ቸልታ ያለባበሰው ኤች አይ ቪ

0
1352

ኤች አይ ቪ ኤድስ በኢትዮጵያ እንዲሁም በዓለም ደረጃ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሶ የነበረበት፣ የበርካታ ወጣቶች ሕይወት እየረገፈ የነበረበት ጊዜ ካለፈ ብዙ ዓመታት የተቆጠሩ ይመስላል። ነገር ግን ባለሥልጣናት፣ የኪነጥበብ ሰዎች፣ ተጽእኖ ፈጣሪ የሆኑ ግለሰቦች ሳይቀሩ በጋራ ‹ማለባበስ ይቅር› ‹መላ መላ› ብለው አገር ሲቀሰቅሱና ‹ይብቃ!› ሲሉ የነበረበት ጊዜ ካለፈ 12 ዓመት እንኳ የሚሞላ አይደለም።
ስለቫይረሱ የታየው ዝምታም ብዙዎች ቫይረሱ የጠፋ ያህል እንዲሰማቸው አድርጓል። ሆኖምቀላል የማይባል ቁጥር ያለው ወጣት አሁንም በቸልታ በተለባበሰው ቫይረሱ ምክንያት ሕይወቱን እያጣ ይገኛል። እንደውም አሁን ያለበት ስርጭት በወረርሽ ደረጃ ሊጠራ የሚችል እንደሆነም መገናኛ ብዙኀን አቅርበውት የነበረ ጉዳይ ነው። ይህን መነሻ በማድረግ፣ የተለያዩ ዘገባዎችን በማገላበጥና የሚመለከታቸውን በማነጋገር የአዲስ ማለዳው በለጠ ሙሉጌታ ጉዳዩን የሐተታ ዘማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎታል።

መንደርደሪያ
ኤች. አይ. ቪ. በሰው ልጆች ሰውነት ውስጥ የሚገኙ በሽታ ተከላካይ የሆኑ ነጭ የደም ሴሎችን በተለይም ‹ሲዲፎር ሊንፎሳይትስ› የተባሉትን በማጥቃት እና ቁጥራቸውን በመቀነስ የሰውነትን በሽታ የመከላከል አቅም በማዳከም ሰዎችን ለሌሎች በቀላሉ ሊድኑ የሚችሉ በሽታዎች በማጋለጥ፣ ለሞት የሚዳርግ እና ሰዎችን ብቻ የሚያጠቃ ቫይረስ ነው።
የቫይረሱ አስከፊ ገፅታ ሰዎች በቫይረሱ ከተጠቁ በኋላ እንኳን ለበርካታ ዓመታት ምልክት አለማሳየቱ ነው። ከጊዜ ሒደት በኋላም በሰውነት ውስጥ በመስፋፋት ተጠቂውን በማዳከም ለበርካታ ህመሞች እና የጤና እክሎች በመዳረግ ያዳክመዋል። በዚህን ጊዜ ነው፤ ታማሚው የሰውነት የበሽታ መከላከል አቅሙን አጥቶ የኤድስ ታማሚ ሆነ የሚባለው።
ጥንቃቄ የጎደለው ልቅ የግብረ ሥጋ ግንኙነት፤ ኤች. አይ. ቪ. ካለባት እናት ወደ ፅንስ እና በደም አማካኝነት ማለትም በኤች.አይ.ቪ የተያዘ ሰው ደም እንዲሁም ሌሎች የሰውነት ፈሳሾች ንክኪ ቫይረሱ ከሰው ወደ ሰው ከሚተላለፍባቸው መንገዶች ጥቂቶቹ ናቸው።
በተለይም ታማሚው የቫይረሱ ተጠቂ መሆኑን በምርመራ አረጋግጦ ተገቢውን ጥንቃቄ እስካላደረገ ድረስ፣ በሽታውን ከሰው ወደ ሰው የማስተላለፍ አቅሙ በከፍተኛ ደረጃ ይጨምራል።
አሁን ዓለማችን የደረሰችበት የሕክመና ጥበብ አንዴ በቫይረሱ የተጠቃ ግለሰብን ሙሉ በሙሉ ለመፈወስ የሚያስችሉ መድኀኒቶችም ሆኑ የሕክመና ዘዴዎች ማስገኘት አለመቻሉ፣ የቫይረሱ አስከፊ ገፅታ ተደርጎ ይነሳል።
በዚህ ቫይረስ ምክንያትም በርካታ ጎጆዎች ፈርሰዋል፣ ቤተሰብ ተበትኗል፣ ልጆች ያለ አሳደጊ ቀርተዋል። ባለፉት ዓመታት በተሠሩ በርካታ ሥራዎች ስለ ቫይረሱ መፍጠር በተቻለው ግንዛቤ፣ አበረታች ውጤቶችን ማግኘት ተችሎ የነበረ ቢሆንም፣ ከጥቂት ጊዜያት ወዲህ የተፈጠረውን መቀዛቀዝ መነሻ አድርጎ በኢትዮጵያ የስርጭት መጠኑ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሶ ይገኛል።
ቫይረሱ በዓለማችን
ቫይረሱ በዓለማችን በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1980ዎቹ እንደተከሰተ ብዙዎች ይስማማሉ። ታዲያ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከ 74 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል። ከእነዚህ ውስጥም ወደ 32 ሚሊዮን የሚጠጉት ከቫይረሱ ጋር ተያይዘው በሚመጡ በሽታዎች መተኪያ የሌለው ሕይወታቸውን አጥተዋል።
