ከአንድ ዓይነት ተግባር የተለየ ውጤት እየጠበቅን ይሆን?

0
1096

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በየእለቱ ማለዳ ላይ በሚቀርብ የትራፊክ አደጋ መረጃዎች ላይ በርካታ ቀላልና ከባድ አደጋዎች እንደሚደርሱ ይነገራል። ከሚደርሰው የንብረት ውድመትና ኪሳራ ውጪ የብዙ ሰዎች ሕይወትም በአሰቃቂና አሳዛኝ ሁኔታ ያልፋል። የትራንስፖርት ሚኒስቴር ጉዳዩን ልብ ብሎ ‹እንደርሳለን› የሚል ንቅናቄ በኅዳር ወር ያዘጋጀ ሲሆን፣ በንቅናቄው የተካሔዱና በዘላቂነት የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ ይኬድባቸዋል የተባሉ መንገዶች፤ ከአንድ ዓይነት ድርጊት የተለየ ውጤት መጠበቅ እንዳይሆን ሲሉ ቤተልሔም ነጋሽ ስጋታቸውን ገልጸዋል። በአሽከርካሪዎችም ላይ ብቻ ሳይሆን በእግረኞችም ላይ ሊሠሩ የሚገቡ ተግባራት እንዳሉና ጉዳዩን በተለየ መንገድ ለመፍታት መሞከር ያሻል ሲሉም ምልከታቸውን ገልጸዋል።

አልበርት አነስታይን “የእብደት ትርጉም ተመሳሳይ ነገርን በተደጋጋሚ ማድረግ፣ ነገር ግን የተለየ ውጤት መጠበቅ ነው” ፤ “The definition of insanity is doing the same thing over and over again but expecting different results.” የሚል ተጠቃሽ አባባል አለው። ምናልባት ይህን መሰል ድርጊት እብደት መባሉ ለአገላለጽ ተጋነነ ብንል፣ ለአንድ ችግር ተመሳሳይ መፍትሔ በተደጋጋሚ መጠቀም ግን የሁላችንም የሰው ልጆች ባህሪ እንደሆነ አጥኚዎች ይገልፃሉ። የሰው ልጅ ሕይወት በተደጋጋሚ በቅደም ተከተል በሚከናወኑ ድርጊቶች የተሞላ ነውና። ይሁንና ይህን የአነስታይን አባባል እውነትነት አይለውጥም። ቀደም ብለን ባከናወንነው ተግባር ውጤት ሳንረካ ከቀረንና ደግመን ማድረግ ካለብን፣ የተለየ ውጤት ለማግኘት የተለየ አካሔድ ወይም ዘዴ መጠቀም የግድ ይላል።
ይሄ ሁሉ ዙሪያ ጥምጥም በትራፊክ አደጋ ዙሪያ ለዓመታት ያካሔድነው ሥራ ከጥቂት መሻሻል በስተቀር ለምን ጥሩ ውጤት አላስገኘልንም? የሚል ጥያቄ ለማንሳት ነው። መነሻ የሆነኝ ደግሞ በትራንስፖርት ሚኒስቴር በኩል “እንደርሳለን” በሚል በኅዳር ወር የግንዛቤ ማስጨበጫ ንቅናቄ መደረጉ ነው። ንቅናቄው ውይይቶች፣ የሚዲያ ዘመቻ እንዲሁም የጎዳና ላይ ትርኢት ያካተተ ሲሆን፣ የፕሮግራሙ ማጠቃለያ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በተገኙበት በአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን አዳራሽ ተካሒዷል።
“እንደርሳለን” በሚል መሪ ቃል የመንገድ ትራፊክ ደኅንነትን ለማሻሻልና አደጋን ለመቀንስ ታስቦ በተዘጋጀው አገራዊ ንቅናቄ፣ በ2011 ብቻ 4 ሺሕ 597 ሰዎች ሕይወታቸውን ማጣታቸው ተገልጿል። በዚህ ንቅናቄ ማጠቃለያ መርሃ ግብር ደግሞ ከሁሉም ክልሎች የተገኙ 122 ጠንቃቃ አሽከርካሪዎችና 6 ልዩ ተሸላሚዎች እውቅና እና ሽልማት ተበርክቶላችዋል።
