ሕዝባቸውን ያሳዘኑት ለቀስተኞች

0
817

ከሰሞኑ መነጋገሪያ ከነበሩ ዓለም ዐቀፍ ጉዳዮች መካከል የእንግሊዟ ንግሥት ሥርዓተ ቀብር ላይ የታየው የቀብር ታዳሚዎች ሁኔታ ቀዳሚው ነበር። በ96 ዓመታቸው ሕይወታቸው ያለፈው ንግሥት፣ ‹ያለእድሜያቸው ተቀጠፉ› ተብሎም ባይሆን ያዘነላቸው ብዙ ነው።

እንደሥልጣን ዘመናቸው ርዝመት የቀብራቸው ሥነሥርዓትም ተንዛዛ ያሉ በርካቶች ነበሩ። ከእለተ ሞታቸው ጀምሮ ለቀብራቸው ሲባል ስለሚወጣው ወጪ እንዲሁም ስለቤተሰቦቻቸው ሁኔታ ተረስተው የነበሩትን የንጉሣዊ ቤተሰብ ያማከለ ዘገባ በየሚዲያው ሲሰራጭ ቆይቷል።

አንዳንዶቹ በጎ ጎናቸውን እያነሱ ሥማቸውን ለማግዘፍ ሥርዓታቸውንም ለማሞካሸት ሲጥሩ፣ የተወሰኑት ደግሞ ቅኝ ገዢ የነበሩ መሆናቸውንና በሥማቸው በሚሊዮኖች ላይ የተሠራውን ግፍ እየጠቀሱ ሲያጣጥሏቸው ነበር።

አንዳንድ የታሪካቸው ተጋሪ አገራት መሪዎች የሀዘን መግለጫ ለማውጣት ሲሽቀዳደሙ፣ ሌሎች ደግሞ ከቤተሰባቸው በላይ ያዘኑ ለመምሰል ጥረዋል። ጎረቤታችን ኬንያን የመሳሰሉ የቀድሞ ቅኝ ተገዢዎችም፣ ባንዲራቸውን ጭምር ለቀናት ዝቅ አድርገው ለቀድሞ ገዢዎቻቸው አጎበደዱ እየተባሉ በዜጎቻቸው ጭምር ተተችተዋል።

የንግሥቲቱ ሞት የተለያዩ ጎራዎችን ሐሳብ እንድንሰማ ቢያደርግም፣ የቀብራቸው እለት ለመጨረሻ ጊዜ የአገር መሪዎች ተገኝተው ሲሸኙዋቸው የተደረገው ብዙዎችን ያስገረመ ነበር። እንደለመዱት በዓለ ሲመት አፍሪካውያን ገዢዎች ከድሃ አገራቸው ሀብት ላይ ዝቀው፣ እንዲህ የሚሰባሰቡበት አጋጣሚ ላይ ቢገኙም እንደለቀስተኛ ያሳማቸው ታሪክ ተከስቶ አያውቅም።

የኃያላን አገር መሪዎች በቅንጡ መኪናዎች ወረፋ ተጠብቆላቸው በየተራ ወደ ስንብቱ ቦታ እንዲገቡ ሲደረግ፣ ለአፍሪካዊያን መሪዎችና ለጥቂት የሌላ አገራት ተሳፊዎች የታዘዘላቸው ትራንስፖርት ግን ጉድ ያስባለ ነበር። የትራፊክ መጨናነቅና የደኅንነት ጉዳይ ነው በሚል በተለምዶ አጀብ የሚያበዙ የአፍሪካ መሪዎችን ብዛት ከመገደብ አልያም አትምጡ ከማለት ይልቅ፣ እንደአገራችን የክፍለ አገር ቀብር አውቶቡስ አምጥተው አጭቀው ወስደዋቸዋል።

ይህን መድሎ የተጠናወተውን ተግባራቸውን በመደበቅ ፋንታም፣ እንደበጎ ሥራ በምስል አስቀርተው ለሞቱ ንግሥቲቱ ክብር ሲሉ የራሳቸውንና የወከሉትን ሕዘብ ክብር አሽቀንጥረው እንደጣሉ ለማሳየትና ለማዋረድ የቀደማቸው ስላልነበር ብዙዎች ሐሳቡንም ሆነ ተግባራቸውን ተችተዋል።

በርካቶችን የገረመው አማራጭ አጥተው ይሁን ተስማምተው እንደሆነ የተጓዙት ሳይብራራ ምስላቸው መውጣቱ ብቻ ሳይሆን፣ ደስተኛ መስለው በፈገግታ ታጅበው ለፎቶ መመቻቸታቸው ነው። በተለይ የቀድሞ ቅኝ ተገዢዎቻቸው የነበሩ፣ መሪዎቻቸው እንዲህ የዓለም መሳለቂያ መደረጋቸው አብግኗቸው እንደነበር ከቀብሩ በላይ ሲወራ ሰንብቷል።

እኛ ኢትዮጵያዊያን የቅኝ ተገዢዎች ሥነልቦና ባይኖረንም፣ ለሌሎቹ አፍረን ይህን ባደረጉት ዘመናዊ ጨቋኞች ስናዝን ብዙ ሳይቆይ እኛን የሚያኮራ ተግባር በፕሬዝዳንታችን መፈጸሙን ሰማን። ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ የወከለኝን ሕዝብ አዋርጄ በአውቶቡስ ከምሳፈር ቢቀርብኝ ይሻላል የሚል ቆፍጣና አቋም በመውሰዳቸው ራሳቸውንና ሕዝባቸውን በማስከበራቸው ሲመሰገኑም ተሰምቷል።

በአውቶቡስ ታጭቀው የተጓዙት አፍሪካዊያን መሪዎች ምን አይነት አቀባበል ሕዝባቸው ያደርግ ይሆን ቢባልም፣ ወደየአገራቸው ለየብቻ አውሮፕላን ተኮናትረው ድምጽ አጥፍተው መግባታቸው ተገምቷል። ለአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ በተደጋጋሚ መንገድ ያዘጉን ይሆን?


ቅጽ 4 ቁጥር 203 መስከረም 14 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here