ማራቶን ሞተር የኤሌክትሪክ መኪኖችን ለገበያ ሊያቀርብ ነው

0
811

የኮሪያው የመኪና ኩባንያ ሀይዉንዳይ ምርቶችን በኢትዮጵያ የሚገጣጥመው ማራቶን ሞተር በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ መኪኖችን ለኢትዮጵያ ገበያ ሊያቀርብ መሆኑን ይፋ አደረገ።
በቤት ውስጥ በሚገኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ይሞላሉ የተባሉት እነዚህ መኪኖችን ገጣጥሞ ለማቅረብ ውል ተፈፅሞ የመጀመሪያ ዙር ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን ድርጅቱ አስታውቋል። አምስት በመቶ ብቻ ቀረጥ የሚጣልባቸው እነዚህ መኪኖች፣ ከሚመጡበት አገር ሲገዙ እስከ 250 በመቶ ድረስ የዋጋ ጭማሪ ቢኖራቸውም ወደ አገር ሲገቡ ግን ኤክሳይስ ታክስን ጨምሮ የተለያዩ ክፍያዎች ስለተነሱ ዋጋው ተመጣጣኝ እንደሚሆንም ድርጅቱ አስታውቋል። አንድ ባለ 1600 የፈረስ ጉልበት ያለው መኪና ከሚሸጥበት ዋጋ ከ 10 በመቶ በላይ ጭማሪ እንደማይኖርም የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መልካሙ አሰፋ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ከሀይዉንዳይ መቀመጫ ኮሪያ ውጪ ለመጀመሪያ ጊዜ ለዓለም ገበያ ይቀርባሉ የተባሉት የኤሌክትሪክ መኪኖች፣ በነዳጅ ከሚሠሩት መኪኖች በተለየ ከባትሪ ውጪ ምንም ዓይነት ዘይትም ሆነ ቅባቶችን የማይጠቀሙ እና የመለዋወጫ ወጪ የሌላቸው በመሆኑ ተመራጭ እንደሚሆኑንም ኀላፊው ገልፀዋል።

ከአንድ ዓመት በፊት ተገባድዶ ሥራ የጀመረው የሀይዉንዳይ የመገጣጣሚያ ፋብሪካ፣ እስከ አሁን ድረስ ከ 10 በላይ የተለያዩ ሞዴል መኪኖችን የገጣጠመ ሲሆን፣ በመስመር ላይ ያሉትን ጨምሮ ከ800 እስከ 1000 የሚሆኑ መኪኖችን ለገበያ አቅርቧል። ከእነዚህ መኪኖች ውስጥ አንድም መኪና ተበላሽቶ ለጥገና ወደ ፋብሪካው እንዳልተሰበሰበ የሚናገሩት ኀላፊው፣ የደረሰ የመኪና አደጋ ያለመኖሩም ለድርጀቱ ትልቅ ስኬት እንደነበረ አስታውሰዋል።

ይህ መገጣጠሚያ ፋብሪካ ሲገነባም የኤሌክትሪክ መኪኖችን ለመገጣጠም እንዲያስችል ሆኖ መገንባቱን ገልፀው፣ የሰው ኃይል ሠልጥኖ መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል።

‹‹በነዳጅ የሚሠሩ መኪኖችን መገጣጠም ከባድ ነው። የኤሌክትሪክ ግን ባትሪ እንጂ ሌሎች ውስብስብ የሞተር ክፍች ስለሌሉት በሰው ኃይል በኩል እንብዛም አንቸገረም›› ሲሉ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ለአዲሰ ማለዳ አስታውቀዋል።

አዲስ የረቀቀው የኤክሳይስ አዋጅ ባገለገሉ መኪኖች ላይ የያዘው አቋም አግባብ ነው ያሉት መልካሙ፣ አንድ ያረጀ መኪና አገር ውስጥ ገብቶ ጥቂት ዓመት ተነድቶ ከተገዛበት ዋጋ በላይ መለዋወጫ ስለሚጠይቅ ላለው የውጪ ምንዛሬ እጥረት መባባስ ምክንያት ይሆናልም ብለዋል። አዲስ መኪና ቢያንስ ኹለት መቶ ሺሕ ኪሎ ሜትር ወይም ለአምስት ዓመት ዘይት ብቻ እየተቀየረ ያገለግላል ብለዋል። ይህም ከውጪ ምንዛሬ ባሻገር ለጤና፣ ለአየር ብክለት እንዲሁም ለመኪና አደጋ መጨመር ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው ጠቅሰዋል።

‹‹አሮጌ መኪኖች ላይ መንግሥት ለመጣል ያሰበው ቀረጥ አዳዲስ መኪኖች ላይ ያለው ፍላጎት እንዲድግ አድርጓል። ነገር ግን የፍላጎት ችግር የለም፣ ሁሌም ሰዎች በሰልፍ ነው መኪና የሚገዙት። የውጪ ምንዛሬ እጥረቱ ግን ይህንን ፍለጎት ማሟላት እንዳንችል አድርጎናል›› ሲሉ መልካሙ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

አንድ ባለ 1600 የፈረስ ጉልበት ሀይዉንዳይ ክሪትያ መኪና አንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ብር አካከቢ የሚሸጥ ሲሆን፣ የኤክትሪክ መኪኖቹ ሲገቡ እስከ ኹለት ሚሊዮን ብር ድረስ ሊያወጡ እንደሚችሉም ይገመታል።
ድርጅቱ በበኩሉ የውጪ ምንዛሬ ገበያው ላይ ያለውን ተለዋዋጭነት ከግምት ውስጥ በማስገባት በመጪው ሦሰት ወር የሚኖረውን ዋጋ መተንበይ ከባድ ይሆናል ብሏል።

በተጨማሪም በመጪው ሳምንት ሦስት አዳዲስ ሞዴሎችን ወደ ሥራ የሚያስገባው ማራቶን ሞተር፣ ከእነዚህም ፓሊሴድ የተሰኛ አዲስ፣ በመጠኑ ከፍ ያለ የቤተሰብ እና የስፖርት አገልግሎቶችን ያጣመረ (Sport utility vehicle) መኪና ይገኝበታል። እስከ 45 ኩንታል የመጫን አቅም ያለው የደረቅ ጭነት ተሽከርካሪ እና አቶስ የተሰኘችውን አውቶሞቢልም እንደሚያስመርቅ ድርጅቱ አስታውቋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 61 ታኅሣሥ 25 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here