“ኢንሹራንስ ቅንጦት አይደለም”

0
1185

መታወቂያ ፍለጋ ነበር መጀመሪያ ወደ መድን ድርጅት ቢሮ ያቀኑት። በጊዜው የነበረው የፖለቲካ እንቅስቃሴ የአንዱ ቡድን አባል ያልሆነ የሌላው እንደሆነ የሚታሰብበት ነበርና፣ ያንን የፖለቲካ እንቅስቃሴ ሽሽት ነው መታወቂያ ያስፈለጋቸው። ታድያ ከመድን ድርጅት መታወቂያ ከማግኘት ባለፈ አሁን ላይ ‹እረፍትና መዝናኛዬም ነው› እስኪሉ ድረስ የሚወዱትን የኢንሹራንስ ሥራ ተዋወቁበት። ጌጤነሽ ኃይለማርያም።

ጌጤነሽ በኢንሹራንስ ዘርፍ ከ25 ዓመታት በላይ የቆዩ ሲሆን፣ ከመድን ድርጅት ሲወጡ በዘርፉ ያዩትን ክፍተት ሊሞሉ የሚችሉበትን መንገድ ቀይሰው ነበር። በዛ መሠረትም ጌጤነሽ ኃይለማርያምና ብርሀን ተስፋዬ የመድን ሥራ አዋዋይና አማካሪ ድርጀት መሠረቱ። አሁንም የድርጅቱ ማኔጂንግ ዳይሬክተር በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ።

በድርጅታቸው የ25ኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዩ መነሻነት በዚህ በተያዘው ጥቅምት ወር 2015 የመጀመሪያው የ‹ኢንሹራንስ› ወር ይከበራል። በኢትዮጵያ 18 የሚጠጉ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ያሉ ሲሆን፣ ከሥልጣኔ እና ከአዲስ ግኝት ጋር አብሮ ያድጋል የሚባለው ይኸው ዘርፍ ግን በኢትዮጵያ ያለበት ደረጃ ብዙ የሚቀረው እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲነገር ይሰማል።

ይህን መነሻ በማድረግም የግል ልምዳቸውን እንዲሁም በኢንሹራንሱ ዘርፍ ያሉ ነባራዊ ሁኔታዎችን በሚመለከት በማንሳት፣ ጌጤነሽ ኃይለማርያም ከአዲስ ማለዳዋ ሊድያ ተስፋዬ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርገዋል።

እርስዎ በግልዎ የምን የምን ኢንሹራንስ ገዝተዋል ከሚለው እንጀምር?

ጥሩ ጥያቄ ነው (ሳቅ)

ከቢሮ ብንጀምር ሁላችንም የሥራ ላይ ዋስትና ኢንሹራንስ ተጠቃሚ ነን፤ እኔን ጭምሮ። የሕክምና ኢንሹራንስ ተጠቃሚ ነን። በግል የቤት ኢንሹራንስ ዋስትና አለኝ። ለመኪናዬ አስገዳጅ ሦስተኛ ወገን ብቻ ሳይሆን፣ በድርጅትም ሆነ በግል ለምንጠቀምባቸው ኢንሹራንስ አለን። እና የኃላፊት ግዴታ የምወጣበት የፕሮፌሽናል ኢንዴምኒቲ ኢንሹራንስም አለኝ።

25 ዓመት ብዙ ነው። ይህን ያህል ዓመት አንድ ዘርፍ ላይ መቆየት ቀላል አይመስለኝም። እንዴት ወደዚህ ዘርፍ ገቡ የሚለውን መለስ ብለን እናስታውስ?

ወደኋላ መለስ ብዬ ሳስብ፣ ፈቅጄ፣ ፈልጌና አምኜ የገባሁበት የሙያ ዘርፍ ነው። ከዚህ በፊት የኢትዮጵያ መድን ድርጅትን ነው እንደ ትምህርት ቤት የማየውና የተቀጠርኩበትም። መድን ድርጅት ደግሞ በእውነት ራሱን እንደቻለ ትምህርት ቤት ነው።

ሙያው የተለየ በመሆኑ በትምህርት ቤት የሚገኝ ሳይሆን ሙያው ላይ ሆነሽ የምትማሪውና የምትሠለጥኚው ነው። እንደዛም እንድንማር በጣም ነበር ድርጅቱ [መድን ድርጅት] የሚተጋው። በሙያ ብቃትና በሠለጠነ የሰው ኃይል የሚያምን ድርጅት ነበር። ሙያውን የበለጠ እያወቅሽ፣ እየተማርሽና በሥራ ላይ እየተለማመድሽ ስትመጪ የሚፈጥርብሽ ተነሳሽነት አለ።

