በዓሉ ግርማ: በ40 ዓመታት ውስጥ ያልተመለሰው ጥያቄ

0
1483

የካቲት ለኢትዮጵያ ታሪካዊ ወር ነው። በ1888 ኢትዮጵያን ቅኝ ለመግዛት የመጣውን ወራሪውን የጣሊያን ጦር ቀደምቶቹ አድዋ ላይ ያሸነፉት በዚህ በያዝነው ወር፤ የካቲት 23 ቀን 1888 ነበር።

ፋሺስት ኢጣሊያ በድጋሚ ከ1927 እስከ 1933 ለአምስት ዓመታት ኢትዮጵያን በወረራ ይዞ በቆየበት ወቅት በጣሊያን ጦር ላይ ጉዳት ለማድረስ ከተደረጉ ሙከራዎች አንዱ የፋሺስቱ እንደራሴ ሮዶልፎ ግራዚያኒንን በቦምብ የመግደል ሙከራ ነው። ሙከራው ሲከሽፍ በግራዚያኒ ትዕዛዝ በሦስት ቀናት ጭፍጨፋ በአዲስ አበባ ብቻ ከ30 ሺህ በላይ ሰዎች በግፍ የተጨፈጨፉት በዚሁ ወር የካቲት 12 ቀን 1929 ነበር።

የካቲት ወር 1966 ደግሞ የትግል ችቦ የተለኮሰበት፤ አርሶ አደሮች ከባላባታዊ የጭሰኝነት ሕይወት ለመላቀቅ ያመጹበት፣ ለተመጣጣኝ ሥራ ተመጣጣኝ ክፍያ የተጠየቀበት፣ መምህራን አዲሱን የትምህርት ፖሊሲ «ሴክተር ሪቪው»ን የተቃወሙበትና በማህበራቸው ደህንነት የሞገቱበት፣ ታክሲ ነጂዎች በነዳጅ ጭማሪ ምክንያት ሥራ ያቆሙበት ነው።

እንዲሁም ሙስሊሞች የሃይማኖት እኩልነት ብለው በአደባባይ ሰልፍ የወጡበት፣ ተማሪዎችና ተራማጅ ኃይሎች “መሬት ለአራሹ” መፈክርን ከፍ አድርገው ሥር ነቀል ለውጥ የጠየቁበት እና የመጨረሻውን የሰለሞናዊው ስርወ መንግሥት ንጉሠ ነገሥት የአጼ ኃይለ ሥላሴን መንበር የነቀነቀውና ከስልጣን ያወረደው አብዮት የተቀጣጠለውም በዚሁ ወር ነበር።

ከ100 ሺህ ያላነሱ ወታደሮች በተሠዉበት የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ሻዕቢያ የነበረውን የባድመ ምሽግ ደምስሶ፣ የኢትዮጵያ ሠራዊት ድል የተቀዳጀውም በወርኃ የካቲት 1991 ነበር።

በየካቲት ወር በተለያዩ ዓመቶች ብዙ የስነ-ፅሁፍ ኮከቦች ያለፉበት እና የጠፉበት ወርም ነው። አቤ ጉበኛ የካቲት 2 ቀን፣ ስብሐት ገብረ እግዚአብሄር የካቲት 12 ቀን፣ ጸጋዬ ገብረመድኅን የካቲት 18 ቀን፣ ማሞ ውድነህ የካቲት 23 ቀን ይጠቀሳሉ።

ደራሲና ጋዜጠኛ በዓሉ ግርማ እንደወጣ ቀረ የተባለውም የካቲት 24 ቀን 1976 ነበር። በዓሉ በህይወት አለ ወይስ የለም? ካለስ የት አለ? ከሞተስ መች? የት? እንዴትና ለምን ሞተ? የሚለው ጥያቄ ዛሬም ልክ እንዳለፉት በርካታ ዓመታት እንደ አዲስ ይጠየቃል።

አንዳንዶች ይኽ ሰው “በክፍለ ዘመናችን ተንቦግቡገው ከነበሩ ጮራቸው ፈንጥቆ ወዲያው ከጠፋ ስመጥር ጸሃፍት መካከል ምናልባት ግንባር ቀደሙ ሳይሆን አይቀርም” ይላሉ።

“ይህችን ውድ የሆነች ትንሽ ቁራሽ ሕይወት እንደ አብርሃም ቤት የለኝ፣ እንደ ሙሴ መቃብሬ ላይታወቅ። መኖር – መጻፍ – ሕይወትን በተስፋ ወደፊት እየኖርኩና ወደኋላም እያስተዋልኳት” በማለት የራሱን እጣ ፋንታ የተነበየ የሚመስለው እውቁ ጋዜጠኛና ደራሲ በዓሉ ግርማ ከመኖሪያ ቤቱ እንደወጣ ቀረ ከተባለበት የካቲት 24 ቀን 1976፤ 40 ዓመታት ተቆጥረዋል።

ባለቤቱ ወይዘሮ አልማዝ አበራ በዘመነ ኢሕአዴግ ስለ ባለቤቷ ከቤት እንደወጣ መቅረት ጉዳይ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ቀርባ ምስክርነቷን እንድትሰጥ ተደርጋ ነበር። ያንን የእሷን የፍርድ ቤት የምስክርነት ቃል የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንም ካስተላለፈው  ሶስት አስርት ዓመታት  ሊቆጠሩ ነው።

ባለቤቱ የካቲት 24 ቀን 1976 ዕለት የተፈጠረውን ለከፍተኛው ፍርድ ቤት የምስክር ቃላቸውን ሲሰጡ “የካቲት 24 ቀን 1976 ቀን ላይ አስፋው ዳምጤ እቤት ስልክ ደወለ፡፡ በዓሉ ቤት አልነበረምና ስልኩን አነስቼ ያነጋገርኩት እኔ ነበርኩ፡፡ የእግዜር ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ በዓሉ እንደመጣ እዚያ ቀጠሯችን ቦታ ባስቸኳይ እንድትመጣ ብሎሃል በዪልኝ ብሎ ስልኩን ዘጋ። በዓሉ ወደ አሥራ አንድ ሰዓት ገደማ ወደ ቤት ሲመጣ መልእክቱን ነገርኩት። ወዲያው ሻወር ወስዶ ወጣና ለመሄድ ሲጣደፍ፣ እደጅ ውለህ መምጣትህ ነውና እባክህ ትንሽ እህል ብጤ ቀምሰህ ውጣ ብለው፤ አልችልም… ብርቱ ቀጠሮ አለንና ወደዚያው መፍጥን አለብኝ ብሎኝ ፈጥኖ ከቤት ወጣ” ሲሉ ገልጸዋል።

