ከመፈንቅለ መጅሊሱ ወደ መፈንቅለ ሲኖዶስ የዞረው ወራዳ ተግባር

0
1944

ሃይማኖት፤ የሰው ልጆች በምድር ላይ ፈጣሪ ብለው የሚያመልኩትን አምላክ በመታዘዝና በመከተል፣ ገነትን ለመውረስ የሚያልፉበት መንገድ ነው። ምንም እንኳ የየሀይማኖቱ መልዕክት ቢለያይም፤ አንድ የሚያደርጋቸው ነገር አብዛኛዎቹ የሰው ልጅ የሞራል እሴትን፣ ሰብዓዊነትን፣ አሳቢነትና መልካምነትን የሚሰብኩ መሆኑ ነው። ለምሳሌ ውሸትን የሚጠየፍ እንጂ የሚሰብክ ሀይማኖት አታገኙም። ሰዎች ይዋሹ ይሆናል እንጂ፣ ሰላም የማይሰብክ ሀይማኖት የለም። በጎን የራሳቸው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም፤ ክብርና ልዕልና የሚፈልጉ ሰዎች ቢኖሩ እንጂ ሀይማኖት የዓለም ሕዝብን ከሞራል ልሽቀትና ከፀያፍ ተግባራት እንዲርቁና መልካም መልካሙን ይሠሩ ዘንድ ያስተምራል። የሀይማኖት አባቶች ሚናም ይኽንኑ ለሰዎች ማድረስ ሲሆን፣ በሚሰብኩት ሁሉ ለሰው መልካም አርዓያ እንዲሆኑ መታዘዛቸው የሚጠበቅ ነው።

አንድ ሰው ራሱን ሳይመራ ሌሎችን ሊመራ፣ ቅን ጎዳና ሊያመላክት አይችልም። በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር የአይሁድ እምነት፣ የክርስትና እምነትና የእስልምና እምነት ከብዙ ሀገራት ቀድማ ተቀብላለች። ተቀብላም በየጊዜው በነፃነት በማስተናገድና በእምነት ነፃነት በኩል በተደጋጋሚ ሥሟ በሁሉም ተነስቷል ማለት ይቻላል። ለአብነትም በመፅሐፍ ቅዱስና በነብዩ መሀመድ (ሰ.ዐ.ወ.) ሀዲስ ላይ በሰፊው ተጠቅሷል። ታዲያ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ እምነቶቹ አመለካከታቸውን በተለያየ መልኩ ሲያሠራጩ ኖረው እዚህ ደርሰዋል።

በሀይማኖቶቹ መካከል የተለየ ፀብ ባይኖርም የፖለቲካ ሥልጣን ባመጣቸው የየጊዜው መልኮች አለመግባባቶች አልፈዋል፡፡ ይሄ በየትኛውም የጥንት ሀገረ-መንግሥት ውስጥ የሚያጋጥሙ ክስተቶች ነበሩ። ምክንያቱም ‘ሀይማኖት እና መንግሥት የተለያየ ናቸው’ የሚለው መርህ አልነበረም። ይልቁንም ሁለቱ በጥምረት ነበር የሚሠሩት። ሌላው ደግሞ ኃይል ያለው በኃይል አሸንፎ የሚገዛበት ሥርዓት እንጂ ዴሞክራሲ የሌለበት፣ የነገሥታት ልጆች እንኳ በተራራ ላይ እስር ቤት ከዓለም ተለይተው እንዲኖሩ የሚደረግበት የጉልበት ጊዜ ነበር። እናም በሀይማኖቶች መካከል አልፎ አልፎ መለካከፍ ቢፈጠር የሚደንቅ አይደለም።

እነዚህ ሀይማኖቶች ከዚህ በዘለል በራሳቸው ምዕመናን ዘንድ የሚከበሩ፣ ወጥ ቀኖና አስተምህሮ፣ የሹመት እርከን ያላቸውና እጅግ የሚፈሩ ነበሩ። የሀይማኖት አባቶች፣ ሸሆች፣ ቄሶች፣ ዳዒዎችና ሰባኪዎች በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል ዘር ቀለም ሳይለዩ ያመኑበትን የሀይማኖት መልዕክታቸውን ለማዳረስ ትልቅ መከራና መስዋዕትነት ከፍለዋል። በዚህም ሀይማኖት ዘር ቀለም የማይለየው መሆኑ አሳይተው አልፈዋል። ይህንንም እሴት አቆይተውልናል፤ አባቶቻችን።

