የአገር ሽማግሌዎች ፖለቲካዊ ሚና

0
795

የአገር ሽማግሌዎች ቀደም ብለው ሊደርስ ስላለው አስከፊ ሁኔታ ሲናገሩ ተሰሚ አልነበሩም የሚሉት አበበ አሳመረ ፤ በተለይ አሁን ላይ ስለምርጫ እየታሰበ ባለበት ጊዜ እንዲሁም ለወደፊቱ በሚኖሩ የፖለቲካ አስተዳደር መዋቅሮች ውስጥ የአገር ሽማግሌዎችን የፖለቲካ ውክልና ተሳትፎ ማሰብ ያስፈልጋል ሲሉ ሐሳባቸውን ያካፍላሉ። ምክር ቤቶችም ጨምሮ ፓርላማ ድረስ የአገር ሽማግሌዎች ድርሻና ድምጽ ተወካይነትም ቢኖር፤ ችግሮችን ከመሠረታቸው መፍታትና አገር ሽማግሌዎችን እሳት ለማጥፋት መጣራት አይኖርም ሲሉም አመላክተዋል።

በአሁኑ ጊዜ ግጭትና ትርምስ በበዛ ቁጥር የአገር ሽማግሌዎችን ሰብስቦ መምከር እና ማስመከር የተለመደ እየሆነ መጥቷል። የሃይማኖት አባቶችም ሚና ተመሳሳይ ቢሆንም ከሚናው የተለየ ባህሪ የተነሳ የእነሱን ጉዳይ በሌላ እራሱን በቻለ ጽሑፍ እመለስበታለሁ። የአገር ሽማግሌዎች ሚና ከግጭት በኋላ ብቻ ባይሆንና ከግጭት በፊት እና በአጠቃላይ በፖለቲካ አስተዳደር ኺደት ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ ክፍተኛ እንዲሆን እድል ተሰጥቶ ቢሆን ኖሮ የአገራችን ፖለቲካ በካድሬ ብቻ የሚዘወር ላይሆን ስለሚችል ዛሬ የደረስንበት የፖለቲካ ምስቅልቅል ላያጋጥመን ይችል ነበር ብዬ አምናለሁ።
በዚህ የተነሳ አሁን አሁን አንዳንድ ሽማግሌዎች ‹‹ችግር ከተፈጠረ በኋላ ነወይ የምትፈልጉን?›› ‹‹እነዚህ ችግሮች ሊከሰቱ እንደሚችሉ በተደጋጋሚ ተናግረን ነበር፤ አልሰማችሁንም።›› ‹‹ተገቢውን ክብር አልሰጣችሁንም…››› ወዘተ እያሉ በምሬት ሲናገሩ እና በመንግሥት ላይ ቅሬታቸውን ሲያቀርቡ አያዳመጥን ነው።
በቅርቡ ፕሮፌሰር ሕዝቅያስ አሰፋ የተባሉ እውቅ እና በርካታ አገሮች ውስጥ የተከሰቱ ግጭቶችን በተመለከተ በማደራደር እና ሰላም በመገንባት (peace building) ጉልህ ሚና የተጫወቱና አሁንም እየተጫወቱ ያሉ ምኁር እንደተናገሩት፣ የአገር ሽማግሌዎቻችን ለሰላም ግንባታ እና ለግጭት መወገድ ከፍተኛ ሚና መጫወት እንደሚችሉ ቢታወቅም እንደ አለመታደል ሆኖ የሚፈለጉት ግጭት ከተከሰተ በኋላ ፖለቲከኞቻችን ችግሩን መፍታት ሲያቅታቸው ነው። በዚህ የተነሳ በሰላም ግንባታ ውስጥ አገር ሽማግሌዎች ያላቸው ሚና በጣም ዝቅተኛ ነው ብለው ነበር።
ከዚህ በተጨማሪም የችግሩን መሠረታዊ መንስኤ በመመርመር እና ዘላቂ መፍትሄ በማፈላለግ በኩል ብዙም እንዲገፉ ስለማይደረግና በአብዛኛውም ‹‹አርፋችሁ ዝም በሉ›› ስለሚባሉ፣ ፖለቲካውም ጫና ስለሚሳድርባቸውና ስለሚፈሩ በሰላም ግንባታ ውስጥ ሚናቸው የኮሰሰ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
