ቆይታ ከኢትዮጵያዊው ቢሊየነር ጋር

0
754

ከዛሬ ኹለት ዓመት በፊት በፎርብስ መጽሔት ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ ቢሊየነሮች ውስጥ ሥማቸው ለሕዝብ ይፋ ከሆኑት ባለሃብቶች መካከል አንዱ የሆኑት ብዙአየሁ ታደለ ቢዜኑ፣ በሥሩ 17 ድርጅቶችን ያቀፈው ኢስት አፍሪካ ሆልዲንግስ ግሩፕ ሊቀመንበር እና መሥራች ናቸው።

ድርጅታቸው የተለያዩ በተደጋጋሚ ጥቅም ላይ የሚውሉ ምርቶችን እና ሲሚንቶ በማምራት የሚታወቅ ሲሆን፣ ከዚህ በተጨማሪ በትራንስፖርት፣ ሪል ስቴት፣ ማዕድን እና የሕትመት ሥራዎች ላይ ተሰማርቷል። ብሔራዊ ሲሚንቶ ፋብሪካ፣ ኢስት አፍሪካን ታይገርስ፣ ኢስት አፍሪካን ሪል ስቴት እና ሃማሬሳ የዘይት ፋብሪካ ድርጅታቸው ካቀፋቸው ታዋቂ ኩባንያዎች መካከል ይጠቀሳሉ።

ብዙአየሁ ኢስት አፍሪካ ሆልዲንግስን የመሠረቱት ከ25 ዓመታት በፊት ሲሆን፣ በቤተሰባቸው ንግድ ላይ በመሰማራት ሦስተኛ ትውልድ ናቸው። በጥበብና በትዕግስት እንዲሁም በግልጽነት ሥራን የመሥራት ዋጋን አጥብቀው የሚያነሱት ብዙአየሁ፤ አያታቸው ከ100 ዓመታት በፊት የጀመሩት ንግድ በደርግ ጊዜ ፈተና ቢገጥመውም፣ ዳግም እንዲነሱ የረዳቸው ይኸው ጥንካሬና የሥራ ፈጠራ ክህሎት እንደሆነ ያወሳሉ።

በአሁኑ ሰዓት እርሳቸው በሊቀመንበርነት የሚመሩት ኢስት አፍሪካ ሆልዲንግስ ከ5000 በላይ የሥራ ዕድል ለዜጎች ፈጥሯል። የድርጅቱ ዓመታዊ ገቢ ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ ሲሆን አገሪቷ ውስጥ ከሚገኙ ጥቂት ከፍተኛ ግብር ከፋዮች ውስጥ ይመደባል። ባለፈው በጀት ዓመት ብቻም ከግማሽ ቢሊየን ብር በላይ ግብር ከፍለዋል።

የአዲስ ማለዳው ሳምሶን ብርሃኔ ስለ ስኬታቸው እንዲሁም ወቅታዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ከብዙአየሁ ጋር ቆይታ አድርጓል።

ኢስት አፍሪካን ሆልዲንግስ ከ100 ዓመት በላይ ታሪክ ያለው ድርጅት ነው። ከየት ተነስቶ የት ደረሰ? በመካከል ለግሉ ዘርፍ የማይመች ጊዜ ነበር፤ በተለይ የደርግ። ያንንስ እንዴት አለፋችሁት?
የእኛ ሥራ የጀመረው በ19ኛው ዘመን መባቻ ላይ አያቴ ናቸው የጀመሩት። ቢዜኑ ይባላሉ። ሲጀመር ባህላዊ ነበር፤ በከብት የሚነገድ፣ የቆዳና የዝሆን ነበር። ከዛ በኋላ የእርሳቸው ልጆች ሥራውን ወሰዱት፤ የእኔ አባት ማለት ነው። እነሱ ሲወስዱት ከቀደመው በተሻለ አንድ ደረጃ ሄደው በቡና ሥራ፣ ቡና በማጠብ፣ የጀነሬተር መብራት፣ የውሃና የእህል ወፍጮ፣ የቡና መፈልፈያዎችን በመሥራት በደቡብን እና በአዲስ አበባ ደግሞ ሪል እስቴቶች ሠሩ፤ ወንድማማቾች በጋራ ነው የሠሩት።

ይህ እስከ 1974 በዚህ መንገድ ቀጠለ። በ1974 አብዛኛው የቤተሰቡ ንብረት ተወረሰ። በዚህ ሰዓት በእኛ የነበረው የሥራ ፈጠራውና ዲሲፕሊኑ ነበር። ያንን ደርግ መውሰድ አልቻለም። ያንን ይዘን በጥበብ፣ በትዕግስት፣ በተለይ በግልጽነት በመሥራትና ያንን በማዳበር ልንሻገር ችለናል።

በአገራችን እንዲህ ያሉ ስኬታማ ቢዝነሶችን ማግኘት ቀላል አይደለም። እና የስኬታችሁ ምክንያት ምንድን ነው?
ለእኛ ትልቁ ለስኬት የረዳን የምንሠራበት የቢዝነስ ፍልስፍናችን ነው። አብዛኛውን ወደ ኢንደስትሪ ነው የሄድነው። እነዚህ ደግሞ ተሻጋሪ ናቸው። ዘላቂ በሆነና ተቋማዊ መንገድ ስለምንሠራ፣ ባለሙያ ስለምንጠቀም፤ ያልተማከለ ስርዓት በመያዝ ድርጅቱን ውጤታማ አድርገናል። ለዛ ነው በዚህ ልክ ስኬታማ መሆን የተቻለው። ግልጽነት በጣም ትልቅ አስተዋጽኦና ለስኬታችንም እገዛ አድርጎልናል።

