ለሴቶች ምቹ ያልሆነችዋ አዲስ አበባ

0
769

መዲናችን አዲስ አበባ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ የሚከናወንባት፣ በርካታ ግዙፍ የመንግሥት እና ዓለማቀፋዊ የንግድ ተቋማትን በውስጧ አቅፋ የያዘች ሰፊ ከተማ ነች። የከተማዋ የዳቦ ቅርጫትነት፣ የሕንጻዎቿ ውበት እና የመብራቷ ድምቀት ተረክ ሆዱን እያባባው መዳረሻውን አዲስ አበባ ላይ የሚያደርገው ሰው እያየለ መሔድ የከተማዋ የሕዝብ ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ እንዲሄድ አድርጎታል።

የማለዳዋን ፀሐይ መውጣት ተከትሎ ከየቤቱ የሚወጣው ነዋሪዋ፣ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴውን ለማከናወን ከወዲያ ወዲህ ማለት ሲጀምር የከተማዋን መንገዶች እንደጎርፍ ለማጥለቅለቅ የሚፈጅበት ጊዜ አጭር ነው። አንዳንዶቹ መንገዶች እንደውም ከሚችሉት ሕዝብ በላይ የሚንቀሳቀስባቸው በሚመስል ሁኔታ ሰው ከሰው ጋር እየተገፋፋ የሚሔድባቸው ናቸው።

ይህንን የሕይወት ሩጫ ከሚጋፈጡት መካከል ደግሞ ሴቶች እኩሌታውን ይይዛሉ። ነገን ተስፋ አድርገው ዛሬን ለሥራ አሊያም ለትምህርት አውለው ሕይወታቸውን ለማቃናት የሚተጉ አዲስ አበባ የእኔም ከተማ ናት ብለው በእኩልነት ስሜት የሚንቀሳቀሱ ሴቶች፣ የዚሁ ሕይወትን ለማሸነፍ የሚደረግ እንቅስቃሴ አካላት መሆናቸው አያጠራጥርም።

በእነዚህ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች መካከል በሴቶች ላይ ከቃላት ውርወራ ጀምሮ እስከ አካላዊ እና ወሲባዊ ጥቃቶች እንደሚፈፀምባቸው አይተናል፤ በስፋትም ተነግሮናል። ጥቃቶቹም ከመንገድ ላይ ጀምሮ የሕዝብ መገልገያ በሆኑ የመጓጓዣ አማራጮች፣ በመዝናኛ ስፍራዎች አለፍ ሲልም በሥራ ቦታ እና በትምህርት ቤቶች እንደሚፈፀሙ ምስክር የሚሆኑ በርካታ ክስተቶች አሉ።

ጽዮን ደመረ ኑሮዋን በአዲስ አበባ ያደረገች ወጣት ናት። በከተማዋ በተለይም በመንገድ ላይ እና በሕዝብ መጓጓዣ ላይ የሚፈፀም ጥቃት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ መምጣቱን ትናገራለች። ሴቶች በተለይ ብቻቸውን እንደልባቸው በቀንም ሆነ በማታ መንቀሳቀስ የማይችሉበት ሁኔታ እንዳለ ጽዮን ትገልጻለች። በአንዳንድ አካባቢዎች ለከፋ ከሚባለው የቃላት ውርወራ ጀምሮ መጎንተል እና መጎተት ሲመሽ ደግሞ ተገዶ ከመደፈር እስከ ግድያ የሚደርሱ ጥቃቶች በሴቶች ላይ እንደሚፈፀሙ የራሷን እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ በነበረችበት ወቅት በምትሳተፍበት በቢጫ ንቅናቄ (yellow movement) መታዘቧን ለአዲስ ማለዳ አጫውታታለች።