ብዙ ጊዜ ኢንሹራንስ ላይ ሰዎች ውሉን ለመግዛት በሚመጡበት ጊዜ፣ ስለውሉ በተገቢው መንገድ ለማስረዳት አንደኛ የጊዜ እጥረት አለ። እያንዳንዱን ማስረዳት አይቻልም። ኹለተኛ አንዳንድ ነገሮችን እንንገራቸው ብንል እንኳ ደንበኞች ጊዜ ስለሚያጥራቸውና ሌላ ጉዳይ ስለሚኖራቸው ቁጭ ብሎ የማዳመጥ ነገር አይኖርም።

ስለዚህ አደጋ በሚደርስበት ጊዜ ነው ፍጥጫ የሚመጣው። ያኔ የተሸጠው ፖሊሲ ወደ ትርጉም ነው የሚሄደው። በዚህ ጊዜ ይህን ማሟላት ነበረብህ፣ ይህ ይጎድላል፣ ያንን አሟላ የሚለው ነገር ሲመጣ፣ ሰዎች ከጠበቁት ውጪ ይሆንባቸዋል። እናም ድሮስ ኢንሹራንስ ለምን አስፈለገን ይላሉ። ይህ ነው ክፍተትም እየፈጠረ የነበረው።

እኔን ያነሳሳኝ ነገር፣ ፖሊሲውን ሰዎች በደንብ እንዲረዱት ቢደረግ ካሳ ጥያቄ ላይ ችግሮችን በተወሰነ መንገድ መቅረፍ ይቻላል የሚለው ነጥብ ነው። ከዛ በኋላ ነው ወጥቼ መሥራት እችላለሁ ብዬ በልበ ሙሉነት ይህን ወደማቋቋም የገባሁት።

ባለፉት 25 ዓመታት መጀመሪያ ከተነሱበት ዓላማ አንጻር ምን ያህል ውጤታማ ሆነናል ይላሉ? ወይስ የሚቀሩ ነገሮች አሉ?

ገና ብዙ ይቀራል። እኛ ስንነሳ ለምሳሌ እድገታችን ወይም ጉዞአችን ቀላል የሚባል አልነበረም፤ ተግዳሮት የበዛበት ነበር። አንደኛ ደንበኞች እንዲህ ያለ አገልግሎት ስለመኖሩ ብዙ አያውቁም። ኹለተኛ በኢንሹራንስ ኩባንያዎችም በኩል የእኛን አገልግሎት ለመቀበል ብዙ ፍላጎት የለም። ለምን ቀጥታ እኛ ደንበኛውን አናገኘውም የሚል እሳቤ ነበራቸው።

የለም! እኛ ደንበኛው ፖሊሲውን በደንብ እንዲረዳና ይዘቱን አውቆ ወደ እናንተ እንዲመጣ ነው የምናደርው። የካሳ ጥያቄ ላይ ደግሞ አማክረነው ትክክለኛ ጥያቄ ከሆነ እንዲከፈለው፣ የማይመለከተው ከሆነ የእሱም የእናንተም ጊዜ እንዲቃጠል አይሆንም በሚል ከብዙ ሂደት በኋላ ነው ይህ መግባባት የመጣው። አሁን ላይ ኢንሹራንስ ኩባንያዎቹ በተገቢው መንገድ አገልግሎታችንን ያውቃሉ። ደንበኞችም ከተወሰኑት በቀር እምነት አላቸው ብዬ አስባለሁ።

በተለይ አገልግሎታችን ተጠቃሚ ደንበኞቻችን (ፍጹም ነኝ ወይም አገልግሎቱ ፍጹም ነው አልልም፤ ምክንያቱም መደነቃቅፎች አሉ፤ ግን አስፈላጊ እንደሆንን ያምኑበታል።

በእርግጥ የምንፈለገውን ያህል ሄደናል ወይ? አልሄድንም። ምክንያቱም ይህ በጋራ የሚሠራ ሥራ ነው። መጀመሪያ ኅብረተሰቡ ማወቅ አለበት። ስለኢንሹራንስ ጽንሰ ሐሳብ ማወቅ አለበት። ፖሊሲው ብሎም ኢንሹራንስ ለምን እንደሚያስፈልግ ማወቅ አለበት።

