በተያዘው አመት ይካሄዳል አካሄድም በሚሉ ሁለት ክርክሮች መካከል የነበረው የ2012 አገር አቀፍ ምርጫ በመጨረሻም ነሃሴ 10 እንዲካሄድ በቀረበው ረቂቅ የግዜ ሰሌዳ መሰረት መካሄዱ እሙን ሆኗል። ምንም እንኳን ሰሌዳው ገና ባይፀድቅም ይህ ዜና መሰማቱን ተከትሎ የተለያዩ ጥያቄዎች ሲነሱ ተደምጠዋል። የአዲስ ማለዳዋ ሐይማኖት አሸናፊም ምርጫውን እና ሰሌዳውን ተከትሎ የተነሱ አንኳር ጥያቄዎችን ከፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ ከባለሞያዎች እና ሌሎች ጉዳዩ ይመለከታቸዋል የሚባሉ አካላትን አነጋግራ የሐተታ ዘማለዳ ርእስ አድርጋዋለች። በተለይም በኮማንድ ፖስት ስር ስላሉ አካባቢዎች፣ አዲስ ስለቀረቡ እና ለመቅረብ በዝግጅት ላይ ስላሉ ጥምረቶች እንዲሁም የቅድመ ምርጫ ስጋት ሃሳቦች ተንሸራሽረዋል።
የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በ 2012 ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀውን አገር አቀፍ ምርጫ ለማካሄድ የጊዜ ሰሌዳውን ይፋ አድርጓል። ነሐሴ ዐስር የምርጫው ቀን እንዲሆን የሰሌዳውን ረቂቅ ያቀረበው ቦርዱ፣ በስምንት ወራት ገደብ ያዘጋጀው ሰሌዳ በምርጫ ቦርድ የክልል ቢሮዎችን ማደራጅት የሚጀምር ነው።
ሰሌዳው እንዴት እንደተዘጋጀ የቦርዱ አመራሮች ያስረዱ ሲሆን፣ የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ የሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 58 ላይ የአጠቃላይ ምርጫ የሚደረግበትን ጊዜ አስመልክቶ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አምስት ዓመቱን ከመፈፀሙ ከአንድ ወር በፊት መጪው ምርጫ መካሄድ አለበት የሚለውን እንደ ሕግ ገደብ መወሰዱን ተናግረዋል።
ይህም የምክር ቤቱ የሥራ ዘመን ከመስከረም ወር የመጨረሻ ሳምንት ሰኞ ጀምሮ እስከ ሰኔ 30 ድረስ በስራ ላይ ይሆናል የሚል ሲሆን፣ የአምስተኛውን ዓመት ሰኔ ወር የሥራ ዘመኑ እንደሚያበቃ መሰላቱ አግባብ አይደለም ይላሉ። ብርቱካን ግን ስብሰባ በቋሚነት የሚዘጋበትን ጊዜ እንደ ሥልጣን ዘመን ማብቂያ መመልከት አግባባ አይደለም ሲሉ ተናግረዋል። አምስት ዓመት የሚሞላውም ሥራ በጀመረበት ጊዜ ነው ያሉት ሰብሳቢዋ፣ ይህንንም በመመሥረት ቦርዱ የጊዜ ሰሌዳውን በሕግ ላይ ተመሥርቶ ወስኗል ብለዋል።
ቦርዱ ከፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች እና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ረቡዕ ጥር 6/2012 በምርጫ ሰሌዳው ዙሪያ ውይይት ባካሄደበት ወቅት እንደገለፀው፣ የተለያዩ መረጃዎችን በመሰብሰብ መውጣቱን ገልጿል። ቦርዱ በአዋጅ በተሰጠው ሥራ እና ኃለፊነት ላይ አተኩሮ ይሠራል ያሉት ሰብሳቢዋ፣ ቦርዱ በሕግ ራሱን ገድቦ እየተንቀሳቀሰ ነው። ይህንን ወደ ጎን አናደርግም ሲሉ የጊዜ ሰሌደው የተዘጋጀበትን መንገድ አብራርተዋል።
‹‹ዛሬ አንዱን አዋጅ ወደ ጎን ካልን በኋለ ንትርክ ብቻ ነው የሚቀረን፣ አንዱ ሌላውን ልንጠቅም ያወጣነው መንገድ አድርጎ ነው የሚያየው›› ብለዋል። ‹‹እኛ አምስት ሰዎች ነን፣ ጥሩ ሰዎች ነን ብለን እናምናለን፣ ግን ሕግ ወደ ጎን የማለት እድል ግን ልትሰጡን አይገባም›› ሲሉ ሰብሳቢዋ ተናግረዋል።
ቦርዱ ቅድመ ዝግጅት ካካሄደበት አካባቢዎች አንዱ ተፈላቅለው ለሚገኙ ከ 700 ሺሕ በላይ ዜጎች ባሉበት አካባቢ ሆነው እንዲመርጡ እንደሚመቻች ማድረግ ነው። በዚህም ግን ከተፈናቃይ ዜጎች መካከል ለመምረጥ እድሜአቸው የደረሱ ዜጎች ቁጥር ያን ያህል የተጋነነ እንዳልሆነ ተገልጿል። ተፈናቃዮች ተፈናቅለው ከመጡበት አካባቢ ላይ የሚቀርቡ እጩዎችን ለመምረጥ እንዲችሉ ይመቻቻል ሲል ቦርዱ ይፋ አድርጓል።
ምርጫው የሰላም ስጋት ይሆን ይሆን?
የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ሰብሳቢ የሆኑት ልደቱ አያሌው፣ አብዛኛው የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫው መካሄድ አለመካሄድ ላይ አስተያየተ ሳይሰጡ የድመፅ መስጫ ቀኑ ላይ ማተኮራቸው እንደሚያስገርማቸው እና ምርጫውን ማካሄድ ይቻላል አይቻልም የሚለው ላይ ውይይት አለመኖሩ እንደሚያሳስባቸው ገልፀዋል።
‹‹የሕዝብ ቆጠራ ማካሄድ ያልቻለ መንግሥት እንዴት ምርጫ ማካሄድ ይችላል? አንድ አገር ውስጥ የምንኖር ከሆነ ምርጫ ለማካሄድ የሚሆን ሁኔታ እንደሌለ እያወቅን ይህንን ችላ ማለት አግባብ አይደለም። እናም ምርጫው ወደ ለየለት ቀውስ እንዳይወስደን እሰጋለሁ›› ሲሉ አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
ቦርዱ በሕግ ማእቀፎች ላይ ተመሥርቶ የምርጫውን ሰሌዳ ማውጣቱን መግለጹን እንደ አሳማኝ ምክንያት የማያዩት ልደቱ፣ ‹‹ሕግም ቢሆን የአገር እና የሕዝብ ደኅንነትን የሚፃረር ሲሆን ይሻራል፤ ይለወጣል›› ይላሉ። አክለውም ‹‹ደርግ የኃይለ ሥላሴን ሕገ መንግሥት ቀዶ ጥሎ ነው ሥልጣን ላይ የወጣው፣ ኢሕአዴግም የደርግን ሕገ መንግሥት ቀዶ ጥሎ ነው ለውጥ ያመጣው። ከእነሱ የተሻለ የፖለቲካ ኃይል ስላለ ተቀዶ ይጣል አላለም። ነገር ግን ለአገር ደኅንነት ሲበላ ሕግ ይሻሻል። የሞት እና ሽረት ጉዳይ አድርጋችሁ የሕግን ጉዳይ አታቅርቡት›› ሲሉ ልደቱ ተናግረዋል።
‹‹የሰላም እና የሕግ የበላይነት በሌለበት ሁኔታ ምርጫ እናካሂድ ማለት ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ማካሄድ አይቻልም›› ሲሉ ልደቱ ተናግረዋል።
የቦርዱ አባል የሆኑት ጌታሁን ካሳ (ዶ/ር) የፀጥታ እና የደኅንነት ሁኔታ ምርጫውን ለማካሄድ የሚያስችል ነው ወይ? በሚለው ላይ በሰጡት ምላሽ፣ መንግሥት ሕጉን ጠብቆ ምርጫውን ለማካሄድ የሚያስችል ሁኔታ የመፍጠር ግዴታ አለበት። ይህንንም ይወጣል ብሎ ቦርዱ እንደሚያምን ተናግረዋል።
ነገር ግን ቦርዱ የሰላም እና የደኅንነት ጥያቄ ከመንግሥት ብቻ የሚመጣ ሳይሆን ፖለቲካ ፓርቲዎችም የራሳቸውን ድርሻ የሚወጡበት መሆን እንዳለበት ተናግረዋል። አክለውም ‹‹ሁሉም ኃላፊነቱን ከተወጣ ሰላማዊ ምርጫ እናካሂዳለን። ሰላም እና ደኅንነት ከሌለ ግን ምርጫ ሳይሆን አገርም ጥያቄ ውስጥ ይገባል። ስለዚህ ሁሉም ኃላፊነቱን መውሰድ አለበት›› ሲሉም ተናግረዋል።
የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን በበኩላቸው፣ ቦርዱ ዋና ሥራው ሰላምን ማስጠበቅ ባይሆንም ነገር ግን መራጮችን በጥይት መካከል እያለፋችሁ ድምፅ ስጡ አንልም ብለዋል። ፖለቲካ ፓርቲዎች ብሔራዊ መግባባት የሚፈጥሩ ከሆነ፣ ያን ያህል የሚፈራውን ስጋት ማስቀረት ይቻላል ብለዋል።
‹‹ሰላም እያደፈረሰ ያለው መንግሥት ብቻ አይደለም። ግጭቶችን መፍታት የሚችለውም መንግሥት ብቻ አይደለም። ፓርቲዎችም ተወዳድራችሁ ሥልጣን ለመያዝ እያሰባችሁ ሰላማዊ ያልሆነ ሁኔታ አብሮ አይሄድም። ስለዚህ ደጋፊዎቻችሁን በሰላም መንገድ እንዲሄዱ ካለደረጋችሁ በሕግ መሰረት እርምጃ እንወስዳለን›› ሲሉ አሳስበዋል። ‹‹ይህንን ካላደረግን ቢሮውን ዘግተን ደሞዝ መቀበል ማቆም አለብን›› ሲሉም አፅንኦት ሰጥተዋል።