ደርግ ንብረት ሲወርስ ብዙ ሀብት ያስቀረላችሁ አይመስለኝም። ወደሥራ ስትገቡ ገንዘብ ከየት አመጣችሁ?
ያኔ ስንወረስ ትሬዲንግ ውስጥ እንሠራ ነበር፤ በእጃችን ገንዘቦች ነበሩ። በቡና መፈልፈያ ሥራ የተወሰኑ ገንዘቦችና የተወሰኑ ያልተወረሱም ነበሩ። ያንን በመያዝ ነው። ዋናው የጠቀመን የሥራ ፈጠራችንን መያዛችን ነው። ፍራቻ አልነበረም፤ ዋናው እሱ ነበር። ጽናታችንን፣ ርዕያችንን ደርግ ሊወስድ አልቻለም። ትልቁ ምስጢርም እሱ ነው።
ያኔ የሥራ ፈጠራም ስለነበረን ወዲያው በአጭር ጊዜ ነው ራሳችንን ያቋቋምነው። እና ዋናው የሥራ ፈጠራ ነው። ብዙ ሰው የሚሻገረው በሥራ ፈጠራ ነው ብለን ስላምናምን ብዙም አልደነገጥንም። ለመኖር እንኖራለን፤ ወደዚህ ለመሻገር ግን እነዚህን እሴቶች ስለነበሩን እነሱን ይዘን ነው። በተለይ ዲሲፕሊን ባህል አለን። ግልጽነት፣ ሐቀኝነት የምንላቸው እንደ ቤተሰብ መመሪያችን ነው። ያንን ይዘን ልንሻገር ችለናል።

ከ1983 በኋላስ እንደ አዲስ ወደ ቢዝነስ ስትመለሱ የነበረው ፈተና ምን ነበር?
ከ1983/91 በኋላ የተሻለ ጊዜ ነው። ፖሊሲ ቀርጸዋል፤ ገብቷቸዋል። ያኔ ደግሞ ቀዝቃዛው ጦርነት ያለቀበት ነበር። ያኔ እንደውም ወደ ኢንደስትሪው እንድትገባ ይገፋፉ ነበር። ብዙ ድጋፍም አድርገዋል። የተወሰነ መስመር፤ የሄዱበት መንገድ አለ። በዛ ውስጥ ሠርተናል። ግን ያ ስለረዘመ ነው ችግር የተፈጠረው። ኢኮኖሚው በጊዜ ቢከፈት ኖሮ ብዙ ለውጥ እናመጣ ነበር።

ኢንዱስትሪው በዘርፍ ደረጃ ለኢኮኖሚው ያለው አስተዋጽአ አነስተኛ ነው። በተጨማሪም ፈታኝ ነው። ለምን በተለየ መንገድ በዚህ ዘርፍ ላይ አተኮራችሁ?
ከ1983 በኋላ ሥራውን ስንጀምር እንደ ፍልስፍና የወሰድነው እነዚህ ኢንደስትሪዎች ውስጥ ብንገባ ተሻጋሪ፣ ዘለቂ፤ ለአገር በሥራ ፈጠራም ቢሆን የሚጠቅሙ ናቸው። እና ከዚህ ውጪ የነበረው ምርጫ በትሬዲንግ እና መደበኛ ባልሆነ በኅቡዕ ሥራ ውስጥ መግባት ነበር። ያ ደግሞ የራሱ የሆነ ችግር አለው፤ ዘላቂም አይደለም።
በዛ ቢዝነስ ውስጥ ዳጎስ ያለ ገንዘብ ወይም ጥሩ ጥቅም ማግኘት ይቻል ይሆናል። ግን ዘላቂ አይደለም። እንቅስቃሴው በእኛ እሳቤ ፈጠራን የሚገድል፣ ፍራቻ የሚያመጣ ነው። አንድ የፈጠራ ሥራ ፍራቻ ውስጥ መግባት የለበትም የሚል አካሄድ አለን። ፍራቻ ከመጣ ደግሞ ተወዳዳሪ መሆን አትችልም። እኛ ይህኛውን ዳጎስ ያለ ጥቅም ባይኖረውም አገራዊ ጥቅም አለው፣ በጣም እርካታ አለው፣ በሥራ ፈጠራ ውስጥ መሥራት ይቻላል።

ይህን ይዘን የነበረው ጉዞ በጣም ፈታኝና አስቸጋሪ ነው። ግን እናውቀዋለን። ከዛኛው መንገድ ይሻላል በሚል ሄድን። በዚህም ውጤታማ እየሆንን ቀጠልን። ያደረግነው አንዱ አንዱን በማቻቻል፣ የፈጠራ አቅምና እውቀት በመጠቀም፤ የአገር ውስጥና የውጪ ሰዎችን በማምጣት በጣም ነው የደከምነው። ትርፍን ኹለተኛ አድርገን ነበር የምናየው። ማትረፍ ወሳኝ ነው፤ ለዘላቂነት አስፈላጊ መሆኑን እናውቃለን። ያም ሆኖ ይህ ቀጣይና አሻጋሪ ስለሆነ ለቀጣይም ጉዞ ስለሚጠቅም ነው ኢንደስትሪ ላይ ያተኮርነው። በዚህም ደግሞ ውጤታማ ነን ብለን እናስባለን።
በአገራችን አብዛኛው ባለሀብት ግን ወደዚህ ለመሄድ ፍርሃት አለ፤ መንግሥትም በቂ ማበረታቻ አይሰጥም።