አክለውም “የማታ ማታ ወደቤት ይመለሳል ብዬ እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ ብጠብቅም የውሃ ሽታ እንደሆነ ቀረ። ቢቸግረኝ አስፋው ቤት ደወልኩ። ሚስቱ ስልኩን አነሳች። አስፋው እቤት ገብቷል? ስል ጠየቅኋት። አዎን ገብቷል አለችኝ። ይሄኔ ግራ በመጋባት፤ ባሌን ከቤት ጠርቶ ወስዶት የት ጥሎት ነው እሱ ከቤቱ የገባው? እያልኩ አፋጠጥኳት። ቀጥዬም እስኪ አቅርቢልኝና ላናግረው ስላት፤ የገባ መስሎኝ ነበር እንጂ አልገባም ብላ የመጀመሪያ ቃልዋን አጠፈችብኝ። የስልክ ንግግራችንም በዚሁ ተቋጨ። ሌሊቱንም እሱን ያየ እያልኩ በየቦታው እየደወልኩ ብጠይቅም፤ አየነው የሚል ሰው ሳላገኝ ነጋ።

“አሁንም ለክቡር ፍርድ ቤቱ አቤት የምለው፤ አስፋው ዳምጤ ባለቤቴን በዓሉ ግርማን ከቤት ጠርቶ ወስዶ የት እንዳደረሰው ቀርቦ እንዲጠየቅልኝ ነው” ሲሉም ነበር የገለጹት።

ኢሕአዴግ ሥልጣን መያዙን ተከትሎ በዘመነ ደርግ በገመድ የተገደሉ ሰዎች አጽም በጅምላ የተቀበሩበትን ጉድጓድ እያስቆፈረ አስወጥቶ በቴሌቪዥን ያሳይ ነበር። አንድ ዕለት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን መስኮት ላይ የቀረበ በፊልም የተደገፈ ዘገባ፤ አንድ አዲስ ዜና ይዞ ብቅ ብሎ የነበር ሲሆን፤ ከራስ አሥራተ ካሣ ግቢ ውስጥ ከተቆፈረ ጉድጓድ ውስጥ የእውቁ ደራሲና ጋዜጠኛ በዓሉ ግርማ አጽም መገኘቱን ገለጸ።

እንዳለ ጌታ ከበደ በ2008 ለህትመት በበቃው ‘በዓሉ ግርማ ሕይወቱና ሥራዎቹ’ በተሰኘው መጽሓፉ በዓሉ ግርማ አስራተ ካሳ ቤት ዉስጥ ሬሳው ተገኝቶ መውጣቱን ኢቲቪም ይህንን መዘገቡን ከዕዉነት የራቀ እንደሆነ መረጃዎችን ጠቅሶ አፋልሷል። ይህ በኢቲቪ የቀረበው መረጃ ለተራ የፖለቲካ ፍጆታ የዋለ እንደሆነ ባለቤቱን ጨምሮ የደራሲው እማኞችም በብርቱ ይከራከራሉ። 

ለዛም ይመስላል የጋዜጠኛና ደራሲ በዓሉ ግርማ እንደወጣ መቅረት ጥያቄ መልስ ያላገኘው፤ በተለያዩ ወቅቶች በዓሉን በተመለከቱ ጽሁፎች ስራዎች እና ጥያቄዎች ድንገት ብቅ የሚሉትም ለዚህ ነው።

ደራሲ ገነት አየለ ስለ በዓሉ መጥፋት ‘የሌተናል ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ትዝታዎች’ በሚል ርእስ ባዘጋጀቻቸው ሁለት ቅጽ መጽሃፎቿ ላይ፤ ሌተናል ኮሎኔል መንግሥቱንና ይመለከታቸዋል ያለቻቸውን የደርግ ሹማምንቶች ሁሉ አነጋግራ በመጽሐፏ ገጾች ላይ አካታዋለች።

መጽሐፏ ሁለት ቅጾች ያሉት ሲሆን የመጀመሪያው በ1994 ፣ ሁለተኛው ደግሞ 2002 ለህትመት የበቁ ሲሆን፤ ስለ በዓሉ ግርማ ከጠየቀቻቸው የደርግ ባለስልጣን መካከል ሌተናል ኮሎኔል መንግሥቱ  ኃይለ ማርያም፣ ጓድ ቁጥር 53 ብላ የሰየመቻቸው የደርግ ባለስልጣን እንዲሁም ኮሎኔል ተስፋዬ ወልደስላሴ  ይገኙባቸዋል።

ደራሲ ገነት አየለ ጠበቅ ብላ ስለ በዓሉ ግርማ ጉዳይ በስፋት ያነሳችበትና ያጠያየቀችበት መጽሐፏ የመጀመሪያው ቅጽ ሲሆን መጽሐፏ ላይ ለሌተናል ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም፣ ካነሳችላቸው ጥያቄዎች መካከል “እውቁ ጋዜጠኛ በዓሉ ግርማ ከቤቱ እንደወጣ የት እንደደረሰ ሳይታወቅ ቀርቷል። ከጠፋ ከጥቂት ቀናት በኋላ መኪናው መንገድ ላይ ቆማ ተገኝታለች። ‘ኦሮማይ’ በተባለው መጽሐፉ የተነሳ እንደተገደለ ይገመታል። ስለዚህ ምን ይላሉ?” የሚል ነበር።

