የትግራይ ጥያቄ ምንድን ነው?

0
766

ወጣት መሐሪ አዳነ ትውልድና እድገቱ በራያ እንደሆነ ይገልጻል። አሁን ወቅት የትግራይ ወጣቶች ማኅበር አባልና የሥራ ዕድል ፈጠራ ከፍተኛ ባለሙያ ሆኖ በማገልገል ለይ ይገኛል። የትግራይ ሕዝብ የዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ደጋፊ እንደሆነ በመጥቀስ የሕዝቡ በተለይም የወጣቱ ጥያቄ የሕግ ይከበርና የመልማት እንጂ በዐቢይ አስተዳደር ላይ ተቃውሞ እንደሌለው ያነሳል። በሙስናና ሰብኣዊ መብት ጥሰት የተጠረጠሩ ሰዎች መያዝም ሕዝቡን እንዳላስከፋው በመጥቀስ ሕዝቡን ያስቆጣው ‹‹ብሔር ላይ ያነጣጠረ መምሰሉና እና በመገናኛ ብዙኃን በኩል የተከፈተው ዘመቻ ነው›› ይላል። በትግራይ ውስጥ የማንነት ጥያቄ እንደሌለ የሚገልጸው ወጣቱ ተወልዶ ባደገበት ራያ እስካሁንም ከሕዝቡ በኩል የማንነት ጥያቄን አለመስማቱን ያክላል። በዐሥር ሺህዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆች የሞቱትና ለ17 ዓመታት የታገሉት ሕግ እንዲከበር በመሆኑ አሁንም ሕዝቡ የሚያነሳው ጥያቄ ሕገ መንግሥቱ እንዲከበር፣ ብሔር ተኮር ጥቃቶች እንዲቆሙና የሕግ የበላይነት እንዲረጋጋጥ፣ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች እንዲመለሱለት እንዲሁም የመሠረተ ልማት እጥረቶች እንዲፈቱ ጭምር ነው የሚል እምነት አለው።
የትግራይ ክልልም በተደጋጋሚ መግለጫዎቹ የማንነት ትያቄ እንደሌለ ሲናገር ተደምጧል፣ ራያ የማንነት ጥያቄ እንዳለው የሚገልጹ ወገኖች ደግሞ ክልሉ የሚሰጠው ‹የማንነት ጥያቄ የለም› የሚል መግለጫ ተቀባይነት እንደሌለው ይሞግታሉ። ‹‹የሕዝቡ ጥያቄ ሕወሓት እንዲወገድለት ነው›› የሚሉት የዓረና ትግራይ ሊቀ መንበር አብርሃ ደስታ በበኩላቸው የማንነትና የአስተዳደር ጥያቄ ሊለያይ አይገባም ይላሉ። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪና መምህሩ ሙሉ ነጋ (ዶ/ር) በትግራይ ያለው ዋናው ጥያቄ ከሕወሓት አፈና የመነጨ ነው ይለሉ። በዚህ መሐል የማንነት ጥያቄ ‹‹የለም›› እና ‹‹አለ›› የሚሉ ሕዝባዊ ሰልፎች እየተካሄዱ ናቸው።
በትግራይ የማንነት ጥያቄ ላይ ያለ ውዝግብ
