የዶላር እቀባው እና የምጣኔ ሐብት ሕመም

0
2115

ጦርነትና የሰላም መደፍረስ የሰዎችን የግል ሕይወት ከማመሳቀል ጎን ለጎን የአገርን ኢኮኖሚ መላ እና ቅጡን እንደሚያሳጡ እሙን ነው።
ኢትዮጵያ በጦርነት እና ባለመረጋጋት እየተፈተነች ባለችበት በዚህ ወቅት፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረትና የሕገወጥ የምንዛሬ ዝውውር ጉዳይ በእንቅርት ላይ እንዲሉት ሆኖባታል። ይህንንም ለመታገል ይመስላል ብሔራዊ ባንክ ሕገወጥ የተባሉ መንዛሪዎችን በጥበቅ ከመከታተልና ከመያዝ አልፎ የተወሰኑ ምርቶች ላይ የምንዛሬ ማእቀብ ጥሏል።

ይህ ማእቀብ ምን ትርፍ ያስገኛል፣ ኪሳራስ ሊኖረው አይችልም ወይ? የሰሜኑ ጦርነትስ በዚህ የምንዛሬ ጉዳይ ላይ ያለው አሉታዊ አስተዋጽኦ ምንድን ነው? የአዲስ ማለዳው መርሻ ጥሩነህ እነዚህን ጥያቄዎች በማንሳት፣ የምጣኔ ሀብት ባለሞያዎችን በማነጋገር ጉዳዩን የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎታል።

የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መጥቶ፣ እንደ አገር የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ ክምችት የአንድ ወር ወጪ እንኳን መሸፈን የማይችልበት ደረጃ ላይ መድረሱን የዓለም ዐቀፉ የገንዘብ ፈንድ (አይ ኤም ኤፍ) ትንበያ ያመላክታል። የውጪ ምንዛሬ እጥረቱ የኢትዮጵያን ምጣኔ ሀብት እድገት በእጅጉ እየፈተነ ነው። ይኸው እጥረት ከውጭ ጥሬ ዕቃ የሚያስፈልጋቸው የአገር ውስጥ አምራች ኢንዱስትሪዎች ምርት እንዲቀንስ፣ የዋጋ ግሽበት እንዲከሰትና አለፍ ሲልም በመንግሥት የተያዙ ፕሮጀክቶች እንዲቆሙ ምክንያት ሆኗል።

የውጭ ምንዛሬ እጥረቱ ስር እየሰደደ መሄዱን ተከትሎ፣ በተለይ ባለፉት አራት ዓመታት የውጭ ገንዘቦች ምንዛሬ ለጥቁር ገበያ ወይም ለሕገ ወጥ የገንዘብ ምንዛሬ ተጋልጦ ቆይቷል። በዚህም ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የውጭ ገንዘቦች የምንዛሬ ዋጋ በባንክ ከሚመነዘርበት ዋጋ ከእጥፍ በላይ በሆነ ዋጋ በጥቁር ገበያ የሚሸጥበት ደረጃ ላይ መድረሱ የሚታወስ ነው። ይህንኑ ተከትሎ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሕገ ወጥ የውጭ ገንዘብ ዝውውርን ይገታሉ ያላቸውን የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፏል።

የውጭ ገንዘብ ከባንክ በላይ የሚንሸራሸርበት ጥቁር ገበያን ለማስቆም ብሔራዊ ባንክ ከወሰዳቸው እርምጃዎች መካከል፣ ሕገ ወጥ የውጭ ገንዘብ አዘዋዋሪ ያላቸውን 391 ግለሰቦች የባንክ አካውንት ማገድ አንዱ ነው። ባንኩ የውጭ ገንዘቦችን በሕገ ወጥ መንገድ በማዘዋወር ለችግሩ መባባስ ምክንያት ሆነዋል ያላቸውን አካላት፣ የባንክ ሠራተኞችን ጨምሮ አካውንታቸውን ከማገድ በተጨማሪ፣ የሕግ ተጠያቂ ለማድረግ ምርምራ እንዲደረግባቸው ለፍትሕ ሚኒስቴር አሳልፎ እንደሰጠም አስታውቋል።