በዛው የማጠቃለያ ክዋኔ ወቅት፣ የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ዳግማዊት ሞገስ ዘርፈ ብዙ ቀውስ እየፈጠረ የሚገኘውን የመንገድ ትራፊክ አደጋን ለመከላከል፥ ከዓለም ባንክ በተገኘ የ107 ሚሊዮን ብር ብድር የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል። በዚህም በአሽከርካሪዎች ብቃት፣ በመንገድ ደኅንነትና መሰል ዘርፎች ሥልጠና እየተሰጠ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል። ሚኒስትሯ በሰው ሕይወትና በአገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርሰውን የትራፊክ አደጋ ለመከላከል ሕዝቡ በጋራ ሊሠራ ይገባልም ብለዋል።
የትራፊክ አደጋ በመገናኛ ብዙኀን ተደጋግሞ ከመነገሩና ከአነጋገሩም ላይ ‹ለእግረኛ ቅድሚያ በመከልከል› ዓይነት ‹የአሽከርካሪ ጥፋት› ተደጋግሞ የሚጠቀስ ከመሆኑ የተነሳ፣ ብዙ ሰዎች [መረጃው ያለውም የሌለውም] ለሚደርሱት የትራፊክ አደጋዎች ተጠያቂው ሙሉ በሙል አሽከርካሪዎች ናቸው የሚል እምነት አላቸው። የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ከአንባቢዎች ሰበሰብኩት ካለው መረጃ ተነስቶ ያሰናዳው ዜናም፣ አስተያየት ሰጪዎች “የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ለትራፊክ አደጋ ዋነኛ መንስዔ ነው” ብለዋል የሚል ነው። የዜናው ሐሳብ ሲጨመቅ እንደሚከተለው ነው።
የመንገድ ትራፊክ ደኅንነት ቢሮ ባወጣው መረጃ መሠረት ከትራፊክ አደጋ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ በየቀኑ በአማካይ 14 ሰዎች ሕይወታቸውን ሲያጡ፣ 31 ያህሉ ደግሞ ለከባድ የአካል ጉዳት ይዳረጋሉ።
የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በማኅበራዊ ሚዲያ በኩል ‹‹የዜጎችን ሕይወት በአስከፊ ሁኔታ እየቀጠፈ ያለውን የትራፊክ አደጋ ጉዳት ለመቀነስ ከመንግሥት፣ ከአሽከርካሪዎች፣ ከእግረኞች እንዲሁም ከሚመለከታቸው አካላት ምን ይጠበቃል ይላሉ›› በሚል በፌስቡክ ያሰባሰበውን አስተያየት ውጤትም እንደሚከተለው ገልፆ ነበር። ይህን አስተያየት የሰበሰበውም ‹አደጋው የበዛው ለምንድነው?› ለሚለው መንስዔውን ማወቅ ለመፍትሔውም ይጠቅማል በሚል ነው።
ከአስተያየት ሰጭዎች መካከል 39% ሰዎች የአሽከርካሪ መንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ችግርን አንስተዋል።
ይህም በዝምድና፣ በገንዘብ፣ ያለ በቂ ሥልጠና፣ የብቃት ደረጃ ዕድገትን መሠረት ያላደረገ መንጃ ፈቃድ አሰጣጥ፣ ሐሰተኛ መንጃ ፈቃድ መኖር እና የመንጃ ፈቃድ ሥልጠና የሚሰጡ ትምህርት ቤቶች ብቃት ችግር የሚሉትን ጉዳዮችን ጠቅሰዋል።