የእርሷን ገጠመኝ ስታካፍልም፣ ‹‹ትምህርት ቤት አምሽቼ ወደ ቤቴ ለመሄድ አንድ ታክሲ ተሳፈርኩ። ማታ መሆኑን ተከትሎ ታክሲው ትርፍ በመያዙ አጠገቤ አንድ ወንድ እና አንድ ሴት ነበሩ›› ብላ ጀመረች። «ጥቂት እንደተጓዝን አጠገቤ ያለው ልጅ መቁነጥነጥ ጀመረ። ከትንሽ ቆይታ በኋላ የነበሩ ሰዎች ወርደው ከኋላ እኔ እና እርሱ ቀረን። በዚህ ጊዜ ሀፍረተ ስጋውን አሳየኝ። ድርጊቱን እንዳየሁ ጮኽኩኝ፤ የነበረኝ አማራጭ ከታክሲው መውረድ ስለነበር በጊዜው ያንን አድርጊያለሁ» ስትል ጽዮን አስደንጋጭ ገጠመኟን ገልጻለች።

አዲስ አበባ ለሴቶች ምቹ አይደለችም የምትለው ጽዮን፣ በተለይ ሰው ተጨናንቆ በሚሳፈርባቸው ታክሲዎች እና አውቶብሶች ላይ መጎንተል፣ አላስፈላጊ የሰውነት ንክኪ ማድረግ፣ አለፍ ሲልም መመታት የተለመደ እየሆነ ነው ትላለች።

በዚህም ምክንያት ሴቶች ነፃነት እንዳይሰማቸው ሆነዋል የምትለው ጽዮን፣ ድርጊቱ ተፈጸመብን ብለው ቢናገሩ እንኳን ‹‹የተለመደ አይደል ወይ፤ አንቺ ዝም ብለሽ ነው›› የሚሉ ማሸማቀቂያዎች ዝም እንዲሉ ያደርጓቸዋል ትላለች። እንደ እርሷ አባባል ደግሞ፣ ይህ ሁኔታ ወንዶች የተለመደ እና መብታቸው እስኪመስላቸው ድረስ የሚፈፅሙት ድርጊት እየሆነ እንዲመጣ አድርጎታል።

እንደዚህ ዓይነት ድርጊቶች ሲፈጸሙ እንደ ፖሊስ ያሉ የፀጥታ አካላት እንኳን ‹‹ምን ይደረግ ታዲያ! የተለመደ አይደል ወይ!›› የሚል ምላሽ ይሰጣሉ ስትል ገልጻለች። በተለይ ሲመሽ ችግሩ ተባብሶ ይስተዋላል የምትለው ጽዮን፣ ከመሸብኝ ወደ ቤቴ ለመግባት የኮንትራት ታክሲ እጠቀማለሁ አለበለዚያ ወደ ሰፈሬ እንኳን ለመግባት ከፍተኛ ስጋት ይሰማኛል ስትል ትናገራለች።

በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 35 መሰረት ሴቶችን የሚጨቁኑ፣ በአካላቸው ወይም በአዕምሯቸው ላይ ጉዳት የሚያስከትሉ ሕጎች፣ ወጎችና ልማዶችን ከመከላከል ባሻገር መንግሥት የሴቶችን ከጎጂ ድርጊቶች ተፅዕኖ የመላቀቅ መብታቸውን የማስከበር ኃላፊነት እንዳለበት በግልፅ ያስቀምጣል። ሴቶች በበታችነትና በልዩነት በመታየታቸው የደረሰባቸውን ጎጂ የታሪክ ቅርስ ከግምት ውስጥ በማስገባት፤ ይህ ቅርስ እንዲታረምላቸው ልዩ የድጋፍ እርምጃዎች ተጠቃሚ የመሆን መብት እንዳላቸው ይደነግጋል።

የመብት ጥሰቶቹ ግን ሴቶች በተለያዩ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ላይ በፈለጉት እና በተመኙት ልክ እንደይሳተፉ እንቅፋት እየሆኑባቸው ነው። ይህንንም በሚመለከት ሴቶችን ከጥቃት ለመከላከል እና መብቶቻቸውን ለማስከበር እንዲተጉ የሚታገሉ ሴቶች ከምን ጊዜውም በላይ ድምፃቸውን ለማሰማት እየጣሩ ይገኛሉ።