የጎሳ/ የዘር ፖለቲካው የፖለቲካ ስርዓታችን መሰረት ሆኖ ሲጠነሰስም ሆነ ተግባራዊ ሲደረግ የአገር ሽማግሌዎች ደስተኞች እንዳልነበሩ በርካታ ዋቢዎችን መጥቀስ አያስፈልግም። ስርአቱ ገና ከጅምሩ አማራን የጥቃት ዒላማ አድርጎ በየቦታው አማራ የግፍ ገፈት ቀማሽ መሆን ሲጀምርና ካድሬ ሁሉ አማራን ማጥላላትና በአማራ ላይ የጥላቻ ፖለቲካ ተራኪና የጥላቻ ፖለቲካ አባቶች ቀምረው የሰጡትን ትርክት አነብናቢ በነበረበት፣ በየአካባቢው የነበሩ የአገር ሽማግሌዎች ‹‹እባካችሁ ይህን አብሮ የኖረን እና የተዋለደን ሕዝብ አታባሉት›› እያሉ ፖለቲከኞችን ሲማጸኑ፣ ልጆቻቸውን ሲመክሩ እና የጥቃቱ ሰለባ እንዳይሆኑ በየቤታቸው ሲደብቁ፣ ጎረቤቶቻቸውን ሲጠብቁ ነበር።
ለረዥም ጊዜ ኦሮሚያ ውስጥ የኖሩት ዘመዶቼ ስለ ኦሮሞ ሽማግሌዎች እጅግ ግሩም ሰብእና ሲያወሩ ሁሌም ይገርመኝ ነበር። በዚህ የተነሳ በሰሞኑ ድርጊት ምክንያት በኦሮሞ ላይ በጅምላ ተገቢ ያልሆነ አስተያየት ሲሰጥ በጣም ይከፋኛል። ጅምላ ፍረጃ እጅግ መጥፎ የፖለቲካ ባህላችን እየሆነ መምጣቱ ያሳዝናል፣ ተራ ክስተትን መሠረት አድርጎ በጅምላ መኮናነን ትክክል ነው ብለን እስከመቀበል የደረስን መሆናችንን ሳስብ፣ እንደ ማኅበረሰብ ችግር ውስጥ እንደሆንን አምናለሁ።
‹‹እየተፈጠሩ ያሉትን ችግሮች ሁሉ እናንተው የተከላችሁት የዘር ፖለቲካ ውጤት ስለሆነ፣ እሱን ችግር በግልጽ አምናችሁ እስካልተዋችሁ ድረስ የእኛ ለጊዜው ማስታረቅ እና አንተም ተው አንተም ተው ብሎ ማሸማገል ዘላቂ መፍትሔ ሊያመጣ ስለማይችል ዋጋ የለውም።›› በማለት ደፍረው የተናገሩ እና ከሽምግልና እራሳቸውን ያገለሉ፣ በዚህ አባባላቸው የተነሳ በፖለቲከኞች የተገፉ፣ አንዳንድ ጊዜም የከፋ ችግር የገጠማቸው በርካታ ሽማግሌዎች እንዳሉ ይታወቃል። የሰላም እና የእድገት ኮንፈረንሶች እየተባሉ ሲቀለድባቸው የነበሩና የአበል መጫዎቻ የሆኑ የተለያዩ ስብሰባዎች ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ፋይል ውስጥ ወጥተው ቢታዩ የአገር ሽማግሌዎች ምን ሲሉ እንደነበር ታዝበን በራሳችን እናፍር ነበር፣ ማፈርን የምናውቅ ከሆነ።
የአገር በቀል እውቀት እና የአገር ሽማግሌዎች ድንቅ ተፈጥሮአዊ አስተዋይነት ብሎም የሕይወት አተያይ የተመሠረተው በአብዛኛው ሰዋዊ አብሮነትን ዋጋ በመስጠት፣ ያለውን ተጋርቶ በመብላት እና በመጠጣት፣ ችግሮችን ተመካክሮ በመፍታት ላይ ነው። የሃይማኖት እና የብሔር ወይም የጎሳ ልዩነት ለእነሱ ትርጉም የለውም። አባቴ በአንድ ወቅት የመርሃቤቴ አውራጃ አስተዳደሪ ስለነበሩትና ሁሌም ስማቸውን በጥሩነት ስለሚያነሳው ስለ ደጃዝማች ገለታ ቆርቾ ሲያወራን አንድም ቀን ምግባራቸውን ከብሔረሰባቸው ጋር አገናኝቶት አያውቅም።
