ኦፌኮ፣ ኦነግ እና ኦብፓ ጥምረት መሰረቱ

0
670

በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱት የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ)፣ የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦነግ) እና የኦሮሞ ብሔራዊ ፓርቲ (ኦብፓ) ዓርብ፣ ታኅሣሥ 24/2012 በጥምረት ለመሥራት ሲያደርጉ የቆዩትን ድርድር በማገባደድ ስምምነት ላይ ደረሱ።

ዓርብ ከቀትር በኋላ በኢሊሊ ሆቴል ባደረጉት ስምምነት፣ ፓርቲዎቹ የመግባቢያ ሰነድ የተፈራረሙ ሲሆን የስምምነቱ ዝርዝር ግን ይፋ አልሆነም። ከኦፌኮ መረራ ጉዲና (ፕሮፌሰር) እና በቅርቡ ፓርቲውን መቀላቀላቸውን ይፋ ያደረጉት ጃዋር መሐመድ፣ ከኦነግ ዳውድ ኢብሳ እና ከኦብፓ ብርጋዴል ጄኔራል ከማል ገልቹ በስምምነቱ ላይ ተገኝተው ተፈራርመዋል።

ፓርቲዎቹ ከስምምነት ላይ ከደረሱ በኋላም ማመልከቻቸውን ለምርጫ ቦርድ ማስገባታቸውን የቦርዱ የኮምዩኒኬሽን አማካሪ ሶሊያና ሽመልስ ለአዲስ ማለዳ አረጋግጠዋል።

‹‹ቦርዱ በሕጉ መሰረት ጥያቄውን የሚያስተናግድ ይሆናል፣ መልስ ለመስጠት የሚያስፈልገውን ጊዜ አሁን መተንበይ አልችልም፣ ነገር ግን ማመልከቻቸውን ተቀብለናል›› ሲሉ ተናግረዋል።

‹‹ትብብር ለዲሞክራሲ ፌደራሊዝም ›› በሚል መመዝገባቸውን አዲስ ማለዳ አረጋግጣለች ።

የምርጫ አዋጁ ‹ቅንጅት› የሚለውን በሚዘረዝርበት የትርጓሜ ክፍሉ ላይ ‹‹ኹለት እና ከዛ በላይ የሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተናጠል ሕጋዊ ህልውናቸው እንደተጠበቀ በምርጫ ወቅት ምርጫውን ለማሸነፍ ለሌላ ጊዜያዊ መሰል ዓላማ በጋራ ለመሥራት ተስማምተው የመቀናጀት የምስክር ወረቀት የሚያገኙበት ሁኔታ ነው›› ሲል ያብራራል።
የአዋጁ አንቀፅ 94 እንደሚያስረዳው፣ በአዋጁ መሰረት የተመዘገቡ ኹለት ወይም ከዛ በላይ ፓርቲዎች በተወሰኑ ጉዳዮች ዙሪያ እና ለተወሰነ ጊዜ ተቀናጅተው በአገር አቀፍ ወይም በክልል ደረጃ ሊንቀሳቀሱ እንደሚችሉ ደንግጓል። በተመሳሳይ አንቀፅ ላይ ከጠቅላላ ወይም ከአካባቢያዊ ምርጫ ኹለት ወራት በፊት ጥያቄውን ለቦርዱ ማቅረብ እንዳለባቸውም ያስቀምጣል።

ፓርቲዎቹ ተስማምተው ሊቀናጁ ስላሰቡባቸው አካባቢዎች የሚገልጽ ሰነድ ለቦርዱ ማቅረብ እንደሚገባቸው የሚደነግገው ሕጉ፣ ቦርዱ የመቀናጀት ጥያቄው በአዋጁ መሰረት መቅረቡን አረጋግጦ ጊዜያዊ የምስክር ወረቀት እንደሚሰጥም አስቀምጧል።

ቦርዱ ባሳለፍነው ሳምንት በማኅበራዊ ድረ ገጹ ይፋ እንዳደረገው፣ በእነ ብ/ጄ ከማል ገልቹ ለሚመራው እና በምዝገባ ሂደት ላይ ላለው ‹የኦሮሚያ ብሔራዊ ፓርቲ› የፓርቲው ሰንደቅ ዓላማ አሁን አብረው ቅንጅት ከፈጸሙት ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር ጋር በመመሳሰሉ እንዲያብራራ ጠይቄዋለሁ ማለቱ አይዘነጋም።