ሌተናል ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም “በዓሉ ግርማን የማውቀው ከአብዮቱ በፊት ነበር። እኔ ከአሜሪካን አገር እንደመጣሁ ወደ ሐረር ከመሄዴ በፊት ለጥቂት ቀናት አዲስ አበባ አንድ ሆቴል ውስጥ አርፌ ነበር። እዛ ሆቴል ሙዚቀኛዋ ብዙነሽ በቀለ ቡና ለመጠጣት ጎራ ትላለች የሚያውቋት ሰዎች ዝፈኝልን ይሏታል። እሷም ስትዘፍን ለማዳመጥ እንሰበሰባለን፤ እዛ ቦታ ነው በዓሉ፣ ብዙነሽ በቀለ እና እኔ የተዋወቅነው ይላሉ”።

ኮሎኔሉ አክለውም “ለማስታወቂያ ሚኒስትር በመጀመሪያዎቹ ወራት ሰው ለማግኘት ተቸግረን ነበር። ስለሆነም በዓሉን ስንመርጠው ያኔ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ጓድ ግርማ ነበር። ፖለቲካውን በተመለከተ ሚኒስቴሩ ይቆጣጠራል በዓሉ በሱ ስር ሆኖ ይረዳዋል ብለን ሾምነው። ችግር የመጣው በቀይ ኮከብ ዘመቻ ጊዜ ነበር። በዘመቻው በዓሉ በሽመልስ ማዘንጊያ ስር ሆኖ ጋዜጠኞችን እንዲያስተባር እና የፕሮፖጋንዳ ስራዎችን እንዲሰራ አስመራ ከእኛ ጋር ተንቀሳቀሰ፤ የተሰጠውን የስራ መመሪያ በእጄ ጽፌ ያረቀቁት እኔ ነኝ። ይኼም ምንድነው የመንግስት ፖሊሲና የፖለቲካው አካሄድ በተመለከተ ከሽመልስ ማዘንጊያ እየተቀበለ እንዲሰራ ጋዜጠኞች እንዲያሰማራ ለነሱ የሚያስፈልግ ሎጂስቲክ የገንዘብ እና የቴክኒክ ድጋፍ እየተከታተለ እንዲሰጥ የሚል ነው” ሲሉ አብራርተዋል።

ኮሎኔል መንግስቱ እና በዓሉ የተለየ ቀረቤታ እንዳላቸው በተደጋጋሚ የሚነሳ ሲሆን፤  ለዚም ማሳያ ደግሞ ስብሃት ገብረእግዚብሔር የሚከተለውን ጽፏል፤ “የዚያድ ባሬን ወራሪ ሠራዊት የእኛ ሠራዊት እየነዳው ሄዶ ጅጅጋ ገባ። ትልቅ ድል ነበር ጓድ ሊቀ መንበር ለበዓሉ የምስራቹን በስልክ ነገሩትና በመገናኛ ብዙሃን የሚነበብ ጽሑፍ እንዲያዘጋጅ አዘዙት። ጻፈና አነበበላቸው። 

“ጓድ በዓሉ! ባንዲራችን ካራማራ ተራር አናቱ ላይ ተተክላ ትውለበለባለች ብለሃል። እኛኮ የተከልናት ታች ጂጂጋ ውስጥ አሉት። በዓሉም ጓድ ሊቀ መንበር ለእኔ የታየችኝ ተራራው ላይ ነው። አናውርዳት። እዚያው እኔ የተከልኳት ቦታ ትውለብለብ። እሺ! እዚያው ትሁንልህ! አሉ ጓድ ሊቀ መንበር እየሳቁ”።

በዚህ መሃል ደራሲዋ ገነት አየለ ሌላ ጥያቄ ታቀርባለች፤ “ስለዚህ እርስዎ ቀይ ኮከብን በተመለከተ በዓሉ ግርማን መጽሓፍ ጻፍ ብለውታል የሚባለው እውነት ነዋ?”። “አላልኩትም፡፡ እሱ የፕሮፓጋንዳውና የሥነ ጽሑፍ ዘመቻው አካል ነው እንጂ በግሉ እንዲጽፍ የታዘዘው አንድም ነገር የለም። ‘ኦሮማይ’ን ጻፈ፡፡ መጽሐፉን ጽፎ ሲጨርስ ሊያሳትም ሄደ በዓሉ ለሚመለከተው ሁሉ አሳይቷል፡፡ አልፎልኛል ብሎ አሳተመ፡፡ ተሰራጨ። መጽሐፉን አምጡልኝ አልኩ፡፡ አንድ ሳምንት ፈጀብኘ፡፡ ማታ ማታ ነው የማነበው፡፡ ጭቅጭቅ እንዳስነሳ ስለተነገረኝ በደንብ አድርጌ አንብቤ ጨረስኩት፡፡ እኔን እንዳውም አመሰገነኝ እንጂ አልነቀፈኝም። ሌሎች ብዙ የተበሳጩ ሰዎች ነበሩ። ምክንያታቸው ግን ይለያያል” አሉ።

አንድ ቀን በዓሉ ለቀይ ኮከብ ዘመቻ አስመራ በነበረበት ወቅት አስፋው ዳምጤ ቢሮ ደወለ “አንድ ኖቭል ጀምሬያለው እኮ!” አለው። ዘመቻው ሙሉ ጊዜ የሚወስድ እረፍትና እንቅልፍ የሚነሳ በመሆኑ ተገርሞ “ከመቼው?” ብሎ ይጠይቀዋል። በዓሉ ግርማም “ታውቅ የለ እኔ የምጽፈው ውጥረት ውስጥ ስሆን ነው። ሥራ ሲደራረብብኝ ጻፍ ጻፍ የሚለኝ ስሜት ከውጥረቱ ጋር ተያይዞ ይመጣል” ብሎ መለስለት።