ብሔራዊ ባንክ ይህን ውሳኔ እንዲወስን ካደረጉት ምክንያች መካከል፣ ኢትዮጵያ እንደ አገር ገጥሟት የማያውቀው የውጭ ምንዛሬ እጥረት እና  የውጭ ገንዘቦች ምንዛሬ በባንክ ምንዛሬ ዋጋ ከጥቁር ገበያው ምንዛሬ ጋር ያለው ልዩነት ከእጥፍ በላይ መሻገሩ ነው።

ብሔራዊ ባንክ ይህን ውሳኔ እስከወሰነበት ቀን ድረስ አንድ ዶላር የጥቁር ገበያ ምንዛሬ በባንክ ከሚመነዘረበት ዋጋ ከእጥፍ በላይ ጨምሮ 105 ብር ድረስ እየተሸጠ መሆኑን አዲስ ማለዳ በግብይቱ ላይ ባደረገችው ክትትል ተገንዝባለች።

ሕገ ወጥ የውጭ ገንዘብ አዘዋዋሪዎች ወይም መንዛሪዎች ላይ ብሔራዊ ባንክ እርምጃ እስከወሰደበት ቀን ድረስ አንድ ዶላር በባንክ 52 ብር ከ63 ሳንቲም የሚመነዘር ሲሆን፣ ከጥቁር ገበያ ጋር ያለው ልዩነት 52 ብር 37 ሳንቲም ነበር። የአንድ ፓውንድ የባንክ ምንዛሬ 57 ብር ከ 13 ሳንቲም ሲሆን፣ በጥቁር ገበያ ከሚሸጥበት ዋጋ ጋር ያለው ልዩነት 57 ብር ከ87 ሳንቲም ላይ መድረሱን አዲስ ማለዳ መዘገቧ ይታወሳል።

እስከ መስከረም 26/2015 ድረስ አዲስ ማለዳ በአዲስ አበባ ከተማ የጥቁር ገበያ በሚከናወንበት ብሔራዊ አካባቢ ተገኝታ ባደረገችው ምልከታ፣ የአንድ ዶላር የጥቁር ገበያ መሸጫ ከ98 ብር እስከ 105 ብር ደርሶ ነበር። በጥቁር ገበያ የዶላር ዋጋ በሚጨምርበት ፍጥነት አብዛኛውን ጊዜ የተጋነነ ጭማሪ የማይታይበት የፓውንድ ጥቁር ገበያ ዋጋ፣ በባንክ ከሚመነዘርበት ዋጋ ከእጥፍ በላይ አድጎ አንድ የእንግሊዝ ፓውንድ 115 ብር እየተሸጠ ነበር።

በኢትዮጵያ የዶላር ምንዛሬ በሕጋዊ መንገድ በባንክ ከሚደረገው ግብይት ይልቅ፣ ከባንክ ውጪ በጥቁር ገበያ ወይም በትይዩ ገበያ የደራበት ሁኔታ በተለይ ባለፉት ተከታታይ ሦስትና አራት ዓመታት ተስተውሏል። ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣው የጥቁር ገበያ አንድ ዶላር በባንክ እና ከባንክ ውጪ የሚመነዘርበትን ዋጋም በከፍተኛ ፍጥነት እንዲሰፋ በር ከፍቷል። የውጪ ገንዘቦች የጥቁር ገበያ ዋጋ ከባንክ ምንዛሬ በሰፊ ልዩነት ያደገው የውጪ ምንዛሬ እጥረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱን ተከትሎ ነው ሲሉ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች እንደ ምክንያት ያነሳሉ።