የቀድሞው የአየር ሃይል አዛዥ እና የሰላም እና የደኅንነት መምህር የሆኑት ሜጀር ጄነራል አበበ ተክለሃይማኖት እንደሚሉት፣ ምርጫው ያለምንም የፀጥታ ችግር ይካሄዳል ማለት እንደማይቻል ነው። ነገር ግን ምርጫው ሳይካሄድ ቢቀር ሊኖር ከሚችለው ቀውስ ቢካሄድ የተሻለ እንደሚሆን ይናገራሉ።
‹‹የኢትዮጵያ ወጣት በዚህ ኹለት ዓመት ብዙ የሚጠብቀው ነገር ነበር። ነገር ግን አንዱም አልተሳካለትም፣ ይህም የቁጣ መንፈስ ውስጥ ከትቶታል። ይህ ምርጫ ካልተካሄደ ወደ ግር ግር ውስጥ ሊከተው ይችላል›› ሲሉ ያብራራሉ። ‹‹ምርጫው በክረምት መካሄዱ የተለያየ ጉዳት ሊያመጣ ቢችልም፣ አሁን ያለው የተዘጋጀ ወጣት ዝናብም ወንዝም የሚያቆመው አይመስለኝም›› ብለዋል አበበ። አያይዘውም ‹‹የወጣቱ የፖለቲካ ንቃት እና ጉጉት ምርጫው በዝናብ ወይ መጎርፍ ያስተጓጉለዋል ማለት ግን ከባድ ነው›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ገዢው ማሸነፍ አለማሸነፉን በመጠራጠር በተለይም ታች ያለው የመንግሥት መዋቅር፣ ፓርቲው ከተሸነፈ አደጋ ላይ ወድቃለሁ በሚል የመንግሥት መዋቅሩ የሚፈጥረው ችግር ይኖራል ብለው እንደሚሰጉ እና ይሄም ቀድሞ ከግምት ውስጥ መግባት አለበት ብለው እንደሚያምኑ ይናገራሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ዋናው ችግር፣ የፖለቲካ ልሂቁ ጋር ያለው ግትርነት እና ላለመስማማት መስማማት የሚል መንገድ አለመኖሩ ነው ሲሉ ይናገራሉ። ለምሳሌም በሕገ መንግሥቱ ዙሪያ ያሉ መካረሮች ለሕዘቡ ውሳኔ ከማቅረብ በራሳቸው የሚፈጥሩት ችግር አለ ሲሉ ያነሳሉ።
ምርጫ እና ኮማንድ ፖስቱ
በ2009 ታውጆ ከነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በኋላ ወደ ሥራ የገባው እና በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመረጡ አባላትን ያካተተ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አፈጻጸም እንዲከታተል ነበር የተቋቋመው። ኮማንድ ፖስቱ የተለያዩ የፀጥታ አካላትን በማቀናጀት እና ከፌዴራል መንግሥት በመሚሠረት እዝ መሰረት የክልሎችን የፀጥታ መዋቅር ይዞ የሚያስተዳድር ነው።
በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል፣ በኦሮሚያ ክልል በወለጋ እና ጉጂ በሚገኙ ዞኖች በተለያዩ ጊዜያት ታውጆ በሥራ ላይ ያለው የኮማንድ ፖስት የፀጥታ መዋቅር በአካባቢዎች ለሚወዳደሩ ብሎም የሰፊ ድጋፋችን ምንጭ ነው ለሚሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ስጋት ሆኗል። በተለይም የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ስጋቱን በተደጋጋሚ የገለፀ ሲሆን፣ የፓርቲው ቃል አቀባይ ቀጀላ መርዳሳን ለአዲስ ማለዳ እንደሚሉት ኮማንድ ፖስቱ ካልተነሳ ምርጫ ማድረግም ሆነ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ የምርጫ ቅስቀሳ ለማድረግ የማያስችል መሆኑን ይናገራሉ።