አስራ አንድ በመቶ አስተያየት ሰጪዎች እንዲሁ አሽከርካሪዎች አደንዛዥ ዕፆች ተጠቅመው፣ መጠጥ ጠጥተው እና ሙዚቃ ላይ ትኩረት አድርገው ከቀልብ ሳይሆኑ በማሽከርከራቸው የተነሳ አደጋዎች ይከሰታሉ ብለዋል።
የአሽከርካሪዎች ሕግ አለማክበር ማለትም በፍጥነት ማሽከርከር እና ትርፍ መጫን የሚሉ ጉዳዮችን ደግሞ 20% ሰዎች ለትራፊክ አደጋ በምክንያትነት ጠቅሰዋል። በአንጻሩ 8% አስተያየት ሰጭዎች በአሽከርካሪዎች እና በደንብ አስከባሪ አካላት (ደንብ አስከባሪዎች፣ ትራፊክ ፖሊሶች እና ሌሎች ሕግ አስከባሪ ተቋማት) መካከል የጥቅም ትስስር እና ተደራዳሪነት መኖር ለአደጋው መባባስ አስተዋጽኦ ማድረጉን አመልክተዋል።
18% የሚሆኑት ደግሞ በቂ መንገዶች፣ የመንገድ ላይ የትራፊክ ምልክቶች፣ ዘመናዊ የትራፊክ መቆጣጠሪያ ስርዓት አለመኖር እና የእግረኞች ንቃተ ኅሊና ላይ በቂ ግንዛቤ አለመሠራት የሚሉ ምክንያቶችን ዘርዝረዋል።
4% አስተያየት ሰጭዎች አደጋዎች የሚከሰቱት በአሮጌ ተሽከርካሪዎች የተነሣ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ከዚሁ ሁሉ ውስጥ ግን እግረኞች ያላቸው አስተዋጽኦ አልተነሳም። በግሌ እንደ አሽከርካሪ ሳየው በተለይ በከተማ አካባቢ ከትራፊክ ፍሰቱ ከሚያስተጓጉሉ ነገሮች አንዱ የእግረኞች ኃላፊነት የጎደለው የዜብራ አጠቃቀምና ከዜብራም ውጪ መንገድ ለመሻገር መሞከር ናቸው። ይህ በተለይ በአንዳንድ መኪና የሚበዛባቸው አዳዲስ መኖሪያ አካባቢዎች የሚበዛ ሲሆን፣ መንግሥት በመንገዶች አካፋይ ላይ የብረት አጥር እንዲያስቀምጥ አስገድዶታል፤ ለተጨማሪ ወጪም ተዳርጓል።
ከዚህ ጋር የሚያዘውና በቂ የትራፊክ ምልክቶች አለመኖር ጋር አብሮ መነሳት የሚችለው ሌላ ነጥብ በቂ የመንገድ ላይ መብራት አለመኖር ነው። እንደሚታወቀው ከዋና ዋና መንገዶች ከጥቂቶቹ በስተቀር ሌሎቹ ዋና እና መጋቢ መንገዶች በቂ መብራት የሌላቸው ሲሆን፣ አብዛኞቹ የአዲስ አበባ መንገዶች ጭራሽ መብራት የላቸውም። በዚህም ምክንያት እግረኞች በተሸከርካሪዎቹ መብራት ብቻ ለማየት የሚገደዱ ሲሆን፣ በአገራችን የመኪኖች ይዞታ ሁኔታ በትክክል የሚሠራ (ረጅም መብራት እያበራ ሌላውን አሽከርካሪ ከሚረብሸውና ከመርዳት ይልቅ አስቸጋሪ ሁኔታ ከሚፈጥረው መብራቱ በከፊል ወይም ጨርሶ እስከማይሠራው) መብራት ማግኘት ሌላ ራስ ምታት ነው።
በእርግጥ ከተሽከርካሪዎች የቴክኒክ ሁኔታም በላይ ዋነኛ የአደጋ መንስዔ በተለይ የበርካታዎችን ሕይወት በመቅጠፍ የሚታወቀው፣ ከከተማ ውጪ በሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ላይ ከተፈቀደ ፍጥነት በላይ ማሽከርከር ነው። ምናልባት እዚህ ላይ ከላይ በጠቀስኩት አስተያየት የተመለከተውና በጥናትም ተረጋግጧል የተባለው የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ችግር በአብዛኛው ከአሽከርካሪ ባህሪ ጋር ተደምሮ ለአደጋው መንስዔ ነው ሲባል የመፍትሔ ሥራውንም ከዚህ ጋር ማያያዝ የግድ ይላል።