በአብዛኛው ላለው፣ ለተመቸው ተደርጎ ነው የሚታሰበው። ኢንሹራንስ ቅንጦት ተደርጎ ይታሰባል። ግን ኢንሹራንስ ቅንጦት አይደለም። እንደውም ሀብት ያለው ሰውማ ሀብቱም ይደርስለታል፣ ጓደኞቹም ይደርሱለታል። ኢንሹራንስ የመክፈል አቅም እስካለው ድረስ፣ ልክ እንደ ቤት ኪራይና ትምህርት ቤት ክፍያ ወይም አንዳንድ ወጪዎችን መሸፈን የሚችል ሰው ከትንሽ እስከ ትልቅ መግዛት የሚችለው የፖሊሲ ዓይነት ነው።

የሕይወት ኢንሹራንስ በይው፣ የኃላፊነት ግዴታ መወጫ ይሁን፣ የቤት ኢንሹራንስ በየው፤ እንደዛ ነው። ቤት ከ200 እና 300 ሺሕ አንስቶ በብዙ ሚሊዮን እስከሚቆጠረው ድረስ፤ አከፋሉ ይለያል እንጂ በዓመት ፕሪምየም 300 እና 500 ብር ከፍሎ ነው የሚገባው። ድንገተኛ የእሳት ቃጠሎ ከጎረቤት ሊነሳ ይችላል፤ ቤት ውስጥ ከምንጠቀመው ጋዝ ሊነሳ ይችላል። አይታወቅም፤ ሁሌም የአደጋ ስጋት አለ። መቼ እንደሚሆን ነው የማናውቀው።

እና የእኛ የመንገር ወይም ሐሳቡን የማስተላለፊያ መንገዱን ብዙም አላጤንነውም። ወደ ኅብረተሰቡ ዘንድ አላሰረጽነውም። እንጂ ሐሳቡ ቢሰርጽ ብዙዎች ያለስጋት የአእምሮ ሰላም አግኝተው መኖር ይችላሉ።

ኢንሹራንስ የአእምሮ ሰላም ይሰጣል። ‹ኢንሹራንስ አለኝ፣ እኔኮ አንድ ነገር ብሆን ልጆቼ በእኔ የሕይወት ዋስትና ኑሮአቸውን ሊመሩ ይችላሉ› ነው። ፍቅርን አይተካም ኢንሹራንስ ግን ቢያንስ የተቋረጠ ገቢ እንዲመለስ ያደርጋል። በሠራተኛ ኢንሹራንስ አንድ አሠሪ እሱ ከሚከፍል ይልቅ የኢንሹራንስ ኩባንያ ቢሸፍንለት፣ አንድ ቢዝነስ በተለያዩ የተፈጥሮም ይሁን ከተፈጥሮ ውጪ የሆነ ድንገተኛ አደጋ ቢመጣና ንብረት ቢወድም፣ ተበድሮ የሠራነውና የገነባው ፋብሪካ በይው ሕንጻ በባንክ እዳ ከሚያዝ፣ ኢንሹራንስ ይተካዋል። እና የአእምሮ ሰላሙ ከገንዘብ ካሳው ያልተናነሰ ነው።

ኢንሹራንስ ማለት ስኮርት ጎማ በመኪና ይዞ እንደመሄድ ነው። ሰዎች ስኮርት ጎማ ሳይዙ ከቤት መውጣት ይጨንቃቸዋል። ያለኢንሹራንስ መሆን ማለትም ስኮርት ጎማ ሳይዙ እንደማሽርከር ነው።

ሌላው ኢንሹራንስ የገዛው ወይም የገባው ሰው ላይ የተባለው ጉዳት ባይደርስ እንኳ ሌላ ሰው ላይ ይደርሳል። ከሁሉ የተዋጣው ገንዘብ ነው ለጥቂቶች ለተጎዱት የሚሄደውና ሌላውን አቋቁሟል፣ ለሌላው ደርሷል፣ የሌላውን ቢዝነስ እንደገና እንዲቋቋም፣ ቤተሰብ እንዳይበተን አድርጓል።