ከብሔራዊ ባንክ በተጨማሪ የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት በዚሁ በሕገ ወጥ የውጭ አገራት ገንዘብ ማስተላለፍ ወንጀሎች ጋር ግንኙነት እንዳላቸው የተጠረጠሩ 665 የባንክ ሂሳቦች እንዳይንቀሳቀሱ ማገዱን ይፋ አድርጓል። በአገልግሎቱ የታገዱት የባንክ ሂሳቦቹ ሕጋዊ የውጭ አገራት ገንዘብ ማስተላለፍ ፈቃድ ሳይኖራቸው በሕገ ወጥ መንገድ በአገር ውስጥ እና በውጭ አገራት ካሉ አካላት ጋር ትስስር በመፍጠር በሕገ ወጥ መንገድ የገንዘብ ማስተላለፍ ተግባር ላይ ተሰማርተው የተገኙ ናቸው ተብሏል።

የብሔራዊ ባንክ እና የፋይናንስ አገልግሎት ሕገ ወጥ የውጭ ገንዘብ ዝውውር ላይ ተሰማርተዋል ባላቿው አካላት ላይ እርምጃ በወሰደ በአንድ ሳምንት ልዩነት፣ ሕገ ወጥ የውጭ ገንዘብ ምንዛሬን ዋጋን ለመቀነስ መንግሥት 38 ምርቶች ላይ የውጭ ምንዛሬ እገዳ መጣሉን ይፋ አድርጓል።

ከውጭ እንዳይገቡ እገዳ ከተጣለባቸው ምርቶች መካከል ከሞተር ነክ ምርቶች የቤት አውቶሞቢሎችና ባለሦስት እግር ተሽከርካሪዎች የተካተቱ ሲሆን፣ ከረሜላዎች፣ ብስኩቶች፣ የለስላሳ መጠጦች፣ ሳሙናዎች፣ ሽቶዎችና የተለያዩ የመዋቢያ ዕቃዎች ይገኙበታል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከጥቅምት 4/2015 ጀምሮ ሕግ ወጥ የውጭ ምንዛሬ ዋጋን ግስጋሴ ለማርገብ እገዳ የጣለባቸው 38 ምርቶችን ከውጭ ለማስገባት የውጭ ምንዛሬ መጠየቅን ከልክሏል። ዕገዳው ላልተወሰነ ጊዜ የሚቆይ ነው የተባለ ሲሆን፣ የውጭ ምንዛሬ ላይ የሚታየውን ችግር ያቃልላል ተብሎ በመንግሥት በኩል ተስፋ ተጥሎበታል።

የእቀባው ትርፍና ኪሳራ

የብሔራዊ ባንክ ውሳኔ በመንግሥት በኩል ሕገ ወጥ ውጭ ምንዛሬንና የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ከማቃለል አንጻር አዎንታዊ ለውጥ ያመጣል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል። ይሁን እንጂ ውሳኔው የሚያስከትላቸው ችግሮች እንደሚኖሩ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች እየገለጹ ነው። የውጭ ምንዛሬ ላይ የተከሰተው ችግር አጠቃላይ በኢኮኖሚው ላይ የሚፈጥረው አሉታዊ ተጽዕኖ ቀላል የሚባል እንዳልሆነና የመንግሥት ውሳኔ ዘላቂ መፍትሔ ሊሆን እንደማይችል ሲናገሩ ይደመጣል።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ማኅበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው መንግሥቱ ከተማ (ፕ/ር)፣ መንግሥት ከሕገ ወጥ የውጭ ገንዘብ ዝውውርና የምንዛሬ እጥረት ጋር የሚገናኘውን ችግር ለመፍታት የወሰነው ውሳኔ ጥቅምና ጉዳትም እንዳለው ለአዲስ ማለዳ በሰጡት አስተያየት ይገልጻሉ።