በመገባድድ ላይ እስከሚገኘው የፈረንጆቹ ዓመት ድረሰም 38 ሚሊዮን ሰዎች ከቫይረሱ ጋር ሲኖሩ፣ 36 ሚሊዮን የሚሆኑት በአዋቂነት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ጎልማሶች ናቸው። 1.7 ሚሊዮን የሚሆኑት ዕድሜያቸው ከ 15 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት ሲሆኑ፣ የተቀሩት ቫይረሱ በደማቸው መኖሩን እንኳን በምርመራ ያላረጋገጡ መሆናቸውን የዓለም ዐቀፉ የጤና ድርጅት መረጃ ይጠቁማል። በዚሁ ዓመት ውስጥም ከ 700 ሺሕ በላይ ሰዎች በቫይረሱ ምክንያት ለሞት ተዳርገዋል።
በእየ ዓመቱም 1.7 ሚሊዮን ሰዎች እንደ አዲስ በቫይረሱ ይያዛሉ የሚለው መረጃው፣ ከእነዚህ ከቫይረሱ ጋር ከሚኖሩ ሰዎች ውስጥ ወደ 25 ሚሊዮን የሚጠጋ ቁጥር ያላቸው ሰዎች የፀረ ኤች አይ ቪ መድኀኒቶችንና አስፈላጊ ሕክምናዎችን እንደሚከታተሉ ያሳያል።
በእያንዳንዱ ሳምንትም 6 ሺሕ የሚሆኑ ዕድሜያቸው ከ 15 እስከ 24 የሚሆኑ ወጣት ሴቶች እንደ አዲስ በቫይረሱ ይያዛሉ። በተለይም ከሰሃራ በረሃ በታች በሚገኙ የአፍሪካ አገራት ተስፋፍቶ የሚታየው በሴቶች ላይ የሚፈፀም ጥቃት፣ ሴቶች ለቫይረሱ ተጋላጭ እንዲሆኑ እንዳደረጋቸው ዓለም አቀፍ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በዓለማችንም 35 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች በሕይወት ዘመናቸው ቢያንስ አንድ ጊዜ አካላዊ እንዲሁም ተገዶ እንደመደፈር ያሉ ጥቃቶች እንደሚገጥሟቸው የዓለም አቀፉ የጤና ድረጅት መረጃ ያትታል።
የዓለማችንን ስድስት በመቶ የሚሆነውን የሕዝብ ቁጥር የምትይዘው አፍሪካ፣ ከ 20 ሚሊዮን በላይ ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ሰዎችን ይዛ ትገኛለች። ይህ አሃዝ ከአጠቃላይ የዓለማችን የ ቫይረሱ ተጠቂዎች 54 በመቶ የሚሆኑት በአፍሪካ እንደሚገኙ ያሳያል። በእያንዳንዱ ዓመትም 800 ሺሕ ሰዎች በኤች አይ ቪ ይያዛሉ።
በወሲብ ንግድ ላይ የተሰማሩ እና ከተመሳሳይ ጾታ ጋር ወሲብ የሚፈፅሙ ሰዎች እንዲሁም አደንዛዥ እፆችን መርፌ በመውጋት የሚጠቀሙ ግለሰቦች በዓለማችን ከሌሎች ሰዎች በተለየ መልኩ ተጋላጭ እንደሚሆኑ የተለያዩ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ኤች. አይ. ቪ. በኢትዮጵያ
ኤች አይ ቪ በአገር አቀፍ ደረጃ የስርጭት መጠኑ 0.91 በመቶ ላይ ይገኛል። ዓለም ዐቀፉ የጤና ድርጅት በሚያስቀምጠው መለኪያ፣ በአንድ አገር ውስጥ የስርጭቱ መጠን ከ አንድ በመቶ ሲዘል ቫይረሱ በወረርሽኝ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ያስገነዝባል።
በኢትዮጵያ ቁጥራቸው ጥቂት በማይባሉ ክልሎች ከ አንድ በመቶ የዘለለ የስርጭት መጠንን በማስመዝገብ ላይ መገኘታቸው ቫይረሱ ድምፁን አጥፍቶ የነገ አገር ተረካቢ እና ባለተስፋ የሆኑ ወጣቶችን በገፍ እየጨፍጨፈ እንደሆነ ማሳያ ነው።
የበሽታው ስርጭት በአገር ደረጃ ከ አንድ በመቶ በታች ምጣኔ ይኑረው እንጂ፣ በክልል ከተሞች አሁንም ስጋት በሚፈጥር ደረጃ በመስፋፋት ላይ ይገኛል። ለዚህም ማሳያ የሚሆነው እንደ ጋምቤላ ባሉ ክልሎች እስከ 4.8 በመቶ፣ በአዲስ አበባ ከተማ 3.4፣ የትግራይና የአማራ ክልል እያንዳንዳቸው 1.2 በመቶ የስርጭት ምጣኔ ይዘው መገኘታቸው ነው።
እንዲሁም በድሬዳዋ፣ የሐረር፣ የአፋርና የቤንሻንጎል ጉሙዝ ክልሎች ኤች አይ ቪ በወረርሽኝ ደረጃ ላይ አይገኝ እንጂ፣ አሁንም በርካታ ሰዎች በ ኤች አይ ቪ እየተተቁ እንደሚገኙ የፌዴራል የ ኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ጽሕፈት ቤት ይገልጻል።