በትግራይ ክልል ውስጥ የሚገኙት ራያና ወልቃይት የማንነት ጥያቄ እንዳላቸው በሚገልፁና የማንነት ጥያቄ ሳይሆን የመልካም አስተዳደር ነው በሚሉ ወገኖች መካከል በሚነሱ የተቃርኖ ሐሳቦች እየተናጡ ነው። ወጣት መሃሪ ሕዝቡ በትግራይም ይተዳደር በአማራ ክልል ሁለቱም ጋር ያለው ገዥው ኢሕአዴግ በመሆኑ ልዩነት ስለሌለው የማንነት ጥያቄ አለ ብሎ እንደማያምን ይገልጻል። ዋናው ጥያቄ በምጣኔ ሀብትና በፖለቲካ በዕኩል ያለመጠቀምና ያለመሳተፍ ቅሬታ እንደሆነ ያነሳል። ራያ ላይ ‹‹ሰው በሚፈልገው ቋንቋ ሳይሸማቀቅ ይግባባል የሚለው ወጣት፣ ሰው በሚፈልገውና በአፍ መፍቻ ቋንቋው እንዲማርና እንዲዳኝ መጠየቁ ተገቢ ነው›› ይላል።
የማንነት ጥያቄ አለ የሚሉት ወገኖችን ግን እንደማያምንም ያክላል። ምክንያቱ ደግሞ እሱ ተወልዶ ባደገበት ራያ የማንነት ጥያቄ አለ በሚል እየተንቀሳቀሱ ያሉ የኮሚቴ አባላት አሁን ላይ በአካባቢው የማይኖሩና ሕዝቡም ወክሏቸዋል ብሎ እንደማያምን በመጥቀስ ነው። የእውነት የማንነት ጥያቄ አለ ቢባል እንኳን ለትግራይ ክልል ቀርቦ ካልተፈታ ወደ ፌደራል መሄድ ሲገባው የተኬደበት አግባብ ይህ ባለመሆኑ ሕጋዊ ጥያቄ ነው ብሎም አያምንም።
የራያ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ሰብሳቢው አግዘው አዳሩ ግን የራያ ሕዝብ ጥያቄ የማንነት ነው በሚል ይሞግታሉ። ኮሚቴውም ቢሆን በሕዝቡ የተመረጠ እንደሆነ በመጥቀስ ከ1984 መጨረሻ ጀምሮ ጥያቄው እየተነሳ በሕወሓት ሲዳፈን የኖረ እውነተኛ የማንነት ጥያቄ እንደሆነም ይገልጻሉ። ራያ የሚዳኘውና የሚማረው ‹‹በማያውቀው የትግርኛ ቋንቋ›› መሆኑን በመጥቀስም በማንነቱ ምክንያት ከፖለቲካውም ሆነ ከሌሎች መድረኮች ሆነ ተብሎ መገለሉን ይጠቅሳሉ።
አሁን ላይ ራያ ማንነቱም ተከብሮለት ቢሆን በትግራይ ክልል ውስጥ የመተዳደር ፍላጎት እንደሌለውም ያክላሉ። ከወልቃየት በኩልም ከዚህ ቀደም ‹‹በማንነታችንና አማራ በመሆናችን›› ተፈናቅለናል በሚል ወደ አዲስ አበባ ለአቤቱታ የመጡ የአካባቢው ነዋሪዎች ለመፈናቀላቸው ምክንያቱ ለመስቀል በዐል ‹በአማርኛ እየዘፈናችሁ ተጨውታችኋል› የሚል መሆኑን ሲገልጹ ነበር። በራያ በኩል የማንነት ጥያቄውን ለምን ቀድሞ ለትግራይ ክልል አልደረሰም ለሚለው ጥያቄ፣ ለ27 ዓመት ጥያቄውን ሲቀርብለት የኖረው ሕወሓት ምላሽ በመስጠት ፈንታ የማፈንና ጥያቄውን የሚያነሱ ሰዎችን እስከመረሸን እርምጃ ሲወስድ መኖሩን በመጥቀስ አሁንም ጥያቄው በክልሉ ይፈታል ብለው እንደማያምኑ ያክላሉ። 26 ሺሕ ኗሪዎች የፈረመበትን ሰነድ ለክልሉ በፖስታ የላኩ መሆኑን በመጥቀስ መፍትሔን የሚሹት ከፌደራሉ መንግሥት እንደሆነ ይጠቅሳሉ።