አገራችን የተጠና ጥናት ቢኖር፣ ምን ያህሉ ነው ቤት ውስጥ አባት ሞቶ ልጆች መንገድ ላይ ልመና የሚወጡት። ምን ያህሉ ነው የቤተሰብ እርሻ በተለያየ አደጋ ሲወድም፣ ከተማ ገብቶ አጉል የሆነው? ግን [የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ይህን ለብቻቸው መቋቋም አይችሉም] እንዲህ ያሉ በመንግሥትም የሚታገዙ ኢንሹራንሶች ቢኖሩ ጥሩ ያግዛሉ። መፈናቀልና ከአካባቢ ወጥቶ ሄዶ በየከተማ ውስጥ ያለውን ሥራ ፈትነት በከፍተኛ ደረጃ ሊቀርፍ ይችላል።

ከፍተኛ የሆነ የግብርና ምርትም ማግኘት ይቻላል። ምክንያቱም ልጆች በአካባቢው ሆነው ቤተሰባቸውን ይረዳሉ። ኑሮአቸውም በተሻለ እንዲመሩ ሊመቻች ይችላል። የሕይወት፣ የጤና፣ የግብርና የከብቶች (የበሬ ኢንሹራንሰ የሚባል አለ። ለአርብቶ አደሩና ቆላማ አካባቢዎች የግመል) ኢንሹራንሶች አሉ። ይህንንን ግን ብቻቸውን የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ሳይሆኑ በጋራ ከመንግሥት ጋር ሆኖ ቢሠራ ትልቅ እድገት ለአገራችን ማምጣት ይቻላል ነው የምለው።

በኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ዘርፉ ምን ያህል ውጤታማ ነው?

በተቻለ መጠን አሁን ብዙ ቢዝነሶች ያለ ኢንሹራንስ አይንቀሳቀሱም። ብድር ሊኖር ይችላል፤ ለብድሩ ሲል ኢንሹራንስ ይገባል፤ ብድሩ ሳይከፈል አደጋ ቢደርስ የሚለውን ለመሸፈን። የአበባ እርሻም ሆኑ ሌሎች አምራች ድርጅቶች ኢንሹራንስ አላቸው። ቁጥራቸው ግን እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ያላት አገር ናት። ከዛ ውስጥ እንኳ ትልቁ መሠራት ያለበት ብለን የምናምነው የሕይወት ኢንሹራንስን ነው። 20 እና 30 ሚሊዮን ለሚሆነው ሕዝብ እንኳ ኢንሹራንስ ቢሰጥ፣ የኢንሹራንሱን እድገት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ሊያደርስ የሚችል ነው።

ኹለት ጥቅም አለው። አንደኛ ለኅብረተሰቡ ዋስትና ይሰጣል። ኹለተኛ ደግሞ ከዛ የሚገኘው ገንዘብ ደግሞ የተባለው አደጋ እስኪደርስ ድረስ፣ ኩባንያዎቹ ይህን ገንዘብ በተጠና ሥራ ላይ ያውሉታል። ለምሳሌ ሪል እስቴትም ይሁን ድርሻ መግዛት ይሆናል። ከዛ የሚያገኙትን ደግሞ ተጨማሪ ሠራተኛ ሊቀጥሩበት ይችላሉ። ሥራ አጥነቱን በተወሰነ ደረጃ ሊቀንሱ ይችላሉ። በታክስና መሰል በሆነ መንገድ ለመንግሥት ፈሰስ የሚያደርጉት ቀላል አይደለም። ለባለድርሻዎች የሚያካፍሉት ገንዘብም አለ።

ከምንም በላይ ኅብረተሰቡ ራሱ ዋስትና ኖሮት ሕይወቱን በሰላም መምራት ይችላል።

ከዛ ውጪ በአዲስ አበባ የሚታዩ በርካታ ሕንጻዎችና ቪላዎች ሁሉ ኢንሹራንስ የላቸውም። ይህን ከመንግሥት ጋር ነው መሥራት የሚቻለው። ሐሳቡ መምጣት ያለበት ከባለሞያው ነው። የተጠኑ ጥናቶች ተደርገው ወደሚመለከተቻው የመንግሥት አካላት ቢሄድና አስገዳጅ ሆነው እንዲወጡ ቢደረግ ይቻላል። የእኔ ቤት ተቃጠለ ማለትኮ ዞሮ ዞሮ የኅብረተሰብ ንብረት ነው የወደመው። ያንን ቤት ዳግም ለመሥራት የሚወጣው ገንዘብ ለሌላ ነገር ይውል ነበር። አብዛኛው ቁሳቁስ ደግሞ ከውጪ የሚመጣ ነው።

እናም ኢንሹራንስ በጣም ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው ዘርፍ ነው። ለአገር፣ ለሕዝብ፣ ለኢኮኖሚና ለራሱ ለባለሞያውም ጭምር።

በኢንሹራንስ ኩባንያዎች መካከል እርስ በእርስ ያለው ትብብር ወይም በአንጻሩ ፉክክር ምን ይመስላል? ያንን ለእድገትስ ምን ያህል እየተጠቀሙበት ነው?