ማበረታቻው አነስተኛ መሆኑ ያለው ተጽእኖ አልተጫናችሁም?
ነገሩ አልጋ በአልጋ አልነበረም። ጉዞው በጣም ኃይለኛ ነበር። እንዳልኩት ምርጫው ኹለት ነው። ትሬዲንግ እና ኢንፎርማል ግሩፕ የራሱ ችግር አለው፤ በጊዜው። እኛ ሦስተኛ ትውልድ ነን። የሥራ ፈጠራው፣ ተጋላጭነቱ ቀድሞም አለ፣ ይህ የራሱ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው። በጣም አስቸጋሪ ቢሆንም፣ በጊዜው ዘርፉ አትራፊ የሚሆንበት ሰዓት ነበር፤ በተለይ አንዳንድ ዘርፎች ላይ። ለምሳሌ የሻይ ቅጠል። በዚህ በግል የገባነው ለመጀመሪያ ጊዜ እኛ ነበርን። ሌላው መንግሥት ያቋቋመው ነው። የቤተሰብ ባህልም አዎንታዊ ተጽእኖ ነበረው።

ችግር ግን ነበር። በንጽጽር ሲታይ ግን ዘርፉ ሀብትን ያሳድጋል፣ ትማርበታለህ፣ እውቀት ይገኝበታል። ይህ ራሱ ተሻጋሪ ነው። አንድን ቢዝነስ ስታይ ገንዘቡን ብቻ ከታየ ችግር ነው። ቀጣይነትን ካየህ ግን፣ እኛ ለምሳሌ እውቀት አዳብረናል። ይህን በገንዘብ አታየውም።

የመንግሥት እርዳታ ጥሩ ነበር። ማሽን ለማስገባት፣ ብድርም ይሰጠን ነበር። ይህን ለመጠቀም እንፈልግ ነበር፤ ብዙ ሰው አልገባበትም። የከፋ ችግርም አይደለም፤ ቢረዱን ጥሩ ነበር። ዋናው ባለሀብቶች ያልገቡት የሚመስለኝ ተቋማዊ ተጋላጭነት ወይም ልም የመያዝ ጉዳይ ይመስለኛል።

የገንዘብና የፋይናንስ ተቋማት እጥረት አለ ይባላል። ወደ ሼር ካምፓኒ መለወጥም የተለመደ አይደለም። በእናንተ በኩል እንዴት አድርጋችሁ ነው ይህን ችግር የምትጋፈጡት?
እኛ ወደ ፐብሊከ የመሄድ ትልቅ እሳቤ አለን። ለማደግና ዓለማቀፍ ለመሆንም አማራጩ እሱ ነው። ልክ ነው፤ ችግር አለ። ይህ ግን የማክሮ ኢኮኖሚክ ፖሊሲ ነው። የመንግሥት ይዞታዎች የግል መደረግ አለባቸው ብለን የምናምን ሰዎች ነን። አንዱ ችግር ይህ ነው፤ የፋይናንስ አማራጮች የሉም። እና ለማደግ ትልቅ ማነቆ ናቸው። ይሄ ኢኮኖሚው ነፃ ከተደረገና ከተመቻቸ፣ ጥሩ እድሎች አሉ ብለን እናስባለን። ትልቁ የገጠመን ችግር የፋይናንስ አማራጭ አለመኖራቸው ነው። ሌሎች አገራት ኬንያ ለምሳሌ ምንም የውጪ ምንዛሬ ችግር የለባቸውም፤ በፖሊሲው ምክንያት። እዚህ የምንሟገተው ለዚህ ነው። እንደውም በጣም የዘገየ ነው። ነፃ ማድረግ ሲባል በሙሉ የፋይናንስ ዘርፉ ክፍት መሆን ነፃ መደረግ አለበት። ጊዜ ይፈልጋል፣ ጥናት ይፈልጋል።

ግን ፖለቲካውም ኢኮኖሚውም ተያይዘው ነው ያሉት፤ አትለያቸውም። እና ኢኮኖሚው ነጻ መደረግ አለበት።
ውድድሩን ማለፍ የምትችሉ ይመስላችኋል?
አሁንም ማየት ያለብን ከኹለት አንጻር ነው። ከራስ እይታ ከታየ ሌላ ነው፤ ከአገር ከታየ ሌላ ጉዳይ ነው። ኢኮኖሚው ቶሎ ካልተለወጠ አሁን ባለው ሥራ አጥነት፣ እኛም መቆየት አንችልም። አሁን ትልቅ የእውቀት ክፍተት፣ የሥራ ባህል ችግር በኢትዮጵያ አለ። ይህን የምትፈታው የአገሪቱን ኢኮኖሚ በመክፈት ነው። እኛ ለመቆየት የራሳችን አካሄድ ሊኖረን ይችላል። እኛ የምናስበው ለአብዛኛው ወጣት እንጂ ለጥቂት ባለሀብት ከተባለ ባይከፈት በጥቂት ከለላ መኖር ይቻላል። የሚከፈል ዋጋ ይኖራል፤ አገሪቷ ከቀጠለች ግን ትልቅ ፈተና ነው። አሁን ያለው ሥራ አጥነት ትልቅ ችግር ነው።