በሕወሓት/ኢሕአዴግ የሚመራው የትግራይ ክልል መንግሥት በራያና በወልቃይት ላይ የማንነት ሳይሆን የመልካም አስተዳደርና የልማት ጥያቄዎች መኖራቸውን በመጥቀስ ጥያቄዎቹን ለመመለስ እንደሚሠራ አሳውቋል። የማንነት ጥያቄ አለን የሚሉ ወገኖች ሕዝብን እንደማይወክሉም ያሰምርበታል። ለአብነትም ጥቅምት 13/2011 ባወጣው መግለጫ በራያ በተከሰተው ግጭት “የአማራ ክልል ባወጣው መግለጫ የተከሰተው ግጭት መነሻው የራያ አካባቢ ሕዝብ የማንነት ጥያቄ ሲሆን ይህንን ጥያቄ ከሕዝቡ ጋር በመነጋገር ሕገ መንግሥታዊ ምላሽ መስጠት እንደሚገባ በአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርትም ሆነ በኢህአዴግ ጉባኤዎች አቅጣጫ መቀመጡ ይታወሳል” በማለት “ሕገ መንግሥቱ በማንነት ጉዳይ ላይ ያስቀመጠውን ስርዓት በመጣስ በሌላ ክልል የውስጥ ጉዳይ ጠልቃ መግባቱን የሚያረጋግጥ መግለጫ ነው። በመግለጫው በግልፅ እንደተቀመጠውም በራያም ሆነ በወልቃይት አካባቢዎች ለተፈጠሩ ችግሮችም የአማራ ክልል መንግሥት ኃላፊነቱን መውሰድ ይኖርበታል” ሲል መውቀሱ ይታወሳል።
አብርሃ ደስታ በበኩላቸው ጥያቄዎቹን መሠረታዊና ከለውጡ ጋር የመጡ ብለው ይከፍሏቸዋል። መሠረታዊ የሚሏቸው ነጻነት፣ ፍትሕ፣ ልማትና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን የሚጠይቁ ሲሆኑ፤ ከለውጡ ጋር የተያያዙት ደግሞ የትግራይ ሕዝብ ከሌላው ኢትዮጵያዊ በእኩል ዐይን መታየት እንዳለበት ወይም ሕወሓትና ሕዝቡ የተለያዩ መሆናቸው እንዲታወቅለት የሚጠይቁ ናቸው።
የማንነት ጥያቄ የለምወይ ለሚለው ፓርቲያቸው የማንነትና የአስተዳደር ጥያቄን ለያይቶ እንደማያያቸው ያነሳሉ። የአስተዳዳር ጥያቄዎች ካልተመለሱ ጥያቄው የማንነት እንደሚሆን በመጥቀስ የሚነሱት የማንነት ጥያቄዎች የሕወሓትና አዴፓ (ብአዴን) የፖለቲካ ሹክቻ ያጋጋላቸው እንደሆነም ያምናሉ። አዴፓ በፌደራል ያለውን ስልጣን ለማብዛት መንገድ እስከመዝጋት እየደረሰ የፌደራሉን መንግሥት የማስጨነቅና በዚህም ሥልጣኑን የማጠናከር ፍላጎት እንዳለው ያነሳሉ። በሌላ በኩል ሕወሓት የትግራይን ሕዝብ እንደተወረረ በመንገርና በሐሳብ በማሸበር ሕዝብን የሚያድነው ሕወሓት እንደሆነ እንዲያምን በዚህም ሕዝቡን በመያዝ በፌደራሉ መንግሥት ተፈሪነቱን ይዞ ለመቀጠል እንደሚፈልግም ይጠቅሳሉ።