አንድ የሚገርም ታሪክ ላካፍላችሁ፤ ኸድር ታጁ የተባለው ወንድሜ በሸይኽ አሊ ጎንደር ታሪክ ካሰፈረበት ድርሳኑ የተዋስኳት ነች፡፡ ከሸይኽ አሊ ጎንደር ሀሪማ (በዛሬ ቋንቋ የሀይማኖት ዩኒቨርስቲ) ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ሰዎች ወደእርሳቸው ሄደው የሀይማኖት ትምህርት ይቀስሙ ነበር።

ትምህርት ሲያጠናቅቁም የሀይማኖት ተልዕኳቸውን (ዳዕዋቸውን) ለመፈፀም የሚመድቧቸው ራሳቸው ሸይኹ መሆናቸውን ይገልፃል። እና ሸይኽ አሊ አንድ እጅግ ከፍ ያለ እውቀት የገበዩ ሸይኽ አብዱልሀኪም የተባሉ ደረሳቸውን ሲመድቡ፤ የአማራ ተወላጅ ቢሆኑም ሀይማኖት ድንበር የለውምና የእስልምና ሀይማኖትን ወደ ጅማ ከትመው ሕዝቡን ወደ ሀይማኖት እንዲጣሩ መላካቸውን ያትታል። በመፅሐፉም እኚህ የተከበሩ ሸህ ሕዝቡን አስተምረው ከዛው ከጅማ ኦሮሞ ተጋብተው መኖራቸውን ይገልፃል። ታዲያ የሠለጠነው ሕዝብስ ምን አለ? አማራ ስለሆነ አልሰበክም ያለ እንዳይመስላችሁ! እንደውም በፍቅር መኖሪያ ችሯቸው በነፃነት ለመኖር ችለዋል።

በእስልምና አስተምህሮ ”ጊዜ በገፋ ቁጥር ደንቆሮ ትውልድ ይፈጠራል። ይህ ትውልድ ትላልቅ አዋቂዎችን በመናቅ ራሱን እንደአዋቂ ይቆጥራል። ከፊትም ሆኖ ካልመራሁ የሚል ትውልድ ይመጣል” ሲል ይገልፃል። እንደ ክርስትና አቡነ ጴጥሮስ ከፊቼ ኦሮሞ አካባቢ የመጡት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ እምነትን ሲሰብኩ፣ አማኙን ሲያንፁ፣ የሀገር ፍቅር ሲያስተምሩ እንጂ እሳቸውም ሆነ የሚመሩት ሕዝብ ስለእርሳቸው የዘር ወይም የቀለም ማንነት ገዶት የማያውቅ ነው። ይኸውም የሆነው ትክክለኛ እምነትን የተረዳ ሀይማኖት ድንበር የሌለው መሆኑን ስላወቁ ነው።

ወደ ዋናው ነጥቤ ስመለስ፤ ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ ሀይማኖት የፖለቲካ መጠቀሚያ ለማድረግ ሲሞከር ሳይሆን በግልፅም መንግሥት ጭምር እጁን በመክተት ሥልጣኑን በመጠቀም ከሕገመንግሥታዊ አሰራር ውጪ ነገሮችን ሲያጨማልቅ፣ ሲያቦካ ተስተውሏል። ይሄ በእውነት ትልቅ፣ ኢትዮጵያ በዘመኗ ገጥሟት የማያውቅ ሰይጣናዊ መቅሰፍት ነው ብል፤ ከሀይማኖት መርህ አኳያ አልተሳሳትኩም። ለአብነት ያህል የኢትዮጵያ ነባር ሙስሊሞች አባቶች ያቋቋሙትን እስልምና ጉዳዮች ላይ ብቻ በመንግሥት፣ በፖለቲካ ጥቅምና በግል ዝናና ሀብት የናወዙ ሰዎች ጋር በመሆን ለዘመናት በሰላም የምናውቀው የሙስሊም ተቋም በአፈሙዝ በኃይል መፈንቅል ያደረጉትን መውሰድ ይቻላል። ብዙ ሰው በሙስሊሞች መካከል ያለው አለመግባባት የእምነት ይመስለዋል። ነገር ግን ጉዳዩ ከሀገሪቱ ከሁሉም ክልሎች ታሪክና ትውፊት ጋር የተጋመደው ነባር የእስልምና እምነት ጉዳይ ቢሆንም፤ በተቃራኒው መንግሥት መጅሊሱ ለተቆጣጠረው አካል በብሔርተኝነት ስም የፖን አረብ የፖለቲካ አመለካከት ይዘው ወደ ሀገር የገቡ መሆናቸው ነው።