የኤች አይቪ ስርጭት በክልል ደረጃ ሲታይ በስርጭት መጠን በመቶኛ ከፍ ያለ ቁጥር ተመዝግቦባቸዋል። ይሁንና ኢትዮጵያ አሁንም በወረርሽኝ ደረጃ ላይ አይደለም የምትገኘው ሲሉ የ ኤች አይ ቪ ኤድስ መከለከያ እና መቆጣጠሪያ ጽሕፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ዳንኤል በትረ ገልፀዋል።
በአጠቃላይም ከ640 ሺሕ በላይ የሚሆኑ ዜጎች ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝ ሲሆን፣ በእየ ዓመቱም 23 ሺሕ የሚሆኑ ሰዎች እንደ አዲስ ይያዛሉ። ቁጥራቸው ከ 11 ሺሕ የሚዘሉ ደግሞ ሕይወታቸውን በማጣት ላይ ይገኛሉ።
ለስርጭቱ መስፋፋትም ከዚህ ቀደም ለበሽታው ሲሰጠው የነበረው ትኩረት መቀነሱ ኅብረተሰቡ የኤች አይ ቪን ጉዳይ እንዲተወው አድርጎታል። አንዳንዶች እንደውም በሽታው ስለመኖሩም እንዲዘነጉት ሆነዋል። በተለይ ወጣቱ የማኅበረሰብ ክፍል ከ በሽታው ይልቅ እርግዝናን የሚፈራ መሆኑ፤ እንዲሁም በ ወሲብ ንግድ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ሴቶች ‹ሙሉ እድሜን ተቸግሮ ከመኖር አጭር እድሜን በደስታ ማሳለፍ ይሻላል› የሚል አስተሳሰብ ውስጥ መግባታቸው፣ በምክንያትነት እንደሚጠቀስ በበሽታው ላይ የሚሠሩ ተቋማት ይገልጻሉ።
ለአብነትም አዲስ አበባ ከተማ የኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ጽሕፈት ቤት በከተማዋ ባደረገው ጥናት እድሜያቸው ከ 15 ዓመት እስከ 24 ዓመት የሚሆናቸው ወጣቶች ተጋላጭነት መጨመሩን ያሳያል። ለዚህም በምክንያትነት የተጠቀሰው ስለ በሽታው ያለው ግንዛቤ አናሳ መሆን ነው ሲሉ የጽሕፈት ቤቱ ዘርፈ ብዙ ምላሽ ዋና ኀላፊ ፈለቀች እንግዳ ይገልፃሉ። አብዛኛው ወጣት የቫይረሱን መተላለፊያ መንገዶች ቢያውቅም፣ ስለ ቫይረሱ ያለው ግንዛቤ የሚገጥሙትን በርካታ ፈተናዎች እንዲቋቋም የሚያደርግ አይደለም ይላሉ።
ከዚህ በተጨማሪም በመዲናዋ እና በክልል ከተሞች የሚገኙ ሕገ ወጥ የወሲብ ንግድ የሚከናወንባቸው ቡና ቤቶች፣ ሆቴሎች፣ ማሳጅ ቤቶች፣ ሺሻ ቤቶች እንዲሁም የእንግዳ ማረፊያዎች ቁጥር መጨመሩ ቀላል የማይባል አስተዋፅኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
‹‹ተጋላጭ የሆኑትም በእነዚህ ሆቴሎች እና ቡና ቤቶች በወሲብ ንግድ ላይ የተሰማሩ ሴቶች ናቸው›› የሚሉት ፈለቀች፣ በጉልበት ሠራተኝነት የሚሠሩ ወጣቶች፣ የታክሲና የረዥም ርቀት አሽከርካሪዎች፣ ከትዳር አጋሮቻቸው የተለያዩ አልያም አንደኛው የትዳር አጋር በቫይረሱ የተጠቃ መሆን፣ ከገጠር ወደ ከተማ የተሻለ ኢኮኖሚያዊ አማራጭን ፍለጋ ከሚከናወን ፍልሰት ጋር ተዳምሮ ችግሩን አሳሳቢ አድርጎታል።
በአዲስ አበባም በ 52 ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ 90 መንደሮች ተለይተው ይገኛሉ። እነዚህ መንደሮችም ከገጠራማ አካባቢዎች የሚመጡ ሰዎች የሚገኙባቸው እንዲሁም የምሽት ጭፈራ የሚዘወተርባቸው፣ የወሲብ ንግድ የተስፋፋባቸው እንደሆኑ ጽሕፈት ቤቱ ይገልጻል።
ጥንቃቄ የጎደለው የወሲብ ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ መምጣቱን በጥናቱ ውስጥ መታየቱን የሚናገሩት ኀላፉዋ፣ ይህም ከትዳር ውጪ እንዲሁም በወሲብ ንግድ ከተሰማሩ ሴቶች ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት መፈፀምን ያካትታል ይላሉ። ይህም ለትዳር አጋር ታማኝ የመሆን ሁኔታ እየቀነሰ መምጣቱን የሚያመላክት ነው።
ከዚህ በተጨማሪም በኅብረተሰቡ ዘንድ ስለ ቫይረሱ ያለው አመለካከት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መጥቷል። በተለይም ከ 1995 በኋላ በተሠሩ ሰፊ ሥራዎች እና የፀረ ኤች አይ ቪ መድኀኒቶች መምጣት ብሎም ሕክምና መጀመር ያመጣው ለውጥ፣ በቫይረሱ ምክንያት የሚከሰትን የሞት መጠን ከ 70 በመቶ በላይ ቀንሶ ነበር። ይህ መሆኑም በሽታው የለም የሚል አመለካከትን ፈጥሯል የሚሉት ፈለቀች፣ ከመገናኛ ብዙኀኑ እና የመንግሥት ተቋማት ዝምታ ጋር ተዳምሮ ችግሩን የተዳፈነ እሳት አድርጎታል ሲሉ አብራርተዋል።