የፓርቲያቸው አቋም የሕዝብ ፍላጎትን የሚከተል እንደሆነና ከሕዝብ የሰበሰቡት ሐሳብ በመላ ትግራይ ያለው ጥያቄ የአስተዳዳር በደል የወለደው እንደሆነ ያነሳሉ። ሆኖመ የአስተዳደር ጥያቄዎች ካልተመለሱና ሰው በማንነቱ ከተጨቆነ ወደዚህ እንካለል የሚል ጥያቄ እንደሚከተልም ያክላሉ። ለዚህ ማሳያውም ከወልቃይትና ከራያ ባለፈ አድዋ ውስጥም እምአሲኔቲ በሚባል አካባቢ ‹ተበድለናል ወደሌላ አካባቢ መከለል አለብን በሚል ከፍተኛ ውጥረት መኖሩ› እንደሆነ ይጠቅሳሉ። በተለያዩ አካባቢዎች የተለያየ ቋንቋ የሚናገሩ ሕዝቦች መኖራቸውን በመጥቀስ ሁሉም በቋንቋው እንዲግባባና ማንነቱ እንዲከበርለት ማድረግ እንጂ በቋንቋ መሠረት እየተደረገ አንዱን ወደዚያ አንዱን ወደዚህ ማካለል አስቸጋሪ እንደሚሆን ያምናሉ። የብሔር ፖለቲካ የአገሪቱን ሠላም እያወከ እንደሆነም ይጠቅሳሉ።
በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ መምህሩ ግደይ ደገፉ በኢትዮጵያ የማንነት ጥያቄዎች መኖራቸውን በመጥቀስ ጥያቄዎቹ ከፖለቲካ ልሂቃኑ አልፈው የሕዝብ መሆናቸውንም ይገልጻሉ። ከመንግስት በኩልም የሚጠበቀው ሕዝቡን እያዳመጡ ሕጋዊ በሆነና በሰከነ ውይይት መፍታት እንጂ ማፈኑ የበለጠ አደጋ የሚጋርጥ እንደሆነ ይመክራሉ።
ተመራማሪና መምህሩ ሙሉ ግን ሕዝቡ እንደሌላው ኢትዮጵያዊ ያልተመለሱት በርካታ የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ቢኖሩም በሕወሓት አፈና ውስጥ በመኖሩ ዛሬ የሚስተዋለው ችግር መከሰቱን ያነሳሉ። የማንነት ጥያቄ ናቸው ለማለት እንደሚቸገሩ በመግልጽ ሕዝቡ በጭቆና ውስጥ ስላለ ወዴት ክልል ብካለል የተሻለ አስተዳደርና ልማት አገኛለሁ ከሚል እንደሚመነጭ ይጠቅሳሉ። ይሁንና በየቦታው የሚስተዋሉት ጥያቄዎች የማንነት ናቸው ከተባለም ቋንቋ ላይ የተመሰረተውን አከላለል አንደገና ማጥናት ያስፈልጋል ይላሉ። ለዚህም እየተደራጁ ያሉት የማንትና ወሰን ጉዳዮች እንዲሁም የእርቅ ሠላም ኮሚሽኖች በገለልተኛ ባለሙያዎች ተሳትፎ ‹ማንነት ምንድን ነው› የሚለው ጨምሮ ግልፅ መመዘኛዎችን እያወጡ ጥያቄዎችን መመለስ ያስልጋል ሲሉ መክራሉ።
አሁን ግን ሕዝቡን በግልጽ ማወያየት ሲገባ በተቃኒው በፖለቲከኞች ቁማር እየተጎዳ ነው ይላሉ። ሕወሓት የአንድ አካባቢ ሰዎች በዝምድናና በጥቅም ትስስር የያዙት ፓርቲ እንደሆነ የሚያምኑት ተመራማሪው አሁን ባለው ቁመና የሕዝቡን ጥያቄ መፍታት እንደማይችል፣ ከሕዝብ ጥቅም ይልቅ የግለሰቦች ጥቅምና ፍላጎት የሚያሸንፈው መሆኑንም ያብራራሉ። አንድ አመራር 27 ዓመታት ሙሉ እንደኃውልት መቀመጥ የለበትም፤ ሕወሓት ሕዝቡን የሚመጥን ማሻሻያ ያስፈልገዋል ይላሉ። የክልሉ መንግሥት ዞኖችን ሳይቀር እኩል እንዲለሙ እድል ከመስጠት ይልቅ ሲያበላልጥ እንደኖረ ይናገራሉ። ለአብነትም በሽሬ ዙሪያ ካሉ አካባቢዎች