የፖለቲካ አመለካከታቸውም የሳዑዲ የፖለቲካ ርዕዮት በወሓቢዝም ሰንሰለት የሚቀዳ ሲሆን የግብፁ አንድ ዓመት መምራት የተሳነው በሰይድ ቁጥብ የተሰረቀው ‘የብራዘር ሁድ’ አመለካከት ነው። እነዚህ አካላት ላለፉት በርካታ ዓመታት ወደዚህ እርከን ለመምጣት ብዙ ጥረዋል። ከእነዚህ እንቅስቃሴዎቻቸው መካከል አንደኛው የድምፃችን ይሰማ ኅቡዕ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ነው። የዚህ አመለካከት አራማጆች ዛሬ የት እንዳሉ ምን እንደሚያቀነቅኑ የታወቀ ነው። ለዚሁ የፖለቲካ መሠላልነት መወጣጫነት እንዲጠቅማቸው ከሚጠቀሟቸው ማታገያዎች አንደኛው መጅሊስና የትላልቅ አባቶች ስም በወጣቶች ማጉደፍ ነው። ሌላኛው እንደ ብሔር አማራንና የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን በጠላትነት በመፈረጅና በተደጋጋሚ በመክሰስ፤ የአንድ የኦሮሞ ፖለቲካ ብሔር ብሔርተኝነትን ማራመድ ለኢትዮጵያ ሙስሊም አርነት መሆኑን በተደራጀ መልኩ ፍላጎታቸውን ለማስፈፀም ሲሠሩ ሰንብተዋል።

በዘመነ ኢሕአዴግ በእስር የነበሩት እነዚሁ በሀይማኖት የሚሸቅጡ አካላት ከሪፎርም ተብዬው ማግስት ከኦሮሚያ ርዕሰ መስተዳድር ቢሮ እስከ የቤተመንግሥት ሽርጉድ ማብዛታቸው ዓለም ያወቀው ነው። እነዚሁ ቤተመንግሥትን የእናታቸው ጓዳ ያህል የሚዘይሩት ሰዎች፤ ከተወሰነ ቆይታ በኋላ መንግሥት መጅሊሱን ሊያስረክበን ይገባል መግለጫ አወጡ። የኢትዮጵያ ሕገመንግሥት የምንለውና አሁንም በሥራ ላይ መንግሥት እየሠራበት ያለው ሕገመንግሥት፤ መንግሥት እና ሀይማኖት እንዲሁም ሀይማኖት እና መንግሥት የተለያዩ ናቸው ይላል። አንቀፅ 11: 27 እና 9 በዚህ ዙሪያ በግልፅ መንግሥት በሀይማኖት ጣልቃ እንደማይገባ ቢያስቀምጥም፤ ዛሬ ሀገሪቷ ወዴት እየሄደች እንደሆነ የማይነግሩን የኢፌዴሪ ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ የቀድሞ የኢ/እ/ጉ/ጠ/ም/ቤት ፕሬዝደንት ከኃላፊነት እንዲለቁ መጠየቃቸው ዘግይቶም ቢሆን ታውቋል። ከዛም ፕሬዝደንቱ ለቅቄአለሁ ሲሉ ጉባኤዉ አልተስማማም፤ ይቀጥሉ በሚል ይወስናሉ።