ፓርቲውም ‹‹የኦነግ ሰንደቅ ዓላማ ኮከብ ያለው ሲሆን፣ ኦሮሚያ ብሔራዊ ፓርቲ የለውም›› የሚል እንዲሁም ‹‹ኦዳን ከቦ ያለው ቢጫው ቀስት የኦነግ ከ30 በላይ ሲሆን፣ የእኛ ግን 22 ነው (11 ትላልቅ እና 11 ትናንሽ)›› የሚል ምላሽ ማቅረቡን ቦርዱ እንዳላሳመነው አስታወቆ ነበር። መራጮችን እንዲሁም ለሌሎች ባለድርሻ አካላት የሚያምታታ በመሆኑ፣ እንዲቀይር ቦርዱ መወሰኑን አስታውቆም ነበር። ከዚህ ጋር ተያይዞ ፓርቲው ይህ ጽሑፍ ለህትመት እስከገባበት ጊዜ ምዝገባ አለማግኘቱን አዲስ ማለዳ አረጋግጣለች።

በሕጉ መሰረት ቅንጅት ለመመስረት በአዋጁ መሰረት መመዝገብ ቅድመ ሁኔታ ነው። ኦብፓ ደግሞ አልተመዘገበም በሚል ከአዲስ ማለዳ ጥያቄ የቀረበላቸው ሶሊያና ‹‹በዝርዝር ጉዳዮች ላይ መልስ ለመስጠት አሁን አልችልም፣ ምክንያቱም ጥያቄው ገብቷል ልበል እንጂ ዝርዝር ነገሮችን አልተመለከትኩም›› የሚል መልስ ሰጥተዋል።

ቅንጅቱ በኦሮሚያ ክልል ላለው ፉክክር ምን ሚና አለው?
ፓርቲዎቹን በቅርበት የሚያውቁት እና በተለይም የኦሮሚያ ክልልን ፖለቲካ በመተንተን የሚታወቁት ደረጄ ገረፋ እንደሚሉት፣ ይህ ጥምረት በተለይም ለብልፅግና ፓርቲ በኦሮሚያ ክልል የሚኖረውን ድጋፍ የሚገዳደር መሆኑ ግልፅ ነው።

ባለፉት ምርጫዎች ላይ በተለይም በ1997 በተደረገው አገር ዐቀፍ ምርጫ ላይ፣ ከ50 በላይ መቀመጫዎችን አግኝቶ የነበረው ኦፌኮ፣ ጃዋር መሐመድን ይዞ መምጣቱ በተለይም በመሀል ኦሮሚያ ሰፊ ድጋፍ አለው ተብሎ ለሚገመተው የበፊቱ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እና ለአሁኑ ብልፅግና ፓርቲ ፈታኝ መሆኑ አይቀሬ ነው፤ ደረጄ ያስረዳሉ።

ከዚህ ቀደም ለኦዴፓ በሚሰጡት ጠንካራ ድጋፍ የሚታወቁት፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ጠንከር ያለ ትችት የሚሰነዘሩት እና ‹‹ይህ አገር ዐቀፍ ምንጫ ላይ አስገዳጅ ነገር ካልመጣ የማንም ፓርቲ ጠንካራ ደጋፊ አልሆንም›› የሚሉት ደረጄ፣ ብልፅግና አሁን ይዞ የመጣው ቅርጽ ላይ ትኩረት ሰጥተው ያትታሉ።

ኦዲፒ ወደ ብልጽግና ከመምጣቱ በፊት፣ እንደ ደጋፊ ብሔረተኝነት እንዲህ ሰማይ በነካበት ወቅት ላይ ቅርፁን መቀየሩ ዋጋ ያስከፍለዋል በሚል መተቸታቸውን ያስታውሳሉ። በተለይም ጋዲሳ ሆገንሳ ኦሮሞ በተባለው ሰባት የፖለቲካ ፓርቲዎች ሲሳተፉበት በነበረው ጥላ ውስጥ የነበረው ኦዲፒ፣ ከእነዚህ ፓርቲዎች ጋር እስከ ጥምረት እንዳይጓዝ ይዞ የመጣው አዲስ መዋቅር እንቅፋት ሳይሆን እንዳለቀረም ይናገራሉ።