ወርቅን ጨምሮ በርካታ ሀብቶች በኤፈርት ኩባንያዎች ቢወጡም የአካባቢው ሕዝብ እንዳልተጠቀመ፤ በአጠቃላይም ኤፈርት ለሕዝቡ ሳይሆን ለፓርቲው ሰዎች ጥቅም አንደቆመ ይገልጻሉ። ሕወሓት ግን ኤፈርት በኢንዶመንት ሲቋቋም ለሕዝብ እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲገልጽ ኖሯል። በቅርቡ ከፓርቲው አመራሮች አንዱ የሆኑት ጌታቸው ረዳ በቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርበው ሲናገሩ የሚቆጫቸው ኤፈርት የሕዝቡን ተጠቃሚነት ባለማሳደጉ እንደሆነ ተናግረዋል።
የትግራይ ሕዝብ ስለዐቢይ መንግሥትና ተጠርጣሪዎች መያዝ
ወጣት መሐሪ የትግራይ ሕዝብ የዐቢይ መንግሥት ደጋፊ እንደሆነ ይገልጻል። ዐቢይ የቆሙለትን ሠላምና ሕግ የማስከበር አቋም ሕዝቡ በየሰልፉ ‹‹ሕገ መንግሥቱ ይከበር፣ ብሔር ተኮር ጥቃት ይቁም›› እያለ እያንጸባረቀውና ለዚህም የበኩሉን እየተወጣ እንደሆነም ይጠቅሳል። የዐቢይ አስተዳደርም ሕግን እንዲያስከብርላቸው ይጠይቃል።
በሙስና ወንጀልና ሰብኣዊ መብት ጥሰት ተጠርጥረው በተያዙ ሰዎች ቅሬታ እንደሌለው በመጥቀስ ሕዝቡን ያስቆጣው ‹‹ሚዲዎች ተጠርጣሪዎችን በወንጀለኛነት ፈርጀው ዘመቻ መክፈታቸው ነው›› ይላል። ሕግ ይከበር በሚል ሰልፍ የሚወጣ ሕዝብ የወንጀል ተጠርጠሪ ተያዘ ተብሎ አይከፋም፤ የተያዙትም ቢሆኑ ትግራዋይ ብቻ እንዳይደሉ ያነሳል። ሕዝቡ ብሔር ተኮር ጥቃት ይቁም የሚለው ጥቃቱ በትግራይ ተወላጆች ላይ ብቻ ደርሷል ብሎ ሳይሆን በየትኛውም ኢትዮጵያዊ ላይ የሚደርሰውን ጥቃት በመቃወም ጭምር ነው ይላል።
አብርሃ እንደሚሉት የሕዝቡ ጥያቄ ‹የህወሓት ይወገድልኝ› ነው። አሁን በትግራይ ያለው መንግሥት ሕዝቡን በአግባቡ እያስተዳደረ እንዳለሆነና ሕዝቡ እንደሌላው ኢትዮጵያዊ እኩል እንዲታይ እንደሚፈልግ ያነሳሉ። እንደ አብርሃ ገለጻ ሕወሓት መጥፎ ከሆነ መጥፎነቱ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ እንጂ ለትግራይ ብቻ መልካም አሳቢ ሆኖ ሊሳል እንደማይገባም ሕዝቡ ይጠይቃል። አሁንም በትግራይ አፈና መኖሩንና ሕዝብን የበደለ ስርዓት ተወግዶ በነጻነት የሚኖርበት አገርና መንግሥት እንዲመሠረት የሚፈልግ ሕዝብ እንደሆነም ያክላሉ። ሠልፍ የሚወጣው ሕዝብም ተገዶ እንጂ የሕወሓት ደጋፊ ሆኖና በሠልፉ አምኖበት እንዳይደለ ይገልጻሉ። መፈክሩም በሕወሓት ሰዎች የሚጻፍ እንደሆነ በመጥቀስ ሕዝቡ ‹‹ሠልፍ አልወጣም›› ቢል በነጋታው የሚደርስበትን ስለሚፈራ ነው ይላሉ።