ቀደም ሲል በአንዳንድ የመገናኛ ብዙኀን እንደተነገረው፣ የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ አሠራር ሥርዓቱን ወደ ድሮው ዓይነት (እንደ አሁኑ በአንድ ጊዜ የሕዝብ ማመላላሻ እና የጭነት ተሽከርካሪ መንጃ ፈቃድ የሚሰጥበት ሳይሆን በድሮው ደረጃውን ጠብቆ ከማሽከርከር ልምድ ጋር ወደሚቀጥለው መንጃ ፈቃድ ኹለት ሦስት አራት አምስት እያሉ የሚሸጋገሩበት ይሆናል) ይመለሳል ቢባልም ‹መቼ?› ለሚለው ጥያቄ መልስ አልተሰጠም።
በአዲሱ ሥርዓት መንጃ ፈቃድ እንዳወጣ ሰው የተረዳሁት ጉዳይ፣ መንጃ ፈቃድ እንዲያሠለጥኑ ፈቃድ የተሰጣቸው ተቋማት አንዳንዶቹ በተለይ በቂ ደረጃውን የጠበቀ ተሽከርካሪና አስተማሪ የሌላቸው ናቸው። ሒደቱም ቢሆን በሙስና የተጨማለቀ፣ ‹ጉቦ ያልከፈለ አያልፍም› እስኪባል ድረስ በገንዘብ ብቻ መንጃ ፈቃድ ይገዛበት የነበረ እንደነበር አገር ያውቀው ሃቅ ነው። እንዲውም ከጥቂት ዓመታት በፊት የተጠና የተባለ ጥናት፣ በአዲስ አበባ ከሚገኙ 58 የአሽከርካሪ ማሠልጠኛ ተቋማት ብቃት ያላቸው 10 ብቻ ናቸው የሚል ውጤት አስነግሮ ነበር።
የተቀመጠውን መስፈርት አላሟሉም የተባሉ 48 ተቋማት ለጊዜው ማሠልጠን እንዲያቆሙ ተወስኖ በዚህ ላይ ትርምስ እንደነበርም ይታወሳል። ይህ ድርጊት ምን ያህል ውጤት አመጣ? እነኝህ ተቋትስ ተዘጉ፣ አሻሻሉ ወይስ ሥራቸውን እንዲቀጥሉ ተደረጉ? ሌላው ጥያቄ ነው። በእነኝህ ተቋማት ላይ ስር ነቀል ለውጥ ባልተካሔደበት፣ በብዙዎች ሐሳብ ለትራፊክ አደጋ ትልቁ ምክንያት ነው የሚባለውን ችግር ማስወገድ አይቻልም። በቅስቀሳ፣ መንጃ ፈቃድ ትምህርቱ ላይ ሥነ-ባህሪ የሚል ምዕራፍ በመጨመር (መላው ማኅበረሰብ በሞራል ልሽቀት ውስጥ በሚኖርበት ሲያድጉ ያልተሰጠ የሥነ ሥርዓትና የሌሎችን መብት ማክበር ወዘተ እሴት) ኀላፊነት የሚሰማቸው፣ ለሌላው ቅድሚያ የሚሰጡ አሽከርካሪዎችን ማፍራት ከባድ ነው።
ይልቁንም የመንጃ ፈቃድ ሥርዓቱ ሌላ በሽታ የሆነው ተቆጣጣሪው አካል ውስጥ ያሉ የሚኒስቴሩ ሠራተኞች ራሳቸው የመንጃ ፈቃድ ትምህርት ቤቶች ባለቤት የመሆናቸው የአደባባይ ምስጢር ካልታየ፣ አነስታይን እንዳለው ደጋግሞ አንድ ተግባር እያከናወኑ ከቀደመው የተለየ ውጤት መጠበቅ ነው። ከሁሉም በላይ በርካታ ገንዘብ እየፈሰሰበት ያለው መንገዶችን የማሻሻል እና ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ ለምን የሚፈለገውን ውጤት አላመጣም የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ቆም ብሎ ለመመርመር ጊዜው አሁን ነው።

ቅጽ 2 ቁጥር 59 ታኅሣሥ 11 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here