ተጋላጭ ናቸው ተብለው በተገመቱ አካባቢዎች ላይ ሰዎች የኤች ኣይ ቪ ምርመራ እንዲያደርጉ ለማድረግ እና ሰዎች ራሳቸውም አውቀው ህክምና እንዲጀምሩ ለማድረግ እየተሠራ ሲሆን፣ በ 2011 ከ 374 ሺሕ በላይ ሰዎች ምርመራ እንዲያደርጉ ተደርጓል። ከእነዚህም ውስጥ 9 ሺሕ የሚሆኑት ቫይረሱ በደማቸው በመገኘቱ የሕክምና ክትትል እንዲጀምሩ መደረጉ ተገልጿል።
በሽታው የብዙዎችን ሕይወት በቀጠፈበት ወቀት ለመቁጠር በሚያዳግት መልኩ ኅብረተሰቡን ሲወተውቱ እና ሲያሳሰቡ የነበሩ እንደ ፊልም፣ ሙዚቃ፣ የቴሌቪዥን ማስታወቂያዎች ከቅረብ ዓመታት ወዲህ ተቀዛቅዘው ከነአካቴውም ዝም ብለዋል በሚባልነት ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ግንዛቤ ለመፍጠር ጉልህ ሚና የነበራቸው እነዚህ የኪነ ጥበብ ውጤቶች፣ በአዲስ መልክ ባይሠሩ እንኳ የተዘናጋውን ንቃ ለማለት ያህል በድጋሚ ሲሰራጩ አይስተዋልም።
ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ወገኖች ድምፅ
አሁን ላይ ስለ ኤች አይ ቪ በቂ ግንዛቤ የሌላቸው፤ አልፎም ምንም ግንዛቤ የሌላቸው ሰዎች አሉ። ለዚህ ማሳያ ሊሆኑ ከሚችሉ ነጥቦች መካከል የአንዲት ሴት ታሪክ አለ፤ በ ወሲብ ንግድ ሥራ ላይ ተሠማርታ የምትገኘው መሠረት አለባቸው (ስሟ የተቀየረ)። መሠረት በዚህ ሥራ ውስጥ በርካታ ዓመታትን ቆይታለች፤ ሆኖም ግን ስለ ኤች አይ ቪ ም ሆነ ስለ ኮንዶም ምንም ግንዛቤ አልነበረኝም ትላለች። አልጠየቀችም፣ የነገራትም የለም።
በአንጻሩ ሌላኛዋ በዚሁ ሥራ የተሰማራች ወጣት መቅደስ ኀይሉ (ስሟ የተቀየረ)፣ ግንዛቤው ቢኖረኝም ከመደበኛው ክፍያ ጨምሮ የሚከፍል ከመጣ ያለ ኮንዶም ግንኙነት እፈጽም ነበር ስትል በግልጽ ትናገራለች። ‹‹በአንድ ወቅት ግን በጣም ታመምኩ፤ በሰውነቴ ላይም ቁስል መሰል ነገር መውጣት ጀመረ›› የምትለው መቅደስ፣ በጓደኛዋ አማካኝነት ፖፑሌሽን አትዮጵያ ወደ ተባለ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት በመሔድ ምርመራ ማድረጓን ትገልፃች።
‹‹ቫይረሱ በደሜ ውስጥ እንደሚገኝ ሲነገረኝ አላመንኩም ነበር›› ስትልም ሁኔታውን ለአዲስ ማለዳ አስታውሳለች።
በ ፖፑሌሽን ኢትዮጵያ በኩልም መድኒኀቱን መከታተል መጀመሯን የምትገልፀው መቅደስ፣ ከሥራው መላቀቅ ባትችልም የነፃ የፀረ ኤች አይ ቪ መድኀኒት፣ ኮንዶም እንዲሁም የምክር አገልግሎት እንደምታገኝ እና አሁን በመልካም ሁኔታ ላይ እንደምትገኝ ጠቅሳለች።
ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥሩ እየቀነሰ ይምጣ እንጂ ከቫይረሱ ጋር በሚኖሩ ሰዎች ላይ የሚደርሰው መገለል እና መድሎም፣ ጥርጣሬው ያላቸው ሰዎች እንኳን ወደ ጤና ተቋማት ሔደው ምርመራውን እንዳያደርጉ ስጋት እየሆነ ይገኛል።
መቅደስ እንደምትለው በ ፖፑሌሽን ኢትዮጵያ የሚሰጠው አገልግሎት ለችግሩ በይበልጥ ተጋላጭነት ባላቸው ሴተኛ አዳሪዎች ላይ በመሆኑ ያለምንም መሳቀቅ አገልግሎት ታገኛለች። እናም በሌሎች የሕክምን ተቋማት ጋር ብሔድ መገለል ይደረስብኛል ከሚል ስጋት ነፃ መሆኗንም ትናገራለች።
ኤች አይ ቪ በሴቶች ሕፃናት እና ወጣቶች ላይ
በኢትዮጵያ የሴቶች ተጋላጭነት 62 በመቶ፣ በወንዶች 38 በመቶ እንዲሁም በሕፃናት 9 በመቶ ላይ ደርሶ ይገኛል። እንደ ግርዛት፣ ያለእድሜ ጋብቻ እና ጠለፋ ያላቸው አስተዋጽኦ ቀላል የሚባል አይደለም።
ከ20-24፤ ከ25-29፤ ከ35-39 ዕድሜ ክልሎች ውስጥ የሴቶቹ ተጋላጭነት ከወንዶቹ በሦስት ዕጥፍ ከፍ ብሎ ይስተዋላል። በተጓዳኝ ከ15-19 እና ከ30-34 ባለው የእድሜ ክልል ደግሞ 4 ዕጥፍና ከዚያ በላይ በሆነ መጠን የሴቶቹ ተጋላጭነት ከወንዶቹ የላቀ ሆኖ ይታያል።