የቅርብ ጓደኛው ስለነበሩት የጋሞ ሰው ሲያነሳም ብሔራቸው ትዝ ብሎት አያውቅም። የቀደመው ትውልድ የአገር ማማ ሆኖ አንድነታችንን ባይሸከመው ኖሮ ኻያ ሰባት ዓመታት ሙሉ እንደተረጨው የዘረኝነት መርዝ እንደ አገር መቀጠል ባልተቻለ ነበር። በዚህ ምክንያት ‹‹ሽማግሌ አይጥፋ›› የሚባለው አባባል ትልቅ ዋጋ ያለው አባባል እንደሆነ በተግባር አይተናል። አዎ፣ አሁንም ሽማግሌ አያሳጣን ብሎ መጸለይ መልካም ነው።
ከሰሞኑ አንድ በቴሌቪዥን በተላለፈ ስብሰባ ላይ ‹‹ለመሆኑ አማራ እና ትግሬ ሽማግሌ የላቸውም ወይ?›› በሚል አንድ ትልቅ ሰው የተናገሩት በጣም አሳዛኝ ነበር። ካድሬ ብቻ አድራጊ ፈጣሪ በሆነበት አገር ሽማግሌ ቢኖርስ ምን ይፈይዳል፣ ማን አክብሮት?
በሀመር ብሔረሰብ በአስተማሪነት የሠሩ የሌላ ብሔረሰብ አባላት ከሀመር ተወላጅ ጋር ትዳር እንዲመሠርቱ ይበረታታሉ፣ አብሮነትን ለማጠናከር እና ፍቅራቸውን ለማሳየት። በዚህ መልክ ተጋብተው፣ ወልደው እና ከብደው የሚኖሩ እጅግ በርካታ የተደባለቁ ብሔሮች አሉን። በቅርቡ የወጣ አንድ መረጃ እንዳመለከተው 53 ሚሊዮን የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን የተደባለቀ ብሔረሰብ/ የጎሳ ማንነት ያላቸው ናቸው። በጎሳ ማንነት ላይ የተመሠረተው የፖለቲካ ስርአታችን ለእነዚህ ሁሉ ዜጎች የአካታችነት ቦታ የለውም።
አንድ የኦሮሞ አባት መመረጥ ስለማይችለው የልጃቸው ባል ሲነግሩኝ ‹‹ተዋልደናል፣ አንድ ነን የምንለው ለካስ ውሽት ነው፣ የእኔን ልጅ ያገባ ሰው እዚህ ተመርጦ እኛን ካላገለገለ መዋለዳችን ምንድነው ትርጉሙ።›› ብለውኝ ነበር። ስር የሰደደው የፖለቲካ ሴራ የገባቸው እየቆየ ነበር። ሰሞኑን በተደረገው የአገር የሽማግሌዎች ስብሰባም አንድ የኦሮሞ እናት ‹‹ልጆቼ አማራ ነው ያገቡት፣ በዚህ መልክ የተጋባን እና የተዋለደን ሕዝብ ለማጣላት መሞከር ተገቢ አይደለም።›› በማለት ሲመክሩ ነበር።
በ21 ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ይህን የመሰለ የጨካኝ የጎሳ ፖለቲከኞች ሰለባ ስንሆን ከጥቂት ባለውለታ ምኁራን በቀር ደፍረው ‹‹ይህ ፖለቲካችሁ ትክክል አይደለም›› በማለት በየአደባባዩ ሲናገሩ የኖሩት የአገር ሽግሌዎች ብቻ ናቸው ለማለት ይቻላል።
