከተማ ቻርተር፤ የወሰን ጉዳይ በኹለቱ አስተዳደር አካላት ይፈታሉ ተብሎ በሚያስቀምጠው መሰረት ስምምነት ላይ እንደተደረሰ ነው።

ዳሩ ግን ከሕዝቡ የተሰማው ምላሽ በወሰን ማካለሉ ቅሬታ ስለመፈጠሩ ሲሆን፤ የሕግ ባለሙያዎችም በሕገ መንግሥቱ መሰረትም ቢሆን ኹለቱ አካላት በጉዳዩ ዙሪያ ሕዝቡን ሲያወያዩ ተቀባይነት ካላገኘ ጉዳዩ ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ማቅናት እንደሚኖርበትም ሕጉ ይደነግጋል ነው ያሉት።

የአዲስ አበባ ከመጠን በላይ መለጠጥ ወሰን ለማካለል አሳማኝ ምክንያት እንዳልሆነም የሕግ ባለሙያው ሳይናገሩ አላለፉም።

በኦሮሚያ ፖለቲከኞች በኩል አዲስ አበባ የኦሮሚያ አካል ናት የሚል አስተሳሰብ ወይም ፍላጎት አላቸው ያሉት ጥጋቡ፤ ይህ ፍላጎትና አስተሳሰብ ያላቸው ፖለቲከኞች የኛ የሚሉት ቦታ ቢሰፋም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንጂ ጉዳት የለውም ብለዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 198 ነሐሴ 14 2014

አስተያየት

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here