‹‹እኔ በግሌ የብሔር ፖለቲካውን በተወሰነ መልኩ መቀየር እና ብልፅግና አሁን ይዞ የመጣውን ቅርፅ መተግበር አስፈላጊ መሆኑን አምንበታለሁ። አሁን ግን ጊዜው አልነበረም፣ ይሄ ለኢትዮጵያ አንድነትም ቢሆን አይጠቅምም ስንል ነበር›› ሲሉ ብልጽግና ከዚህ ቅንጅት ሊገጥመው ስለሚችለው ተግዳሮት ያስረዳሉ። ‹‹ነገር ግን ያለፈው አልፏል። አሁን ባለውም መዋቅር በተለይ ለፌዴራል መንግሥትነት በትብብር አብረው መሥራት ይችላሉ፣ ይህንንም እንደ ሕንድ ያሉ አገሮች እንደሚቻል አሳይተዋል›› ብለዋል።

‹‹እነዚህ ድርጅቶች የክልሉን ሥልጣን ይዘው ፌዴራል ላይ ከብልፅግና ጋር መደራደር እና ሥልጣኑን መጋራት ይችላሉ›› እንደ ደረጄ ገለጻ።

ጥምረቱን አዎንታዊ እርምጃ ሲሉ የገለፁት የምርጫ ሕጎችን በተመለከተ የተለያዩ ጽሑፎችን ያዘጋጁት እና በኔዘርላንድ ሄግ መሠረቱን ባደረገው የዓለማቀፍ የሕገ መንግሥት የምርምር ኢንስቲትዩት (አይዲኢኤ) አርታኢ የሆኑት አደም ካሴ (ዶ/ር) እርምጃው ከመጪው ምርጫ ባለፈ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ መሻሻል ትልቅ ሚና ይኖረዋል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ቅንጅቱን ‹‹ስትራቴጂያዊ›› ሲሉ ገልጸው ለዚህም ‹‹ቅንጅት መመስረትን ውህደት ከማድረግ የሚለየው ፓርቲዎቹ የየራሳቸውን ፕሮግራም ይዘው እና ልዩነቶቻቸው ተጠብቀው፣ ነገር ግን አብረው በመሥራት ለመራጮቻቸው በአንድ ድንጋይ ኹለት ወፍ እንዲሉ የተለያዩ አማራጮቻቸውን በአንድ ጥቅል የሚያቀርቡበት ነው›› በማለት ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ከዚህ በኋላ የቀሩት የኦሮሞ ፓርቲዎች ወደ ብልፅግና ወይም አሁን ከተመሰረተው ጥምረት ጥላ ሥር ካልገቡ ተፅዕኗቸው እጅግ ይቀንሳል ያሉት አደም፣ ከዚህ በኋላም ከምርጫው በፊት ሌሎች ብዙ ጥምረቶችን ልንታዘብ እንችላል ሲሉም መላምታቸውን ያስቀምጣሉ።

የቅንጅቱ መሥራቾች የቀደመ ልዩነት በውጤቱ ላይ ጫና ያመጣ ይሆን?
በዚህ ስምምነት ስር የታቀፉት ግለሰቦች በተለያየ ጊዜ የተለያየ ፖለቲካ አቋም በመያዝ ያላቸው ቅራኔ ፖለቲካቸው ላይ ጫና አይኖረውም የሚሉት አደም፣ ‹‹በፖለቲካው ዓለም ቋሚ ወዳጅ ወይም ጠላት የሚባል ነገር የለም›› ሲሉ ይናገራሉ።

የተወሰኑ ልዩነቶች ካሏቸውም ለጊዜው እነሱን ወደ ጎን ብለው በሚያስማማቸው ነገር ላይ መስማማት ያን ያህል አይከብዳቸውም የሚሉት አደም፣ ይህ ግን በቀላሉ የሚካሄድ ይሆናል ማለት እንዳልሆነ ይናገራሉ።
‹‹ፓርቲዎቹም ሆነ መሪዎቹ መሰረታዊ የሚል ልዩነት የላቸውም፣ የምርጫ ሕጉም የመራጮችን ድምፅ መሰነጣጠቅን አያበረታታም። ለዚህም ነው ውሳኔው ስትራቴጂአዊ ነው የምለው›› ሲሉ ይናገራሉ።

በአደም ሐሳብ የሚስማሙት ደረጄ በበኩላቸው፣ ‹‹የግለሰቦቹ እስከዛሬ የመጡበት የሐሳብ ልዩነት ያን ያህል የሚያመጣው ለውጥ የለም። ምክንያቱም ብሔረተኝነት ማን የተሻለ ፖሊሲ አለው የሚለው ሳይሆን ማን ይጠብቀኛል የሚለው ነው። ጭቆና አለ ብሎ የሚያምን ሕዝብ ማን መብቴን ይጠብቅልኛል የሚለው ነው የሚያሳስበው። ይህ ማለት ደግሞ ፖለቲከኞቹም መሰረታዊ ልዩነት የላቸውም ማለት ነው። የኔ ግምት ከምርጫ በኋለ የተወሰኑ ልዩነቶች ሊኖሩ ይችላሉ ብዬ ነው የማስበው›› ይላሉ።