ውድድር መኖር አለበት፤ ትክክል ነው። ውድድር ሲባል ግን የዓይነት ለውጥ ነው መሆን ያለበት። ሲወዳደሩ ለኅብረተሰቡ፣ ለቢዝነሶቹ፣ ለደንበኞቻቸው ምን ዓይነት አገልግሎት ለመስጠት ነው ያሉት የሚለው መሆን አለበት። ግን ብዙ የምናየው የዋጋ ውድድር ነው። ይህ ግን ፍጹም ጤናማ ያልሆነ ውድድር ነው።

ኢንሹራንስ ቃል ነው፤ ቁስ አይደለም። አንድን ቁስ ዐይቶ የት ተሠራ፣ ከምን ተሠራ፣ ምን ያህል ሊቆይ ይችላል የሚለው ታይቶ ነው ዋጋ የምንደራደረው። አምነንበት ነው የምንወስደው። ኢንሹራንስ ግን ቃል ነው እንጂ የሚታይ ነገር የለውም። ይህ ግን ሊሆንም ላይሆንም ይችላል። ከሆነ ጊዜ በኋላ ግን እንደኢንሹራንስ ተቋም በምን ያህል ፍጥነት ነው ያንን ቃል የምጠብቀው፤ ላገለግልሽ ወይም ችግርሽን ልቀርፍ የምችለው? አንዱ መሠረታዊ ነገር እሱ ነው፤ አገልግሎት።

መተኮር ያለበት አገልግሎት ላይ እንጂ ዋጋ ላይ አይደለም። ኅብረተሰቡ እንደውም እኛ ነን ዋጋ እንዲቆራረጥ ያስለመድነው እንጂ ጥያቄው የዋጋ ሳይሆን የአገልግሎት ጉዳይ ነው። ጥሩ አገልግሎት ካገኘ ዋጋም ጨምሮ ኢንሹራንስ ከመግባት ወደኋላ ይላል ብዬ አላስብም። እናም መወዳደር ያለብን በአገልግሎት ላይ ነው።

ኹለተኛ የምንሰጣቸው አገልግሎቶች ላይ ነው። እኔ የምሰጠው አገልግሎት የአንቺን ስጋት ምን ያህል ይሸፍነል፤ ወይም በአብዛኛው ይሸፍናል? ቁንጽል ነው ወይስ ሙሉ ለሙሉ ይሸፍናል? አንቺ ስጋትሽን በሙሉ ወደ ኢንሹራንስ ተቋም አስተላልፈሻል? ያ ነው መሠረታዊው ነገር።

ሙሉ ለሙሉ ባልተላለፈ የስጋት ዓይነት ላይ ለምሳሌ፡- አንድ መኪና አሁን ላይ ባለው ገበያ ዋጋው አንድ ሚሊዮን ነው እንበል። አንቺ ኢንሹራንስ የገባሽው ከሰባት ወራት በፊት በ500 ሺሕ ከሆነና መኪናው አሁን ከባድ ጉዳት ከገጠመው፣ ‹አይ! መኪናውኮ 500 ሺሕ ብር አይደለም። አንድ ሚሊዮን ብር ነው መሆን የነበረበት፤ ስለዚህ ከዚህ በላይ ያለውን መቻል ያለብሽ ራስሽ ነሽ። ገበያው ላይ ባለው ልክ አይደለም ኢንሹራንስ የገባሽው› ብትባይ ምን ይሰማሻል?