አንዳንድ የአገር ሽማግሌዎች ‹‹ከእናንተ መማር የእኛ መሀይምነት ይሻላል›› በማለት በምሁራኖቻችን ላይ ይሳለቃሉ፣ አሁንም ይህንኑ የሚናገሩ አሉ። አንድ አንጋፋ የአገር ተቆርቋሪ አዛውንት ኢትዮጵያ የተረገመችው በምሁራኖቿ አማካኝነት ነው ይሉ ነበር። አንዱ ችግር በመፍጠር፣ ሌላው በማባባስ፣ ሌላው ዝም በማለት ሁላችንም ለትውልድ የሚተርፍ መዘዝ ስናመጣ ማንም ለሽማግሌዎቻችን ተማጽኖ እና ምክር ጆሮ አልሰጠም። እያደር ቢገባንም በግልጽ ይቅርታ የጠየቀም ሆነ ለውለታቸው እውቅና የሰጠ የለም። አሁን ግን ያ ጊዜ እየቀረበ ይመስላል። ከፖለቲከኞቻችን በፊት እነሱ እያሻገሩን የመጡ ለመሆኑ የሚካድ አይመስለኝ።
እነዚህ ሁኔታዎች የሚከተለውን ጥያቄ ሊያሳስቡ ይገባል ብዬ አስባለሁ። የአገር ሽማግሌዎች በፖለቲካ አስተዳደር ስርዓታችን ውስጥ ምን ዓይነት አዎንታዊ ሚና እንዲኖራቸው ሊደረግ ይገባል? በሌላ አነጋገር ከግጭት በኋላ ‹አንተም ተው አንተም ተው› ከማለት ይልቅ በፖለቲካ ተሳትፎ እና በሰላም ግንባታ ውስጥ ጉልህ ሚና እንዲኖራቸው ምን ሊደረግ ይገባል የሚለውን ማሰብ ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ተቋማዊ እና ሕጋዊ መዋቅሮችን መመልከት ያስፈልጋል። በተለይ በአሁኑ ጊዜ ስለምርጫ ብዙ እየታሰበ ስለሆነ ከዚህ ጋር ተያይዞ ለወደፊቱ በሚኖሩ የፖለቲካ አስተዳደር መዋቅሮች ውስጥ የአገር ሽማግሌዎችን የፖለቲካ ውክልና ተሳትፎ ማሰብ ተገቢ ነው የሚል እምነት አለኝ።
የአገር ሽማግሌዎቹን ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ በማድረግ ውግንና አልባ የሆነ እና የሕዝብን እውነተኛ ፍላጎት አንጸባራቂ ሚና እንዲኖራቸው በማድረግ፣ ፖለቲከኞች ከሕዝብ ፍላጎት ብዙ እንዳይርቁ የመቆጣጠሪያ ስርዓትና የሕዝብንም ትክክለኛ ፍላጎት አሰባሳቢ (Public Interest Mobilizer) አድርገን ልንጠቀምባቸው እንችላለን። ምንም እንኳን በዴሞክራሲያዊ ምርጫ የተመረጡ የሕዝብ ተወካይ ፖለቲከኞች የሕዝቡን ፍላጎት በሚገባ የሚያንጸባርቁ እና የሚወክሉ ናቸው ሊባል ቢችልም፣ ሁሌም የሕዝብን ፍላጎት መሠረት አድርገው ያገለግላሉ ለማለት አይቻልም።
የውክልና ዴሞክራሲ ሁሌም የተወሰኑ እንከኖች እንዳሉበት በግልጽ የሚታወቅ ነው። በባህሪውም ሆነ በተግባር ፍጹም ዴሞክራሲ የሚባል ነገር የለም። በተለይ በብዙ ውስብስብ ፖለቲካዊ ፍላጎቶች በተተበተበው እና በተወጠረው የአገራችን ፖለቲካና ገና ባልተጀመረው የምርጫ ዴሞክራሲ ባህል ሁሉንም የፖለቲካ ውሳኔ ሰጪነት ሚና ለተመረጠው አካል መስጠት ተገቢ ላይሆን ይችላል። የዴሞክራሲ ባህላችን ስር እየሰደደ ሲመጣ እና የማኅበረሰባችን አስተሳሰብ የአገር ሽግሌዎችን ሚና እምብዛም የሚፈልግ አለመሆኑን ስናረጋግጥ፣ የምርጫ ሕጎቹን በማሻሻል የአገር ሽማግሌዎቹን ሚና መቀነስ ወይም ማስቅረት ይቻላል።
