የፌደራል መንግስት እና የትግራይ ጊዜያው አስተዳደርን ያላስማሙት የወሰን እንዲሁም የምግብ እጥረት አደጋ ደረጃ 

0
481

ዛሬ በተደረገው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 14ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጡ “እስካሁን” ባለኝ መረጃ በረሃብ የሚሞት ሰው የለም፤ ያለው ችግር ከድርቅ ጋር ተያይዞ የሚመጡ በሽታዎች ናቸው፤ ይህ ከአቅም በላይ የሚሆን ነው ብለዋል። 

የኢትዮጵያ የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ ጥር 21 ቀን 2016 ባወጧቸው የተናጠል መግለጫዎች በአማራ እና ትግራይ ክልሎች እንደ ቅደም ተከተላቸው ከ370 በላይ ሰዎች እንዲሁም በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በረሃብ ስለመሞታቸው አስታውቀው ነበር። 

ለህዝብ ተወካዮች በዛሬው ዕለት ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ዘንድሮ በትግራይ የተወሰነ አካባቢ፣ በአማራ የተወሰነ አካባቢ፣ ኦሮሚያ በምስራቁም እንዲሁ ድርቅ አለ፤ ምንም ጥያቄ የለውም ድርቅ አለ” ብለው ድርቅን ግን መንግስት አላመጣውም በማለት ገልጸዋል። 

ችግኝ መትከል እና ስንዴ መትከል ምንድን ነው ብለን አሁን ድርቅ መጣ አይባልም ያሉት ዐቢይ አህመድ፤ ባለፈው ዓመት ቦረና እና ሶማሌ ክልል የተከሰቱትን ድርቆች “ተርባብርበን ሰው እንዳይሞት አድርገናል” ብለዋል። 

“ግን ድርቁን እንደፖለቲካ መሳሪያ መጠቀም አይሰራም”፤ ኢትዮጵያ በታሪኳ እንደዚህ ዓመት አምርታ አታውቅም የሚሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግስት ዝም ቢል እንኳን አርሶ አደሩ ወገኑ ሲሞት ዝም አይልም ሲሉ ተናግረዋል። 

በሌላ በኩል በዛሬው የምክር ቤት ስብሰባ የተነሳውን የአማራ እና ትግራይ ክልሎ የይገባኛል ትያቄ የሚያነሱባቸውን አካባቢዎች የተመለከተ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከሰሞኑን በመንግስት ኮምኒኬሽን አገልግሎት በተሰጠው መግለጫ የተጠቀሰውን የህዝበ ውሳኔ የመፍትሔ ሃሳብ ጠቅሰዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአማራ እና ትግራይ ክልሎች በኩል የሚነሱ የቦታ የይገባኛል ጥያቄዎች በህዝበ ዉሳኔ ሊፈቱ የሚችሉበት አማራጭ መኖሩን ገልጸው ጥያቄዎቹ “ሰላማዊ በሆነ መልኩ በንግግር እና ዉይይት እንዲሁም የህዝብን ምላሽ መሰረት ባደረገ መልኩ በህዝበ ዉሳኔ እንዲፈቱ መንግስት ፍላጎት” እንዳለዉ ለምክር ቤቱ አባላት አስረድተዋል። 

ይሁን እንጂ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር አስቀድሞ የወጣውን የመንግስት ኮምኒኬሽን አገልግሎት መግለጫ በመቃወም የትግራይ ክልልል ጊዜያው ኢስተዳደር ባወጣው መግለጫ “መንግስት የመፍትሔው አካል ከመሆን ይልቅ የችግሩ አካል ለመሆን የወሰነ ይመስላል” በማለት የህዝበ ውሳኔውን ሃሳብ እስካሁን እንዳልተስማሙበት አሳውቋል። 

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር “ከትግራይ ሉአላዊ ግዛት መረጋገጥ ጋር በተያያዘ ጉዳዩን በሪፈረንደም ለመፍታት መረዳዳት ተደርሶ ነበር” በሚል የቀረበውን መግለጫ “ፍፁም የተሳሳተ ነው” በማለትም አውግዞታል። 

መንግስት በመግለጫው “ትክክለኛ” ተፈናቃዮች ተመልሰዋል ማለቱን “እጅግ አደገኛና በጉልበት የአገሪቱን ካርታ ለመቀየር የተደረገን አውዳሚ እንቅስቃሴ ሕጋዊ ሽፋን ለመስጠት የሚያግዝ ነው” ያለው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር “ትክክለኛ ተፈናቃይ፤ ትክክለኛ ያልሆነ ተፈናቃይ በሚል መፈታት የነበረበትን ችግር የበለጠ የሚያባብስ አደገኛ ትንታኔ” ስለሆነ ተቀባይነት አይኖረውም ብሏል።

የጊዜያዊ አስተዳደሩ መግለጫ እንዳለው “ከሚልየን በላይ ቁጥር ያላቸው ተፈናቃዮች በአስከፊ ሁኔታ በሚኖሩበት፤ ለመፈናቀላቸው ምክንያት የሆኑ ጸረ ህዝብ እና ህገወጥ አስተዳዳሪዎችን መንግስት ከስልጣን ሳያነሳ ይህን መሰል መግለጫ ማውጣት ተገቢ አይደለም” ማለቱን አዲስ ማለዳ ከመግለጫው ተመልክታለች።

አዲስ ማለዳ ከሰሜኑ ጦርነት ጋር በተያያዙ ወንጀሎች በተመለከተ የፌደራል መንስግቱ “ተገቢውን እርምጃ በእርሱ በኩል” ወስዷል ሲል የመንግስት ኮምኒኬሽን አገልግሎት ማስታወቁን መዘገቧ አይዘነጋም።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here