‹‹ኮማንድ ፖስቱ ነገሮችን እያወሳሰበ ነው። ያለ አሳማኝ ምክንያትም የሰዎችን ሰብዓዊ መብት ይጥሳል›› የሚሉት ቀጀላ፣ ‹‹ይህንን ወደ መደበኛው የፀጥታ መዋቅር መመለስ እና እርቅ ማውረድም ቀላል ነው› ሲሉ ይናገራሉ።
በአሁኑ ወቅት ኹለት አይነት የፀጥታ ምልክት ያለባቸው አካባቢዎች አሉ የሚሉት አበበ፣ ‹‹በኮማድ ፖስት ስር ያለ እና አስተዳደሩ በጣም የላላበት በሚል ለኹለት ከፍለን መመልከት ይቻላል›› ይላሉ። የአስተዳደር መዋቅሩ የፈራረሰበት የአገሪቱ ክፍል በኮማንድ ፖስት ስር ካለው ይበልጣል የሚሉት አበበ፣ ይሄ ለምርጫው የራሱ በጎ አስተዋፅኦ እና ጉዳትም አለው ይላሉ። መንግሥት እንደፈለገ ምርጫን እንዳያጭበረብር ደስተኛ ያልሆነ ወጣት ምርጫውን በደንብ ስለሚጠብቀው፣ ስርቆት በደንብ ይቀንሳል። ነገር ግን በደንብ የተደራጀ ወጣት ስላልሆነ፣ በመካከሉ የሚገባ ኃይል ግጭት ውስጥ ሊከተው ስለሚችል በኹለቱም አቅጣጫ መመልከት አስፈላጊ ነው ይላሉ።
የቅድመ ምርጫ ስጋቶች
አዲስ ማለዳ በ 62ተኛ እትሟ ላይ፣ በቤኒሸንጉል ጉሙዝ ክልል ‹‹ቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ›› የተሰኘ ክልላዊ ፓርቲ አቋቁመው የምርጫ ቦርድን መስፈርቶች በማሟላት ለምዝገባ ሲዘጋጁ የነበሩ የዩኒቨርሲቲ መምህራን በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ዘግባለች። ሐሙስ ታኅሳስ 30/2012 የፓርቲዉ ምክትል ሰብሳቢ ጌታሁን መርጋ፣ የሕግ ባለሙያ የሆኑት ጌታቸዉ ወድሻ፣ የድርጅት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ጉዮ ፈረደን (ዶ/ር) በቁጥጥር ስር መዋላቸውን እና ሌሎች የፓርቲው የሥራ አስፈጻሚዎች ላይ የእስር ትዕዛዝ መውጣቱ ይታወሳል።
ጉዳዩን ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማሳወቃቸዉን ተከትሎ፣ የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ የክልሉ ፖሊስ ድርጊቱን እንዲያቆም ደብዳቤ መጻፋቸዉን እና ‹‹ክልሉን የሚያስተዳድረዉ ገዢ ፓርቲ የድርድር ጥያቄ አቅርቦልን ባለመቀበላችን ጫና አሳድሮብናል›› ሲሉ የቦሮ ፓርቲ የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ ዮሐንስ ተሰማ ለአዲስ ማለዳ ተናግረው ነበር።
የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ (ዎብን) ሊቀመንበር አቶ አንዱአለም ታደሰ፣ በወላይታ ሶዶ ከተማ ምሽት ላይ በሚንቀሳቀሱ ወቅት አምስት ቦታ በስልት መወጋታቸውን የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ይናገራሉ። ‹‹ጀርባው ላይ፣ እጁ እና እግሩ ላይ ነው በስለት የወጉት። አመጣጣቸው የከፋ ጉዳት ለማድረስ ቢሆንም እሱ ሮጦ አምልጧል›› ያሉት ተከተል ላቤና፣ ጉዳዩ ከተፈፀመ በኋላ ፖሊስ የአንዷለምን ቃል ቢቀበልም እስከ አሁን ግን ምንም ዓይነት ክስ አልተመሰረተም።
