አምነስቲ በኦሮሚያ ከተሞች የተፈጸውን ጥቃት አወገዘ

0
1051

ባሳለፍነው ቅዳሜ የካቲት 7/2012 በኦሮሚያ ክልል በወለንጭቲ እና ቡራዩ ከተሞች በተቃዋሚ ፓርቲ ደጋፊዎች እና ግለሰቦች ላይ ተገቢ ያልሆነ ጥቃት ተፈፅሟል ሲል ዓለም አቀፉ አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አምነስቲ ኢንተርናሽናል ድርጊቱን አወገዘ፡፡

በክልሉ ልዩ ኃይል ፖሊሶች በተፈጸመው ጥቃት የአንድ ሰው ሕይወት በወለንጭቲ ከተማ ጠፋቷል ያለው አምነስቲ ኹለት አርቲስቶችን ጨምሮ በሌሎች ንፁኃን ዜጎች ላይ ጉዳት እንደደረሰም ትላንት አመሻሽ ላይ ባወጣው ሪፖርቱ ላይ አመላክቷል፡፡

በኢትዮጵያ የሚደረገውን አገራዊ ምርጫው መራዘሙ በተነገረበት ማግስት በአሮሚያ ነጻ አውጪ ግንባር (ኦነግ) ደጋፊዎች ላይ የክልሉ ልዩ ኃይል ጥቃት መፈጸሙን ይፋ ያደረገው አምነስቲ በግለሰቦች ላይም አስለቃሽ ጋዝ መተኮሱን በሪፖርቱ ላይ አስፍሯል፡፡

በተመሳሳይ ቀን፤ የቡራዩ ከተማ ፖሊስ ከሆቴል ምርቃት ጋር በተያያዘ ሙዚቀኛዋን ሀዊ ኃይለየሱስ ቀነኒ ጨምሮ 30 ለእንግድነት የመጡ ሰዎችን አስሮ ወደ ስታድየም በመውሰድ አካላዊ ጥቃት እና ወከባ እንዳደረሰባቸው ያስታወሰው ሪፖርቱ ድርጊቱን በኢትዮጵያ የመሰብሰብ እና ሃሳብን በነጻነት የመግለፅ መብቶችን የሚገደብ ነው ሲል አምነስቲ ኮንኗል፡፡

በተጨማሪም፤ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ምስራቅ እና ደቡብ አፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር የሆኑት ሴፍ ማጋንጎ መንግስት ነጻ እና ገለልተኛ በሆነ አካል ምርመራ ማድረግ ይኖርበታል በማለት ጠይቀዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስትም እንዲህ ዓይነቱን ተግባር መደገፍ የለበትም ሲሉ ምክትል ዳይሬክተሩ አሳስበዋል፡፡

 

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here