‹መጀመሪያ ለምን አላሳወቃችሁኝም፣ መክፈል ስለማትፈልጉ ነው› የሚል ነገር ይነሳል። ይህም አመኔታ ያሳጣል። ይህ ክፍተት እንዳይኖር ነው መሥራት ያለብን። በየጊዜው ከዋጋ መዋዠቅ ጋር የሚሄዱ ነገሮች መስተካለል አለባቸው። እንዲህ ያሉ ቀዳዳዎችን መድፈን ያስፈልጋል። ይህን ለማድረግ በተቻለ መጠን የእውቀት ሽግግር በመፍጠር ነው፤ ለደንበኞችና ለኅብረተሰቡም።

ደንበኞች ታድያ ብዙውን ጊዜ አንብበው ነው ውሉን የሚቀበሉት ወይስ እንዳሉት ችግር ከተፈጠረ በኋላ ነው?

በአብዛኛው እንደሱ ነው። የችግራችን ምንጭም እንደዛው ነው። አንደኛ እንዳልኩት ካለው የሰው ኃይል አንጻር ለእያንዳንዱ ሰው ማስረዳት አይቻልም። ሊሆን የሚችለው በሚድያ፣ በበራሪ ጽሑፍ ቀለል ባለና ሰዎች ሊረዱ በሚችሉበት ቋንቋ ማድረስ ነው።

ይህም አዲስ አበባ ከተማ ብቻ አይደለም። በየክልሎች ኤፍ ኤም ጣቢያዎች አሉ። ሚድያ ላይ ይቻላል። እኛ ራሳችን ተገን የሚባል ፕሮግራም ነበረን። ሰባት ዓመት ከሄዷ በኋላ ነው ያቆምነው። ያም በጣም አስፈላጊ መሆኑ የገባኝ ፕሮግራሙ ከተዘጋ በኋላ ነው። ምክንያቱም በማናውቀው ነገር ላይ እምነት አይኖረንም፤ ተጠራጣሪ ነው የምንሆነው።

ከካሳ ክፍያ መጓተት ጋር በተያያዘ የሚታየው ችግር ከደንበኞች በቂ መረጃ አለመያዝ ጋር የተገናኘ ነው ወይስ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች አፈጻጸም ላይ ክፍተት አለ?

መጀመሪያ በቂ ግንዛቤ ሊኖር ይገባል። ለምሳሌ አንድ የሕይወት ኢንሹራንስ የገዛ ሰው ካለ፣ ፖሊሲው በግልጽ እንደሚያስቀምጠው ሞትን ነው የሚሸፍነው። ሞት ሲባል በአደጋ ወይም በሕመም ሊሆን ይችላል። እዛ ጋር እንደቅድመ ሁኔታ የሚያስቀምጣቸው ነገሮች ይኖራሉ።

ኢንሹራንስ የገባው ሰው ከሞተ፣ ኢንሹራንስ ኩባንያው ያ ሰው እንዴት እንደሞተ ማስረጃ እፈልጋለሁ ይላል። ያ ሰው መጀመሪያ ላይ ወደ ኢንሹራንስ ሲሄድ እድሜ ሲባል ሀምሳ ዓመት ከሆነ አርባ ቢል፣ ሕመም እያለበት ምንም ሕመም የለብኝም ሊል ይችላል። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሞት ቢፈጠር፣ ኢንሹራንስ ኩባንያው ዝም ብሎ አይከፍልም። ማስረጃዎች ይፈልጋል። ሕጋዊ ወራሾች እነማን ናቸው ይላል፣ ከዛም የሞት ማረጋገጫ ሰርተፍኬትና የሕክምና ማስረጃ ይጠይቃል።

የሕክምና ወረቀቱ ላይ ሰውየው የሞተው በከባድ የልብ ሕመም ነው ሊል ይችላል። ቀድሞ የተሞላው ላይ ግን ሕመም የለም፣ ጤነኛ ነኝ ይላል። እውነት አልተነገረም፣ ተዋሽቷል። ስለዚህ ካሳ ጥያቄው ላይ ጥያቄ ያስነሳል፤ ካሳውን ለማስተናገድም ችግር ይፈጠራል። ኢንሹራንስ ትልቁ መሠረቱ እምነት ነው። ፖሊሲ ስሸጥልሽ ቃልሽን ወስጄ ነው። እናም እውነትን ካለመናር የሚመጡ ችግሮች አሉ። ይህ ከደንበኞች የሚነሳ ችግር ነው።