የካፒታል፣ የሰው፣ የእውቀት ችግር አለ። እና መከፈት አለበት፣ ፈተና ይገጥማል መታገል ያስፈልጋል። እንደውም ፈተና የሚገጥመን ከሩቅ አይደለም፤ ከቅርብ ከኬንያ ነው። ኬንያዎች ቢመጡ እኛን ለቁርስ ነው የሚያደርጉን። ግን በሂደቱ እንማራለን። እነሱ ቢያንስ የሥራ እድል ሊፈጥሩ፣ የሥራ ባህል ሊያመጡ ይችላሉ።

ለምን ሥያሜው ‹ኢስት አፍሪካ› ተባለ፤ በምሥራቅ አፍሪካ የመስፋፋት ግብ አላችሁ?
እውነቱን ለመናገር፤ ኢትዮጵያውያን ዓለምአቀፍ ካልሆንን ዋጋ የለንም። ትልቁ ያመለጠን እድል እሱ ነው። እድሉ ነበረን። ችግር የተፈጠረው የኢኮኖሚ ፖሊሲው ስለገደበ ነው። እንጂ በቀላሉ ዓለማቀፍ ልንሆን እንችላለን። ኢትዮጵያ ውስጥ መሻሻል ካለባቸው ነገሮች አንዱ፤ አቅም ያላቸው የኢትዮጵያ ባለሀብቶች ዓለማቀፍ መድረክ ላይ መሄድ አለባቸው፤ በሕጋዊ መንገድ። አሁን ግን መሄድ አትችልም፤ በፖሊሰው ምክንያት። ፖሊሲው ቢሻሻል መሄድ ይቻላል። አሜሪካ ለምሳሌ ትልቅ የኢትዮጵያዊ አቅም አለ። ፖሊሲው ለመሄድ ቢፈቅድልን፣ ትልቅ ተዓምር መሥራት ይቻል ነበር።

ኬንያውያን ቢመጡ ቁርስ ነው የሚደርጉን ባሉት አገላለጽ፤ እኛ ውጪ አገር ሄደን ለመሥራት አቅሙ ይኖራል?
እንዳልኩት ስላልተዘጋጀን ነው። ይህ የኹለትና ሦስት ዓመት ችግር ነው። ውጪ ብንሔድ እኛም እንማራለን፤ ኒውክሌር ሳይንስ አይደለም። የሰው አቅም ነው። ዛሬም የሰው አቅም አለ። ዓለማቀፍ ስትሆን ዓለማቀፍ አስተሳሰብ፣ ተጋላጭነት፣ ሀብትም ይኖርሃል። ሀብት ታመጣለህ። አሁንኮ ፖሊሲው ሀብት እንድትወስድ እንጂ እንድታመጣ አያደርግህም።

ይሄ አነጋጋሪ ነው፤ የኢኮኖሚ ባለሙያዎችም አላዩትም። ለምሳሌ ኬንያ ውስጥ የኬንያ ከብት በኮንትሮባንድ አይወጣም። ለምን እኛ አገር ይወጣል? ወርቅ ይወጣል፣ ቡና ይወጣል፣ ጥራጥሬ ይወጣል፤ ለምን? ፖሊሲ አውጪዎቹ በዚህ ዙሪያ አላጠኑም የሚል ግምት አለኝ።

በአሜሪካ ያለውን አቅም ለምሳሌ አልተጠቀምንበትም። በአሜሪካ የአበሻው ብቻ የነፍስ ወከፍ ገቢ በቢሊዮን የሚቆጠር ነው። ያንን እንኳ ማግኘት ይቻል ነበር። ግን አንችልም፤ ሕጉ ይከለክላል። ብዙ ያላየነው ያልገባን ነገር ስላለ ነው። ላለፈው 45 ዓመት የነበረውን አስተሳሰብ ስናይ፣ ሀብት መፍጠር እጹብ ድንቅ የሆነ ነገር ሆኖ ሳለ፤ ሰዎች ግን በክፉ ፈርጀውታል።

በቅርቡ ፎርብስ ላይ ከመጀመሪያ አምስት ኢትዮጵያውያን ቢሊየነሮች መካከል ተጠቅሰው ነበር። እስቲ ምን ያህል ግብር እንደከፈሉ፣ የፈጠሩትን የሥራ ዕድል ይንገሩን?
እውነት ለመናገር ኢትዮጵያ ውስጥ ቢሊየነሮች አሉ ብዬ አልቀበልም፤ በአንጻራዊ ደረጃ ይኖራል፤ በዓለም አቀፍ እይታ ሲታይ ብዙዎቻችን በዛ ደረጃ አይደለንም። እንዳልኩት አንጻራዊ ስለታየ እንጂ ኢትዮጵያውያን ሀብታም አሉ ብዬ አልቀበልም። ገና ነን፤ በዚህ ደረጃ የሚታይ ሀብ የለም።