‹‹ለቫይረሱ ከወንዶች ይልቅ ሴቶች በይበልጥ ተጋላጭ ናቸው›› የሚሉት በኢፌዴሪ ሴቶች፣ ሕፃናት እና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ኤች ኣይ ቪ መከላከል እና መቆጣጠር ባለሙያ ያሬድ ዳኜ ናቸው። እርሳቸው እንደሚገልፁት፣ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች፣ ማኅበራዊ ቀውሶች እና ጎጂ ባህላዊ ድርጊቶች ሴቶችን ለቫይረሱ ይበልጥ ተጋላጭ እንዲሆኑ አድርጓል።
በኢትዮጵያ እንደየአካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ ከ140 በላይ የሚሆኑ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በስፋት እንደሚታዩ የሚገልፀው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ፣ ድርጊቶቹ በሴቶችና ሕጻናት ላይ እንደሚፈጸሙ በዋናነት ከሚጠቀሱት መካከልም የሴት ልጅ ግረዛት፤ ያለእድሜ ጋብቻ፤ ጠለፋ፤ የውርስ ጋብቻ፤ በሴቶች ላይ የሚደርስ የወሲብ ጥቃት ይጠቀሳሉ።
ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረገው ፍልሰት በከተማው ካለው ከፍተኛ የሥራ አጥ ቁጥር ጋር ተዳምሮ፣ በርካታ ሴቶች ወደ ወሲብ ንግድ ሥራ እንዲገቡ ምክንያት ሆኗቸዋል። በዚህ ሥራ ላይ በተሠማሩ ሴቶች ላይም የቫይረሱ ስርጭት 23 በመቶ ደርሷል።
ተመርምረው ከቫይረሱ ጋር መኖራቸውን ያረጋገጡ ሕፃናት ቁጥርም ከ9 ሺሕ ላቅ ይላል። ከእናት ወደ ልጅ የመተላለፍ እድልን ለመቀነስ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ቢገኙም፣ አሁንም በሕክመና ተቋማት ክትትል እና ምርመራ አድርገው የሚወልዱ እናቶች ቁጥር ከ 60 በመቶ አይዘልም።
በኢትዮጵያም የኤች ኣይ ቪ ምርመራን ሰዎች ታመው ወይም ለሌላ የጤና ጉዳይ ወደ ጤና ተቋማት ብቅ ባሉበት አጋጣሚ ምርመራውን እንዲያደርጉ የመገፋፋት አሰራር ነው ያለው የሚሉት ያሬድ፣ በገጠራማ እና ምርመራውም ሆነ ሕክመናው ባልተስፋፋባቸው አካባቢዎች የሚወለዱ እናቶች በከተሞችም ቢሆን በግል የሕክመና ተቋማት የእርግዝና ክትትል የሚያደረጉ ሴቶች በእርግዝና ወቅት ምርመራውን አያደረጉም ይላሉ። አክለውም ‹‹የግል የሕክመና ተቋማት ሴቶቹ ምርመራውን እንዲያደረጉ አይገፋፉም፤ ይህም የቫይረሱን ስርጭት የመቆጣጠሩን ሥራ አስቸጋሪ አድርጎታል›› ሲሉ ገልጸዋል።
ባለሙያው ሲቀጥሉም፣ በተደረጉ ጥናቶች ስለ ቫይረሱ በኅብረተሱቡ ዘንድ ያለውን ግንዛቤ ለመለካት ጥናች ተደርገዋል። ‹‹በእነዚህም 38 በመቶ የሚሆኑ ወንዶች እና 28 በመቶ ሴቶች ብቻ ስለ ቫይረሱ የተሟላ ግንዛቤ ያላቸው ሆነው ተገኝተዋል›› ይላሉ። ይህም ባለፉት 10 እና 15 ዓመታት የተፈጠረው መዘናጋት፣ በዛን ጊዜ ህፃናት የነበሩ ልጆች አሁን የወጣትነት እድሜን ሲቀላቀሉ፣ ስለ ኤች አይ ቪ በቂ ግንዛቤ ሳይዙ እንዲያድጉ አንዳደረጋቸው አብራርተዋል።
በአዲስ አባባ ከተማ ብቻ ከ 100 በላይ የወጣት ማዕከላት ቢኖሩም፣ የተሟላ የሥነ ተዋልዶ ትምህርት የሚሰጡ አነስተኛ ክሊኒኮች እንኳን የሌላቸው ናቸው።
ወጣቶች ጊዜያቸውን በጫት ቤቶች እና በጭፈራ ቤቶች ማሳለፋቸው፣ አደንዛዥ ዕፅና ዕጾችን የመጠቀም ሁኔታ በከተማዋ በስፋት መኖሩ እንዲሁም ወጣቶች ወሲብ የሚጀምሩበት እድሜ ከ ጊዜ ወደ ጊዜ ዝቅ እያለ መምጣቱ በምክንያትነት ይነሳል። ቀደም ባሉ ጊዜያት ወሲብ የሚጀመረው በአማካይ በ17 እና 18 እድሜ ላይ አንደነበር በማንሳት፤ በአሁኑ ጊዜ ግን በአስራዎቹ መጀመሪያ ድርጊቱ እየተፈፀመ መሆኑ ወጣቶችን ይበልጥ ተጋላጭ አድርጓቸዋል።
መንግሥት እና የሚመለከታቸው ተቋማት ምን እየሠሩ ይሆን?