ኹለተኛ ግን ፖሊሲውን በሐቅ ካለመረዳት የሚመጣ ችግር ነው። ‹እንዲህ መስሎኝ ነውኮ!› የሚል ነገር አለ። ትክክል ነው! ማስረዳት ሲገባን ሳናስረዳ ቀርተን የሚመጣ ነው። ለምሳሌ አንድ መኪና በተለይ ለንግድ ሥራ የሚውል ሆኖ የራሴን ወይም የድርጅቴን ንብረት ብቻ ነው የማጓጉዘው፣ ለኪራይ አልሰጥም ብለሽ ትገቢያለሽ። በዛ የተነሳ የምታገኚው የአርቦን ቅናሽ አለ። ለአደጋ ብዘ የተጋለጠ አይደለም ተብሎ ነው ቅናሹ የሚወሰነው።

ግን ለኩባንያው ሳታሳውቂ ‹ዝም ብሎ ከሚቀመጥ ላከራየው› ብለሽ ልታከራይው ትችያለሽ። ያኔ ለደጋ የመጋለጥ መጠኑ ይጨምራል። በዚህ የተነሳ ተጨማሪ ክፍያ ነበር መክፈል የሚጠበቅብሽ። ይህን ባለማወቅ መኪናውን ታከራያለሽ፤ ድንገት አደጋ ይፈጠራል። ያኔ የፖሊስ ሪፖርት ሲመጣና ከአካባቢው መረጃ ሲጠናቀር፣ ውሉን ስንሰጥሽ በዚህ አይደለም። ከውል ውጪ ሄደሻል ብሎ አልከፍልሽም ይላል። ይሄኔ እኔ መች አውቄ ትያለሽ። እነዚህ የመረጃ ክፍተቶች ናቸው አለመግባባት ሊፈጥሩ የሚችሉት።

ሌላው አገልግሎት ላይ የሚታየው እንደ ልምድ የሆነ የአገር በሽታ አለ። ቶሎ ብሎ ይሆናልም አይሆንምምኮ መልስ ነው። የሚሆን ከሆነ ይህ ይህ ይሟላ ይከፈላል ማለት ነው። ዛሬ አንድ ሰነድ አምጣ ይባላል፣ በሚቀጥለው ሲሄድ ይህን አላመጣህም አምጣ ይባላል። ይሄ በጣም ያበሳጫል።

በውጪ አገራት በተለይ የኢንሹራንስ ተቋም የሠለጠነና ያደገ ነው ተብሎ ነው የሚታመነው። በቴክኖሎጂና በኢንተርኔት በመታገዝ ነው ክፍያም የሚፈጸመው። እዚህ ግን ቢሮ እየተሄደ ሥራ ተፈትቶ ነው። እና የመንግሥታዊ ተቋማት ዓይነት አሠራር ሲሆን ያበሳጫል። በትልቁ መሠራት ያለበትም አገልግሎት ላይ ነው።

ከሙያተኛ አንጻር ታድያ በምን የሠለጠኑ ናቸው ወደዘርፉ የሚገቡት፣ ከባለሞያ አንጻርስ ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል?

ኢንሹራንስ ከትምህርት ቤት ተመርቀሽ የምትወጪበት አይደለም። ብዙ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ሲቀጥሩ ቢያንስ ዲግሪ ወይም ዲፕሎማና ጥሩ ውጤት ያላቸውን ይፈልጋሉ። ከዛ በኋላ ግን ተከታታይ የሆነ ሥልጠና ያስፈልጋል፤ ከሙያው ጋር ለመቀራረብ። ልምምድ ይጠይቃል። ቅን መሆን፣ የሚሰጠኝ መረጃ ትክክለኛ መሆኑን ማመን አለብኝ። እንደማይከፈል እያወቅሁ እንዲገቡ ብቻ የማይከፈለውን ይከፈላል ማለትም የለብኝም።

ይህ ራሱን ችሎ የሚሰጥ የኢንሹራንስ ኮርሶች አሉ። በቻርተርድ ኢንሹራንስ ተቋም የሚባል ለንደን ውስጥ ያለ ተቋም አለ። ከዛ በዲፕሎማ መመረቅ ይቻላል። አገር ውስጥ ሥልጠናዎች ይሰጣሉ። እነዛ ግን በቂ አይደሉም፣ ሙሉም አያደርጉም። ሙሉ ለመሆን በደንብ ሙያው ውስጥሽ እንዲገባ ያስፈልጋል። ታማኝነትን እና አገልጋይነትን መላበስ ያስፈልጋል። ያ እንዲሆን ደግሞ በእውቀት መበልጽግ ያስፈልጋል። ያም በራስ መተማመንን ይሰጣል።