በሥራ ፈጠራ ከ5 ሺሕ ሰው በላይ የሥራ እድል ፈጥረናል። በታክስ ባለፈው ዓመት የከፈልነው በጠቅላላ 500 ሚሊዮን ነው።

ሀብትን ወደ ግል በማዞር ሂደት ውስጥ በብዛት የሚሳተፉት የውጪ ድርጅቶች ናቸው፤ ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች አይታዩም። የእናንተ ድርጅት በዚህ ደረጃ ምን ለውጥ ያመጣል?
መጀመሪያ የግል መደረጉ ላይ መከፈት አለበት ከሚሉ ወገኖች አንዱ ነኝ። ዋጋ ሊያስከፍለን ይችላል። ግን የአገር ውስጥ ባለሀብት በዛ ደረጃ የተዘጋጀ አለ ብዬ አላስብም። ችግር ሊመጣ ይችላል። ምንአልባት መንግሥት ፖሊሲው የአገር ውስጥ ባለሀብቶችም እንዲገዙ ማድረግ ቢቻል፤ ቢያደርግም ጥሩ ነው።

ግን መከፈቱ ይጠቅማል ነው የምለው። ዘግተህ መቆየት አትችልም። ጥሩ ማሳያ አለ። ቢራዎች መጥተዋል፣ ከየት ተነስተው የት እንደደረሱ ማየት ይቻላል። በሰው ሀብት ልማት ዙሪያ፣ በታክስ ክፍያና መስፋፋት ላይ ጥሩ አስተዋጽኦ አድርገዋል። ቀደም ብሎ ቢከፈት እኛም እንዘጋጅ ነበር። በእኔ ድርጅት በኩል አንዳንድ ነገሮች እየተዘጋጀን እያጠናን ነው ያለነው።

በሲሚንቶ ማምረት ላይ እየሠራችሁ ነው። ለውጪ ገበያ ማቅረብ ላይ ከፍተኛ ገቢ ያመጣ ዘርፍ ነበር። አሁን ግን እየቀነሰ መጥቷል፤ ለምን ይመስልዎታል?
እውነት ለመናገር የፖሊሲ ችግር ነው የሚመስለኝ። ፖሊሲ አውጪዎች ማየትና ማጥናት አለባቸው ብዬ አስባለሁ። ግለጽ ነው፤ ለምሳሌ ወርቅ በጥቁር ገበያ ይወጣል። ለምንድን ነው የሚለውን ጉዳይ ማጥናት ያስፈልጋል። ለምን ኬንያ አይሄድም? የሚለው ጉዳይ መጣራት አለበት። በፍጹም የፖሊሲ ችግር ነው። የኢትዮጵያን አንድ ሺሕ ኪሎሜትር ድንበር በወታደር ልትጠብቅ አትችልም፤ በፖሊሲ ነው የምትከላከለው። ለምሳሌ ከብት ወደ ጅቡቲ ከወጣ፣ ጥራጥሬ ኬንያ ወይም ሶማሊ ከሄደ፣ ለምን ይወጣል። ኢትዮጵያውያን በተፈጥሮ ሌባ ስለሆኑ ነው? አይመስለኝም።

ኢኮኖሚውን ነጻ ስታደርገው ገበያውን የሚቆጣጠሩ ግለሰቦች አሉ። ገበያው የሚመራ ከሆነ፤ ሰዎች ኬንያ አይሄዱም። ኬንያ መሄድኮ ውድ ነው፤ በጥቁር ገበያ ለመሄድ የሚከፈል ክፍያ አለ። ግን እዚህ ቁጭ ብለህ ብትለቀው ይቻላል ነው። ይህ ቀላል ነገር ነወ። ያልታየበት የራሱ የሆነ ምክንያት ይኖራል።

ስለዚህ ተስፋ እናደርጋለን፤ ነገሮች ይሻሻላሉ። በጣም በጎውን የማስብ ሰው ነኝ። ግንዛቤ አለ ብዬ አስባለሁ። ኢኮኖሚው ቢከፈት ምንም ዓይነት የጥቁር ገበያ አይኖርም። ግልጽ ነው፤ ኬንያ ውስጥ ጥቁር ገበያ የለም።

ሲሚንቶ ፋብሪካዎች ላይ የተቸገራችሁበት ጊዜ ነበር። በተለይም ከፖለቲካ አለመረጋጋት ጋር ተያይዞ፤ ያ ተጽእኖ የለውም?
አንደኛ እንዳልኩት ፖሊሲ ነው። ሌላው የሠላም ጉዳይ ነው። ማንም ባለሀብት አገሩ ውስጥ ተንቀሳቅሶ ካልሠራ አይሆንም። የመንግሥት ቅድሚያ ሊሆን የሚገባውም የሰላም ጉዳይ ነው። ጊዜያዊ ነው ብለን ስለምናስብ፤ የአጭር ጊዜ እቅድ በማዘጋት እየተከላከልን እንጂ፣ ብዙ ቦታ አስቁመውናል፣ ማሽኖቻችን ተይዘዋል።

