በ310 ወረዳዎች ለሚገነቡ የውሃ ፕሮጀክቶች ዘጠኝ ቢሊዮን ብር ብድር ተገኘ

0
636

ብድሩ በ38 ዓመታት ውስጥ ተከፍሎ የሚያልቅ ነው

በያዝነው ዓመት ተጀምሮ በቀጣይ አምስት ዓመታት በ16 ቢሊዮን ብር ወጪ በ310 ወረዳዎች እና በ58 ከተሞች ለሚተገበረው ለኹለተኛው አገር አቀፍ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ ሳኒቴሽንና ሀይጂን ፕሮጀክት የዓለም ባንክ ዘጠኝ ቢሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ።

ብድሩ የስድስት ዓመታት የችሮታ ጊዜን ጨምሮ በ38 ዓመታት ውስጥ ተከፍሎ የሚያልቅ ብድር ሲሆን፣ ከወለድ ነፃ እንደሆነም ለምክር ቤቱ የቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ያስረዳል።

የአንድ ቋት ፕሮጀክትን በመጠቀም ወጪው የሚሸፈንለት ይህ ፕሮጀክት፣ ከዓለም ባንክ ውጪ ሌሎች ለጋሾችም ይሳተፉበታል። በዕርዳታ ቀጥታ እርዳታ ከሰጡት መካከልም የአፍሪካ ልማት ባንክ፣ የእንግሊዝ መንግሥት፣ የተባበሩት መንግሥታት የህፃናት ፈንድ (ዩኒሴፍ)፣ የኮሪያ መንግሥትና የፊንላንድ መንግሥት እንደሚገኙበት በውሃ ልማት ኮሚሽን ውስጥ ዳይሬክተር የሆኑትነ አቶ ታምሩ ደገፉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ብድሩ ባሳለፍነው ሳምንት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ የፀደቀ ሲሆን፣ የገቢ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበት ከአገራችን የብድር አስተዳደር ስትራቴጂ የሚጣጣም በመሆኑ እንዲጸድቅ ለምክር ቤቱ መቅረቡን ለማወቅ ተችሏል።

የተደረሰው ስምምነት የዓለም ባንክ ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር በሚያደርገው ስምምነት መሰረት የሚለቀቅ ብድር መሆኑን የተናገሩት የገንዘብ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ሃጂ ኢብሳ፣ ኢትዮጵያ ያለባት የብድር ጫና 50 ቢሊዮን ዶላር በመድረሱ ምክንያት ተጨማሪ የብድር ውል ስምምነት በሚደረግበት ጊዜ ምክር ቤት ቀርቦ እንዲፀድቅ መደረጉን ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ በ ዘጠኙ ክልሎችና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በሚገኙ ወረዳዎች እና ከተሞች የሚተገበር ሲሆን፣ የገጠርና ከተሞች ንፁህ የመጠጥ ውሃ ሥራዎች፣ በድርቅ በተደጋጋሚ የሚጠቁ አካባቢዎችን የውሃ አቅርቦት፣ የትምህርት ተቋማት እና ጤና ኬላዎች የመጠጥ ውሃ አቅርቦትን እንዲሁም የአቅም ግንባታ ፕሮግራም ማስተባበርን ያካተተ ነው።

አስራ አንድ በመቶው የሚሆነው የዓለማችን ሕዝብ የንጽህ ውሃ መጠጥ ተደራሽ ባለመሆናቸው ከውሃ ጋር በተያያዘ መከላከል በሚቻሉ ህመሞች በዓመት 2.2 ሚሊዮን በላይ ህጻናት ሞት ምክንያት እየሆነ ነው።

በዓለማችን ከ1982 ጀምሮ በ10 ዓመታት ብቻ 2 ቢሊዮን የሚሆነው የዓለም ሕዝብ የንጹህ የመጠጥ ውሃ አንዲያገኝ ማድረግ ተችሏል።
በኢትዮጵያ የሚተገበረው አገር አቀፍ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ ሳኒቴሽንና ሀይጂን ፕሮጀክት ለውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ተጠሪ የሆነው የውሃ ልማት ኮሚሽን በፌዴራል ደረጃ የማስተባበር ኀላፊነት እንዳለበት የኮሚሽኑ የሥራ ኀላፊ ታምሩ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

በተቋማት ደረጃ ለሚተገበረው የፕሮጀክቱ ክፍልም የትምህርት ሚኒስቴር እና የጤና ሚኒስቴር የማስፈፀም ኀላፊነት ያለባቸው ሲሆን፣ የገንዘብ ሚኒስቴር የገንዘብ አቅርቦቶችን በሚኒስቴሩ በተከፈተው አካውንት ከልማት አጋሮች የተገኘውን ገቢ በማሰባሰብ የሚያከፋፍል ይሆናል።

ቅጽ 2 ቁጥር 53 ጥቅምት 29 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here