የዓለም አገራት በ አውሮፓውያኑ 2030 ኤች አይ ቪ ኤድስን የማቆም ርዕይ ሰንቀው በመሥራት ላይ ይገኛሉ። ኢትዮጵያም ይህንን ርዕይ ከግብ ለማድረስ በመሥራት ላይ ትገኛለች።
ከእነዚህ ግቦች መካከልም ‹‹ሦስቱ 90ዎች›› የሚል ሥያሜ የተሰጠው እና በቀጣይ ስምንት ዓመታት ቫይረሱ በደማቸው ከሚገኝ ሰዎች ውስጥ 90 በመቶ የሚሆኑት ተመርምረው ራሳቸውን እንዲያውቁ፣ ተመርምረው ቫይረሱ በደማቸው መገኘቱን ካወቁት ውስጥ ደግሞ 90 በመቶ የሚሆኑት የሕክመና ክትትል እንዲያገኙ ማድረግ፣ እንዲሁም ሕክምናውን ካገኙት ውስጥ 90 በመቶ የሚሆኑት የቫይረሱን ቁጥር በደማቸው ውስጥ በመቀነስ ረዥም ዕድሜ እንዲኖሩ ማድረግ የሚሉ ግቦችን ለማሳካት ሥራዎች በማከናወን ላይ ይገኛሉ።
መንግሥት እና የሚመለከታቸው አካላት ስለ ቫይረሱ ግንዛቤ ከመፍጠር ጀምሮ በደማቸው ለሚገኝ ወገኖች የፀረ ኤች አይ ቪ ኤድስ ሕክምና በማመቻቸት፣ በማማከር ሥራ ላይ እንደሚገኙ ይገልፃሉ።
አዲሰ አበባ ከተማ የኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ጽሕፈት ቤት በበኩሉ፣ በርካታ ጥናቶችን በማከናወን ላይ መሆኑን ይገልፃል።
ከዚህ በተጨማሪም የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን በማዘጋጀት በበሽታው ዙሪያ የተፈጠረውን መዘናጋት ለማስቀረት እና መንግሥታዊ እንዲሁም መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር የጋር ዕቅድ በማዘጋጀት የሕዝብ ግንኙነት ሥራዎችን ከ ስድስት በላይ በሚሆኑ መገናኛ ብዙኀን ጽሑፎችን እና ፕሮግራሞችን በማሠራጨት ላይ ይገኛል።
ከመንግሥት በተጨማሪ የተለያዩ በቫይረሱ ዙሪያ ግንዛቤ ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱ በውስጣቸው እድሮችን፣ ሲቪክ ማኅበራትን እና በርካታ ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን አቅፈው የሚገኙ ማኅበራት አሉ። ከእነዚህም ውስጥ በአዲስ አባባ እና በክልሎች በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኘውና በአዲስ አበባ ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝ ዜጎች ያቋቋሙት የማኅበራት ጥምረት አንዱ ነው።
በጥምረቱ ውስጥ ከ 19 ሺሕ በላይ ዜጎች በ 15 ማኅበራት ታቅፈው ይገኛሉ። ጥምረቱም ማኅበራቱን አቅም ለመገንባት እንዲሁም በማኅበራት ውስጥ ያሉ በጎ ፈቃደኞች ያላቸውን ልምድ እንዲያካፍሉ በማድረግ እና ሰዎች ተመርምረው ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ መኖር አለመኖሩን እንዲያውቁ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን፣ የማኅበሩ ኀላፊ ዕድላን ገብረሥላሴ ይገልጻሉ።
በአዲስ አበባ ከተማ 83 በሚሆኑ የጤና ተቋማት ላይ የ ኤች ኣይ ቪ ምርመራ እና የማማከር አገልግሎቶችን በመደገፍ ላይ የሚገኘው የማኅበራቱ ጥምረት፣ ‹‹በቫይረሱ የተያዙ ዜጎች የሕክመና ክትትል አግኝተው ረዥም እድሜ መኖር እንዲችሉ ማድረግን፣ በቫይረሱ ላልተያዙት ደግሞ ግንዛቤ ማስጨበጫዎችን በማዘጋጀት ራሳቸውን መከላከል እንዲችሉ ለማድረግ በስፋት እየተንቀሳቀስን ነው›› ሲሉ ዕድላን ገልፀዋል።
ፖፑሌሽን ሰርቪስ ኢትየጵያ ትኩረቱን በወሲብ ንግድ ስራ ላይ የተሰማሩ ሴቶች ላይ አድርጎ የሚሰራ መንግስታዊ ያለሆነ ድርጅት ሲሆን ለሴቶች ከነፃ የኤች አይ ቪ ምርመራ ቫይረሱ በደማቸው ለተገኘባቸው የህክመና ክትትል በአዲስ አባባ እና በአማራ ክልል በደሴ እንዲሁም በ ባህርዳር በመስጠት ላይ ይገኛል።