‹‹ከዎላይታ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ዎሕዴግ) ጋር በቅንጅት ለመሥራት መግባባት ላይ መድረሳችን አስፈርቷቸው። እናም አደጋውን አድርሰው ይሆናል›› የሚል ስጋት እንደላቸው የሚናገሩት ተከተል፣ ነገር ግን የምርጫው ቀጣይ ሂደቶችን አይተው እንጂ ከአሁኑ ኢ-ፍትሐዊ ይሆናል የሚል ድምዳሜ ላይ ለጊዜው አለመድረሳቸውን ይናገራሉ።
የምርጫ ክልል
የሶማሌ ክልላዊ መንግሥት ኅዳር 30/2012 ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በፃፈው ደብዳቤ፣ የሶማሌ ሕዝብ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሊኖረው የሚገባውን 32 መቀመጫ ተቀንሶ 23 መቀመጫ ብቻ እንዳለው እና ለዚህም መከራከሪያ ሆኖ የቀረበው የ 1987 የሕዝብ እና ቤት ቆጠራ ላይ መሰረት ያደረገ ነበር።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሐመድ የፈረሙበት ይህ ደብዳቤ፣ በወቅቱ 3.1 ሚሊዮን ሆኖ የተቆጠረው የክልሉ ሕዝብ በሕገ መንግሥቱ መሰረት ሊኖረው ከሚገባው መቀመጫ ላይ ዘጠኝ መቀመጫ ቀንሶበታል ሲል አቤቱታው ለምርጫ ቦርዱ ቀርቧል።
የካቲት 24/ 2012 ይፋ እንደሚሆን በረቂቅ የጊዜ ሰሌዳው ላይ ቀን የተቀመጠለት የምርጫ ክልልን ይፋ በማድረግ ወቅት፣ ምንም አይነት የምርጫ ክልል ወሰንን የተመለከተ ለውጥ እንደማይደረግ የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ተናግረዋል። ለዚህም ምክንያት የሆነው ከተቀመጡ ምክንያቶች መካከል፣ በቅርቡ የተደረገ የሕዝብ እና የቤት ቆጠራ ባለመኖሩ እና ከዚህ በፊት ባለው ውጤት ወይም ከዛ በኋላ በተደረጉ የፕሮጀክሽን ግምቶች ላይ በተመሠረተ ለውጥ ይደረግ ቢባል፣ ጊዜው ስለማይበቃ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህም የቦርዱ ሥራ ብቻ ሳይሆን የፌደሬሽን ምክር ቤትን ተሳትፎ ከመጠየቁ ባሻገር፣ ከምርጫ 180 ቀናት በፊት ለሕዝብ ክፍት ሀኖ መቆየት ስላለበት ይህንን ለማድረግ የጊዜ እክል መኖሩንም አስረድተዋል፤ ብርቱካን።
ነገር ግን ከዚህ ቀደም ከነበሩ ምርጫዎች ለየት ባለ ሁኔት የምርጫ ካርታን ቦርዱ ይፋ እንደሚያደርግም ብርቱካን ገልፀው ‹‹ለቦርዱ ራሱ ግራ የሚያጋቡ አሰራሮች እና በአግባቡ እና ግልፅ በሆነ መልክ የተቀመጠ አይደለም። እሱን አጥርተን አስተካክለን እና አሟልተን ምርጫ ከመድረሱ በፊት ይፋ እናደርጋለን›› ሲሉ ገልፀዋል።
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር በበኩሉ፣ ይህ የምርጫ ካርታ ይፋ ከመደረጉ በፊት ቅድሚያ ውይይት እንዲደረግበት ጠይቋል። ቦርዱም ይህንን ሐሳብ ተቀብሎ ቀድሞ ለውይይት እንደሚያቀርበው በመድረኩ ላይ ተገልጿል።
የቦርዱ የቤት ሥራዎች ለነፃ ምርጫ
