ዳሰሳ ዘ ማለዳ ኅዳር 8/2012

0
730

1-በቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ከ12 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት አደገኛ አደንዛዥ ዕፅ መያዙን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ።አደንዛዥ እፁ እሁድ ኅዳር 7/2012 በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በዓለም አቀፍ መንገኞች ማስተናገጃ ተርሚናል በጉምሩክ ኢንተሊጀንስ ሰራተኞች፣ በኢንተር ፖል አባል እንዲሁም በሰዓቱ ከነበረ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ሰራተኛ ትብብር በቁጥጥር ስር መዋሉ ተገልጿል።መነሻውን ሳዎ ፖሎ ያደረገ ሲሆን የበረራ ቁጥር ET 507 እንደነበር ተገልጿል። (አዲስ ማለዳ)
……………………………………………………………………
2-በውጭ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት ለደንበኞቹ የተሽከርካሪ ሰሌዳ ቁጥር መስጠት እንዳልቻለ የትራንስፖርት ባለስልጣን አስታወቀ።በፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን የሰሌዳና ምልክቶች ምርትና ስርጭት ዳይሬክተር ገዛሀኝ ግራባን በበኩላቸው ደንበኞች ያቀረቡት ቅሬታው ትክክል ሲሆን ችግሩ የተከሰተው በኹለት ምክንያቶች ነው ሲሉ ተናግረዋል።ሰሌዳዎቹ ከውጪ ሚገቡ በመሆናቸዉ ምክንያት የውጪ ምንዛሬ እጥረት ስለገጠመን ሰሌዳዎቹን ለማዘዝ ረጅም ጊዜ ፈጅቶብናል ብለዋል።(ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8)
……………………………………………………………………
3-ለሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ ድምፅ ለመስጠት ከ2 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ መራጮች መመዝገቡን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቋል።ከጥቅምት 27 እስከ ኅዳር 6/2012 ድረስ በተካሄደው ምዝገባ ከ2 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ሰው መመዝገቡን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ የመራጮች ምዝገባ ሙሉ በሙሉ ሰላማዊ በሆነ መልኩ መጠናቀቁን የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚዴቅሳ አስታውቀዋል።(አዲስ ማለዳ)
……………………………………………………………………
4-ብሔራዊ የገበያ መረጃ አገልግሎት በ157 ወረዳዎች የሙከራ ስርጭት መጀመሩን የንግድ ሚኒስቴር አስታወቀ።ሚኒስቴሩ ብሔራዊ የንግድ ስርዓትን የሚያዘምን፣ አርሶ አደሩን የምርቱ ተጠቃሚ የሚያደርግ እና አላስፈላጊ የሆነ የግብይት ሰንሰለትን የሚያሳጥር ብሔራዊ የገበያ መረጃ አገልግሎት በስልክ ቁጥር 6077 መጀመሩን ገልጿል።በዚህ መሰረትም በአማራ ክልል 42፣ ኦሮሚያ ክልል 64፣ ትግራይ ክልል 15 እና በደቡብ ክልል 34 ወረዳዎች በድምሩ በ157 ወረዳዎች የሙከራ ስርጭት መጀመሩ ተነግሯል።(አዲስ ማለዳ)
……………………………………………………………………
5-ባለፈው ሳምንት በወሎ ዩኒቨርሲቲ ተከስቶ በነበረው ግጭት ምክንያት ቆስሎ በሕክምና ሲረዳ የነበረ አንድ ተማሪ ሕይወት ማለፉን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል።(አዲስ ማለዳ)
……………………………………………………………………
6-የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከበረራ የታገደውን ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላኖች ለመቀበል ከውሳኔ አለመድረሱን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ተወልደ ገብረማርያም ተናገሩ። በዱባይ በመካሔድ ላይ በሚገኘው የአውሮፕላን አምራቾች አውደ ርዕይ በመሳተፍ ላይ የሚገኙት ተወልደ ገብረማርያም በቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላኖች የበረራ መቆጣጠሪያ ሶፍትዌር እና በሥልጠና ላይ አምራቹ እያደረገ ያለው ማሻሻያ “ገና በሒደት ላይ ነው” ብለዋል።አያይዘውም ማሻሻያው “ተጠናቆ ልናየው ይገባል። ተጨማሪ የሙከራ በረራዎች ውጤቶች ገና ወደፊት የሚታዩ ናቸው” ሲሉ ተናግረዋል።(ዶቼ ቬለ)
……………………………………………………………………
7-ተቀማጭነቱ አሜሪካ ያደረገው እና ቪሌጅ ሶሊሽን የተባለ የእርዳታ ድርጅት ከአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) ጋር በመተባበር በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ዘመናዊ መንደር መገንባት የሚያስችል የመሠረት ድንጋይ አስቀመጠ።በዘመናዊ መንደር ፕሮጀክቱ በጎንደር ዙሪያ ወረዳ ደረስጌ ማሪያም ቀበሌ 100 ቤቶችን ግንባታ እንደሚያከናውንና የተሟላ የመሠረተ-ልማት ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸው የቪሌጅ ሶሊሽን ዓለማቀፍ ፕሪዝዳንት ስቴቭ ጅዋንስ ተናግረዋ።ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ 38 ሔክታር መሬት መዘጋጀቱን ታውቋል።(ዋልታ)
……………………………………………………………………
8-ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ለተሰንበት ግደይ በኔዘርላንድ በተካሄደ የ15 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር አሸናፊ ሆናለች።አስራ አምስቱን ኪሎ ሜትር ለማጠናቀቅ የፈጀባት ጊዜ 44 ደቂቃ ከ21 ሰከንድ ብቻ ሲሆን ከ2 ዓመታት በፊት ፕራግ ላይ በኬንያዊቷ አትሌት ጆይሲሊን ጄፕኮስጌይ የተመዘገበው 45 ደቂቃ ከ37 ሰከንድ የነበረውን የዓለም ፈጣን ሰዓት ከ1 ደቂቃ በላይ በሆነ ጊዜ አሻሽላለች።(ኢቢሲ)

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here