ይህ የሆነው ላለፈው አራትና አምስት ዓመት አካባቢ ነው። ከፍተኛ ችግር ነው። ኢንቨስትመንት ይጎዳል፤ ይህ ካልተስተካከለ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ነፃ ቢደረግ፣ ፖሊሲ ቢሻሻል ሰላምና መረጋጋት ካልመጣ የትም መሄድ አይቻልም። ስለዚህ መንግሥተት የህግ የበላይነት ላይ መሥራት አለበት። ተስፋ የሚደረጉ ነገሮችም አሉ። ወደ ፖሊሲ የምትሄደው ሰላምና መረጋጋት ሲኖር ነው።

የችግሩ አንዱ ተወቃሽ ራሳቸው ፋብሪካዎች ናቸው፤ የአካባቢውን ሰው ተጠቃሚ በማድረግ በኩል ችግር አለባቸው ተብሎ ወቀሳ ይሰማል። እናንተስ ምን ምን ሠርታችል?
ይህን በኹለት ነገር እንየው። አንዱ አካታችነት የሚባለው ነው። በአካታችነት ላይ እኛ ፖሊሲ ነድፍን የአካባቢው ሰዎች ተጠቃሚና የድርሻ ተካፋይ እንዲሆኑ እየሠራን ነው። ለምሳሌ ከሰል ላይ ከወጣቶች ጋር እነርሱ እንዲያመርቱ፣ እኛ ደግሞ ምርቱን ገበያ ላይ ማቅረብ የሚል እቅድ አውጥተን እየተነጋገርን ነው። በየአካባቢውም በዛ መልክ እየሠራን ነው። ይህን ሠርተን የሰላም ጉዳይ ትእግስት አልሰጠውም። እንጂ ይህን ቀርጸን ኦሮሚያ ላይ አቅርበን ተነጋግረንበታል።

ማኅበራዊ ኃላፊነትስ ላይ?
እሱም ላይ እየሠራ ነው። አንድ ድርጅትም አቋቁመናል። ማኅበራዊ ኃላፊነት ጽንሰ ሐሳቡ ሰፊ ነው። በተለይ ከኢትዮጵያ ቢዝነስ ከባቢ አንጻር ሲታይ ብዙ ፈተና አለ። እኛ እያልን ያለነው፣ በጣም ደክመን ብዙ ትግል ነው የምንሠራውና፤ 5000 ሠራተኛ ይዘናል። ይህን ይዘን መጓዝ ራሱ ትልቅ ማኅበራዊ ኃላፊነት ነው። ያ እንደተጠበቀ ሆኖ አሁን እያጠናን ነው። አሁን የምናስበው ከምናገኘው ገንዘበ የተወሰነ ትርፍ መስጠትን ነው።
ግዴታ መሆኑ ይጠቅማል ባይ ነኝ። እኛ አገር ባህሉ የለም።

የቢዝነሳችሁ መነሻ አያታችሁ ናቸው፤ ለአያታችሁን እውቅና ለመስጠት አልዘገያችሁም?
የተንቀሳቀስንባቸውን ዓመታት ማየት አለብህ። በሠራንበት ዘመን ስርዓቱ ተዘርግቶ አልነበረም። በሚወጣው ፖሊሲ ትሠራለህ እንጂ፣ የራስህ ፍልስፍና መጠቀም ከባድ ነው። ያኔ ሶሻሊዝም ነበር፣ አሁን አብዩታዊ ነው። በዚህ ውስጥ የቤተሰቡን ሌጋሲ ማቆየታችን እንደውም በራሱ ያኮራናል። በዓለም ደረጃ መጀመሪያ ትውልድ ወደ ኹለተኛ የሚቆየው 30 በመቶ ነው፣ ሦስተኛ ትውልድ 3 በመቶ ነው። እናም ደስተኛ ነን። ብዙ ሥራ ሠርተናል የሚል ግምት የለንም፤ ግን የቤተሰብ ሌጋሲ አስቀጥለናል።

እድሜዎ ስንት ነው?
ከ60 በላይ (ሳቅ)

ጡረታ መውጫዎ አልደረሰም?
አሁን ኦፕሬሽን ላይ አልሠራም፤ ቦርድ ውስጥ ነኝ። ድርጅታችን ያልተማከለ ነው። ስለዚህ የምሠራው ፖሊሲ ላይ፣ ኢንቨስትመንት ሥልጠና ላይ ነው። አብዛኛውን ሰው መምራት ላይ ነው የምሠራው። በዚህ ብዙ አግዛለሁ። ጥበብ ይፈልጋል፤ ትዕግስት ይፈልጋል። ያለኝን ልምድ አካፍላለሁ፤ ይፈልጉኛልም።

የቢዝነስ ፍልስፍናዎ ምንድን ነው?
ኢንዱስትሪ ብዙ ይጠቅማል፤ ብዙ የሰው ኃይል በሥራ ፈጠራም ይጠቅማል። በዚህ ውስጥ ትልቁ ፍልስፍናዬ ግልጽነት ነው። የቤተሰቡ ባህልና እንደ ፖሊሲ ነው፤ በጣም ነው የጠቀመን። አቅምና ጉልበት፣ በራስ መተማመንም ሰጥቶናል። ግልጽነት ካለ፣ ከሰረቅክ ትፈራለህ፣ ስትፈራ ጠባቂ ከለላ ያስፈልግሃል። እኛ አሁን እንደ ፖሊሲ ያደረግነው እዛ ላይ አንደራደርም። አባቴ ከሰጡን አንዱ መመሪያ ንጹህ ያልሆነ ገንዘብ ይዘህ አትምጣ፤ የማታ ማታ ያጠፋሃል የሚል ነው። እኔም ልጆቼን የምነግራቸው ይህን ነው። በመርኅ ነው የምንመራው፤ ይህን የመንግሥት ባለሥልጣናትም ያውቃሉ። በዛም መቆየት ችለናል።

