በ3 “የትራፊክ ፖሊሶች” ድብደባ የደረሰበት ግለሰብ ቅሬታዬ መልስ አላገኘም አለ

0
1079

በጥር 1 ቀን 2016 አዲስ አበባ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ አለም ባንክ በተባለው አካባቢ ልዩ ስሙ ‘ሸማቾች’ የሚባል ቦታ ላይ የባጃጅ ሾፌር የሆነው ግርማ በቀለ በሶስት የትራፊክ ፖሊስ አባላት ድብደባ እና ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበት ለአዲስ ማለዳ ገልጿል።

ከደበድቡት በኋላ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሲወስዱት እራሱን ስቶ በመውደቁ አስፓልት ላይ ጥለውት መሄዳቸውንም ግለሰቡ ለአዲስ ማለዳ ተናግሯል። “ከዚህ በፊት ምንም አይነት የግል ጸብም ሆነ ቂም የለብንም” የሚለው ግርማ “ለምን በዚህ መንገድ ሄድክ ብለው ነው የደበደቡኝ” ብሏል። 

የደበደቡት ሦስቱም ትራፊኮች እንደሆነ ለአዲስ ማለዳ የገለጸው ቅሬታ አቅራቢ “በጭንቅላቴ እና ሆዴ አካባቢ በተደጋጋሚ ስለመቱኝ ለስድስት ሰዓታት አካላቴን ማዘዝ ተስኖኝ ፓራላይዝ ሆኜ ስታከም ቆይቻለሁ” ብሏል። “ምንም እንኳን በዚህ መንገድ እንዳትሄዱ ተብሎ የተከለከለ ነገር ባይኖርም በቦታው ትራፊኮች ሲኖሩ ዋና መንገድ ነው በማለት አያሳልፉንም” በማለትም ገልጿል። 

አሽከርካሪው ግርማ አካባቢው ወደሚገኘ የቤተል አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ሄዶ ክስ ከመሰረተ በኋላ ፖሊስ ሆስፒታል ድረስ መጥቶ ቃሉን እንደተቀበሉት እንዲሁም የምስክር ቃሎችንም የወሰዱ ቢሆንም እስካሁን “ወደ ፍርድ ቤት እንዳልተመራ እና እያጓተቱብኝ” ነው ሲል በምሬት ለአዲስ ማለዳ ተናግሯል። 

“መደብደቤ ሳያንሰኝ 6 ሺህ ብር ከሰውኛል፤ በወቅቱ ሠሌዳ ቁጥር (ታርጋ) እና መንጃ ፍቃዴን ይዘውት ነበር የሄዱት። በጥር 20 ቀን 2016 ወደ ትራፊክ ፖሊስ መምሪያ ሄጄ አማከርኳቸው፤ ሁሉም ከመሄዴ በፊት ጉዳዩን ያውቁት ስለነበር ወደ ኃላፊው ላኩኝ ሲልም ግርማ ይናገራል። 

“ኃላፊው ቀደም ብለህ ብትመጣ እዚሁ አስተዳደራዊ እርምጃ እወስድባቸው ነበር አለኝ። ከጓዶቻቸው ከተመካከሩ በኋላ ባጠፋኸው ልክ ትቀጣለህ አንተም ክስህን ቀጥል አለኝ” እንደተባለ የክሱን ወረቀት ለአዲስ ማለዳ በማሳየት አስረድቷል። በተጨማሪም “ክሱን የጻፉት እኔ በማላውቀው የትራፊክ ፖሊስ አባል (ድብደባ ካደረሱት ሦስት አባላት ውጭ የሆነ) ነው፤ ጉዳዩን ለመሸፋፈን እና ለማስቀረት የሄዱበት ርቀት እጅግ ሚስጥራዊ ነው” ብሏል።

አዲስ ማለዳ ጉዳዩን ከያዘው መርማሪ ባገኘችው መረጃ ክስ ከተመሰረተ በኋላ መረጃዎችን ተሰብስበው ለዓቃቤ ህግ መላካቸውን እና የሁሉንም ቃል መቀበላቸውን አረጋግጣለች። መርማሪው “ድብደባውን ፈጽመዋል የተባሉትንም የትራፊክ ፖሊሶች ቃላቸውን ተቀብለን በዋስ ለቀናቸዋል፤ ድብደባውን እንዳልፈጸሙም ተናግረዋል” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

በተጨማሪም ጉዳዩን ከያዘው ዓቃቤ ህግ ማወቅ እንደተቻለው የተጠናቀረ በቂ መረጃ ባለመኖሩ እና የምስክሮች ቃል መቀያየር የክሱን ሁኔታ እንዳቆየው እንዲሁም “ተከሳሾችን ሊያስቀጣ የሚችል ተጨባጭ መረጃ እንደሌለ” እና የተጓተተ ነገር የለም መባሉን አዲስ ማለዳ ተመልክታለች።

ከዚህ ቀደም በአካባቢው እንዲህ ዓይነት ድርጊት ተፈጽሞ ወደ ህግ ሳይወሰድ በእርቅ እንደተፈታ የጠቆመው ቅሬታ አቅራቢ “በትራፊክም ሆነ በፖሊስ አባላት የሚፈጸም የመብት ጥሰት እንዲሁም ህግን የማስከበር ሂደት ሊታሰብበት ይገባል” ብሏል። ፍትህ ለሁሉም በመሆኑ ሊቀጡበት ይገባል ሲልም ቅሬታውን በአጽንዖት ገልጿል። 

ከዚህ ጋር በተያያዘ ከዚህ ቀደም ህዳር 28 ቀን 2016 ኮንስታብል ማክቤል ሮባ የተባለ የአዲስ አበባ ፖሊስ አባል የሆነ ግለሰብ እስራኤል ጥላሁን የተባለ ግለሰብ ያሽከረክረው በነበረው መኪና ላይ በተኮሰው ጥይት እስራኤልን ለሞት ዳርጓል። የፖሊስ አባሉ “በተራ ግድያ ወንጀል መከሰሱ” አይዘነጋም። 

ለፍርድ ቤት “አልገደልኩም” ብሎ የእምት ክህደት ቃሉን የሰጠው ተጥርጣሪው ለየካቲት 16 ቀን 2016 ቀጠሮ ተሰጥቷል። 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here