ከሳምንታት በኃላም ልብወለዱን ጨረስኩት ብሎ እንደደወለለት እና “አልቋል። ተፈጽሟል። ኦሮማይ!” ማለቱን አስፋው ዳምጤ ገልጿል።

እዚህ ላይ ስብሃት ገብረእግዜብሄር የሰጠውን ምስክርነት ማንሳት ተገቢ ይሆናል- “በዓሉ ችኩል ጸሐፊ ነው። ሲጽፍ ይቸኩላል። እንደ ሌሎቹ ደራሲያን ረጋ ብሎ የመጻፍ መልሶ መላልሶ የማየትና የማረም ትዕግስት ቢኖረው ኖሮ ድርሰቶቹ የትናየት በደረሱ ነበር። ግን ችኩል ነው። ለዚህ የሚዳርገው የጋዜጠኝነት ሙያው ይመስለኛል። ሲጽፍ እንደ ጋዜጣ ጽሑፍ ጫር ጫር ነው የሚያደርገው። እንደዚያም ሆኖ ግን ድርሰቶቹ ማንም እንደሚመሰክርላቸው ለአድናቆት የበቁ ናቸው”።

ኮሎኔሉ ከመነሻው ጥያቄ እየራቁ ተጨማሪ ሶስት ገጾችን ከተጓዙ በኃላ፤ ረቂቁን እንዲያዩ አስቀድሞ በበዓሉ በራሱ ቀርቦላቸው ባለመመቸት ምክንያት ለማንበብ ባለመቻላቸው፤ ሻምበል ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስ፣ እራሱን በዓሉ ግርማንና በኋላም የደህንነቱን ሚኒስትር ኮሎኔል ተስፋዬ ወልደ ሥላሴን ጠርተው በየተራ ማነጋገራቸውን ይገልጻሉ።

በዓሉን ባነጋገሩበት ሰዓትም “አብዮቱን ለመጉዳት የሠራኸው አለመሆኑን እረዳለሁ፡፡ ይሁን እንጂ አሁን ባለህበት ኃላፊነት ቦታ የምትቆይበት ሁኔታ ሊኖር አይችልም።ለማንኛውም አሁን ወደ ቤትህ ሂድ ብዬ አሰናበትኩት” ይላሉ። እንዲሁም ከስራ የተሰናበተበት ደብዳቤ እንደተሰጠው ያነሳሉ።

ኮሎኔሉ በዓሉን ካነጋገሩት በኃላ በዓሉ ምን አለ? ምንስ ብሎ ተናገረ የሚለውን ደራሲ እንዳለጌታ ከበደ ‘በዓሉ ግርማ ሕይወቱና ሥራዎቹ’ በተሰኘው በዓሉ ዙሪያ በርካታ አሰሳዎችን አድርጎ ባሰናዳው መጽሃፉ የበዓሉ ግርማ ባለቤት፣ በወቅቱ አብረውት ይሰሩ የነበሩ ባልደረባዎቹና የቅርብ ጓደኛው የሆነው አስፋው ዳምጤን አናግሮ ይኼን አስፍሯል።

በወቅቱ በገጽታው ላይ ምንም አይነት የማዘን፣ የመናደድ አልያም የጸጸት ስሜት ያልነበረበት ሲሆን “እኔ የታየኝን እና ያመንኩበትን ጽፌያለው” በማለት የሚደርስበትን ለመቀበል ዝግጁ መሆኑ ለኮሎኔል መንግስቱ መግለጹን ያሳያል።

ቀጥሎም ኮሎኔሉ በዓሉ በሙያዬ በግሌ ብሰራ ይሻለኛል ማለቱን በመጥቀስ “ፍላጎትህ ይኽ ከሆነ በግልህ ብትሰማራ የሚከለክልህ የለም ተባለ። በዚህ አይነት በእኛና በሱ መሀል የነበረው የሥራ ግንኙነት ተቋረጠ” ይላሉ።

እንዳለ ጌታ ከበደ በመጽሓፉ የበዓሉ ባለቤት አልማዝ ከስራ ከተሰናበተ በኃላ ያለውን ጊዜ ሲያስታውሱ “ይከታተሉት ነበር። እቤት ከዋለ ጀምሮ በቀን ሶስት ፈረቃ እየተቀያየሩ የቤታችንን ዙሪያ ይጠብቁታል። አየህ በዓሉ! እነዚህ ሰዎች ይከታተሉሀል ስለው፤ እኔን ምን አድርግ ይሉኛል? ከሚያስጨንቀኝ ሃሳብ ለመከላከል ጽፌያለው።  አሁን የምፈልገው በሰላም መኖር ነው። እኔ ረስቻቸዋለው ለምን አይረሱኝም? ይላል። የሚፈልገውን ሰላም ሊያገኝ አልቻለም። ክትትላቸው እየጠበቀ ሄደ” ይላሉ።

የካቲት 24፣ የካቲት 7 ወይንም የካቲት 8 ቀን 1976 (በዓሉ ከቤት እንደወጣ ቀረ በሚል ሶስት ቀናቶች ይጠቀሳሉ)፤ ሆኖም ግን በወርሃ የካቲት እንደወጣ ቀረ። ባለቤቱ አልማዝም “ሲነጋጋ ለሻለቃ መንግስቱ ገመቹ (የጓድ መንግስቱ  ጸሐፊ) ስልክ ደወልኩላቸው። እንኳን እሱ እራሴ ያለሁት በክትትል ስለሆነ መንግስት ነው ያስቀረብኝ እባክዎን የት እንደወሰዱት ጠቁሙኝ ብዬ አለቀስኩ። በኃላም በፍጹም እዚህ የለም! አሉኝ” ሲሉ ገልጸዋል።

የበዓሉ ግርማ ‘ኦሮማይ’ በመጀመሪያ ብዙዎችን ባስገረመ መልኩ ለህትመት በቃ በኃላም እንዳይሸጥ ታገደ፣ መጽሃፍቶቹ ካሉበት ተሰብስበው ተቃጠሉ፣ ከሥራውም ታገደ ከሥራው ከታገደ ከስድስት ወራት በኃላ ደግሞ ከቤቱ እንደወጣ ቀረ።