የሴታዊት የጾታ እኩልነት ንቅናቄ መሥራቾች መካከል ስኂን ተፈራ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የከተማ ኑሮ አንዱ መገለጫ የሕዝብ መጓጓዣ ሲሆን ድርጊቱ ጎልቶ ከሚስተዋልባቸው ቦታዎችም አንዱ ነው ብለዋል። ጾታዊ ጥቃት አዲስ አበባ ወስጥ የሚያሳስብ ደረጃ ላይ ደርሷል የሚሉት ስኂን፣ በፊት ስንሰማ እንዴት ይሆናል እንል ነበር። አሁን ከቃል ትንኮሳ ጀምሮ ለመስማት የሚከብዱ ጥቃቶችን በማታ ብቻ ሳይሆን በቀንም እንደሚፈጸሙ በተደጋጋሚ ይሰማል ይላሉ።

«ሴቷ እንዳታወራ እና እንድትሸማቀቅ ይደረጋል፤ የለበስሽው ልብስ ነው፤ ማን በማታ ውጪ አለሽ የሚሉ ሐሳቦች ይነሳሉ። ወንዶችም ቢሆኑ ድርጊቱን መፈጸምን እንደ መብት መቁጠር ጀምረዋል። ኅብረተሰቡ እነዚህን ምክንያቶች የሚቀበል ከሆነ ከበዳዮች ጋር እየወገነ መሆኑን ሊረዳው ይገባል» ብለዋል፤ ስኂን።

‹‹ሴቶች በተለያዩ ምክንያቶች ሊያመሹ ይችላሉ፤ አገራቸው እስከሆነ ድረስ እና ዜጋ እስከሆኑ ድረስ በነፃነት የመንቀሳቀስ መብት አላቸው›› የሚሉት ስኂን፣ ለሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች ማንንም ማስረዳት እንደማይጠበቅባቸው ይገልጻሉ። ‹‹ነገር ግን…›› ይላሉ ስኂን፣ ‹‹በከተማዋ ያለው ተጨባጭ ሁኔታ ይህንን የሚያሳይ አይደለም።››

ለሴቶች ምቹ የሆነ ከተማን ለመፍጠር ከሚንቀሳቀሱ ተቋማት መካከል የወጣት ሴቶች ክርስቲያናዊ ማኅበር አንዱ ነው። ማኅበሩ ከፕላን ኢትዮጵያ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ለሴቶች ምቹ የሆነ ከተማን ለመፍጠር ከሚመለከታቸው አጋር ተቋማት ጋር በመሆን በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል።

የማኅበሩ የሴት ሕግ ባለሙያዎች ማኅበር ተወካይ እና ኮሚቴ ሰብሳቢ ቤተልሔም ደጉ፣ በሴቶች ላይ የሚፈፀመው ጥቃት ዓይነቱ ብዙ እንደሆነ ያነሳሉ። ቤተልሔም ጉዳቱ ሥነ ልቦናዊ እና አካላዊም ጭምር ነው ያሉ ሲሆን፣ በከተማዋ ያለው የመጓጓዣ አገልግሎት ከሰልፍ እና ከግፊያ ጀምሮ ሴቶችን ለአላስፈላጊ ትንኮሳ የሚዳርግ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

ምቹ መጓጓዣ መፍጠር በሚል ፕሮጀክት በከተማዋ በተደረገ የዳሰሳ ጥናት፣ ሴቶች እንኳን በማታ በቀንም ቢሆን ወንዶች በቁጥር በዛ ያሉበት ታክሲ ውስጥ የሚያስቸኩል ጉዳይ እንኳን ቢኖራቸው ለመግባት እንደማይፈልጉ መግለፃቸውን ቤተልሔም አብራርተዋል። ጥቃቶቹ በተሳፋሪዎች አንዳንዴም በትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች እንደሚፈፀሙም ተናግረዋል።