በአንዳንድ አገሮች እንደታየው የማኅበረሰብ ባህላዊ መዋቅሮች ከዘመን ጋር ሊከስሙ መቻላቸው ተፈጥሮአዊ የማኅበረሰብ እድገት ውጤት ነው። እስከዚያው ግን የፖለቲካ ውሳኔውን ሕዝባዊ ተቀባይነትና ተስማሚነት የሚመዝን እና ይሄ ነገር ቢታሰብበት የሚል፣ አንዳንድ ጊዜም በፓርቲዎች መካከል ፍትጊያ ሲበዛ የሚሸመግሉና የሚያግባቡ፣ ወደ ሕዝቡ እውነተኛ ፍላጎት የሚወስዱና የሚያሳምኑ የአገር ሽማግሌ ተወካዮች ያስፈልጋሉ። የዴሞክራሲ ምኅዳሩ ሲሰፋ በፖለቲከኖች መካከል አለመግባባት መከሰቱ የማይቀር ሊሆን ስለሚችል በዚያም ውስጥ የሽማግሌዎች ሚና ከፍተኛ ይሆናል።
ከዚህ በኋላ የሚነሳው ጉዳይ የአገር ሽማግሌዎቹ የፖለቲካ ተሳትፎ ውክልና በምን መልክ ይደረግ የሚለው ነው። ሕገ መንግሥቱ ያስቀመጠው የፌዴራል ፓርላማ የምርጫ ስርዓት የግድ ተፈጻሚ መሆን ስላለበት ለሚቀጥለው ምርጫ ምንም ለውጥ ማድረግ አይቻልም። ሕገ መንግሥቱ ሲሻሻል ግን ከፓርላም ወንበር ላይ የተወሰኑት ወንበሮች በአገር ሽማግሌነት ለሚመረጡ አንዲሆን ተደርጎ የምርጫ ሕጉ ቢቀመር ይጠቅማል።
የክልል ምክር ቤቶች እና በየደረጃው ያሉ የዞን እና የወረዳ ምክር ቤቶች፣ የከተማ አስተዳደር ምክር ቤቶችን (city councils) በተመለከተ ግን ክልሎች የየራሳቸውን የምርጫ ሕግ ማውጣት ስለሚችሉ ሕጉን በማውጣት የአገር ሽማግሌዎች እንዲወከሉ ማድረግ ይችላሉ። ለምሳሌ የተወሰኑ የአገር ሽማግሌዎች በእጩነት እንዲቀርቡ አድርጎ ከነሱ መካከል የተወሰነ እንዲመረጥ ማድረግ ይቻላል። በዚህ መሰረት ከምክር ቤቶቹ መቀመጫዎች የተወሰኑት በሽማግሌዎች እንዲያዙ ማድረግ ጠቃሚ ነው። ምክር ቤቱንም ከብዛት ይልቅ የጥራት ስብጥር አንዲኖረው ስለሚያስችል ልማዳዊ ከሆነው ድምጽ ሰጥቶ ከመውጣት አዙሪት እንዲወጣ ያስችለዋል።
የፖለቲካ ፈቃደኝነቱ ካለ ዝርዝር የምርጫ ሕጉ እነዚህንና ሌሎችንም የፖለቲካ ፍላጎቶች አካትቶ እንዲቀረጽ ማድረግ ይቻላል። ለምሳሌ ክልሎች የፌዴራሉን የምርጫ ሕግ ስርአት ከመጠቀም ይልቅ የራሳቸውን የምርጫ ሕግ በማውጣት የተመጣጠነ ውክልና ያለው የምርጫ ስርዓት (proportional representation) ወይም ከራሳቸው ነባራዊ ሁኔታ እና ፍላጎት ጋር የተጣጣመ ሌላ የምርጫ ስርዓት ለመጠቀም ይችላሉ። በተለይ ከፍተኛ የድህነት እና የመገፋት ችግር ሰለባ ሆኖ ለኖረው የአማራ ክልል፣ ይህ መፍትሄ በፍጥነት ተግባራዊ ተደርጎ የመራጩ ድምጽ የማይባክንበት አካካሽ የፖለቲካ ተሳትፎ ስርአትን ተግባራዊ ማድረግ ይገባል።