ባለፉት ኹለት ዓመታትም ከ 500 ሺሕ በላይ ተጋላጭ ናቸው ተብለው ለተለዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ምርመራ በማድረግ ከ 17ሺሕ በላይ የሚሆኑ ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝ ዜጎችን በመለየት የፀረ ኤች አይ ቪ የህክመና ክትትልእና መድሀኒት እንዲጀምሩ ማድረጉን ይገልፃል፡፡
በሥራዎች ላይ ያሉ ተግዳሮቶች
በአገራችን ባለፉት ኹለት አስርት ዓመታት ሲካሔዱ በቆዩት ኤች አይ ቪን የመከላከል እና የመቆጣጠር ሥራዎች፣ ከ 90 በመቶ በላይ የሚሆነው የገንዘብ ድጋፍ ከውጪ አገራት የሚገኝ/የተገኘ ነው። ግሎባል ፈንድ እንዲሁም ከአሜሪካ ፕሬዘዳንቶች የአስቸኳይ ጊዜ የኤድስ ዕርዳታ (PEPFAR) ዋነኛ ለጋሾች ሲሆኑ፣ ኢትዮጵያ ባለፉት 20 ዓመታት ከ አራት ቢሊዮን ዶላር በላይ እርዳታ አግኝታለች። በእየ ዓመቱም በአማካይ 250 ሚሊዮን ዶላር እንደሚሆን የፌዴራል ኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ጽሕፈት ቤት መረጃ ያሳያል።
ሆኖም ከ አውሮፓውያኑ 2012 ጀምሮ የሚገኘው የገንዘብ ድጋፍ በመቀዛቀዝ ላይ ይገኛል። ለማሳያም ባሳለፍነው በጀት ዓመት የተገኘው የገንዘብ ድጋፍ ከ 170 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር አይበልጥም። ይህም የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት በሚሠሩ ሥራዎች ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽዕኖ በማሳደር ላይ ይገኛል።
እንደ ፖፑሌሽን ኢትዮጵያ ያሉ በውጪ ዓገራት የገንዘብ ድጋፍ የሚነቀሳቀሱ ድርጅቶች የድጋፉን በቀዛቀዝ ተከትሎ እጆቻቸውን በመሰብሰብ ላይ ናቸው። ለዚህም ማሳያ የሚሆነው ድርጅቱ ከዓመታት በፊት በስምንት ክልሎች ሲሰጥ የነበረውን አገልግሎቱን አሁን በአዲስ አበባ እና አማራ ክልል ብቻ ተገድቡ እንዲሰጥ ማድረጉን ገልጿል፡፡
ሌላው እንደ ተግዳሮት የሚነሳው ቫይረሱ በተከሰተበት ወቅት ከነበረው ሁኔታ አንጻር ለውጥ ይኑር እንጂ አሁንም ከቫይረሱ ጋር በሚኖሩ ሰዎች ላይ የሚፈፀም ማግለል እና መድሎ መኖሩ ነው። ይህም በእርግጥ ያለ እንደሆነ በአዲስ አበባ ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝ ዜጎች ያቋቋሟቸው ማኅበራት ጥምረት ኀላፊ ዕድላን ይገልጻሉ። ይህም ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ዜጎች በበጎ ፈቃድ ሥራዎች ላይ እንዳይሳተፉ እና ያላቸውን ልምድ እንዳያካፍሉ ከማድረጉም በላይ፣ ከፍተኛ የሥነ ልቦና ጫና እያደረሰ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
የሴቶች፣ ሕፃናት እና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስትሩ ያሬድ ዳኜ፣ መንግሥት እና መገናኛ ብዙኀን ለ ጉዳዩ የሰጡት ትኩረት አናሳ መሆኑን በምክንያትነት ጠቅሰዋል። ከዓመታት በፊት በርካታ ዜጎች በቫይረሱ ሕይወታቸውን ሲያጡ ችግሩ የፖለቲካ አጀንዳ ሆኖ ነበርም ይላሉ። በወቅቱም የተሰጠውን ትኩረት መሰረት አድረገው በተሠሩ ሥራዎች ለውጦች መጥተዋል። አሁንም ሚዲያውም ቢሆን የኤች አይ ቪን ጉዳዩ እንዲሁም አጀንዳ ሊያደርገው ይገባል ብለዋል።
በኤች አይ ቪ ዙሪያ ለሚሠሩ ሥራዎች የገንዘብ ምንጮች የእርዳታ ድርጅቶች ብቻ መሆናቸው እና በሌሎች መርሃ ግብሮች ላይ መንጠልጠላቸውን አንስተዋል።
የፌዴራሉ ጽሕፈት ቤት በበኩሉ 90 ከመቶ በላይ የሚሆነው የኅብረተሰብ ክፍል ስለ ኤች አይ ቪ ሰምቶ ያውቃል የሚል ሲሆን፣ ችግሩ አለው ተብሎ የሚታመነው እውቀት ግን ራሱንም ሆነ ሌሎችን ከቫይረሱ ለመከላከል የሚያስችል አለመሆኑ ነው። ይህም በሚሠሩ ሥራዎች ላይ ከፍተኛ ተግዳሮት እየፈጠረ ሲገኝ፤ ትኩረት መቀዛቀዙን እና ቸልተኝነቱን ተከትሎ የመጣ ነው።