ቀጣዩ ጣልቃ ገብነት ዐይን ያወጣ ሕገወጥነት መሆኑን ተመልከቱ! ወደ ቤተመንግሥት ተጠሩ። በሪፎርም መሠረት ሥልጣናቸውን እንዲለቁ ተግሳፅ ተሰጣቸው። በሴራ ተብትበው ዘጠኝ ኮሚቴ በሚል የመካከለኛው ምሥራቅን አስተሳሰቦች ይዘው የሚነጉዱት ዘውጋዊዎቹ ተመቻችተው እንዲገቡና ነባሩን አስተሳሰብ ለማጥፋት በሚደረገው የሥርዓቱ እቅድ እንዲያስፈፅሙ ተደረገ። እንግዲህ መጅሊሱ በተቀዳሚ ሙፍቲ በሚመራበት ወቅት፤ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መታዘብ ከቻለው ነገር፤ ሥርዓቱ አሻንጉሊት አድርጎ ለራሱ መጠቀሚያ አድርጓቸው እንደነበር ነው። ተራ የቀበሌ አስተዳደር ለኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ደብዳቤ የማይታዘዝበት ነበር። ሽባ የተደረገ በሴራ የተጠለፈ ሥልጣን ነበር፡፡

በዚህ ሂደት የተፈፀሙ በደሎች ቢኖሩም ዝርዝሩ ብዙ ነው። መጅሊሱን በዘር ማንነት ለማደራጀትና በብሔር ከፋፍሎ አንድ የነበረው ሙስሊም እና እስልምና የመጅሊሱን ኮታ ልክ እንደ ፓርላማ ወንበር በቁጥር ነው የሚል የብሔር ፌዴራሊዝም ግልባጭ የመጅሊሱ መተዳደሪያ ደንብ ተደርጎ መጣ፡፡ በዚህ መሠረት የመጀመሪያው ሚሽን የነበረው የመጅሊሱ ችግር የአማራና የኦሮሞ ማስመሠል ነበርና ኦሮሞ የሆኑት ኢብራሂም ቱፋ ከፊት ረድፍ ሆኑ። ትልቁ ነገር የነባሩ ሙስሊም ችግር የብሔር ችግር አልነበረም። ላለፉት በርካታ ዓመታት የመጨረሻው የሸህ መሀመድ አሚን መጅሊስ ጨምሮ 70 በመቶ ኦሮሞ የሆኑ አስተዳድረዉታል። አንድም ጥያቄ ያነሳ የለም። ለምን? በሀይማኖት አመለካከት አንድ ስለነበሩ ነው፡፡ ይህኛው መጅሊስ ለምን ተቀባይነት አጣ ሲባል፣ ኦሮሞ በመሆን አይደለም። ይልቁንም በሚከተለው ከሀይማኖት የራቀ የፖለቲካ አመለካከት ሳቢያ ነው። ከመካከለኛው ምሥራቅ በተቀዱ የከሰሩ አመለካከቶችም ሆነ ‘ፌድ’ ባደረገ የዘር ፖለቲካ ሀይማኖት መምራት ስለማይቻል ነው። ምክንያቱም ሀይማኖት ዘር ቀለም ድንበር ስለሌለው።

ለዚህ ሁሉ ነገር ቤተመንግሥት ተጠያቂ ትሆናለች። መንግሥት መጅሊሱ ለሕገወጡ ቡድን ለማስረከብ ባቀደበትና ፈትፍቶ በጨረሰበት ወቅት፤ የነባሩ ሙስሊም ኅብረተሰብ ምሁራን ለማስተኛት ስብሰባ ይኖራችኋል፤ ጉዳያችሁን ተወያይታችሁ ትፈታላችሁ ተብለው ከተነገራቸው በኋላ በነጋታው የዘጋቢ ፊልም ጋጋታ የመጅሊሱ መሠልቀጥ የመንግሥት ስውር እጅና ሴራ የታከለበት ለመሆኑ ግልፅ ወጣ። በሸራተን አዲስ ሆቴል ተወያይታችሁ ችግራችሁን ትፈታላችሁ። ከኹለቱም በኩል ሰው እንዲያቀርቡ ሿሿ ለመሥራት ተሰናዱ። ታዲያ ከዚህ ውጪ አንድም አካል ዝር አይልም ብሎ የጠገረራቸውን አካል በሸራተን በተደገሰው ድግስ ለወንበር ሟሟያ ያልተጠራ የመንደር ጎረምሳ እንደሌለ ጭምጭምታ ተሰማ። ወደ ተቀዳሚ ሙፍቲም ተደውሎ በኃይለ-ቃል ለሸራተኑ መፈንቅለ መጅሊስ እንዲተባበሩ ለማድረግም ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም። የምር ትልቅ ሀገራዊ ቅሌት ነው። በበርካቶች አንደበት መስረፅ የቻሉት ትሁቱ ስሱ አባታችን ተቀዳሚ ሙፍቲም፤ ”የምታደርጉት አድርጉ፤ አልመጣም።” አሉ። ውሳኔያቸው ሆነ። ሐምሌ 10 ቅዳሜም በመንግሥት የተደገፈው የመጅሊስ መፈንቅል በኃይል ለማድረግ መታሰቡን ለኢትዮጵያ ሕዝበ ሙስሊም በመግለጫ ማጋለጣቸው አይረሳም።