የውጭ ምንዛሬ እጥረት በሚከሰትበት ወቅት እንዲህ ዓይነት ውሳኔዎች የሚጠበቁ ናቸው የሚሉት ባለሙያው፣ አገራት የውጭ ምንዛሬ ችግር ሲገጥማቸው ከውጭ የሚያስገቧቸው ምርቶችን መርጠው የማስገባት ወይም የውጭ አገር የቅንጦት ምርቶችና በአገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶች ወደ አገራቸው እንዳይገቡ እቀባ እንደሚጥሉ ያነሳሉ።

መንግሥት አሁን የወሰነው ውሳኔ ከዚሁ ጋር የተገናኘ መሆኑን የሚያነሱት መንግሥቱ፣ የውጭ ምንዛሬ ላይ የተከሰተው ችግር መንግሥት ውሳኔውን እንዲወስን አስገድዶታል ባይ ናቸው።

የመንግሥት ውሳኔ ሕገ ወጥ ንግድን ይቀንሳል ተብሎ ይታሰባል የሚሉት ባለሙያው፣ ከውጭ እንዳይገቡ ዕገዳ የተጣለባቸው ምርቶች ገበያ ላይ መቀጠል አለመቀጠላቸውን መለየት ከተቻለ ሕገ ወጥ የውጭ ገንዘብ ዝውውር የሚያርፍበትን ምርት መለየት እንደሚያስችል ይገልጻሉ። በተጨማሪም እንዲህ ዓይነቱ ውሳኔ የአገር ውስጥ ምርትን ለማበረታታት ዕድል እንደሚፈጥር ባለሙያው ጠቁመዋል።

ይሁን እንጂ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ላይ የተጣለው እቀባ፣ የአጭርና የረዥም ጊዜ ጉዳቶችን እንደሚያስከትል ሳይገልጹ አልቀሩም። ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት መንግሥቱ እንደሚሉት፣ የመንግሥት ውሳኔ ካለው ችግር አንጻር አስገዳጅ ቢሆንም፣ የአጭር ጊዜ እና የረዥም ጊዜ ችግሮችን ሊያስከትል እንደሚችል ጠቁመዋል።

ባለሙያው እንደሚሉት፣ የመንግሥት ውሳኔ በአጭር ጊዜ ከሚያስከትላቸው ችግሮች መካከል የዋጋ ንረት አንዱ ሲሆን፣ ውሳኔው በአጭር ጊዜ ውስጥ የዋጋ ንረት እንዲከሰት ምክንያት የመሆኑ እድሉ ሰፊ መሆኑን ጠቁመዋል። ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ከገበያ በሚጠፉበት ወቅት  እጥረትና አማራጭ ስለሚጠፋ ከውጭ እንዳይገቡ ክልከላ በተጣለባቸው ምርቶች ላይ የዋጋ ንረት እንደሚከሰት ባለሙያው ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ መጥቶ አሁን ላይ ደግሞ አባባሽ ኹነቶች ገጥመውታል። ከጦርነቱ መከሠት በኋላ ደግሞ የዋጋ ግሽበቱ ከወር እስከ ወር እያሻቀበ ሲሆን፣ የአብዛኛውን ማኅበረሰብ ክፍል ኑሮ እየፈተነ ይገኛል። በተለያዩ አባበሽ ክስተቶች የተሰቀለው የዋጋ ግሽበት አሁንም ተጨማሪ አባባሽ ችግሮች እየገጠሙት ነው።

ከውጭ እንዳይገቡ ክልከላ ከተጣለባቸው ምርቶች መካከል፣ አንዱ የሆነው የአውቶሞቢል ምርት ውሳኔው ከተሰማበት ቀን ጀምሮ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ማሳየቱን አዲስ ማለዳ ባደረገችው ምልከታ ታዝባለች። ወትሮውንም ቢሆን በየጊዜው ከፍተኛ ጭማሪ እያሳየ የነበረው አውቶሞቢል ገበያ፣ እገዳ ከተጣለ በኋላ ደግሞ ተባብሶ ቀጥሏል።