“ትንሽ ቆይቶ በዓሉ ግርማ ጠፋ የሚል ወሬ ተነገረኝ። ወዴት ነው የሄደው ስል እኛ አናውቅም አሉኝ። በራሴ መንገድ ለማጣራት ሞከርኩ፡፡ የምጠይቃቸው ሁሉ ሰውዬው ብዙ ጠላቶች አፍርቷል፡፡ በትክክል ስለሆነው ነገር የምናውቀው ነገር የለም፡፡ የየራሳችን ጥርጣሬ አለን፡፡ የተጨበጠ መረጃ ግን የለንም የሚል መልስ ነው የሚሰጡኝ፡፡ ምን ማድረግ ይቻላል? ከዚያ በኋላ በከተማ ውስጥም በዓሉ ተገድሏል በማለት መወራቱ ቀጠለ፡፡ ህይወትም ቀጠለ ስራም ቀጠለ። አሁን ከምወንጃጀልበት አንዱ የበዓሉ ሞት ነው” ሲሉ ጓድ ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማሪያም መልሳቸውን ደምድመዋል።

ሆኖም ግን በዛው መጽሃፍ ዙሪያ በተሰጡ በርካታ ሃሳቦች ኮሎኔል መንግስቱ ሳያውቁ አንድም ባለስልጣን በራሱ ፈቃድ አንድን ሰው አይገድልም፤ አያስገድልም በማለት በእውነቱ ስለ በዓሉ ግርማ አሟሟት ሳያውቁ ቀርተው ነው ማለት እንደሚቸግራቸው ይገለጻል። አልማዝ አበራ ለፍርድ ቤት እንዲሁም በሌላ ጊዜ በሰጡት ቃለ መጠይቅ አስፋው ዳምጤ ደውሎ የቀጠሯችን ቦታ እንገናኝ ማለቱን በማንሳት “አስፋው ዳምጤ ይጠየቅልኝ” በማለት ላነሱት ጥያቄ፤ አስፋው ዳምጤ “ከሺ ሀሰት አንዲት እውነት ትልቃለች” በሚል በሰጠው ርዕስ “የሆነው ሆኖ ግን የዚያን ዕለት ወደ ቤቱ አልሄድኩም፤ ስልክ ደውዬም እፈልገዋለው ብዬ እሷ ዘንድ መልዕክት አላስቀመጥኩም” ሲል የአልማዝን ሃሳብ ይቃረናል።

ከጥቂት ዓመታት በፊት ደራሲና ጋዜጠኛ አበራ ለማ ‘የማይጮኹት በዓሉ ግርማን የበሉት ጅቦች’ በተሰኘው የምርመራ ጦማራቸው የተለያዩ ግለሰቦችን በማንሳት ምላሽ እንዲሰጡና እንዲጠየቁ ካነሷቸው በርካታ ሰዎች መካከል ኮሎኔል መንግስቱ፣ ኮሎኔል ተስፋዬ እና አስፋው ዳምጤ ቀዳሚ ናቸው። እኚው ጋዜጠኛና ደራሲ በጽሑፋቸውም ወይዘሮ አልማዝ በቁጭት ከሚያነሷቸው የአስፋው ዳምጤ ጉዳይ አንዱ፣ ያ ቤተኛ የነበረ ሰው፤ ባለቤታቸው ከታፈነበት እለት ጀምሮ ወደ ቤታቸው ብቅ ብሎ ወይም ስልክ ደውሎ የማያውቅ የመሆኑ ጉዳይ ዋናው ነው፡፡ 

ሆኖም ግን በዚያኑ በዓሉ ግርማ እንደወጣ በቀረበት ሰሞን፣ ከገንዘብ ሚኒስቴር ቋሚ ተጠሪነት ሥራው ተባሮና ለዓመታት ቦዝኖ የነበረው አስፋው ዳምጤ፤ የኩራዝ አሳታሚ ደርጅት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ሁኖ በድንገት በደርግ የመሾሙ ጉዳይ ጥያቄ ማስነሳቱን ይገልጻሉ። የዚህ ሹመት አንድምታው ከበዓሉ ግርማ ሰለባነት ጋር ተዛምዶ፤ በዘመኑ በነበሩ የቅርብ ታዛቢዎች ዘንድ ብዙ ያነጋገረ ጉዳይ እንደነበር በርካቶች ያወሳሉ። 

በአንጻሩ እንዳለጌታ ከበደ መጽሃፍ ውስጥ የስራው ዕድል ቀደም ብሎ የነበረ በወቅቱ መሳካቱን በመግለጽ ከበዓሉ ሞት ጋር መግጠሙ ተጠቅሷል።

እንዲሁም ደራሲ አበራ ለማ በአንድ ወቅት አስፋው ዳምጤ ስለሰጠው ቃለ መጠይቅ አስተያየታቸውን ሲሰጡ “ወዳጅን በግፍ ካለፈ ከ30 ዓመት በኃላ መቃብር ውስጥ አላስተኛ ያለው አጽምን የሚያጎሳቁል ወዳጅ ነኝ የሚል ሰው ነው ሲሉ” ተችተውታል።

ደራሲ ገነት አየለ በዚሁ የሌተናል ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ትዝታዎች፣ ቅጽ አንድ መጽሃፏ የበዓሉን መጨረሻ ለማወቅ ከጠየቀቻቸው ሰዎች መካከል የደህንነት ሚኒስትሩ ኮሎኔል ተስፋዬ ወልደሥላሴ ሲሆኑ “በዓሉ ግርማ እንዴት እንደተገደለ ያውቃሉ?” የሚል ቀጥተኛ ጥያቄ አቅርባላቸው ነበር።