ፓርቲዎቹ ውህደቱን በችኮላ አድርገውታል ብዬ አላስብም ያሉት ደረጄ ‹‹ምክንያቱም ሕዝቡም ቢሆን ሲፈልገው የቆየው ነገር ነው። ምሁራንም በጋዲሳ ስር ሆነው ገዢውም ሆነ ተፎካካሪዎቹ በጋራ ለሕዝቡ የተሻለ ምርጫ እንዲሰጡ ነበር የሚጎተጉቱት። ነገር ግን አልሆነም፤ ስለዚህ የቀሩት ቀጠሉ፤ ምን አልባት አፍጥነውት ሊሆን ግን ይችላል›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ቅንጅቱ ምርጫ 2012 ላይ የሚኖረው ሚና
ደረጄ አሁን ኢትዮጵያ ያለችበትን ሁኔታ ከ1966ቱ አብዮት ጋር የሚያመሳስሉት ሲሆን፣ ያኔ ግን ምርጫ አልነበረም። አሁን ያለው ሁኔታ አገርን እንዳያፈርስ ፓርቲዎቹ ሊጠነቀቁ ይገባልም ብለዋል።

‹‹ወጣት አመፅ ወጥቶ መንግሥት ጥሏል፤ አሁን ያለው የሕዝብ ማስተባበር ሳይሆን ራሱን አስተባብሮ ቁጭ ብሎ የሚጠብቅ ሕዝብን ምርጫ መስጠት ነው። በ 1997ም ቢሆን ፓርቲዎቹ ናቸው ሕዝቡን ያስተባበሩት። አሁን ግን እንደዛ አይደለም። ምክንያታዊ መራጭ አለን ወይ ብሎ ቁጭ ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል። ምርጫ 2012ን ከፉክክር ይልቅ ትብብር ላይ ማተኮር ያስፈልጋል››ም ብለዋል።

‹‹በአመጹ ጊዜ አመፁን የመራው ፓርቲ ውስጥ የነበሩ ሰዎች አይደሉም። ነገር ግን ከፓርቲ ውጪ ያሉ ሰዎች ናቸው፤ አመፁ የመራው ፓርቲ ቢሆን ያ ፓርቲ አሁን መንግሥት ይሆን ነበር›› ብለዋል። ስለዚህ በኢትዮጵያ ታሪክ በእንደዚህ አይነት ሁኔታ ላይ የሚካሄድ ምርጫ በጥንቃቄ ሊታይ ይገባዋል ሲሉ ይደመድማሉ።

አደም በበኩላቸው የዜግነት ፖለቲካን የሚከተሉት ፓርቲዎች ተመሳሳይ ስልታዊ ውሳኔ ካልወሰኑ ውድድሩን የበለጠ ያከርባቸዋል ይላሉ። ‹‹የአንድነት ኃይል የሚባሉት እንደ ኢዜማ ያሉ ፓርቲዎች ከብልፅግና በመደበኛ መልኩ ወይም ኢ-መደበኛ መልኩ አብረው ካልሠሩ የድምፅ መከፋፈል ይኖራል›› ብለዋል።

‹‹ኦዴፓ ለዚህ ጥምረት ምን ምላሽ ይሰጣል የሚለው በራሱ አጓጊ ነው የሚሆነው›› ያሉት ደረጄ፣ በሌሎች ክልሎች ላይ ከፍተኛ ጫና ማምጣቱ አይቀርም። በአማራ ክልል ይህንን ጥምረት ተከትሎ ተመሳሳይ እርምጃ ይኖራል ብዬ አስባለሁ። ይሄ የብሔር ፖለቲካ ባህርይ ስለሆነ፤ እንዲሁም በአዲስ አበባ ላይም›› ብለዋል።
አዲስ ማለዳ በፊርማ ስነ ስርአቱ ላይ የተሳተፉትን ጃዋር መሐመድን፣ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲናን እንዲሁም ዳውድ ኢብሳን በስልክ ብታገኝም፣ አስተያየት ከመስጠት ግን ተቆጥበዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 61 ታኅሣሥ 25 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here