እገዳ ከመጣሉ በፊት በሳምንት እስከ 200 ሺሕ ብር የዋጋ ጭማሪ ይታይበት የነበረው የአውቶሞቢል ገበያ፣ ከውሳኔው በኋላ ውሎ ሳያድር ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቶ፣ በዋጋቸው ከአነስተኛ እስከ መካከለኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ የእገዳው አካል የሆኑ ተሽከርካሪዎች ላይ እስከ አንድ ሚሊዮን ብር የሚደርስ የዋጋ ጭማሪ ተከስቷል።

የመንግሥት ውሳኔ የዋጋ ንረትን ከማባባስ በተጨማሪ፣ በእገዳው ምክንያት መንግሥት ከውጭ ከሚገቡ ምርቶች ላይ የሚያገኘውን እንደሚያጣ መንግሥቱ ይገልጻሉ። መንግሥት እገዳ ከጣለባቸው ምርቶች ላይ ቀላል የማይባል የገቢ ምርት ቀረጥ የሚሰበስብ ሲሆን፣ ከእገዳው በኋላ ገቢውን ማጣቱ ቀላል የሚባል ጉዳት አለመሆኑን መንግሥቱ አንስተዋል። ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ላይ የተጣለው የውጪ ምንዛሬ እገዳ የዋጋ ንረት ከማባባስና የመንግሥትን ገቢ ከማሳጣት በተጨማሪ፣ በገበያ ላይ የምርት አማራጭን እንደሚቀንስ ባለሙያው ጠቁመዋል።

ይህ ዓይነቱ ውሳኔ ዘላቂ መፍትሔ ሊሆን አይችልም የሚሉት ባለሙያው፣ መንግሥት ውሳኔውን ለረዥም ጊዜ ማቆየት እንደሌለበት ይመክራሉ። ለዚህም እንደ ምክንያት የሚያነሱት መንግሥት ያስቀመጠው እገዳ ለረዥም ጊዜ ከቆየ በጊዜያዊነት ከሚያስገኘው ጥቅም ይልቅ የሚያስከትለው ጉዳት ሊያመዝን እንደሚችል በማንሳት ነው።

የምጣኔ ሀብቱ ሕመም ነጸብራቅ

የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት ከውጭ አገር ገንዘቦች ተጽዕኖ ነጻ አለመሆኑን ተከትሎ፣ የውጭ ምንዛሬ ላይ የሚከሰቱ ችግሮች ተጽዕኖ የማያጣው መሆኑን የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ይገልጻሉ። የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት አሁን ላይ በውጭ ምንዛሬ አጥረት እየተፈተነ እንደሚገኝ በርካታ ምልክቶች እየታዩ ነው። ችግሩ አጠቃላይ የምጣኔ ሀብት ምህዳሩ ላይ ተጽዕኖው የሚታይ ሲሆን፣ ለመንግሥት ተቋማት እንዲሁም ለግሉ ዘርፍም ቀዳሚ ችግር ሆኗል።

ይህንኑ ምጣኔ ሀብቱ በተለያዩ ቸግሮች ተወጥሮ ከጤናማ አካሄድ መውጣቱን ባለሙያዎች መግለጽ ከጀመሩ ሰነባብተዋል። የውጭ ምንዛሬ እጥረቱ ደግሞ ዛሬን ብቻ ሳይሆን መጪውም በስጋት ዐይን እንዲታይ የሚገፋፋ ሆኗል። በሰሜኑ ክፍል የተነሳውን ጦርነት፣ ለውጭ ምንዛሬ እጥረቱ ዋነኛ ምክንያት ተደርጎ በምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ይነሳል።

የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት አሁን ላይ ያለበት ሁኔታ ጤነኛ የሚባል አለመሆኑን፣ የምጣኔ ሀብት ባለሙያው መንግሥቱ ይገልጻሉ። ለዚህም እንደ ማሳያ የሚያነሱት በውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ በጦርነትና በተለያዩ የውስጥና ውጭ ተጽዖኖዎች ላይ መውደቁ ያስከተላቸውን መዛባቶች ነው። “ኢትዮጵያ ትልቅ ጫና ውስጥ ናት” የሚሉት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው፣ በየአቅጣጫው የተከሰቱ ጫናዎች ምጣኔ ሀብቱ ላይ ጫና መፍጠራቸውን ጠቁመዋል።

“ኢኮኖሚው ጤነኛ አይደለም” የሚሉት ባለሙያው፣ ኢትዮጵያ ካለችብት ሁኔታ አንጻር የምጣኔ ሀብቱ ጤነኛ አለመሆን የሚጠበቅ መሆኑን ያነሳሉ። ጦርነትና የውጭ ጫና ባለበት ሁኔታ ምጣኔ ሀብቱ ጤነኛ ሊሆን አይችልም የሚሉት ባለሙያው፣ የመንግሥት ውሳኔዎች ትልቅ ችግር ውስጥ ያለችን አገር ምጣኔ ሀብት ለማስቀጥል የሚደረጉ ጥረቶች ማሳያ ነው ይላሉ።

የሰሜኑ ጦርነት በምጣኔ ሀብቱ ላይ ያስከተለው የውስጥና የውጭ ጫና ቀላል አለመሆኑን ባለሙያው ያነሳሉ። “የመንግሥት ትኩረት ከልማት ወደ ጦርነት ዞሯል” የሚሉት ባለሙያው፣ ጦርነቱ በምጣኔ ሀብቱ ላይ ያሳደረው ጫና ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል።

የሰሜኑ ጦርነት ከተጀመረበት ከጥቅምት 24/2013 ጀምሮ እስካሁን በዘለቀበት የኹለት ዓመት ጉዞ፣ በምጣኔ ሀብቱ ላይ ያሳደረው ጫና ከጊዜ ወደ ጊዜ እያየለ መጥቷል። ስር የሰደዱ ችሮች ባሉበት ምጣኔ ሀብት ላይ የተከሰተው ጦርነት፣ ባለፉት ኹለት ዓመታት በምጣኔ ሀብቱ ላይ ትልቅ ጫና መፍጠሩን የዘርፉ ባለሙያዎች በየጊዜው ያነሳሉ።

የሰሜኑ ጦርነት መቋጫ ካላገኘ የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት አሁን ከገባበት ችግር ይወጣል ብሎ ማሰብ እንደማይቻል የሚገልጹት መንግሥቱ፣ የምጣኔ ሀብቱን ከከፋ ውድቀት ለመታደግ ጦርነቱ በአጭር ጊዜ መቋጫ ማግኘት እንዳለበት ይመክራሉ። “ሰላም ከሌለላ ስለ ኢኮኖሚ ማሰብ አይቻልም” የሚሉት መንግሥቱ፣ የዘርፉ ችግሮች ውስብስብ እንደመሆናቸው መጠን የምጣኔ ሀብቱን ጤንነት ለመመለስ ዘርፈ ብዙ መፍትሔዎች እንደሚያሻ ጠቁመዋል።

“ጦርነቱ ከቀጠለ ተስፋ ማድረግ ይከብዳል” የሚሉት መንግሥቱ፣ ምጣኔ ሀብቱን ከልሽቀት ለማውጣት ብዙ ሥራ መሥራት እንደሚፈልግ ጠቁመዋል። አጠቃላይ የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት ካጋጠመው ችግር ለማገገም ብዙ ዓመታትን እንደሚጠይቅም ባለሙያው አንስተዋል።

