በመሳቀቅ እና በኪራይ ጭማሪ እየተሰቃየን ነው፤ ደንቡ ይራዘማል ወይስ ተነስቷል?- የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች

0
1226

የኑሮ ውድነት በከተማ ሆነ በአገር አቀፍ ደረጃ አሳሳቢ እየሆነ መቀጠሉ ከሚስተዋልባቸው ጉዳዮች ዋነኛው ሰዎች ለዕለት ተዕለት ኑሯቸው የሚያወጡት ገንዘብ ሲሆን የመኖሪያ ቤት ደግሞ ከፍተኛውን ወጪ ይወስዳል። 

ነምቤኦ (NUMBEO) የተባለ የአገራትን አማካኝ ለመኖር የሚያስፈልጉ ወጪዎች የሚያሰላ ድርጅት ባወጣው ዓመታዊ ሪፖርት፤ ምንም እንኳን በየጊዜው ተለዋዋጭ ዋጋ ቢኖርም በአማካይ ስሌቱ መሰረት የመኖሪያ ቤት ዋጋ ከፍተኛ ከሆነባቸው አገራት ኢትዮጵያ ከዓለም ሦስተኛ፤ ከአፍሪካ ደግሞ ሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ጠቁሟል። 

ነምቤኦ (NUMBEO) በሰርቢያ አገር መቀመጫውን ያደረገ በቀድሞ የጎግል ሰራተኛ የተመሰረተ የአገራትን የኑሮ ደረጃ የሚመዝኑ መረጃዎችን ለማጋራት የተፈጠረ ድረ ገጽ እንደሆነ ይነገራል። የአገራቱን ዜጎች ገቢ እና የመኖሪያ ቤት ዋጋ ጥምርታን በማነጻጸር በተሰራው ሪፖርት ኢትዮጵያውያን ለመኖሪያ ቤት የሚያወጡት ዋጋ ከገቢያቸው ላይ 43 ነጥብ 1 በመቶ እንደሆነ ተመላክቷል። 

አዲስ ማለዳም ከሰሞኑን በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ ያለውን ወቅታዊ የቤት ኪራይ ዋጋ መናር የተመለከቱ ቅሬታዎች ደርሷታል። ተከራዮችን፣ አከራዮችን እንዲሁም የከተማ አስተዳደሩን በጉዳዩ ላይም አነጋግራለች። 

ቅሬታቸውን ለአዲስ ማለዳ ያቀረቡ የከተማው ነዋሪዎች በቅርብ ዓመታት ውስጥ ተግባራዊ ሲደረግ የነበረው “የተከራዮችን እንግልት” የቀነሰው ደንብ አሁን ያለበት ሁኔታ አለመታወቅ እንዳሳሰባቸው አጽንዖት ሰጥተዋል። 

የአንድ ልጅ አባት የሆነ እና የስምንት ወር ነፍሰጡር ሚስት ያለችው የከተማው ነዋሪ፤ “ተከራይተን በምንኖርበት ቤት በየጊዜው ኪራይ ጨምሩ እንባላለን። ልጄንም ሆነ ባለቤቴን ከማንገላታ እያለኩ ጨምር ያሉኝን እጨምራለሁ” ሲል ይናገራል። 

“አሁን ግን ቤቱን ለቃችሁ ካልወጣችው ብለውናል፣ የደረሰች ባለቤቴን ይዤ በዛላይ ወተን የምናርፍበት ቤት ሳይኖረን ምን አደርጋታለሁ? ቢያንስ ቤት እስካገኝ ታገሱኝ ብልም ሊሰሙኝ ፍቃደኛ አይደሉም፤ ይባስ ብለው እንከሳለን በማለት ያስፈራሩኛል። ችግራችንን መንግስት ይይልን” ሲል ቅሬታውን ገልጿል። 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽህፈት ቤት በዋናነት የመኖሪያ ቤት ተከራዮችን ችግር እና አገራዊ ሁኔታን ከግንዛቤ በማስገባት በማለት ለ90 ቀናት (ሦስት ወራት) የሚቆይ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ዋጋ መጨመር እንዲሁም ተከራዮችን ማስወጣት የሚከለክል ደንብ የከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ ከነሐሴ 18 ቀን 2013 ይፋ ድርጎ ነበር። ደንቡን የማያከብሩ ሰዎችን ለማጋለጥም የስልክ ቁትር አድራሻዎች ጭምር ይፋ ተደርገው እንደነበረም አይዘነጋም። 