እውቀትና በራስ መተማመን ሲኖር፣ የምታውቂውን ነውና የምትሠሪው አገልጋይ ለመሆን ደስተኛ ትሆኛለሽ። የማታውቂውን ነገር መሥራት አደጋ አለው። እና ዝም ብሎ ለሥራ ብቻ የሚሠራ አይደለም። ፍቅርና ፍላጎት እንዲሁም አገልጋይ መሆንን ይጠይቃል።

እዚህ ቢሮ የተለያዩ ሰዎች ይመጣሉ። ባለቤቷ ሞቶ የትም ሳትሄድ፣ አልቆለት ኑ ቼክ ውሰዱ ተብሎ ሲመጡ፣ የሚሰማቸው ደስታ ልዩ ነው። እኔ አይደለሁም የሰጠኋቸው፤ ግን ለተገዛው ኢንሹራንስ ተፈጻሚነት በሀቅ ቆመን በጊዜያዊነት፣ በሰዎቹ እግር ሆነን ለሰዎች ችግር እንዲደርስ ማስቻል ለእኛ ትልቁ ሽልማታችን ነው። የሰው ደስታ ደስታን ይሰጣል።

ስለኢንሹራንስ ዘርፍ መታወቅ አለበት የሚሉትና የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለ እንውሰድ?

ኢንሹራንስ ገና ያልተነካ ዘርፍ ነው። ምንም ያልታየ፣ መንግሥትም ያልጎበኘው ዘርፍ ነው። ከባንኮች ጋር ተቆራኝቶ ነው ያለው። ሁሌም ባንክ ባንክ ነው የሚባለው። ትልቁ የኢኮኖሚ አውታር ግን ኢንሹራንስ ነው።፡ ባንክ ከሚሰጣቸው ብድሮች፣ ከሚንቀሳቀሱ ንግዶች፣ ከውጪ ከሚመጡ እቃዎች፣ ከሚበርረው አውሮፕላን ወዘተ ጀርባ ኢንሹራንስ አለ። ኢንሹራንስ ኩባንያዎች በሆነ መንገድ አንሠራም ቢሉ፣ የዓለም የምጣኔ ሀብት ይወድቃል። መቼም እንዲያ እንዲሆን ባልፈቅድም፣ ሲጎድል ተጽእኖው ይታወቅ ነበር።

ከየአንዳንዱ ግኝት ጀርባ በሙሉ ኢንሹራንስ አለ። ትላልቅ የማዕድን ቁፋሮዎች ያለኢንሹራንስ አይሞከሩም። ያንን የሠለጠኑት ያውቁታል፤ አይደራደሩበትምም።

ይህን የሚያህል ግዙፍ የኢኮኖሚ አውታር፣ ኢኮኖሚውን የበለጠ ደግፎ እንዲኖር የማድረግ ሥራ በዋናነት ለመንግሥት ማሳወቅ አለብን። አስገዳጅ ኢንሹራንስ ይኑር እንላለን። ይህ ኢንሹራንሱን ለመጥቀም አይደለም፤ ኅብረተሰቡን ለመጥቀም ነው።

የሥልጣኔ ምልክት ነው ኢንሹራንስ፤ የመዘመንም አንዱ ማሳያ ነው። ውጪ አገር ፒያንስቶች ለጣቶቻቸው ሳይቀር ኢንሹራንስ ይገባሉ። ሞዴሎች የሚጠቀሙብት የሰውነታቸው ክፍል ኢንሹራንስ አለው። እግር ኳስ ተጫዋቾች ለእግራቸው ኢንሹራንስ አላቸው። ከኑሮ ጋር ቁርኝት አለው። እናም በአንድ ኢንሹራንስ ኩባንያ ወይም በአንድ አዋዋይ የሚሠራ አይደለም። ሁሉም በአንድ ላይ ሆኖ ወደ መንግሥት ማስተላለፍ የሚፈልጉትን በጋራ ማስተላለፍ፤ ኅብረተሰቡን ማሳወቅ የሚገባቸውን በጋራ ማሳወቅ አለባቸው። ብዝኀነት ላይ ማተኮርና ትላልቅ ግብ ለመፈጸም በጋራ መሥራት የግድ ይላል።


ቅጽ 4 ቁጥር 207 ጥቅምት 12 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here