ጦርነት በኢኮኖሚ ላይ ከሚያሳድረው ተጽዕኖ መካከል የመንግሥት ሀብት አጠቃቀም ማዛባት እና የሕዝብ ሀብት አጠቃቀም ላይ ችግር መፍጠር መሆኑን ከወራት በፊት ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) መግለጻቸው ይታወሳል። ባለሙያው እንደሚሉት፣ ኢትዮጵያ የገባችበት ጦርነት የመንግሥትን የልማት በጀት ወደ ጦርነት እስከማዞር የሚደርስ፣ እንዲሁም ለጦርነቱ ድጋፍ የሚሰበሰበው የሕዝብ ሀብት በኢኮኖሚው የሀብት አጠቃቀም ላይ የሚያሳደርው ጫና ቀላል የሚባል አለመሆኑን ይገልጻሉ።

ጦርነት በኢኮኖሚ ላይ ከሚያሳድረው ተጽዕኖ መካከል የመንግሥት ሀብት አጠቃቀም ማዛባት እና የሕዝብ ሀብት አጠቃቀም ላይ ችግር መፍጠር መሆኑን ደምስ ይገልጻሉ። ባለሙያው እንደሚሉት፣ ኢትዮጵያ የገባችበት ጦርነት የመንግሥትን የልማት በጀት ወደ ጦርነት እስከማዞር የሚደርስ፣ እንዲሁም ለጦርነቱ ድጋፍ የሚሰበሰበው የሕዝብ ሀብት በኢኮኖሚው የሀብት አጠቃቀም ላይ የሚያሳደርው ጫና ቀላል የሚባል አይደለም ይላሉ።

በጦርነቱ ካጋጠመው የሀብት አጠቃቀም መዛባት በተጨማሪ፣ የችግሩ ሠለባ በሆኑ አካባቢዎች የመንግሥት እና የሕዝብ ሀብት ውድመት እንዲሁም፣ የዜጎች ከመኖሪያ ቦታ መፈናቀል በኢኮኖሚው ላይ የረዥም ጊዜ ጠባሳ የሚጥል ነው ብለዋል። በጦርነቱ የተከሰተውን የሀብት ውድመት እና የመሠረተ ልማት መስተጓጎል ተከትሎ ዘርፈ ብዙ ሰብዓዊ ችግሮች እንደሚከሠቱ የሚገልጹት ባለሙያው፣ ጦርነቱ በአጭር ጊዜ አለመጠናቀቁን ለአጭር ጊዜ የሕዝብ ኑሮን ከማስተጓጎሉ በተጨማሪ፣ የረዥም ጊዜ እድገትን እንደሚገታ እና ለዋጋ ንረት መባባስ ምክንያት እንደሚሆን ጠቁመዋል።

የሰሜኑ ጦርነት በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ከሚያሳድረው ተጽዕኖ በተጨማሪ፣ የጦርነቱ ሠለባ በሆኑት አካባቢዎች የሚኖረው እና ሀብቱን ያጣው የማኅበረሰብ ክፍል ግንባር ቀደም የችግሩ ተጋላጭ እንደሚሆን ደምስ ጠቁመዋል። በተከሰተው ጦርነት ሀብቱን ያጣው ሕዝብ ለከፋ የኢኮኖሚ ችግር መጋለጡን ተከትሎ ረሀብ ሊከሰት የሚችልበት ኹኔታም ሊያጋጥም እንደሚችል ይገልጻሉ።

ጦርነት በርካታ ችግሮች ያስከትላል የሚሉት ደምስ፣ የጦርነት ሠለባ ከሆነው ኢኮኖሚና ከሚከተሉት ችግሮች እንዴት መውጣት እንደሚቻል አቅዶ መሥራት ተገቢ ነው ይላሉ። በጦርነት ታሪክ ያለፉ የዓለም አገራት ከጦርነት በኋላ የገጠማቸውን የኢኮኖሚ ስብራት ለመጠገን ከወትሮው የተለየ እቅድ ነድፈው እንደሚሠሩም ደምስ አንስተዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 207 ጥቅምት 12 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here