የምርጫ አስፈፃሚዎች ምልመላ ዋናው የምርጫውን ተአማኒነት የሚወስን መሆኑን ተከትሎ፣ ሙሉ በሙሉ አዲስ የምርጫ አስፈፃሚዎችን ለመመልመል መወሰኑን የቦርዱ ሰብሳቢ ተናግረዋል። 250 ሺሕ አስፈፃሚዎች ይመለመላሉ። ‹‹ከዚህ በፊት ከነበሩት አቤቱታዎች በመነሳት፣ በቀደመው አስፈጻሚ ላይ እምነት እንደሌለ በመረዳት አዲስ ተመራቂዎችን ለማሰማራት አስበን ነበር። ይህንን ለማድረግ እንደማይቻል ግን ታውቋል። የአቅም ችግር አለ። ሲዳማ ላይ በነበረው የሕዝበ ውሳኔ ኃላፊነታቸውን የማይወጡ አስፈፃሚዎች በምናገኝ ጊዜ እርምጃ ለመውሰድ አስቸጋሪ እንደሚሆን አይተናል። አዲስ አበባ ላይ የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው እና ስራ የሌላቸው ወጣቶች ሠልጥነው ተሰማርተው ነበር›› ብለዋል፡፡
‹‹የኃላፊነት ችግር ሲመጣ ያንን ለማረም የሚሆን እጅ የለንም፣ ምክንያቱም ወደ ቤታቸው ሄዱ። ሰለዚህ የቻልነው ገንዘባቸውን መያዝ ነበር። ምርጫውን ውጤት የሚያበላሽ ድርጊት ፈፅመው ከጠፉ አሁን ያንን ማድረግ ስለማንችል ከየአካባቢው ነው የምንመርጠው›› ሲሉ ብርቱካን ተናግረዋል፡፡
ምርጫው በክረምት ወር የሚደረግ በመሆኑ ምክንያት የሎጂስቲክ ጉዳይ የተወሰነ እንቅፋት ሊፈጥር እንደሚችል የሚናገሩት የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን፣ ቦርዱም ይህንን ለመወጣት ከመከላከያ ሠራዊት ጀምሮ የተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን ድጋፍ እንደሚጠቀም ተናግረዋል። በረቂቅ የምርጫ ሰሌዳው መሠረትም ከሰኔ ሰባት እስከ ሐምሌ 20/2012 ባለው ጊዜ ቦርዱ ድምፅ መስጫ ወረቀቶችን ህትመት የሚያገባድድ ሲሆን፣ የቅድመ ምርጫ የሎጂስቲክስ ሥራ የመጨረሻ የቤት ሥራ ይሆናል።
ታዛቢ
የሲቪል ማኅበራት በመጪው ምርጫ የሚኖራቸው ተሳትፎ በተለይም ምርጫውን በመታዘብ እና የመራጮች ትምህርት በመስጠት ላይ ከፍተኛ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። ተሻሽሎ በወጣው የምርጫ አዋጅ አንቀጽ 115 መሰረት፣ ምርጫውን ለመታዘብ የሚችሉት የሲቪል ማኅበራት እና ተወዳዳሪ ፓርቲዎች ተወካዮች ብቻ ናቸው። ከዚህ ቀደም የነበረው አዋጅ የሕዝብ ታዛቢ በሚል ቦርዱ መልምሎ የሚያሰማራቸውን ግለሰቦችን የሚያካትት ሲሆን፣ የሲቪል ማኅበራትን ደግሞ እንዳይታዘቡ የከለከለ ነበር።
ጥምረት
የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነምግባር አዋጅ ምዕራፍ ስድስት ስለ ውህደት፣ ግንባር ስለ መፍጠር እና ስለ ቅንጅት ያትታል። ግንባር ለመፍጠር ለቦርዱ የሚቀርብ ማመልከቻ ላይ ምንም ዓይነት የጊዜ ገደብ ባይጥልም፣ ቅንጅት ለመመሥረት ወይም ለመዋሐድ ግን የአገር ዐቀፍ ወይም የአካባቢ ምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ከመውጣቱ ከ ኹለት ወራት በፊት ለቦርዱ የጽሑፍ ማመልከቻ መቅረብ እንዳለበት ይደነግጋል።
የባልደራስ ለዴሞክራሲ ፓርቲ ሰብሳቢ የሆኑት እስክንድር ነጋ እንደሚሉት፣ ይህ ገዢውን ፓርቲ ለመጥቀም የወጣ አሰራር ነው። መጪውን ምርጫ ፍትሐዊ እና ውድድር ያለበት እንዳይሆን የሚያደርግ ነው።
