በአንድ ሳምንት ውስጥ አራት ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ዋጋ የሚያወጡ የኮንትሮባንድ እቃዎች ተያዙ

0
697

ባሳለፍነው ሳምንት በተለያዩ የጉምሩክ ጣቢያዎች በተደረገ ፍተሻ፣ የአራት ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው ጌጣጌጦች፣ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች እና አልኮል መጠጦች መያዙን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ።

ኅዳር 21/ 2012 በከባድ የጭነት ተሽከርካሪ ከጅቡቲ ወደ ኢትዮጵያ ሕጋዊ ዕቃ ጭኖ በመግባት ላይ ሳለ በስካኒንግ ማሽን በተደረገለት ፍተሻ ግምታዊ ዋጋው ብር 461 ሺሕ 600 የሆኑ ሕገ-ወጥ የሞባይል ባትሪዎች ተገኝተዋል። እነዚህንም በተሽከርካሪው የተለያዩ ክፍሎች ላይ ደብቆ ለማሳለፍ ሲሞክር በቁጥጥር ስር ሊውል እንደቻለ ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የተገኘ መረጃ ያመላክታል።

በተመሳሳይ ቀንም ግምታዊ ዋጋው 709 ሺሕ 250 የብር ጌጣጌጥ ከሶማሌ ላንድ ተነሥቶ ወደ አገር ሲገባ በጉምሩክ ሠራተኞች እና በፌዴራል ፖሊስ አባላት በተደረገ ክትትል ተይዞ እቃው ለድሬዳዋ ጉምሩክ መጋዘን ገቢ ተደርጓል።

በቡሌ ሆራ ኬላ የሞያሌ መቅረጫ ጣቢያ ታኅሳስ 16/2012 20 ነጥብ 75 ኪ.ግ የሚመዝን እና ግምታዊ ዋጋዉ 1 ሚሊዮን 304 ሺሕ 875 ብር የሆነ ጌጣጌጥ ከኹለት ተጠርጣሪዎች ጋር ተይዟል። አዋሽና አልበረከቴ ጉምሩክ ጣቢያዎችም ግምታዊ ዋጋቸው 557 ሺሕ 500 የሆነ የተለያዩ የኮንትሮባንድ እቃዎች በጉምሩክ ሠራተኞች እና ፌዴራል ፖሊስ ተይዘዋል ያለው ሚኒስቴሩ፣ በባህር ዳር ጉምሩክ መቆጣጠሪያ ጣቢያ በሸክም ሲያልፍ ከኅብረተሰቡ በተሰጠ ጥቆማ ልዩ ልዩ አልባሳት፣ ጫማ አጠቃላይ ግምታዊ ዋጋ 95 ሺሕ 175 ብር የሚያወጡ እቃዎች ተይዘዋል።

በቤት-ጌዶ መቆጣጠሪያ ጣቢያ በተደረገ ፍተሻም ከመሀል አገር ወደ ነቀምት ሲጓዙ የነበሩ የተለያዩ ኮንትሮባንድ ዕቃዎች፣ ኤሌክትሮኒክስ እና እስቲም፣ እንዲሁም መጠጦች ግምታዊ ዋጋ 220 ሺሕ ብር የሆኑ ዕቃዎች መያዛቸው ተገልጿል።

ቅጽ 2 ቁጥር 61 ታኅሣሥ 25 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here