ጠባቂ ያላቸው ተቋማት ብዙ ድካም አይኖርባቸውም፤ የመንግሠት ወዴት ዘርፍ እንዲሚያዘነብሉ ያውቃሉና ብዙ ጥቅም ያገኛሉ። አይፈትንም?
የሚገርመው ብዙ ወጪ ያስወጣል። እኛ በቤተሰብ እንወያይበታለን። እንደውም ልጆቼ ውጤቱን ካዩ በኋላ፣ የእኔን ጥበብ ወስደዋል። ያ ዘላቂ አይደለም። በፍራቻ ዓለም ትኖራለህ። ፍርሃት ደግሞ ለፈጠራ ሥራ ከባድ ነው። ፈጠራን ይገድላል። ፍርሃት ያለው ሰው የፈጠራ ሐሳብ አይኖረውም። ስለዚህ ጥቅሙን ስታይ ከዛ ከመሞዳድ፣ ተቋም ትፈጥራለህ። ጦር ሠራዊት እንደሚያዘጋጀው፣ ራሳችንን የምንጠብቀው በእውቀት ነው። ብዙ ባለሙያዎችን ነው ከአገር ውስጥም ከውጪም የምናመጣው። ይህን ይዘን ስለምንሠራ፤ ግልጽ ስትሆንም አይነኩህም።
እናም አንድ መቶ አንድ ፐርሰንት ንጹህ ሐብት ነው ያፈራሁት።

የቤተሰብ አስተዳዳሪ ነዎት፣ ልጆች አሉ እንዲሁም በርካታ ድርጅቶችም አሉ። ጊዜዎን እንዴት ነው የሚያብቃቁት?
ድርጅታችን እንዳልኩት ተቋማዊ ቅርጽ ያለው ነው። ባለሙያዎቻችን አቅም ያላቸው ናቸው። ቼክ ፈርሜ አላውቅም። ግማሽ ቀን ነው የምንገናኘው። በፖሊሲ በስትራቴጂ ነው የምሠራው፣ በቦርድ ፕላትፎርም ነው የምንገናኘው። አብዛኛውን ሥራ የሚሠራው አመራሩ ነው። እንደውም ብዙ ጊዜ ነው ያለኝ። አብዛኛውን ጊዜዬን በማሠልጠን፣ በውይይት፣ አዳዲስ ሐሳብ በማምጣት እሠራለሁ።

ለምን ታደያ በግሉ ዘርፍ ጉዳይ ላይ ለምሳሌ ቻምበር ላይ ሲሳተፉ፣ በውይይቶችም ላይ ልምድና ሐሳብዎን ሲያካፍሉ አይታዩም?
እውነት ነው! የራሴ ምክንያት ይኖራል። የቻምበር ፖሊሲ ምንድን ነው፣ መዋቅሩ እንዴት ነው የሚለው ጉዳይ አነጋጋሪ ነው። ዋናው እሳቤው ነው የሚስብህ። እና ሄዶ ለማውራት ብቻ ከሆነ፣ ለውጥ ካላመጣህ ቀድሞ የተዋቀረ አሠራር ውስጥ ነው የምትገባው፣ ነገሩ አልቋል። ኬንያ ብትሄድ ቢዝነስ ውስጥ ያለ ሰው ተጽእኖ መፍጠር ይችላል። በፖለቲካ ውስጥ ቢገቡ የፓርላማ አባል ይሆናሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ ሀብት ያለው ሰው ፖለቲከኛ አይደለም። ስለዚህ የፖለቲካ መዋቅሩ ወሳኝ ነው።

አይዲዮሎጂው ለሲስተም ወሳኝ ነው። ድርጅቶቼ ግን አባላት ናቸው። ቻምበር ሄዶ የመጣ ለውጥ ግን አላየሁም። ቢሆንም ቻምበር እንሳተፋለን፣ አባል ነን።

በቢዝነሱ አለብኝ የሚሉት ድክመት ምንድን ነው?
ማንም ሰው ድክመትም ጥንካሬም ይኖረዋል። ብዙ ጊዜ አቻችላለሁ ነገሮችን። ስርዓቱም ያመጣው ተጽእኖ አለ። በዚህ ወስጥ ስታልፍ፣ ባለፉት 17 ዓመትና አሁን ባለው በራስ መተማመን ላይ ተጽእኖ አድርጓል። በጣም ትዕግስተኛ ነኝ። እያየሁ ጥፋት ቢኖር እርምጃ አልወስድም። የእኔ ትልቁ ሀብት ጥበብ ነው፤ ትልቁ መሣሪያ እሱ ነው።

ጥበብ ሲባል አንዳንድ ነገሮችን ማለፍ፣ ወዴት ይዞን ይሄዳል የሚለውን በጥልቀት ማየት ነው። ይህን ሰው ባሠለጥን ነው የሚሻለው ወይስ ምን ትላለህ። ሌላ አገር ግብ ሰጥተህ ትለቀዋለህ እዚህ ግን እንደዛ አይሆንም ጥበብ ያስፈልጋል። ዋናው ማመዛዘን ነው። ቢዝነሱን የምትመራው ስታመዛዝን ነው። ባለመቸኮል፣ ባለመጓጓት ነው። የረጅም ጊዜ ጥቅምን ማየት ይሻላል ወይም የአጭሩን የሚለውን ጥበብ የሚፈልግ ነው።