ታዲያ በማግስቱ የፖለቲካ ፓርቲ ስብስቦች ባደረጉት ጉባኤ፤ በኋላ መጅሊሱን በፌዴራል ፖሊስ በማስከበብ ሰዒረ መጅሊሱ ሲከናወን በቀጥታ ስርጭት ተመልክተናል። ምንኛ አሳፋሪ ድርጊት እንደሆነ ባወቁት። የመንግሥት ሚዲያዎች አራጋቢ መሆን ከመንግሥት የተሰጠ የሴራው አንዱ አካል መሆኑ ግልፅ የወጣው የዘገባ መዓት ማስታወቂያው ነው። ተዓማኒነት በማታለልና በሕገወጥነት አይገኝም፤ በተለይ ሀይማኖት ተቋማት ሲሆኑ።

መንግሥት በዚህ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ውስጥ ነባር እስልምና ለማጥፋት ዓለም ዐቀፍ ሕግ ከሚፈቅድለት ድንበር ተሻግሮ ማንም ሀይ ባይ በሌለበት በጉልበቱ ያሻውን የሚሠራ መሆኑን በሙስሊሙ ላይ ባደረሰው በደል ማረጋገጥ ይቻላል። ከሰሞኑ ይኸው ፈጣሪንና ግፍን የማይፈራ የሞራል ለከት የሌለው አገዛዝ፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ሲኖዶስ ላይ መፈንቅል ለማድረግ መነሳቱ መነጋገሪያ ሆኗል። ይሄ የሚያሳዝን ቢሆንም ከዘር ፖለቲካ ከመጨማለቅ ውጪ ሌላ ተግባር የማያውቀው ስብስብ በሲኖዶሱ መሪ ላይ በርካታ ‘character assassination’ ሲፈፅም ተስተውሏል። ይህንን በመጠቀምም ቤተክርስቲያኒቷን በአማራና በትግሬ እና በኦሮሞ የተከፋፈለች ለማድረግ ብዙ ጎንጉኗል። እንደምታስታውሱት ብፁዕ አቡነ ማትያስ ለሕክምና ከሀገር ሲወጡ የተነዛባቸው ‘ቅርስ ሰርቀዋል’ን ጨምሮ ያልተከፈተ ዓይነት ሴራ አልነበራም።

በተለይ ከሀይማኖትና ቋንቋ ጋር የሚነሱ ችግሮች በአስተዳደራዊ ችግሮችና ተደራሽነት አኳያ ተወያይቶ የሚስተካከል ቀላል ጉዳይ እንጂ ‘የሚሰብከው የኔ እገሌ ካልሆነ በዚህ አልመራም’ የሚባልበት የሳጥናኤላዊያን ጊዜ አሁን ነው። ይህንን ፈተና ተቋቁማ የሰነበተችው ቤተክርስቲያንም ሆነ ሲኖዶሱ፤ በመጅሊሱ የተደረገው ሕገወጥ መፈንቅለ መጅሊስ እጣ ፈንታ ዞሮ ወደእርሷ በመምጣቱ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ አዝናለሁ። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን መንግሥት ሕግ እንዲያስከብር በመግለጫዋ ጥሪ ብታቀርብም፤ ልክ እንደ ‘ቤርጎ መጅሊስ’ ይኸኛውም ሆቴል መሽጎ መቀመጡ ሕግ ከማስከበር አንፃር ኃላፊነት አልተወጣም ማለት ይቻላል። ከዚህ ባሻገር መንግሥት ጣልቃ አይገባም የሚለውን ለሴራ መጠቀሙ እስከምን ያዋጣል የሚለው እንቆቅልሽ ቢሆንብኝም፤ ሕጋዊው አካል ለእርምጃ ሲነሳ ግን በተቃራኒው እንደሚሆን በተደጋጋሚ በሙስሊሙ ጉዳይ የታየ ተሞክሮ ነው። ሀገሪቱን እየገዛ ያለው ሥርዓት ነባር አስተሳሰቦች ከፋፍሎ ለመጣል ታሪካቸውንና እሴታቸውን ማፍረስ የእለት ሥራዬ ብሎ ይዞታል።

በኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ሥርዓት ፓትርያሪክ ሳይሞት አይሻርም የሚል የተቀመጠ ሕግ፣ ሥርዓት አሠራር አለ። ከዛ ውጪ ሕገወጥ በሆነ መንገድ መንቀሳቀስ ሕግና ሥርዓት በሰፈነበት ሀገር የተማመኑት የፖለቲካ ኃይል ከኋላ ለማስከተላቸው እውነታ ገላጭ ነው። ስለዚህ በሲኖዶሱ ላይ የተከሰተው ተግባርም ሆነ እንቅስቃሴ መጅሊሱ ላይ ከተደረጉት እንቅስቃሴ የተለየ ነገር የለውም። የመጨረሻው ግብ የኦሮሚያ መጅሊስ ከፌዴራል ተገንጥሎ እንደነበረው፤ ‘የኦሮሚያ ሲኖዶስ’ ተገነጠልኩ ብሎ ሌሎቹን በሲኖዶሱ ላይ ለማስነሳት ደፋ ቀና ማለት ሰላምና መረጋጋትን መንሳት ይሆናል፤ ሲኖዶሱን ለማዳከም። በዚህ መሠረት ይህች ሙከራ ነች። የመጀመሪያው የከሸፈው መፈንቅለ ሲኖዶስ ብንለው ሴራው ግን አይቆምም። ለዚህም ይመስላል የአገዛዝ ዘመኑ መርዘም እንጂ ስለዜጎች መሰደድ፣ መራብ፣ መሞት፣ መሰቃየት ግድ የማይሰጠው አገዛዙ የኦርቶዶክስን አጀንዳ ለመሸፈን በአጣዬና አጎራባች አካባቢ ሕዝብ ቀዬውን ለቅቆ እንዲሰደድ በታጣቂዎች ጥቃት እንዲሰነዘርባቸው መንግሥት አለ በተባለበት የተተወዉት።

ማሳረጊያ

ታሪክ የሌለው ትውልድ ስለመጪውም ሆነ ስላለፈው ጊዜ መረዳት ያዳግተዋል። ትውልድን ታሪክ አልባ፣ ሀይማኖት አልባ ማድረግ የመጨረሻ ውጤቱ ሀገር ማፍረስ፣ የሰው ሕይወት ወደሚበላ አውሬያዊ መቅሰፍትነት መቀየር ነው። የዚህ ዳራው እንደ ሩዋንዳ እርስ በርስ መጠፋፋት ነው ትርፉ። ሀይማኖት ተሰሚነት ሲያጣ፣ የፖለቲካ ስብከቶች ጥላቻ ሲያበዙ ወይም የሀይማኖት ጥላቻ ሲበዛ ይህ ዓይነት አደገኛ ቁማር ውስጥ እየተገባ መሆኑን ግልፅ ነው። ስለዚህም መንግሥት ከሀይማኖት ቤቶች ጣልቃ ገብነት ራሱን ሊያቅብ ከሀይማኖታዊ ስርዓት በዘለል አፍራሽ ድርጊት የሚሠሩትን አካላት ከፖለቲካ ወገንተኝነት (ጎጠኝነት) ወጥቶ በትክክል ሕግ ማስከበር ይገባዋል።

ኢትዮጵያ ታፍራና ተከብራ ለዘለዓለም ትኑር!

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here