ኮሎኔሉ “በዓሉ ግርማ በጻፈው መጽሐፍ በኦሮማይ የተነሳ ችግር ሲገጥመው እኔጋ መጣና አነጋገረኝ። ሊቀ መንበሩ ሊረዱልኝ ያልቻሉት ምክንያት አልገባኝም። ጥርስ ተነክሶብኛልና እባክዎን አስረዱልኝ ብሎ ጠየቀኝ። እኔ በእውነቱ እሱ እዚያው አጠገቤ እንደቆመ የሊቀ መንበሩ ረዳት ለሆነው ለሻምበል መንግሥቱ ገመቹ ስልክ ደወልኩ። እባክህን የዚህን ሰው ነገር ለሊቀ መንበሩ አጣመው ያቀረቡላቸው ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ። እንዴት ነው ይሄን ነገር ግልጽ የምታደርግላቸው? ወይም የሚቻል እንደሆነ ሁለታችንም ቀርበን እናስረዳ። አንተ ጋር ልኬዋለሁ የምትችለውን አድርግልት አልኩት። ግድ የለም ይላኩት፤ እኔ አነጋግረዋለሁ። ይሄ ምንም አይደለም አለኝ። ከዚያ ወደዚያው ላኩት። ሌላ ጊዜ ቆይቼ የበዓሉ ነገር እንዴት ሆነ? ብዬ ሻምበል መንግሥቱን ጠየቅሁት። አስረድቻቸዋለሁ፤ ግን እንዴት እንደሆን እንጃ ለጊዜው መለስም አላሉም አለኝ። አይ ይሄ የእሳቸው የተለመደ ባሕሪ ነው። አዝማሚያው መልካም ሲሆን፤ ነገሩን በጽሞና አስረዳቸው አልኩት። በመጨረሻ ንግግራቸውም ከዚያ ውጪ በእኛ መስሪያ ቤት በኩል የምናውቀው ነገር የለም። ዛሬ ምስክሮች ሲናገሩ ሰምተናል። በምንም አይነት እኛ ጋር አልታሰረም። እኔ ምንም የሰማሁት ነገር የለም። እኔን ደግሞ በግሌ በዓሉ ምንም ያደረገኝ ነገር የለም። ሆኖም ግን ያስገደልከው አንተ ነህ ይሉኛል። እኔ በዓሉን የማስገድልበት ምክንያት የለኝም” ሲሉ ጉዳዩን ዘግተውታል።

በተቃራኒው ደራሲ አበራ ለማ ኮሎኔል ተስፋዬ ለደራሲዋ የሰጡት “ችግር ሲገጥመው እኔጋ መጣና አነጋገረኝ” የሚለው ቃል ሀሰተኛ ነው ሲሉ ይወነጅላሉ። ለዚህም ማሳያ “የደራሲ በዓሉ ግርማ የበኩር ልጅ መስከረም በዓሉ በላከችልኝ የኢሜል መልእክት ላይ በእጅጉ ኮንናዋለች፡፡ ቅጥፈት ነውም ትላለች” ሲሉ የኢሜል መልዕክቱን ለማስረጃነት አስፍረዋል።

ደራሲ ገነት በዛው መጽሃፏ ‘ጓድ ቁጥር 53’ ብላ የሰየመቻቸው የደርግ ባለስልጣን “ስለ በዓሉ ግርማና ስለ ጄኔራል ታሪኩ ዓይኔ አሟሟት የማውቀውን ልንገርሽ” ብለው “መንግስቱ በዓሉ ግርማን ስለ ቀይ ኮከብ መጽሐፍ እንዲጽፍ ይጠይቀዋል። ራሱ ጻፍ ማለቱን ማንም ሰው አያውቅም። መንግስቱ ከሲዳሞ ጉብኝት ሲመለስ ‘ኦሮማይን’ እያነበበ ነው የመጣው። አጻጻፉ ብዙ በስልጣን ላይ ያሉ ሰዎችን ስለሚነካካ ብዙ ሰዎችን አስቆጥቷል። ስለመጽሃፏ አስተያየት እንድሰጠው ሲጠይቀኝ እነዚህን ሰዎች መንካት አልነበረብህም” አልኩት ይላሉ።

አክለውም “በእኔ አስተያየት ሰውየው ክፉ ነገር እንዲደርስበት ጠምጥመው ከመንግስቱ ጥርስ ውስጥ ያስገቡት ሸመልስ ማዘንጊያና ተስፋዬ ወልደሥላሴ ናቸው። ሌሎችም ተረባርበዋል። ተስፋዬ ወልደስላሴ በመንግስቱ ታዞ ነው ያስገደለው። እንዲገደል ትዕዛዙን የሰጠው ግን መንግስቱ ነው። ተስፋዬ አስፈጻሚ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።

ከጓድ ቁጥር 53 ምላሽ መረዳት እንደሚቻለው ኮሎኔል መንግስቱና ኮሎኔል ተስፋዬ የሰጡትን ሃሳብ የሚጻረር ይሆናል። ከዚህም በመነሻነት ኮሎኔል መንግስቱ መጽሃፍ ጻፍ አላልኩትም ቢሉም ጓድ ቁጥር 53 ግን “መንግስቱ በዓሉ ግርማን ስለ ቀይ ኮከብ መጽሐፉ እንዲጽፍ ይጠይቀዋል። ራሱ ጻፍ ማለቱን ማንም ሰው አያውቅም” ሲሉ ንግግራቸውን ያፋልሳሉ።

እንዲሁም ሁለቱ ሰዎች ከበዓሉ ግርማ ሞት ጋር በተያያዘ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚያገናኛቸው ነገር እንደሌለ ቢገልጹም ጓድ ቁጥር 53 ግን ሁለቱንም በቀጥታ ተጠያቂ አድርገዋቸዋል።

እንዳለ ጌታ ከበደ በመጽሃፉ አንድ ያልተሰማ ነገር ይዞ ብቅ ብሎ ነበር። ይኼውም፤ ከ1968 ጀምሮ በደርግ ምርመራ ክፍል በሾፌርነት ይሰራ የነበረ ተረፈ ዘመድ አገኘሁ የተባለ ግለሰብ መጋቢት 1 ቀን 1989 ለከፍተኛ ፍርድ ቤት “በዚህ ጊዜ አሮጌ አውሮፕላን ማረፊያ አካባቢ ቤርሙዳ ከተባለው እስር ቤት አንድ እስረኛ ሶስት ጊዜ አመላልሻለው። ሁለት ጊዜ ተሸፍኖ ስለነበር ማንነቱን አልለየሁትም ነበር። በሶስተኛው ጊዜ ግን ተገልጦ ስላየሁት አውቄዋለው” ይላል።