የቀድሞው የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ስር ታቅፈው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሦስት ድርጅቶች እና አምስት አጋሮቻቸው ራሳቸውን በማክሰም ብልጽግና ፓርቲን መመስረታቸውን ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል። ፓርቲዎቹ ራሳቸውን ካከሰሙ በኋላ ብልጽግና የተሰኛ አዲስ አገራ ዐቀፍ ፓርቲ የመሰረቱ ሲሆን፣ ይህም በምርጫ ቦርድ እውቅና እንዲሰጠው ኅዳር 24 ቀን 2012 የጽሑፍ ማመልከቻ ለምርጫ ቦርድ አስገብተዋል።
ቦርዱም ይህንን ጥያቄ በመመልከት ታኅሳስ 06 ቀን 2012 ፓርቲዎቹ ተሰርዘው ብልጽግና ፓርቲ የእውቅና ሰርተፍኬት እንዲሰጠው ወስኗል። የጊዜ ሰሌዳው ጥር 23 ቀን 2012 ይፀድቃል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ የብልፅግና ፓርቲ ማመልከቻ የገባበት ቀን ከተቆጠር 60 ቀን ወይም ኹለት ወር የሚያሟላ ይሆናል።
በምርጫ አዋጁ የትርጓሜ ክፍል ላይ ‹‹ውህደት›› ማለት ኹለትና ከዛ በላይ የሆኑ ፓርቲዎች ሕጋዊ ሰውነታቸውን በመተው አዲስ የፖለቲካ ፓርቲ የሚመሠርቱበት ሂደት እንደሆነ ተቀምጧል። ‹‹ግንባር›› የሚለው ደግሞ ኹለት እና ከዛ በላይ የሆኑ ፓርቲዎች የተናጠል ሕጋዊ ሰውነት እንደያዙ የጋራ ሥያሜ፣ የፖለቲካ ፕሮግራም እና መተዳደሪያ ደንብ ይዘው ለመንቀሳቀስ ሲወስኑ የሚመሰርቱት ነው።
‹‹መቀናጀት›› ማለት ደግሞ ኹለት እና ከዛ በላይ የሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምርጫን ለማሸነፍ ወይም ለሌላ መሰል ጊዜአዊ ዓላማ በጋራ ለመሥራት ተስማምተው የመቀናጀት የምስክር ወረቀት የሚያገኙበት አሰራር ነው።
የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ምንም እንኳን ሕጉ ማንኛውም ጥምረት ለማድረግ የሚያስብ ፓርቲ የጊዜ ሰሌዳው ከመውጣቱ ከ ኹለት ወር በፊት ለቦርዱ በጽሑፍ ያመልክት ቢልም፣ አሁንም የተለያዩ የጥምረት ጅማሮዎች አሉ። ቦርዱ ይህንን እንዴት ያየዋል በሚል የቀረበውን ጥያቄ ሰብሳቢዋ ብርቱካን ‹‹የምንመለከተው ይሆናል›› ብለዋል።
የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ የሚል አዲስ ፓርቲ በመመስረት ጥር 7 ቀን 2012 ጊዜአዊ የምስክር ወረቀት ማግኘት ችሏል። የዚህ ፓርቲ ሊቀ መንበር የሆኑት እስክንድር ነጋ፣ የጥምረቱ ነገር የማይፈቀድ ከሆነ ይጎዳናል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
‹‹ምርጫው ከመደረጉ ኹለት ወር በፊት ቢሆን ኖር ያስኬዳል። ከዛ በፊት ራቅ አድርጎ የሚለው ግን በምን አግባብ ይህን መወሰን እንደተቻለ አላውቅም። ከዚህ በኋላ በዚህ መልክ የሚተገበር ከሆነ ኢሕአዴግን የሚጠቅም መስፈርት ወጥቷል ማለት ነው። ስለዚህ ይህ በምርጫው ሂደት ላይ ጥላሸት የሚቀባ ነውና ይህን አልመክርም። በዚህ መንገድ እንዲሄድ አልመርጥም›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ‹‹ምንም እንኳን ሕጉን ባላየውም ለቦርዱ ስለ ጥምረት