እስከ አሁን ፈታኝ የሚሉት ወቅትና አጋጣሚ ካለ፤ ያንንስ እንዴት እንዳለፉት ቢነግሩን?
ለቢዝነስ ዘርፉ 17 የደርግ ዓመታት ፈታኝ ነበር። ስለ ቢዝነስ የነበራቸው አመለካከት በጣም ወጣ ያለ ነው። ያው የሶሻሊዝም መርህ ነው፤ ያኔ ትዘርፋለህ የጅምላ ፍረጃም ነበር። ያንን ጊዜ ማለፍ ከባድ ፈተና ነበር። በዛ ብዙ ሰው ተጎድቷል። የዘመኑ የሶሻሊዝም ፍልስፍና ነው። አብዛኛው ቤተሰብ አገር ጥሎ ሄዷል።

የኢስት አፍሪካን ሆሊዲንግ ቀጣይ እቅድ ወዴት ነው?
ብዙ ፕሮጀክቶች አሉን፤ ዓለማቀፍ መሆን እንፈልጋለን። በተለይ ኢትዮጵያውያን ያሉበት አገር በሕጋዊ መንገድ በሮች ቢከፈቱ፤ ኮርያና ቻይና እንዳደረጉት ለአገር ብዙ መሥራት ይቻላል። ዳንጎቴ ጋር እንተዋወቃለን፤ በምዕራብ አፍሪካ እየሠራ ነው። የደረሰበትን አይተናል፤ እኛም መድረስ እንችላለን።

ዳንጎቴ በምዕራብ አፍሪካ የፈጠረውን ተጽእኖ እርስዎ በምሥራቅ መፍጠር የሚችሉ ይመስልዎታል?
በትክክል። እኔ ሳልሆን ተከታዮቼን የማዘጋጃቸውና የምሰጣቸው ርዕይም ይህ ነው። በኢትዮጵያውያን አቅም በጣም እምነት አለኝ። እስከ አሁንም ብዙ ዳንጎቴ መፍጠር ይቻል ነበር።

በኢትዮጵያ የግል ዘርፍ ያሉ ባለሀብቶች ከእርስዎ ምን ሊማሩ ይችላሉ?
ሁሉም መረባረብ ያለበት አሁን ኢንቨስትመንት፣ ሥራ ፈጠራ ላይ ነው፤ በዚህ ላይ መግባት አለባቸው። ታክስ መክፈል አለብን። በኢትዮጵያ ትልቅ ፈተና አለ። በጣም አደገኛው ነገር እንደውም ልኂቃኑ ደሃ ነው። በስርዓቱ ምክንያት ሳያውቁት በክፉ ፈርጀውት፣ ልኂቁ ሀብት የማፍራት ፍላጎት የለውም። ሁሉም ሰው ለዛ ነው አክቲቪስት የሆነው። ስለዚህ የኢትዮጵያ ልኂቃን ሀብታም የሚሆኑበት መንገድ ሊፈጠር ይገባል፤ አገር የምትለወጠው ያኔ ነው።
ኢትዮጵያ ውስጥ ሲቪል ሰርቫንቱ ደሃ ነው። ይህን ይዞ አገር መቀየር አይቻልም። እነዚህን ሰዎች ወደ ሀብት ማምጣት ያስፈልጋል። ይህ ሲሆን ባለድርሻ ይሆኑና ስርዓቱን ይጠብቃሉ። አሁን እነዚህ ሰዎች ጨዋታ ውስጥ የሉም።

በቢዝነስ ዘርፍ የሴቶች ተሳትፎ በጣም የተወሰነ ነው። ሴቶችን በማሳተፍ እናንተ ጋር ያለው ልምድ እንዴት ነው?
ከቤተሰበ የመጣ የሠራነው ትልቅ ስህተት ነው። በቅርቡ ያየሁት ነገር ነው። በጣም ስህተት ሠርተናል፤ ከራሴ ጀምሮ። ያን አይታ ቢኖረን ከዚህ በላይ እንሄድ ነበር። ተሰጥተው ነው የሚሠሩት፤ ግልጽ ናቸው፤ ከሙስናም የጸዱ ናቸው። እንደውም አሁን ሳስበው እናቴ ትመስለኛለች በጣም ብልህ። አሁን ዐቢይ የሠራውን ስናይ በጣም ተመስጠን ነበር። ያላየነው ጉዳይ ነው። በዚህ ሐሳብ እስማማለሁ።

እንደ ድርጅት ባለቤት ነው ያየሁት፣ እንደሐሳብ ተቀብለነዋል ግን ብዙ አላሻገርነውም። መጀመሪያ ሐሳብ ነው የሚቀድመው። እዛ ላይ መሥራት እፈልጋለሁ። ተረካቢ ላይ ሐሳብ አለኝ። ግን በፋውንዴሽን ሴቶችን ማብቃት ላይ እየሠራን ነው።

ቅጽ 2 ቁጥር 62 ጥር 2 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here