አክሎም “ይህ ሰው ማስታወቂያ ሚኒስቴር ይሰራ የነበረ እኛ ሰፈር እየመጣ ሲዝናና አየው የነበረ ታዋቂ ሰው ነበር። መጽሓፍም ይጽፋል። በደህናው ጊዜ እንደማውቀው አልነበረም። በድብደባ ብዛት ሳይሆን አይቀርም። መልኩ ቀይ ሆኖ መካከለኛ ቁመናና ደልደል ያለ ሰውነት የነበረው ሰው በጣም ተጎሳቁሎ ነበር። ከዚያ ወዲህ አግኝቼው አላውቅም” ሲል መስክሯል። ይኽ የተገለጸው ሰው በዓሉ ግርማ ነበር።

ቤርሙዳ እስር ቤት አደገኛ ፖለቲከኞች የሚታጎሩበት፣ ሞታቸውን እንዲመኙ የሚደረግበት የትኛውም የአብዮቱ ተቃዋሚ ነው ተብሎ የታሰበ ጭምር የሚጋዝበት ስፍራ ነው። የምስክር ቃል የተቀበለው ፍርድ ቤት በአንጻሩ ተበዳዩ (በዓሉ) መታየት ካቆመበት ጊዜ በኃላ ምን እንደሆነ ወይንም በምን ምክንያት እንደጠፋ ማረጋገጥ አለመቻሉን ገልጾ፤ በዚህ ወንጀል የተከሰሱ ተከሳሾች በነጻ ሊሰናበቱ ይገባል ሲል ወስኗል።

በዓሉ ግርማ በቤርሙዳ እስር ቤት እንደተመለከተው ምስክር ከሆነው ከተረፈ ዘመድ በተጨማሪ በማስታወቂያና መርሐ ብሔር ሚኒስቴር የአብዮታዊት ኢትዮጵያ ድምጽ ቴክኒሽያን የነበረው ኪሮስ ወልደሚካኤል በዓሉ በቤርሙዳ እስር ቤት እንደተመለከተው ገልጿል።

በዓሉ ከጠፋ ከወር በኃላ እሱን እንዳሰሩት የገለጸው ኪሮስ “አንድ ቀን ዓይኔ በጨርቅ ታስሮ ጊቢ ውስጥ ተቀምጫለው። ኮቴዎች ብቻ ሳይሆን ድምጽም ተሰማኝ። የሚያወራውን ለየሁት ሃኪማችን ነው። በዓሉ ግርማ አሁን ምንህን ነው የሚያምህ? ሲለው ሰማሁ። ደነገጥኩ። በዓሉ እዚ ነው እንዴ ያለው? አልኩ። ከአገር ጠፍቷል፤ ተግድሏል የሚባለው ነገር ውሸት መሆኑ አወቅኹ። በዓሉም እየመለሰለት በአጠገቤ አለፉ፤ አላስችል አለኝና ቀስ ብዬ ባልታሰረ እጄ ዓይኔ ላይ የተጋረደውን ጥቁር ጨርቅ ገለጥ አድርጌ አየኋቸው። ራሱ ነው፤ በዓሉ!”።

በዚህ መጽሃፍ በተደረጉ በርካታ ቃለ መጠይቆች አብዛኛዎቹ ሌሎች በርካታ የደርግ ሹማምንት ጨምሮ በበዓሉ መጥፋትና ግድያ ላይ ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማሪያም እና ኮሎኔል ተስፋዬ ወልደስላሴ ድርሻ እንዳላቸው የሚጠቁሙ ነበሩ። ታድያ በዘመነ ኢህዴግ በእስር ቤት የነበሩት ኮሎኔል ተስፋዬ ወልደስላሴ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በወቅቱ ለታራሚዎች ኃይማኖታዊ አገልግሎት በሚሰጡበት ወቅት አንዴ፤ በዓሉ የት እንደገባ እና የገባበት ከሚያውቁት ሰዎች መካከል አንድ እርሳቸው መሆናቸው እንደሚወራ ጠይቋቸው ነበር።

ኮሎኔሉም በቀጥታ ምላሽ ከመስጠት ባሻገር “ከዚህ እንደወጣሁ በምጽፈው መጽሃፍ ላይ መልሱን ታነበዋለህ” ነበር ያሉት። ነገር ግን ኮሎኔሉ በይደር ያቆዩትን እውነት ሳይጽፉ አልፈዋል።

እንዳለጌታ በመጽሃፉ የበዓሉን አጽም ሊገኙ የሚችሉባቸውን ቦታዎች ጠቁሞ ያን ማድረግ ለሚችል ወይም ለሚፈልግ አካል ክፍት አድርጎት አልፏል በዚህም፤ ጴጥሮስ ወጳውሎስ ቤተ ክርስቲያንና ኮተቤ የትምህርት ማዕከልን ጠቁሟል። እንዲሁም በመጨረሻዎቹ ገጾች ለኮሎኔል አርጋው የቅርብ ቤተሰብ የሆነ ሰው የኮሎኔሉ ባለቤት እሱ ካረፈ በኃላ በተደጋጋሚ አንድ መናገር የምትፈልገው ጉዳይ እንዳለ እና <<ጋዜጠኞች ጥሩልኝ እስከ መቼ በሌላ ሰው ላይ ጣት ይቀሰራል>> በማለት ትወተውት እንደነበር ገልጿል።

ይኽች ሴት ካለፈች በኃላም ይኽ የቅርብ ቤተሰብ ልትናገረው የፈለገችውን ጉዳይ እንዲህ ነበር የገለጸው “ማታ ነው። ኮሎኔል አርጋው እሸቴ የሳሎኑን በር ከፍቶ ገባ። ሳሎን ተቀምጣ የነበረች ሚስቱ በፊቱ ላይ ያልተለመደ ደስተኝነት አየችበት። ከዚያም የጓድ መንግስቱ ኃይለማርያምን ዓይነት የሚመስላትን ድፍረት ለብሶ፣ የጓድ መንግስቱ ኃይለማርያምን እብደት ይዞ፣ በጥቁረትም፣ በእጥረትም የእሳቸውን ዓይነት ገጽታ ወርሶ በድል አድራጊነት ድምጽ አንዳች አስደንጋጭ ነገር ነገራት።”

“ያንን! በዓሉ ግርማ የተባለውን ሰው ጨርሼው መጣሁ!”