የከተማ አስተዳደሮችንም በተመለከተ የትኛው የከተማ አስተዳደር ዘይቤ ለዚያ ከተማ አስተዳደር የበለጠ ይጠቅማል በሚል አጥንቶ ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል። ሁሉንም ከተሞች በተመሳሳይ የአስተዳደር ዘይቤ እያስተዳደሩ ስለመቀጠል ማሰብ ተገቢ አይደለም። መሸከም ከምንችለው በላይ ሥራ አጥ ወጣት ባለበት አገር ከተሞችን በፍጥነት ልናሳድግና አዳዲስ ከተሞችን ልንመሠርት የምንችለበትን ስርዓት አለማሰብ አደጋው የከፋ ነው። ለዚህም የአገር ሽማግሌዎችን በከተማ አስተዳደር ምክር ቤቶች ውስጥ አሳታፊ ማድረግና ተገቢ የአቃፊነት ፖለቲካ ማራመድ የግድ ነው።
እስከዛሬ የከተሞች መሬት በማን አለብኝነት ሲዘረፍ ድምጽ አልባ ሆነው ያዘኑት እና የተከዙት የአገር ሽማግሌዎች ነበሩ። ለእነርሱ ተቆርቋሪነት ትንሽ እንኳን ዋጋ ተሰጥቶ ቢሆን ኖሮ ለሕዝብ ጥቅም የሚተርፍ ትንሽ ሀብት አይታጣም ነበር። ይሁን እንጂ እነዚህ ሁኔታዎች እስከአሁን ብዙም የታሰበባቸው ባይመስሉም፤ አሁን ካለው የፖለቲካ ሁኔታ አንጻር ግን ትኩረት ሊሰጣቸው እና የተሻለ የሕዝብ ውክልና እንዲኖር የሚያስችል የምርጫ ስርአትን ስለመከተል ማሰብ ያስፈልጋል።
የአገር ሽማግሌዎች ሚና በጣም አስፈላጊ የሚሆነው ከክልል ጀምሮ ባሉት መዋቅሮች ስለሆነ ክልሎች በምክር ቤቶቻቸው እና በከተማ አስተዳደር ም/ቤቶቻቸው ቢሞክሩት ይመከራሉ። ከዚህ በተጨማሪ ጠቃሚ የሆኑ ባህላዊ ሕጎችንም እንደየ ሁኔታው በሥራ ላይ ለማዋል እና ዘመናዊው የአስተዳደር ስርአት ከባህላዊው የአስተዳደር ስርአት ጋር ስር እየሰደደ ተጣጥሞ እንዲፈጸም እድል ይሰጣል።
የምዕራቡ የዴሞክራሲ አስተሳስብ ለአፍሪካ አይሠራም ሲባል መስማት የተለመደ ነው። በእርግጥ በአፍሪካ ያለው ችግር ዴሞክራሲውን ያለመቀበል እንጂ ዴሞክራሲ በራሱ ችግር ኖሮበት አይደለም። ይሁን እንጂ ሌላው እውነታ የዴሞክራሲ ስርዓቱን ከየአገሩ ባህላዊ የአስተዳደር ስርአት ጋር አጣጥሞ አገርን በተረጋጋ እና ተቀባይነትን ባገኘ ሁኔታ እንዴት ማስተዳደር ይቻላል የሚለው ላይ ትኩረት ሰጥተን ስለማንሠራ ነው የሚል እምነት አለኝ።
በአብዛኛው የአስተሳሰብ መሰረቱ ባህላዊ በሆነ አገር ውስጥ፣ ሙሉ በሙሉ ዘመናዊ የምርጫ እና የአስተዳደር ስርዓትን ለመከተል መሞከር በኹለቱ መካከል ግጭት ሲፈጠር ለማስታረቅ እየተቸገርን ኖረናል። ይህን ሁኔታ ለመቀየር ለየት ያለ አቀራረብን መከተል አስፈላጊ ነው። በዚህ መሰረት ትልቅ የስብእና ዋጋ ያላቸውን የአገር ሽማግሌዎቻችንን ችግር ከተፈጠረ በኋላ ብቻ ከምንፈልጋቸው ከላይ በተመለከተው ሁኔታ በፖለቲካ ውሳኔ አሰጣጥ ሒደት ውስጥ እንዴት ሊሳተፉ ይገባል ለሚለው ጥያቄ መልስ በመስጠት የተሻለች ኢትዮጵያን ስለማየት ማሰብ አለብን።

አበበ አሳመረ
የሕግ አማካሪ እና ጠበቃ ናቸው።

ቅጽ 2 ቁጥር 58 ታኅሣሥ 4 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here