የወጣው ደንብ ተግባራዊነቱ “እምብዛም” እንደሆነ ለአዲስ ማለዳ የሚናገሩት ቅሬታ አቅራቢዎች “ደንቡ ሲኖር በህጉ የሚመራ ባይኖርም የኪራይ ጭማሪ ቢያደርጉብንም፤ ቢያንስ እንደማያስወጡን መተማመኛችን ነበር። አሁን ግን ስጋታችን እየጨመረ ነው” ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል። 

“ዜጎችን ከተለያዩ ጫናዎች ለመከላከል ሲባል” በከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ የጸደቀው ደንብ በየጊዜው እየተራዘመ ቆይቷል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጉዳዩ ላይ ለመጨረሻ ጊዜ ሐምሌ 3 ቀን 2015 ባወጣው መመሪያ መሰረት ለሚቀጥሉት 6 ወራት የቤት ኪራይ ጭማሪ ማድረግ እንዲሁም ተከራይ ማስወጣት እንደማይቻል አስታውቆ ነበር። በዚህም መሰረት በግል ከሚደረግ ስምምነት ውጪ ማንኛውም አከራይ ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት የቤት ኪራይ ጭማሪ ማድረግ እንዲሁም ተከራይ ማስወጣት አይችልም ነበር።

ይኹን እንጂ ከሐምሌ 3 ቀን 2015 ጀምሮ ለ6 ወራት የተራዘመው ደንብ ጥር 3 ቀን 2016 ላይ የተቀመጠውን የጊዜ ገደብ ጨርሷል። ለአዲስ ማለዳ አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች በመሳቀቅ እና በኪራይ ውድነት እየተሰቃየን ነው ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸው የደንቡ ተፈጻሚነት ይራዘማል ወይስ ተነስቷል የሚለውን መንግስት ያሳውቀን ሲሉ ጠይቀዋል። 

በጥያቄያቸው መሰረት አዲስ ማለዳ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽህፈት ቤትን ስለደንቡ መራዘም ጠይቃለች። በምላሹም በስብሰባ ተወስኖ ይፋ እንደሚደረግ የተገለጸ ሲሆን እስካሁን ግን የተወሰነ ውሳኔ አለመኖሩን አዲስ ማለዳ ለማወቅ ችላለች።

እንደተከራዮች ቅሬታ በደንቡ ተገድበው የቆዩት አከራዮች የጊዜ ገደቡ መጠናቀቁን ተከትለው መጠን ያለፈ የኪራይ ጭማሪ እና ያለ ማስጠንቀቂያ ከቤት የማስወጣት ተበራክቷል። አዲስ ማለዳ የተወሰኑ በከተማዋ የሚገኙ የቤት አከራዮችንም አነጋግራለች።

ቤቶችን በማከራየት የሚተዳደሩ የአዲስ አበባ ነዋሪ እናት እንደተናገሩት በኪራይ ገቢ የሚተዳደሩ መሆኑን ገልጸው “የኑሮው ውድነት የምታውቁት ነው። እንደእኔ ብቻውን ለሚኖር ሰው ደግሞ ከባድ ነው። አቅመደካማ እንደመሆኔ በየጊዜው ለሆስፒታል አወጣለሁ፣ የወር ወጭ አለ፣ የመብራት እና ውሃ ስንት ጉዳይ አለ። በመሆኑም እኛም ተቸግረን ተከራዮቹንም እናስቸግራለን” ብለዋል።

በተመሳሳይ ሌላ አከራይ “ተከራዮቹ አንገት ደፍተው ሁለት ሆነው ይገቡ እና ሲላመዱ አምስት ስድስት ሰው በአንድ ቤት እየኖሩ ይገኛሉ። አንዳንዱ ደግሞ ሁሉም ነገር ዘመናዊ እንዲሆንለት ግን ኪራይ እንዳይጨመርበት ይፈልጋል። እኛም ከጭቅጭቅ እንዲለቁ እንጠይቃለን” ሲሉ ጠቁመዋል።

አዲስ ማለዳ የከተማ አስተዳደሩን ቀጣይ ውሳኔዎች ተከታትላ ታደርሳለች።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here