ብርሃንና ሰላም ህትመት የማቆም ሃሳቡን ማራዘሙን ገለፀ

0
915

ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ላለፉት ሦስት ወራት ድርጅቱን ስጋት ላይ በሚጥል ሁኔታ አጋጥሞ የነበረውን የጋዜጣ ማተሚያ ወረቀት እጥረት ለመቅረፍ የኹለት ሚሊዮን ዶላር ግዥ በብሔራዊ ባንክ በመፅደቁ ለጊዜው ከህትመት ማቋረጥ አደጋ መውጣቱን አስታወቀ።

ድርጅቱ በውጭ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት አጋጥሞት የነበረውን የጋዜጣ ማተሚያ ወረቀት እጥረት ለመፍታትም እስከ ቀጣዩ ዓመት ድረስ የሚገለግሉ የህትመት ግብአቶችን ገዝቶ እያጓጓዘ እንደሚገኝ የድርጅቱ የሚድያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያ ተመስገን ደሬሳ ገልፀዋል። ከብሐራዊ ባንክ በተፈቀደለትም ኹለት ሚሊዮን ዶላር የዉጭ ምንዛሬ የተለያዩ የወረቀት ዉጤቶችን በተለይም ለጋዜጣ ሕትመት የሚውሉ ውጤቶችን መሰብሰቡን ተናግረዋል።

ድርጅቱ አጠቃላይ የጋዜጣ ማተሚያ እጥረት አጋጥሞት ስጋት ዉስጥ ገብቶ እንደነበርና የጋዜጣ ህትመት ሊቆም እንደሚችል ስጋት ላይ ደርሶ እንደነበር ተመስገን ተናግረዋል። በዚህም ድርጅቱ 70 ሴንቲ ሜትር የጋዜጣ ህትመት ሙሉ በሙሉ አቁሞ ጋዜጣዎችን በተመሳሳይ ሳይዝ በ84 ሴንቲ ሜትር እያተመ እንደነበርና ወደፊትም በ84 ሴንቲ ሜትር ህትመቱ እንደሚቀጥል የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዉ ገልፀዋል።

ለጋዜጣ ማተሚያ የሚውሉ ወረቀቶች ሙሉ በሙሉ ከውጭ አገር የሚገቡና በአገር ውስጥ የማይመረቱ መሆናቸው እና በአገሪቱ ያለዉ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ብርሃንና ስላም ማተሚያ ድርጅትን አደጋ ላይ የጣሉት ጉዳዮች እንደነበሩ ገልፀዋል። የውጭ ምንዛሬው በዘለቄታዊነት የሚገኝ ካልሆነ የድርጅቱ የማተም አቅም አደጋ ላይ ሊወድቅ እንደሚችል ተመስገን አብራርተዋል። ባለሙያዉ አክለዉም በውጭ ምንዛሬ እጥረቱ ምክንያት ድርጅቱ የደንበኞችን ፍላጎት ማርካት ያለመቻሉንና በሚፈልጉት መጠን እየሠራ እንዳልቻለ አመላክተዋል።

ከውጭ አገር ተገዝተዉ በመጓጓዝ ላይ ያሉ ወረቀቶች 80 ግራም፣ 70 ግራም፣ 60 ግራም እና ባለ 84 ሴንቲ ሜትር የጋዜጣ ማተሚያ ውጤቶች ናቸው።

የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዉ ባለፉት ጊዜ ሲጠቀሙባቸዉ የነበሩት የሕትመት ወረቀቶች ከሦስት ዓመት በፊት የተገዙ እንደሆኑና ለኹለት ዓመት እንዳገለገሉ ገልፀውልናል። ባለሙያዉ እንደሚሉት በድርጅቱ የተፈጠረዉ እጥረት በቅርብ ጊዜ ካልተቀረፈ አደጋዉ ሊከፋ እንደሚችል ስጋታቸዉን ገልፀዉ ብዙ የሕትመት ሥራዎች የሚሠራዉ ድርጅቱ ትልቅ ኃላፊነት የያዘ ስለሆነ ቅድሚያ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነዉ ብለዋል።

በሌላ በኩል ድርጅቱ ሕትመቶችን የሚከናውነው በአሮጌ ማሽኖች መሆኑን የገለፁት የካሜራ ክፍሉ ባለሙያ አለማየሁ የድርጅቱን የሕትመት አቅም የሚገዳደር ስለሆን ከጋዜጣ ሕትመት ወረቀቶች አጥረት በዘለለ አጠቃላይ ድርጅቱ እየተጠቀመበት ያለው የማሽን አቅም አደጋ ላይ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት የሚሰጣቸዉ አገልግሎቶች በመደበኛ ሕትመት ዘርፍ ጋዜጦች፣ መፅሐፍት፣ መፅሔቶች፣ ፖስተሮች ያትማል። ብርሃንና ሰላም በምስጢራዊ የሕትመት ዘርፍ የባንክ ቼክ፣ የሎተሪ ትኬቶችና ሌሎች ምስጢራዊ ይዘት ያላቸው ሰነዶችን የሚያዘጋጅ ከመሆኑም በተጨማሪ የትምህረት አጋዥ መፅሐፍትና ፈተናዎችን በብቸኝነት የሚያትም ድርጅት ነው።

በኢትዮጵያ ብቸኛ የሕትመት ቴክኖሎጂ ኮሌጅ ባለቤት የሆነው ድርጅቱ ከደረጃ አንድ እስከ ሦስት ስልጠና ይሰጣል። ብርሃንና ሰላም በሕትመቱ ዘርፍ ከ90 ዓመት በላይ የዘለቀ አንጋፋ የሕትመት ድርጅት ነዉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 64 ጥር 16 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here