አክለውም፤ በከተማዋ ያለው የመጓጓዣ ችግር እና እጥረት ሰዎች በትርፍ ተጭነው እንዲሄዱ ያደርጋል፤ በተለይም ደግሞ አካል ጉዳተኛ ሴቶች፤ ነፍሰ ጡሮች እና ልጅ የያዙ እናቶች ‹‹አይመችሽም!›› በሚል ሰበብ አገልግሎት ማግኘት ሳይችሉ ይቀራሉ፤ ሲሉ ከተማዋ ምን ያህል ለሴቶች ምቹ እንዳልሆነች ያብራራሉ። ‹‹ሊፍት እንስጣችሁ›› በሚል ሰበብ በርካታ አካል ጉዳተኛ ሴቶች ላይ እስከ መደፈር የሚደርስ ጥቃት እየተፈፀመ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል።
አዲስ አበባችን ለሴቶች ምቹ አይደለችም የሚሉት በሴቶች፣ ሕፃናት እና ወጣቶች ሚኒስቴር ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን መከላከያ ብሔራዊ ጥምረት አስተባባሪ አበባው ቦጋለ ናቸው። ሴቶች በሕዝብ መናፈሻዎች እና መጓጓዣ ላይ እንደልብ መንቀሳቀስ አይችሉም ሲሉ የሚገልጹት አበባው፣ እንደውም ከእምነት ቦታዎች ሳይቀር በጠዋትም ሆነ አምሽተው መመለስ አዳጋች እየሆነባቸው እንደሚገኝ አንስተዋል። ችግሩ በግንባታ ቦታዎች ላይ በሚገኙ ሴቶች ላይ ጎልቶ ይታያል ያሉት አስተባባሪው፣ ሥራ ለመቀጠርም ሆነ በሥራ ላይ ለመቆየት ሴቶች እነዚህን ጥቃቶች በዝምታ እንዲያልፉ እንደሚገደዱ ተናግረዋል።

በተለይ በምሽት ሴቶች በመሆናቸው ብቻ በሕዝብ መጓጓዣ ላይ ተጨማሪ ክፍያ እንዲከፍሉ እንደሚጠየቁም ገልፀው፤ እነዚህን ጥቃቶች ለመከላከልም ሆነ ግንዛቤ ለመፍጠር ተቋማት በጋራ የሚሠሩት ሥራ የለም ብለዋል።

እንደመፍትሔ
በሴቶች ዙሪያ የሚሠሩ ማኅበራት እና የሴቶች መብት ተሟጋቾች በኅብረተሰቡ ውስጥ ሴቶች ከወንዶች እኩል ተንቀሳቅሶ የመሥራት መብት እንዳላቸው የማሳመን ሥራዎች መሠራት እንዳለባቸው አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ባለሙያዎች ጠቁመዋል።

በተለይ በመጓጓዣ አገልግሎት ላይ በሚፈፀሙ ጥቃቶች ላይ ከአገልግሎት አቅራቢው ጀምሮ እስከተሳፋሪው ድረስ አላስፈላጊ የቃላት ጥቃትን ጨምሮ መሰል አካላዊ ንክኪዎችን ማድረግ እንደማይገባ በሕግም እንደሚያስጠይቅ ግንዛቤ መፈጠር እንዳለበትም አሳስበዋል።

መንግሥት ለመጓጓዣ ዘርፉ በቂ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፤ በቂ የመጓጓዣ አማራጮች መኖራቸው ሴቶች ያላቸው ተጋላጭነት እንዲቀንስ ለማድረግ ጉልህ አስተዋፅኦ ያበረክታል ሲሉም ጥሪያቸውን ለመንግሥት አቅርበዋል።
ለአብነትም ለሴቶች ምቹ የሆነ የመጓጓዣ አማራጭ ቢዘጋጅ በተለይ በምሽት ደኅንነታቸው አስተማማኝ የሆኑ በተመጣጣኝ ዋጋ ለሴቶች ብቻ አገልግሎት የሚሰጡ አማራጮች ቢኖሩ ሴቶች ከወንዶች እኩል ተንቀሳቅሰው መሥራት እንዲችሉ ይረዳቸዋል ብለዋል። የሴቶችን ጥቃት ለመከላከል የሚሠሩ ማኅበራት እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ትልቅ ትኩረት በመስጠት በርካታ ጥናቶችን ሊያደርጉ እንደሚገባም በጉዳዩ ላይ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከል የሚሠሩ ባለሙያዎች አንስተዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 62 ጥር 2 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here