የማሳወቅ ዋነኛ ጫላማ ለህትመት በመሆኑ፣ ስለዚህ እንዲህ አይነት መስፈርት ማስቀመጥ በራሱ አግባብ አይደለም›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ተጨማሪ የሕግ ማዕቀፎችን በማዘጋጀት ላይ የሚገኘው ቦርዱ፣ ምርጫውን ለማስፈፀም የሚረዱትን የተለያዩ መመሪያዎች በማርቀቅ ለውይይት ይፋ በማድረግ ላይ ይገኛል። የመራጮች ምዝገባ፣ መንግሥት ለፖለቲካ ፓርቲዎች የሚሰጠውን የገንዘብ ድጋፍ የሚመለከት፣ የምርጫ አዘጋገብ እና ሌሎች ከ 30 በላይ የሚሆን ምርጫውን የሚያስፈፅሙ መመሪያዎችን ከምርጫው በፊት ያወጣል።
የወብን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ተከተል ላቤና እንደሚሉት፣ እነዚሕ ሕጎች በሚወጡ ጊዜ ትርጉም ያለው ውይይት እና ተሳትፎ የሚደረግ ከሆነ፣ ለምርጫው ፍትሐዊነት ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል። ‹‹ከፓርቲዎች ሲሰነዘር የቆየውን ቦርዱ በሕግ ዙሪያ ጠርቶ ቢያወያየንም፣ ግብአታችንን አይጠቀምም›› የሚለውን ወቀሳ የማይቀበሉት የቦርዱ አባል ጌታሁን ‹‹ሁል ግዜ በአንድ አይነት ሃሳብ ላይ
መውጫ
በምርጫው ሰሌዳ ላይ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች እና በምርጫው ሂደት ውስጥ በተለያየ ደረጃ የሚሳተፉ አካላት በአብዛኛው የሚፈለገው የምርጫው ውጤት እና ሂደት የጋራ ውጤት እንደሆነ ይናገራሉ። በምርጫ ሰበብ የወጣቶች ነፍስ መቀጠፍ የለበትም ሲሉ አበበ ተክለ ሃማይኖትን ጨምሮ እነዚህ ባለድርሻዎች ያሳስባሉ።
ቦርዱ የአገሪቱን የሰላም እና የፀጥታ ሁኔታ የሚዳስስ እና እስከ አሁን ኹለት ጊዜ የተከለሰ ካርታ መዘጋጀቱን ይፋ ያደረገው ቦርዱ፣ ከተለያዩ አካላት የሚሰበስበውን መረጃ በመጠቀም ሰላም እና ደኅንነቱን ይለያል። ‹‹ጉልህ የሆነ የፀጥታ ችግር የሚገጥመንን ቦታ ለይተን ለመንግሥት ልከናል፣ በእኛ እምነት አገሩ ላይ ያለው ሃብት በሙሉ ተባብሮ ችግር ተቋቁሞ ለምርጫው መዋል አለበት›› ሲሉ የቦርዱ ሰብሳቢ ይናገራሉ። ‹‹ከመንገዶች ባለሥልጣን የመንገዶችን ሁኔታ በተመለከተ መረጃ ወስደናል። ቀጥለን የሚትዮሮሎጂ ሪፖርት ጠይቀናል። ይህንን ሁሉ ከግምት በማስገባት ስኬታማ ምርጫ ለማካሄድ እንሠራለን››ም ብለዋል።
የፌዴራል ፍርድ ቤቶችም በበኩላቸው የምርጫ ውዝግቦችን ለመዳኘት ዝግጅት እያደረጉ እንደሆነ ይፋ አድርጓል። ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች ምርጫን ምክንያት ያደረጉ ክርክሮች እምብዛም ባለማስተናገዳቸው ምክንያት፣ የአቅም ከፍተት እንዳይፈጠር ፍርድ ቤቶቹ ከመደበኛው ፍትህ አሰጣጥ ሂደት በተለየ እና በተቀላጠፈ መልኩ አገልግሎት ለመስጠት እየተዘጋጀን ነው ሲሉም ይፋ አድርገዋል፡፡
የሰላም እና የደህንነት ጉዳዮች ተንታኙ ሜደር ጄነራል አበበ እንደሚሉት ፖለቲካ ፓርቲዎች በፀጋ ለመሸነፍ መወሰን እና የሕዝቡን ውሳኔ ለማክበር፣ ለምርጫው ከሚደረጉ ዝግጅቶች መካከል መሆን አለበት፣ ይህንን ማድረግ ከተቻለ ምርጫው የሚፈለገውን ግብ እንዲመታ መሰደረግ ይቻላልም ሲሉ ያጠቃልላሉ።