የአማራ ክልላዊ መንግስት፣ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ እና የአብን መግለጫዎች ምን ያሳያሉ?

0
721

  የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት “የዛቻ እና የጠብ አጫሪነት መግለጫ” ሲል የጠራው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ካቤኔ መግለጫ በተሳሳተ ካርታ ወደ አማራ ክልል ተካተዋል ያላቸውን አካባቢ ሕዝቦች ታሪካዊ እውነታን፣ ተጨባጭ ማስረጃዎችን እና ነባራዊ ሐቅን የካደ እና አሳሳች ነው ሲል ገለጸ። 

የአማራ ክልል መንግስት ዛሬ ረፋድ ላይ ባወጣው መግለጫ በትናንትናው ዕለት መጋቢት 18 ቀን 2016 የትግራይ ኃይል “ከነበረበት አካባቢ በመንቀሳቀስ የራያ አላማጣ ወረዳ ቀበሌዎችን በመያዝ ነዋሪዎችን በመግደልና በማሰቃየት ላይ ይገኛል” በማለት ከሷል። 

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ ሰኞ መጋቢት 16 ቀን 2016 ባወጣው መግለጫ “የአማራ ክልል የትግራይ መሬት በካርታው በማስፈር የትምህርት ሰርዓቱ አካል በማድረግ እያስተማረበት ይገኛል” በማለት መውቀሱ አይዘነጋም። 

የጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔው “ክልሉ የትግራይ መሬት በሚመለከት በስርዓተ ትምህርቱ ያሰፈረው ካርታ ኃላፊነት የጎደለው ብቻ ሳይሆን የትግራይ ህዝብ ከፋፍሎ ለማጥፋት ያወጀው ዘመቻ በማስቀጠል በከፋ መልኩ እየሰራበት እንደሚገኝ ማረጋገጫ መሆኑን ተገንዝበናል” ሲል ትችት ሰንዝሮ ነበር። 

በፕሪቶሪያ የተደረገውን የሰላም ስምምነት ትግበራ፤ ጉድለቶች እንዲሁም መንግስት የስምምነቱ አፈጻጸም ላይ የሰራቸውን ስህተቶች ጭምር ቢኖሩም “ለትልቁ አገራዊ የጋራ ሰላም” ሲባል በትዕግስት ስከታተል ቆይቻለሁ ያለው ደግሞ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ነው። 

በፕሪቶሪያው ሥምምነት አንቀጽ 6(F) መሰረት ህወሓት በሰላሳ ቀናት ውስጥ ቀላል መሳሪያን ጨመሮ ጠቅላላ ትጥቅ እንዲፈታ፤ አንቀጽ 3(5) መሰረት ደግሞ የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት ወደ ትግራይ ገብቶ ጸጥታ የማስከበሩን ሥራ በተሟላ ሁኔታ እንደሚረከብ ሥምምነት ላይ ቢደረስም ሁለቱም ተግባራዊ አልሆኑም ሲል ንቅናቄው አሳስቧል። 

ይኹን እንጂ ህወሓት “በጦርነት ጉዳትና መልሶ ግንባታ ስም ከፍተኛ የገንዘብ እና የግብዓት ድጋፍ እየተደረገለት ከመቆየቱ ባሻገር፤ የሰላም ስምምነቱ ይከበር የሚል የምጸት ፕሮፓጋንዳ እና የጦርነት ጉሰማ ላይ በአዲስ መልክ ተጠምዷል” ፓርቲው መግለጹን አዲስ ማለዳ ከመግለጫው ተመልክታለች።

የአማራ ክልላዊ መንግስት ካወጣው መግለጫ አዲስ ማለዳ እንደተመለከተችው የማንነት እና የአስተዳደር መብት ዙሪያ ጥቄዎች ለሚነሳባቸው የወልቃይት ጠገዴ፣ ጠለምት እንዲሁም የወፍላ ወረዳዎች እና የራያ ወረዳዎች የፕሪቶሪያው ስምምነት ከመፈረሙ በፊት ጀምሮ አካባቢዎቹን እንደማንኛውም የአገሪቱ ክፍሎች የአማራ ክልል የልማት ትሩፋቶችን በትምህርት መስክ ጨምሮ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል። 

በአንጻሩ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ ከቻይናው ሲ.ጂ.ቲ.ኤን (CGTN) ጋር የነበራቸው ቆይታ ትላንት ምሽት የተሰራጨ ሲሆን በቆይታቸው በሰሜን እና ደቡብ ትግራይ ክፍሎች የኤርትራ መከላከያ ሰራዊት እንዲሁም የአማራ ክልል ታጣቂዎች አሁንም መኖራቸውን ተናግረዋል። 

የሰላም ስምምነቱን በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ ብዙ ስራዎች ይጠበቁናል ያሉት ጌታቸው ረዳ፤ ነገር ግን “ዳግም ወደ ጦርነት የምንገባበት ምንም አይነት መንገድ የለም” ማለታቸውንም አዲስ ማለዳ ተመልክታለች።

አብን የትግራይ ሕዝብም እራሱን ነጻ ለማውጣት በሚያደርገው ተጋድሎ ድጋፉን እንደሚያደርግ አስታውቋል። 

በተጨማሪም የአማራ ክልልና የፌደራል መንግስት “ህወሓት አሁንም ሌላ ዙር ጦርነት ቀስቃሽ ፕሮፓጋንዳ ውስጥ የገባ በመሆኑ ይህንን ጠብ አጫሪነት” በትኩረት እንዲከታተሉ አብን አሳስቧል። በአማራ ክልል የተፈጠረውን ችግርም በልዩ ትኩረት በውይይትና ድርድር ሰላም የማስፈን ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪውን አቅርቧል።

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ መግለጫ “የአማራ ክልል መንግስት በህዝባችን ላይ አየፈፀመው የቆየውና አሁንም በሃይል በያዛቸው የትግራይ አካባቢዎች እየፈፀመ የሚገኘው ግፍና መከራ ተሰምቶት በመፀፀት ፈንታ ወደ ባሰ ታሪካዊ ስህተት መግባቱ በቀጣይነት ዋጋ እንደሚያስከፍለው በማወቅ በአስቸኳይ እርምት ማድረግ አለበት” በማለት አስስቧል።

የአማራ ክልል መንግስት በመግለጫው በክልሎቹ መካከል የማንነትና የአስተዳደር ጥያቄ የሚነሳባቸው አካባቢዎች “ህወሓት በኃይል ተገፍፎባቸው የነበረውን የማንነትና ጥያቄና ራስን በራስ የማስተዳደር ነጻነት” በሰሜኑ ጦርነት ወቅት ተቀዳጅተዋል ብሏል። “የተፈጠሩ ችግሮችን በህግ አግባብ እንዲፈታ እተደረገ ያለውን ጥረት የአማራ ክልል መንግስት የራሱን ድርሻ እየተወጣ” ነው ሲልም አስታውቋል። 

በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት አፈጻጸም ዙሪያ በፌደራል መንግስቱ እና በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር መካከል የነበረው መወቃቀስ ጋብ ብሎ ተስተውሏል። ነገር ግን የፌደራል መንግስቱ በእነዚህ አካባቢዎች ሕዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ አቋም ይዞ እየሰራ መሆኑ ይፋ ቢደረግም በአማራ እና ትግራይ ክልል አስተዳደሮች መካከል መወቃቀስ ተጀምሯል። 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here