‹‹በከተሞች የቫይረሱ አማካይ የስርጭት መጠን 3 በመቶ ሲሆን፣ በገጠራማ አካባቢዎች ደግሞ እስከ 0.4 በመቶ ይደርሳል›› የሚለው ደግሞ የፌዴራል የኤች አይ ቪ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ጽሕፈት ቤት ነው።
የጽሕፈት ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ዳንኤል በትረ እንደሚሉት፣ ኤች አይ ቪ ስርጭት በቁጥር ሲታይ ባለፉት ጊዜያት ከነበረው እየቀነሰ መጥቷል። ችግሩ የግንዛቤ እጥረት እና መዘናጋት ነው የሚሉት ዳንኤል፣ በዚህ መዘናጋት ውስጥ የቫይረሱ የስርጭት ምጣኔ ማገርሸቱ የማይቀር በመሆኑ፣ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ያለው መዘናጋቱን እና ቸልተኝነቱን መስበር የሚለው ላይ መሆኑን ገልፀዋል።
ዘላቂ መፍትሔ
ያሬድ ዳኜ ጉዳዩ በቅድሚያ የፖለቲከኞችም፣ የሚዲያውም አጀንዳ መሆን ይገባዋል። ለፖለቲካው እና ለሌሎች ጉዳዮች የሚሰጠውን የጊዜ እና የቦታ ሽፋን ለ ኤች አይ ቪ በመጠኑም ቢሆን ሊለገስ ይገባዋል ሲሉ በአንክሮ ያሳስባሉ። ፖሊሲ አውጪዎችም በሽታዎችን ለመከላከል ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ይገባቸዋል ብለዋል።
የተቀረፁ ፍኖተ ካርታዎች በአንድ ወቅት ብቻ የሚተገበሩ ሳይሆኑ ዘላቂነት ባለው መልኩ የሚተገበሩ አልፎም በእቅድ የሚመሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ መንገዶች ማመቻቸት እንደሚገባም አብራርተዋል።
የአገራችን ፖለቲካዊ ሁኔታ ከላይ በሚተላለፉ ትዕዛዞች የሚመራ ነው። ይህም ባለሙያው በራሱ እውቀት ላይ ተመስርቶ እንዳይሠራ ያደረገዋል። ሥራዎች በኮሚቴ እና በትዕዛዝ የሚሠሩ ሳይሆኑ በባለሙያዎች እውቀት ላይ የተመሠረቱ ሊሆኑ እንደሚገባ ያሬድ ጠቁመዋል።
አዲስ አበባ ከተማ የኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከያ እና መቆጣጠሪያም ተመሳሳይ የመፍትሔ ሐሳብን ያንፀባርቃል። በተለይም የማኅበረሰብ መሠረት የሆነው ቤተሰብ ላይ በስፋት መሠራት እንደሚገባው፣ የመረጃ ስርጭቱም ላይ በትኩረት እንቅስቃሴ ሊደረግ እንደሚገባ፣ ብሎም ኅብረተሰቡ እራሱን መከላከል እንዲችል አቅም መፈጠር እንዳለበት ገልጿል።
ከነዚህ ጥረቶች መካከልም ምርመራውንም ሆነ የህክምና ክትትሉን አዳዲስ ፈጠራዎች በተሞሉበት መንገድ ማድረግ እንደ አንድ መንገድ ሊጠቀስ ይችላል፡፡ ለዚህም ማሳያ ፖፑሌሽ ኢትዮጵያ የሚያቀርባቸው ራስን በራስ መመርመሪያ መሳሪያዎች እነዲሁም ተጋለጭ ናቸው ተብለው በተለዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የሚወሰዱ በሽታውን የመተላለፍ አቅም እስከ 90 በመቶ የሚቀንሱ መድሀኒቶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡
በሁሉም አካላት የሚነሳው ጉዳይ ከዚህ ቀድም በቫይረሱ ላይ በስፋት ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የመንግሥት አካላት፣ የኪነ ጥበብ ሰዎች፣ ማኅበራት እና በጎ ፈቃደኞች በቀድሞው ልክ ሥራዎችን ማከናወን እንደሚገባቸው ነው።
በመጠናቅቅ ላይ በሚገኘው የፈረንጆቹ 2019 ሦስቱ 90ዎችን ለማሳካት በተደረጉ ጥረቶች፣ በአማካይ ከ 75 በመቶ በላይ ማድረስ ተችሏል። በ ፈረንጆቹ 2030 ኤድስን ለማቆም የተያዘውን እቅድ ለማሳካትም ከፍተኛ የሆነ ማኅበረሰባዊ እንቅስቃሴ እና የፀባይ ለውጥን የሚጠይቅ ጥረትን ይፈልጋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 58 ታኅሣሥ 4 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here