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር ) በቅርቡ በሰጡት መግለጫ ሕዝቡ በሠላማዊ ሰልፍም ሳይቀር የሕግ የበላይነት እንዲከበር ሲጠይቅ የከረመው በአገሪቱ ውስጥ የሕግ ጥሰት መኖሩን ስለተገነዘበ እንደሆነ በመጥቀስ፣ በማንኛውም አካል የተፈጸሙ ጥፋቶች በትግራይ መንግሥትና ሕዝብም ይሁን በሕወሓት ተቀባይት የሌላቸውና ለድርድር እንደማይቀርቡ መናገራቸው ይታወሳል።
ተጠያቂዎችን መያዙ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እና ለፖለቲካ ፍጆታ እንዳይውል ጥንቃቄ ያስፈልጋል የሚለው የትግራይ መንግሥት በአንድ ብሔርና ክልል ማተኮሩን በመጥቀስ ተቀባይነት እንደሌለውም መናገራቸው ይታወሳል። ሕግ የማስከበሩ ሂደት ላይ የውጭ ጣልቃ ገብነት አለ ብለው እንደሚያምኑም ጠቅሰዋል። የትኛው አገር የሚለው ግን እስካሁን በክልሉ በኩል በግልጽ አልተነገረም። የሕወሓት አመራሮች በተለያየ ጊዜ የትግራይ ሕዝብና ሕወሓት የሚለያይ እንዳልሆነ ደጋመው ሲያነሱ መደመጣቸው አይዘነጋም። አብርሃ ግን በዚህ ሐሳብ አስማሙም፤ ይልቁንም ሕዝቡ በሕወሓት ተጨቁኖ እንዳለ ያነሳሉ።
መምህር ሙሉ እንደሚሉትም ሕወሓት የትግራይ ሕዝብ ከሌላው የተለየ ተጠቃሚ እንደሆነ ተደርጎ እንዲሳል ከማድረጉም ባሻገር የዐቢይን አስተዳዳር የለውጥ እንቅስቃሴ ለሚፈልገው ሕዝብ የሚሰብከው ከእውነታው በተቃራኒው እንደሆነ ያነሳሉ። ሕዝቡን ‹እከሌ ከመጣ ያጠፋኻል› በሚል የማሸበርና ሕወሓትን አምኖ እንዲኖር የማድረግ አካሄድም እንደሚከተል ይጠቅሳሉ። የተጠርጣሪዎች መያዝ ክልሉን ሊያስቆጣው አይገባም የሚሉት መምህሩ ችግሩ ሕወሓት ለግለሰቦች ጥቅም ስለቆመ እንደሆነ ያስረዳሉ። ሰሞነኞቹ ሰልፎችም ቢሆኑ የሕዝቡ ሳይሆኑ የፖለቲካ ልሂቃኑ የሚያነሳሷቸው እንደሆኑ በመጥቀስ ሕዝቡ የተሻለ አስተዳዳር የሚፈልግ ቢሆንም ተገዶ የሚወጣ እንደሆነ ነው የሚያምኑት። በብሔር ፖለቲካ የመደራጀቱ መዘዝም ፖለቲከኞች ሕዝቡ እንዲቀራረብ ሳይሆን እንዲጋጭ የሚያደርግ አካሔድን እየተከተሉ ስልጣንን ለማራዘም የመሞከር መንስኤ እንደሆነ የሚያምኑት መምህር ሙሉ መፍትሔ ካልተሰጠው አካሄዱ ኢትዮጵያን ወደ ሦስት አገርነት የሚቀይር ሊሆን እንደሚችልም የጥናት ግኝቶች መኖራቸውን በመጥቀስ ሥጋታቸውን ያስቀምጣሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 3 ኅዳር 22 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here