ደራሲ በዓሉ ግርማ በመስከረም 1931 በዚሁ ክፍለ ሃገር በሱጴ ቦሩ ወረዳ ተወለደ፡፡ እናቱ የኢሉባቦር ተወላጇ ያደኔ ዳባ ሲሆኑ፣ አባቱ ደሞ የጉጅራት ሕንዱ ተወላጅ ”ባቡ” ወይም ”ጀርማንዳስ” ይባሉ የነበሩት አናጺ ናቸው፡፡

‘ግርማ’ የሚለው ያባት መጠሪያ ስም የሕንዳዊው አባቱ ጓደኛ የነበሩት ያሳዳጊው ግርማ ወልዴ ስም ነው፡፡ በዓሉ ወደ አዲስ አበባ መጥቶ ግርማ ጋር መኖር የጀመረው የዘጠኝ ዓመት ልጅ ሳለ ነበር፡፡ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በልዕልት ዘነበ ወርቅ፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በጄኔራል ዊንጌት ትምህርት ቤት አጠናቋል፡፡

ከዚያም በ1951 ወደ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ በመግባት፤ በፖለቲካል ሳይንስና በጋዜጠኝነት የመጀመሪያ ዲግሪውን ተቀብሏል፡፡ በዚህ ዩኒቨርስቲ ቆይታው ወቅት በተማሪዎች ማኅበር ውስጥ ንቁ ተሳታፊ ከመሆኑም በላይ፤ “VIEWS AND NEWS” የሚሰኝ መጽሔት አዘጋጅ ነበር፡፡

በዚሁ የትምህርት ሕይወቱ ዘመን ውስጥ እያለ፤ ለኢትዮጵያን ሄራልድና ለኢትዮጵያ ሬዲዮ በፍሪላንስ ጋዜጠኝነት ያገለግል እንደነበር ሰነዶች ያመለክታሉ፡፡

በዓሉ የማስተርሰ ድግሪውን ፖለቲካል ሳይንስና ጋዜጠኝነት ያገኘው በአሜሪካን አገር ከሚገኘው ከሚቺጋን እስቴት ዩኒቨርስቲ ነው፡፡ ከአሜሪካ መልስ በማስታወቂያ ሚኒስቴር ተቀጥሮ ከያኔው ኢትዮጵያ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅነት ጀምሮ እስከ ቋሚ ተጠሪነት ደርጃ ድረስ ተጉዟል።

በዚህም የሥራ ዓለም ሕይወቱ ሁሉ ከጋዜጠኝነትና ከደራሲነት ዓለም ሳይወጣ መኖሩን የሕይወት ታሪክ መዛግብቱ ያመለክታሉ፡፡ “በጋዜጠኝነት የጀመረውን ሙያዊ ተልእኮውን ወደ ፈጠራ ደራሲነት የላቀ ደረጃ አሳድጎ የየአገሩን የአማርኛ ስነ ጽሁፍ ደረጃ ከፍ በማድረግ፤ ካድርባይ ብእር ነጭ ወረቀት ይሻላል ያለውን ቃሉን ጠብቆ በአርአያነት አልፏል” ሲሉ ይመሰክራሉ።

ከአድማስ ባሻገር፣ ሀዲስ፣ የሕሊና ደወል፣ የቀይ ኮከብ ጥሪ፣ ደራሲው ለመጥፋቱና መሞቱ ምክንያት የሆነው ኦሮማይን መሰል ዘመን ተሻጋሪ ስራዎችን አበርክቷል።

ጓድ መንግስቱ አገር ለቀው ከመጥፋታቸው ጥቂት ሳምንት ቀደም ብሎ “የትም መቼም የተወሰዱ ብዙ እርምጃዎች አሉ። አንዳንዶቹ እንደ ታሪክ ለምጽ የሚታዩ” ብለው ነበር። ይኼንን ሲሉ ምናልባት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የሞት ፍርድ እንዲፈረዱባቸው የወሰኑባቸው ሰዎች፤ ምናልባትም በዓሉም በአዕምሯቸው መጥቶ ይሆን?

በዓሉ ግርማ ከቤቱ እንደወጣ ከቀረ ዛሬ አራት አስርት ዓመታት ተቆጥረዋል፤ ነገር ግን አሁንም በዓሉ በመጨረሻ የት ነበር? በእሱ መጥፋት ላይ እጃቸው ያለው እነማን ናቸው? የትስ ነው የተቀበረው? የሚሉት ጥያቄዎች ዛሬም መልስ አላገኙም። ምናልባት በወቅቱ በበዓሉ ግርማ ዙሪያ የነበሩ ግለሰቦችና ለመጥፋቱ በቀጥታ ኃላፊነቱን የሚወስዱ አካላት በርካቶቹ በህይወት የሉም ጥቂቶቹም  የዕድሜያቸው ማምሻ ላይ ይገኛሉ። ጥያቄውን ይዘውት ያልፉ ይሆን ወይስ መቋጫውን ይሰጣሉ??

            ኦሮማይ

እንባ እንባ ይለኛል

  ይተናነቀኛል

ግን እንባ ከየት አባቱ

     ደርቋል ከረጢቱ

ሳቅ ሳቅም ይለኛል

ስቆ ላይስቅ ጥርሴ

ስቃ እያለቀሰች

     መከረኛ ነፍሴ።

ጀምበሯ ለመጥለቅ አቆልቁላለች። አድማሱ ቀልቷል። ቀለበቷን በጫማው ረግጦ ለጋት። እንደ እውነቱ ከሆነ ቀለበቷን አልነበረም በጫማው ረግጦ የለጋው የገዛ ህይወቱን ነበር እንጂ። ቻው ፊያሜታ አለ በልቡ። መቃብሯ ጸጥ ብሏል። ከመቃብር ጸጥታ ባሻገር የናቅፋ ተኩስ ተሰማው የጀግኖች ደም ጩኸት እየሰማ ልቡ ወደዚያ ሔደ። ሁሉን ትወዳለህ። በመጨረሻም ሁሉን ታጣለህ። ሴላቪ! ኦሮማይ።

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here